ይድረስ ለአቶ ሞሪ (ዶ/ር ሃይሌ ላሬቦ)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ይድረስ ለአቶ ሞሪ

የዚህን ደብዳቤ መልስ በደምብ ለመረዳት፣ ኀይሌ ላሬቦ በቅርብ ጊዜ “ለመሆኑ ዐማራ ማነው” በሚል ርእስ የጻፉትን በአብዛኞቹ የኢትዮጵያውያን ድረገጾች በአማርኛ ታትሞ የወጣውን አስቀድሞ ማንበብ ይጠቅማል። ጽሑፉ፣ አንድ ሞሪ (Mori) የተባሉ አንባቢ [የብዕር ስማቸው ሊሆን ይችላል]፣ በተጠቀሰው መጣጥፋቸው ላይ ላደረጉት ኂስ (ወይንም ስድብ) የተሰጠ መልስ ነው። በዚህ የደብዳቤ መልስ ላይ ኀይሌ ላሬቦ መጀመርያ ለአቶ ሞሪ በሰጡት መልስ ላይ አንዳንድ ጥቃቅን ማሻሻያና እርማት አድርገዋል። አቶ ሞሪ የተቹት በላቲን ፊደል በተጻፈ አማርኛ ሲሆን፣ ኂሳቸው እንደሚከተለው ነበር።

Mori says:

August 14, 2016 at 2:05 am

Indante Yale dear Zealabaj Terb defar tenkolengna mahaim aiche alawqm Orono tlacha asaytahal dedebnethn lemsale Hochimin Hangariawi. Sayhon Vetnamawi new. Ambassador zaf indeneberk argeh yemtaweraw ke20ametat befit indeqeld be awropa yafrica tamariwoch well neber neber. Lela kftafneth.. Muhur nen bayous Orinowoch , dro gala yemibalu,h/slase promo new y ball, abugida sainsawi new Latin yereqeqe blehal setun thche sntun qzet. Lawra. INE Microsoft Yanten abugida yemiteqemew gn Iyandandu hzb yesedebkbet debtera abath yenegereh teret teret aqaztoh inde awaqi lemehon mokrehal

:

ነሐሴ ፲፭ ቀን ፳፻፲፮ ዓ. ም

ሰላም አቶ ሞሪ፣

ኢጣልያን ከሚመስል ስምዎ ተባዕት (ወንድ) ይሆናሉ ብዬ ስላመንሁ ነው አቶ ያልክዎት። ከተሳሳትሁ በትሕትና ይቅርታ እጠይቃለሁ።

እኔ በጻፍሁት ጽሑፍ ላይ በማቈላመጥም ሆነ በማጥላላት፣ በማወደስም ሆነ በማንቋሸሽ፣ በማመስገንም ሆነ በመሰዳደብ ለሚጽፍልኝ እንደደምቡ መልስ አልሰጥም። እርስዎ በጻፉት ላይ ግን፣ የሚታረም ግድፈት ስላለና፣ አንባቢያንም እንዲማሩና እንዲታነፁበት፣ አሳብ ለአሳብ በመለዋወጥ ትምህርት ቀስመው ዕውቀታቸውን እንዲያዳብሩ ስል፣ መልስ ካለመስጠት ልቈጠብ አልቻልሁም። ብዙ ሐተታ ሳላበዛ ወደ አውራ ነገሮቹ እንድሄድ ይፍቀዱልኝ።

