“የሐጎስ-ቶላ-እርገጤ” ጨዋታ (አፈንዲ ሙተቂ)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


“የሐጎስ-ቶላ-እርገጤ” ጨዋታ
(አፈንዲ ሙተቂ)
—-
ከአሁኑ ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር ባልተገናኘ ሁኔታ የሐጎስ፣ የቶላ እና የእርገጤ ጨዋታን ወደ ሶሻል ሚዲያ ያመጡ ሰዎች ዓላማቸው ምን እንደሆነ አልገባንም፡፡ እኛ እንደምናውቀው በኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ተመችቶት የሚኖር የትኛውም ህዝብ የለም፡፡ በደሉ፣ ድህነቱ፣ ረሃቡ፣ ጭቆናው በሁሉም ክልል ያለ ነው፡፡ ትግራይም ሆነ ኦሮሞ፣ አማራም ሆነ ሶማሊ በበደል ውቅያኖስ ውስጥ እየዋኙ ነው፡፡ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሐት) ሀገሪቱን እንዳሻው እየፈነጨባት ነው ስለተባለ ብቻ መላው የትግራይ ህዝብ ሌሎችን አስገብሮ በባርነት እያሳረሳቸው ማለት ነው…. ? ይህ ሃላፊነት የጎደለው የእብድ ፖለቲካ ነው፡፡
የኦሮሞ ህዝብ “እምቢኝ! አልቀበለውም” በማለት ውድቅ ያደረገው ማስተር ፕላን በትግራይ ህዝብ ሙሉ ስምምነትና እውቅና እንዳልወጣለት ያውቃል፡፡ የአማራ ህዝብም በክልሉ ያለው በደል አንገሽግሾት ለተቃውሞ ሲወጣ የበደሉ ምንጭ የትግራይ ህዝብ እንዳልሆነ ያውቃል፡፡ ሌሎች ህዝቦችም እያሰሙት ያለው ድምጽ “በመልካም አስተዳደር እጦት ተሰቃየን፣ ፍትሕና ነጻነት እንሻለን” የሚል እንጂ “ወያኔዎች አንገቴን ይዘው የትግራይ ህዝብ አሽከር አደረጉኝ” የሚል አይደለም፡፡ ጥቂቶች የራሳቸውን ፖለቲካ ከህዝብ ጥያቄ ጋር እየቀላቀሉ ባያቀያይሙን መልካም ነው፡፡
ይህ አንድን ህዝብ በጅምላ የመፈረጅ አካሄድ በምርጫ 97 ማግስት ተከስቶ ነበር፡፡ በተለይ ከፊውዳል አስተሳሰብ ያልተላቀቁ አዛውንት ፖለቲከኞችና ደቀ-መዛሙርቶቻቸው በልዩ ልዩ ዌብሳይቶች ላይ “ትግሬዎችን የምንጥልበት ጊዜ ስለደረሰ በአንድነት እንነሳ” እያሉ በአንዱ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ መርዘኛ ቅስቀሳ ሲያጣጡፉ እንደነበረ እናስታውሳለን፡፡ ታዲያ ያ አደገኛ ቅሰቀሳ ወያኔን ከመነቅነቅ ይልቅ ብዙዎች ያላሰቡትን ቀውስ አስከትሎ ነው ያለፈው፡፡ ለምሳሌ ለወትሮው ከኢህአዴግ መንግሥት ጋር እሳትና ጭድ መሆናቸውን የምናውቅላቸው የትግራይ ተወላጅ ፖለቲከኞች በዚያ ቅሰቀሳ ልባቸው በመሰበሩ ከተቃውሞ ፖለቲካው ተገልለዋል፡፡ በዚህ ረገድ በቀዳሚነት የሚታወሱት አቶ አብረሃም ያየህ ናቸው፡፡ አቶ አብረሃም በወቅቱ የተናገሩት ትልቅ አባባል ነበረ፡፡ ይኸውም “መለስ ዜናዊንና ከዓለማዊ ህይወት ተገልለው በደብረ ዳሞ ገዳም የሚኖሩትን የትግራይ መነኮሳትን በአንድ ሚዛን ላይ የሚያስቀምጥ የተቃውሞ ፖለቲካ ነገ እኔን ወንጀለኛ ላለማድረጉ ምንም ዋስትና የለኝም” የሚል ነው፡፡
ያ በ1997 የታየው አሳዛኝ ክስተት በፌስቡክ ላይም ተደግሞ አይቼዋለሁ፡፡ አርአያ ተስፋማሪያምን ታውቁታላችሁ አይደለም…. ? አዎን! አርኣያ ማለት “እየሩሳሌም አርኣያ” በሚለው ዝነኛ የብዕር ስም የምናውቀው ተወዳጅ ጋዜጠኛ ነው፡፡ አርኣያ በተለይ የሚታወሰው “ኢትኦጵ” በምትባለው ሳምንታዊ ጋዜጣ ላይ “ከህወሓት መንደር ከቃረምኩት” በሚል ርዕስ ስር ሲጽፋቸው በነበሩት ተከታታይ ጽሑፎች ነው፡፡ አርኣያ ጽሑፎቹን መጻፍ የጀመረው በ1994 መጨረሻ ላይ ይመስለኛል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጋዜጣዋ እስከተዘጋችበት 1998 መጀመሪያ ድረስ በዚህ ርዕስ ሲጽፍ ነበር፡፡