ባንደኛ ደረጃ፣ የአልባንያን መሪ ኤንቨር ሆሻን፣ ከቬትናሙ ሆቺሚኒ ጋር የማዘባረቁን ግድፈት በተመለከተ፣ እኔም ከርስዎ በፊት አስቀድሜ በታተመው ጽሑፍ ላይ አስተውዬው፣ ረቂቁን ደጋግሜ ሳነብ አለማየቴ ገርሞኝ ሲያበቃ፣ ወዲያውኑ ጽሑፉ ለተላከላቸው ድረገጾች አስፈላጊዉን እርማት አድርጌ፣ በፊተኛው ምትክ አዲሱን በድረገጻቸው እንዲለጥፉ ደጋግሜ ልኬ ነበር። ግን ካንድ ድረገጽ አዘጋጅ በስተቀር፣ ሌሎቹ እንደተጠበቀ አላደረጉም። እኔ እንደማውቀው ከሆነ፣ የድረገጾች አዘጋጆች፣ አብዛኞቹ በቀን ተቀን የኑሮ ትግል እንደሁላችንም የሚሯሯጡና፣ ሌላ ሥራ ያላቸው ናቸውና፣ ያልናቸውን ሁሉ ለማስተናገድ ሥራ ይበዛባቸዋል። የድረገጹን ሥራቸው፣ ባገራችን ጉዳይ ላይ እኛ አሳብ ለአሳብ እንድንለዋወጥና እንድንማማር፣ እርስ በርስ እንድንተዋወቅና እንድንቀራረብ፣ ላገራቸውና ለወገናቸው ሲሉ፣ የግላቸውንና የቤተሰባቸውን ድሎትና ቅንጦት ትተው፣ ገንዘባቸውንና ጊዜአቸውን በመሠዋት፣ በትርፍ ጊዜአቸው የሚያካሄዱት ጉዳይ መሆኑ መረሳት የሌለበት ይመስለኛል። እንደነዚህ ዐይነቶቹን ታታሪዎች፣ ፍላጐታችንን ባያሟሉ እንኳን፣ እንደዚህ የመሰለ ምቹ መድረክ በመፍጠራቸው ልናመሰግናቸውና ልናደንቃቸው ይገባል እንጂ፣ በምንም መልክ መወቀስ የለባቸውም ብዬ በጽኑ አምናለሁ። እውነት ነው፣ ባንድ ጽሑፍ ውስጥ ምንም ዐይነት ግድፈት ባይኖር ይመረጣል። ይኸ ግን ምኞት እንጂ፣ ብዙውን ጊዜ ተግባራዊ አይደለም። ምክንያቱ ግልጥ ይመስለኛል። ከእኛም በጽሑፍም ሆነ በንግግር አስተዋፅዖ ከሚናደርገው መካከል፣ ብዙዎቻችን እንደድረገጾቹ አዘጋጂዎች፣ እንደነዚህ ዐይነቶቹን ሥራዎች የምንሠራቸው በትርፍ ጊዜአችን ነው። አንባቢው የሚያየው ግን ጽሑፉን እንጂ፣የጽሑፉ አሳብ በጸሓፊዎቹ ጭንቅላት ከተፀነሰበት ወቅት ጀምሮ፣ በድረገጾቹ እስከታተመበት ጊዜ ድረስ የሚፈጀውን ሥራ፣ የሚከፈለውን መሥዋዕት፣ የሚጠፋውን ገንዘብና ጊዜ አይደለም። ለማስታወስ ያህል፣የመጻፉ አሳብ ሲመጣ አርእስት ይፈለጋል፤ ቤተ መጻሕፍት ተኬዶ መጻፍቶችን አገለባብጦ፣ አንብቦና አመሳክሮ ማስታወሻዎች ይያዛሉ፤ ነጥቦች ይፈለጋሉ፤ በዘርፍ በዘርፉ ይደረግና ረቂቅ ይጻፋል፤ ረቂቁ ተደጋግሞ ሦስቴም ዐራቴም ይከለሳል፤ ይታረማልም። ከዚያ በኮምፑተር ይተየባል። ከዚያም የመጨረሻ እርማቶች ተደጋግመው ይደረጉና፣ ደራሲው ከተደሰተበት፣ ለድረ-ገጾቹ ይላካል። ይኸ ሁሉ የሚሠራው ከቤተሰብና ከግል ምቾት በመገለል በብቸኝነት ነው። እንደሚያዩት የአገርና የወገን ጉዳይ ሁኖ ነው እንጂ፣ በጣም አድካሚ ሥራ ነው።

“ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው” እንደሚባል፣ ልፋቱንና ድካሙን የማያውቅ ገር አንባቢ፣ ብዙውን ጊዜ የጽሑፉን አንኳር መልእክት ትቶ፣ ዐይኖቹ የሚያተኩሩት በጥቃቅን ዋጋ በሌላቸው ነጥቦች ይሆናል። አሁንም እርስዎ ያነሡት ግድፈት መደረግ ባይገባም ቅሉ፣ ዋናው የጽሑፉ መልእክት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ፣ ዐማራ ምን እንደሆነ በየዘርፉ ከነማስረጃው ማሳየት ነው። ጽሑፌ ይኸንን ተግባር አማልቷል ብዬ አምናለሁ። እርስዎም አላሟላም ብለው አንድ ነጥብ እንኳን አላነሡም። እንደመሰለኝ፣ የከነከነዎት የግድፈቱ ጉዳይ ነው። ስለግድፈቱ እንግዴህ፣ እርስዎ ከመናገርዎ በፊት፣ እኔው ራሴ እንደደረስኩበትና፣ እንዲታረም እንደጠየቅሁ፣ ከዚህ በላይ አወያይቼዎትአለሁና፣ አምነው እንደሚቀብሉት ተስፋ ላድርግ።

ሁለተኛው፣ እርስዎ የሚያነሡት ነጥብ “የጋላ ጥላቻ” አለብህ የሚለው ነው። ይኸ ትልቅ ክስ ነው። ሁኖም ግን ባዶ ቃላት ከመወርወርዎ ውጭ፣ ጥላቻዬ እምኑ ላይ እንደሆነ፣ ምንስ በማለቴ እንደሆነ አልነገሩኝም። ቢነግሩኝ ኖሮ መልስ በሰጠሁ። አለበለዚያም፣ ተገቢ መስሎ ከታየኝ፣ በታረምሁና ይቅርታ በጠየቅሁ። አሁን ግን ያንን ዕድል ስላልሰጡኝ፣ አንዱንም ለማድረግ አልችልም። ከንግግርዎ እንደምረዳ ከሆነ ግን፣ ለምን ባገራችን ካለው የፖለቲካ ነፋስ ጋር አብረህ አትሄድም መሰለኝ። ይኸም ማለት፣ የጐሣ ፓለቲካ አቀንቃኞችና አዳባሪዎች ልሂቃንና ምሁራን የሚሉትን፣ ለምን ዝምብለህ አትቀበልም የሚሉኝ ይመስላል። የጋላ ጥላቻዬ መግለጫው ይኸ ነው ካሉኝ፣ በጣም ይገርመኛል። ይበልጥ ደግሞ የሚገርመኝ፣ እርስዎ እንደዚህ እያሉ ያሉት፣ ምናልባት የአሳብ ነፃነት በነፃ እንዲንሸራርሸር፣ አይዞህ አይዞህ በሚባልበት በምዕራቡ ዓለም እየኖሩ ከሆነ ነው። ከኢትዮጵያ ቢሆንማ፣ ምንም አይገርመኝም፤ ምክንያቱም አሳብ ከጦር ይልቅ የሚፈራበትና፣ የሚታፈንበት አገር ስለሆነ፣ እዚያ የአሳብ ነፃነትና ጠላትነት ያው ናቸው ብዬ ስለማምን ነው።

እንግዴህ የጋላ ጠላትነቴ ምልክት፣ እርስዎ በሚደግፉት ሰዎች አስተሳሰብ አለማሰቤ ከሆነ፣ እንደዚያ ዐይነት ነገር ለማድረግ ዝንባሌዬም አይደለም፤ የሠለጠንኩበት ሙያዬም አይፈቅድልኝም። ገና ልጅ ሳለሁ አንድ ነገር ካልጣመኝ የማልቀበል፣ በተፈጥሮዬ ሽፍታ ነበርሁኝ። ስለዚህም ከዚህ የአሳብ ሽፍታነት የተነሣ፣ በጊዜው ያልወጣልኝ ስም አልነበረም። አሁን የምዕራባውያን ፓስፖርትና ሶሻል ሰኩሪቲ ባንድ ስም እንድጸና ታድገውኝ ነው እንጂ፣ ስሞቼ ከመብዛታቸው የተነሣ፣ እውነተኛ ስሜን እንኳን እስከመርሳት ደርሼ ነበር። የተፈጥሮ ዝንባሌዬ አልበቃ ብሎ፣ ሙያዬ ተጨመረበትና የመመራመሬን ዝንባሌን አሰላው። ሕይወታቸው ባጭሩ የተቀጨው ገብረሕይወት ባይከዳኝ፣ የማስተዋል ጸጋ የታደላቸው ታልቅ ምሁር ነበሩ። ቶሎ ባያርፉ ኖሮ፣ ላገራችን ብዙ ዕውቀት ባበረከቱ ነበር ይባላል። እኚህ አስተዋይ ሰው፣ ስለታሪክ ጸሓፊነት አስፈላጊ መስፈርቶች ሲናገሩ፣ ታሪክ መጻፍ በጣም አስቸጋሪ ሙያ ነው ብለው አበክረው ካስገነዘቡ በኋላ፣ መሟላት አለባቸው የሚሉትን ሦስት አንኳር ናቸው የሚሉትን ነገሮች ያማጥናሉ። አንደኛ፣ ድርጊቱን ለማስተዋል አመዛዛኝ ልቡና፤ ሁለተኛ፣ ድርጊቱን ለመፍረድ የማያዳላ አእምሮ፤ ሦስተኛ፣ያመዛዘኑትንና የፈረዱትን ለማስታወቅ የጠራ የቋንቋ አገባብ ናቸው ይላሉ።

የታሪክ ባለሙያ በመሆኔ፣ እኔም ከመላ ጐደል የምከተለው የሳቸውን ምክር ነው። ታሪክን እንደብዙዎቹ የአገራችን ምሁራን ነን ባዮች፣ የግል መጠቀሚያና የፖለቲካ ደንገጡር አድርጌ አልመለከትም። እርስዎ የሚያደንቋቸውን የኢትዮጵያን የታሪክ ምሁራንን የሚተቸው በጣም በሚያሳዝን ሁናቴ፣ የገብረሕይወትን ምክር ለማሟላት ባለመቻላቸው ነው። በጽሑፌ ውስጥ ስለጋላ ያነሣሁትም ነገር ቢኖር፣ ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው። ስለጋላ ታሪክና በኢትዮጵያ ውስጥ ስለደረሰባቸው መከራ እናውቃለን እያሉ የሚናገሩ የታሪክ ምሁራን ነን ባዮች፣ የኢትዮጵያ ነገሥታትና ገዢዎች፣ በጋላ ላይ አደረሱ የሚሉትን ሐተታ ሲዘረዝሩ፣ ጋላውም ይልቁንም ከእረኝነት ሕይወቱ ወደግብርና እስከገባ ጊዜ ድረስ፣ ባካባቢው ሕዝብና ባገሪቷ በጠቅላላ የፈጸመውን ጭቈናና ውድመት ማንሣት አይፈልጉም። የአፄ ምኒልክን የኢትዮጵያን የጥንት አንድነቷን መልሶ የማደስ ተግባር እንደቅኝ ግዛትነት ሲያዩ፣ የጋላውንም ወረራ በዚያው መልክ ማየት እንዳለባቸው ይዘነጋሉ። እኔ በበኩሌ ይኸንን ዐይነት ፍርደገምደልነት አልቀበልም ባይ ነኝ። ለርስዎ ግን ይኸ ሐቅ ልዋጥልዎት ስላልተቻለ፣ የጋላ ጥላቻ እንዳለብኝ አድርገው ፈርጀውኛል። ለኔ ፍርደገምደልነት ቦታ የለውም። እርስዎ አመዛዛኝ ልቡናና የማያዳላ አእምሮ ባይኖርዎት ነው እንጂ፣ በጽሑፌ ውስጥ ጋላ የሚሉት ሕዝብ ከተራ ገበሬና ወታደር እስከባለሙሉ ሥልጣን የመንግሥት የበላይ ጠባቂነት ደረጃ ድረስ፣ ባለቤት ሁኖ በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያስመዘገበ መሆኑን ተናግሬአለሁ። ግድ የሰጠዎት ግን፣ የሙያቸውን ተልእኮ ረስተው፣ የተዛባና አወናባጅ የተረት ታሪክ ምሁራንን መውቀሴ ነው። እንደምረዳው ከሆነ፣ እርስዎ የጋላ ጥላቻ አለህ ሲሉኝ፣ መልእክትዎ ለምን የጋላን ታሪክ፣ ለማንም በማያዳላ መንገድ አመዛዝነህ ታያለህ ማለት ስለሆነ አልቀበለውም።