አርኣያ በጽሑፉ ከውስጠ-አዋቂዎች የተገኙ ሚስጢሮችን ነበር የሚዘረዝረው፡፡ በህዝቡ ዘንድ መነጋገሪያ ለመሆን የበቁ በርካታ ሚስጢሮችን ለመጀመሪያ ለህዝብ ይፋ ያደረጋቸው አርኣያ ነበር (ለምሳሌ አቶ መለስ ዜናዊ በ1996 አጋማሽ ላይ በተካሄደው የኢህአዴግ ም/ቤት ግምገማ ላይ አቶ አርከበ እቁባይን “ሰባት ድስት ጥዳ ሰባቱንም በአንድ ጊዜ ለማማሰል የምትሞክር ባልቴት ትመስላለህ” ማለታቸውን ይፋ ያደረገው አርኣያ ተስፋማሪያም ነበር)፡፡ አርኣያ ሚስጢሮችን ሲነግረን መንገዱ ሁሉ ቀና አልነበረም፡፡ ብዙ ማስፈራሪያዎች ደርሰውታል፡፡ በ1996 ሚያዚያ ወር ላይ ደግሞ ያልታወቁ አካላት ከፍተኛ ድብደባ ፈጽመውበት በደም የራሰ አካሉን ቀበና ድልድይ ላይ ጥለዋል (ነገሮችን እንዲህ የማስታውሰው “ኢትኦጵ” በቋሚነት ከማነባቸው ጋዜጦች አንዷ ስለነበረች ነው)፡፡
እንግዲህ እነዚያን የኢህአዴግና የህወሓት ሚስጢሮች በየሳምንቱ ሲያጫውተን የነበረው አርኣያ ተስፋማሪያም የትግራይ ተወላጅ ነው፡፡ አርኣያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገረ አሜሪካ የሚኖር ቢሆንም አሁንም በዌብሳይቶች አማካኝነት ልዩ ልዩ መጣጥፎችን እየጻፈልን ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሶሻል ሚዲያ ላይ በሚያነባቸው መላ-ቅጥ የሌላቸው ጽሑፎች ስሜቱ እንደተጎዳ እያየን ነው፡፡ በተለይም አምና መሳፍንት ባዘዘው እና ጓደኞቹ “እነዚህ ተባዮች፣ ተባያቸውን አራገፉብን” በሚሉ ጥሬ ቃላት ሲጽፏቸው በነበሩት መርዘኛ ጽሑፎች የተነሳ ከመሳፍንት ጋር የቃላት ጦርነት ገብቶ እንደነበረ እናስታውሳለን፡፡ አሁን በተነሳው አዋራም ሞራሉና ስሜቱ እንደተጎዳ አይተናል፡፡ እና እንዲህ ዓይነቱ የሞራል ተጎጂ ነገ በተቃውሞ ፖለቲካው ተስፋ ቆርጦ የህወሓት ደጋፊ ሆኖ ብቅ ቢል “ድሮውንም ትግራዮች የዘራችሁን ነገር አትተውትም” ልንለው ነው….? የትላንት ግብሩ በዜሮ ተባዝቶለት “ድሮውንም ለስለላ ስራ ተልከህ ነው” ሊባል ነው…?. በጭራሽ…! እርሱን የወለደውን የትግራይ ህዝብ የማያከብር መርዘኛ ጸሐፊ በርሱ ላይ ጣቱን የሚቀስርበት የሞራል መሰረት የለም፡፡
ሰርካለም ፋሲል የታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ባለቤት ናት፡፡ እርሷና ባለቤቷ በጋራ በመሰረቱት የፕሬስ ድርጅት አማካኝነት ምኒልክ፣ ሳተናው እና አስኳል የተሰኙ ጋዜጦችን በኤዲተርነት ሲያዘጋጁ ነበር፡፡ ሁለቱም በምርጫ 97 ጦስ አንድ ላይ ታስረዋል፡፡ ሰርካለም በእስር ቤት እያለች የመጀመሪያ ልጇን ተገላግላለች፡፡ ከእስር ቤት ከወጣች በኋላ ደግሞ ተሰዳለች፡፡ እዚያ ሆና ባለቤቷ እንዲፈታላት ድምጿን በማሰማት ላይ ትገኛለች፡፡ ያቺ ሁለት ዓመታትን በእስር ቤት ያሳለፈችውና ባሏን በእስር የተቀማችው ሰርካለም ፋሲልም በብሄሯ የትግራይ ተወላጅ ናት፡፡ የትግራይ ተወላጅ የሆነው ሁሉ የስርዓቱ ተጠቃሚ ነው የሚባል ከሆነ ሰርካለምንና ህወሐትን የሚያያይዛቸው የጥቅም ትስስር የትኛው ነው?… “ሐጎስ-ቶላ-አዝብጤ” በሚለው አክሲስ ውስጥ ሰርካለምም ትገባለች ማለት ነውን….?
አሉላ አባነጋ፣ ባሻይ አውኣሎም፣ ሃይሉ አርኣያ፣ ግደይ ገብረዋህድ፣ ብርሃነ እያሱ፣ ረዘነ ረዳኢ፣ ገላውዴዎስ አርኣያ፣ ስብሐት ገብረ እግዚአብሄር፣ ምሩጽ ይፍጠር፣ ወርቅነሽ ኪዳኔ፣ አቤሰሎም ይህደጎ፣ ገብረ መድኅን ሃይሌ፣ ኪሮስ ዓለማየሁ፣ ነጋድራስ ገብረ-ህይወት ባይከዳኝ፣ እነዚህ ሁሉ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አንጸባራቂ ስፍራ ያላቸው የትግራይ ተወላጆች ናቸው፡፡ ሁሉንም በጅምላ መወረፍ ከተጀመረ እነዚህ በሙሉ ታሪካቸው ይሰረዛል ማለት ነው፡፡ ህዝብን በጅምላ መፈረጅ ከመጣ ታሪክና አንትሮፖሎጂ ተሳስተዋል ማለት ነው፡፡
እስቲ በአካባቢያችን የምናውቃቸውን ምንዱባን የትግራይ ተወላጆች እናስታውስ፡፡ በዘመነ ደርግ በከተማችን የሚኖረውና ወዝ-አደር ሆኖ ለሰዎች ሸክም ያመላልስ የነበረው የማነ የሚባል ሰውዬ ዛሬም ቢሆን በዚሁ ስራ ነው የሚተዳደረው፡፡ ከገለምሶው የካምቦ ተራራ ስር አንዲት አነስተኛ ቤት ቀልሰው የሚኖሩት አቶ ገብረአምላክ አሁንም ምንም ሳያልፍላቸው በድህነት ኑሮ ህይወታቸውን እየገፉት ነው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች የትግራይ ተወላጆች ቢሆኑም ከህወሓትና ከአመራሩ ያገኙት የተለየ ጥቅም የለም፡፡ እነዚህን ድኩማንና የሕወሓት የነፍስ አባት ናቸው የሚባሉትን ኦቦይ ስብሐት ነጋን በአንድ መነጽር ማየት ይቻላል?
ለስርዓቱ ጉድለቶችና ጥፋቶች የትግራይ ተወላጅ በሙሉ ተጠያቂ የሚሆንበት ቀመር የለም፡፡ በተመሳሳይ መልኩም ሁሉም የትግራይ ተወላጅ የስርዓቱ ተጠቃሚ ነው” የሚል ፍረጃ መዘብዘብ ውሃ አይቋጥርም፡፡ ስለዚህ ጨቅላነት የሚያጠቃቸው አክቲቪስት ነን ተብዬዎች ያልታረሙ እንኮላዎችን በፌስቡክ ላይ እየደፉ ጨዋ ጓደኞቻችንን ባያስከፉብን ይመረጣል፡፡
በሌላ በኩል አንዳንድ ካድሬዎች ይህንን ጨዋታ እያራገቡ የትግራይ ህዝብን ማስፈራራታቸውን መተው አለባቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ፍረጃ ከህዝብ እንዳልመጣ እየታወቀ “የአሁኑን ተቃውሞ የቀሰቀሱት እነዚህ ዘረኞች ናቸው” እያሉ መለፍለፍ በህዝብ መብትና ጥቅም መቀለድ ነው፡፡ ተቃውሞውን የሚያካሄደውና በዚህ ሳቢያም መስዋእትነት እየከፈለ የሚገኘው ብዙሃኑ ህዝብ ነው፡፡ የህዝብ ጥያቄም በግልጽ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ውጥረቱ እንዲረግብ ከተፈለገ ያልሆነውን አሉ እያሉ ማስወራት ሊቆም ይገባል፡፡
ባጠቃላይ ሲታይ ህወሓት የሚባለው ድርጅት እድሜው አርባ ዓመት ብቻ ነው፡፡ ኦሮሞ፣ ትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ሶማሊ፣ ስልጢ፣ ጉራጌ፣ ወዘተ… የሚባሉት ህዝቦቻችን ግን ለብዙ ክፍለ ዘመናት እዚሁ ምድር ላይ ነበሩ፡፡ አብረው ኖረዋል፡፡ ተዋልደዋል፣ ተዛምደዋል፡፡ የተለያዩ መንግሥታት በተለያዩ ዘመናት በየተራ እየተነሱ ቢወድቁም ህዝቦቻችን አብረው እየኖሩ ነው፡፡ ነገም አብረው ይኖራሉ፡፡ መንግሥታት በስማቸው ቢምሉና ቢነግዱም እነርሱን ጠቅመዋል ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ ስርዓትና ህዝብን ማምታታት ተገቢ አይደለም፡፡
መንግሥታት ያልፋሉ፤ ህዝቦች ግን ይኖራሉ፤ እኛ ከህዝቦቻችን ጋር ነን፡፡