እርስዎ ተገንዝበው ከሆነ፣ ከዚህ በላይ አሁን በሥልጣን ያለው መንግሥት፣ በዐዋጅ ያዘዘውን “ኦሮሞ” የሚለውን ቃል ትቼ፣ “ጋላ” የሚለውን ተጠቅሜአለሁ። አንደኛ፣ “የኦሮሞ” ሳይሆን “የጋላ ጥላቻ” አለህ ብለው ስለከሰሱኝ፣ እርስዎ ራስዎ የተጠቀሙትን ቃል ልጠቀም ብዬ ነው። ሁለተኛ፣ ከዚህ በላይ እንዳልኹዎት የማይላቀቀኝ የአሳብ ሽፍታነት ዝንባሌዬ ስለሆነ፣ ሌላውም (መንግሥትም ይሁን ግለሰብ) እያደረገው ነው ብዬ አላደርገውም። አንደኛ፣ በግዴታ ስም መቀየር ያለበት ሁኖ ቢገኝም፣ ተገቢው ጥናት ተካሄዶ፣ ጥቅሙና ጉዳቱ ታይቶ፣ የስሙ ባለቤት ተመክሮ መሆን አለበት እንጂ፣ ራሳቸውን በማያውቁ፣ ተረትና እውነት በማይለዩ፣ በጥቂት ጥቅመኞች ግፊት መሆን የለበትም። አሁን በሥልጣን ያለው መንግሥትም “ጋላ” የሚለውን ቃል፣ “ኦሮሞ” ወደሚለው ስያሜ የቀየረው፣ በዚያ መልክ ማለትም በፖለቲካ ግፊት ነው። የስም አወጣጥ ታሪክ ቢያዩ ይረዳል በሚል አሳብ እስኪ አንዳንድ ነጥቦች ልዳስስና፣ በጥሙና እንደሚያነብቡት ተስፋ አደርጋለሁ። ዋና መነሻዬ ግን የስም መጥፎ የለም ነው። ጥሩና መጥፎ የሚያሰኘው ተጠቃሚውና ሥራው ነው ከሚል ልጀምር።

የስም አወጣጥ ታሪክ ካዩ፣ ለግለሰብም ሆነ ለአገርና ለተወሰነ ቡድን ወይንም ሕዝብ ሌላ ነው ስሙን የሚያወጣው። በመጀመርያ ላይ፣ የገዛ ራሱን ስም ያወጣ የለም። ወላጆች የልጆቻቸውን ስም ያወጣሉ። ያ ስም እንደሁናቴውና እንደኅብረተሰቡ፣ ከግለሰቡ ጋር ተጣብቆ ይቀራል፤ ካልሆነም በተለያዩ ምክንያቶች ሊቀየርም ወይንም ሌሎች ስሞች ሊደራረቡበትም ይችላሉ። በሠለጠነው በምዕራብ ዓለም፣ የግለሰቡ ስም አንዴ ከተመዘገበ፣ ሥርዐቱንና አገባቡን ተከትሎ ካልሆነ (ለምሳሌ ፍርድ ቤት ሄዶ አመልክቶ) በስተቀር፣ አይቀየርም። ዘመድ አዝማድና ጓደኞች የሚጠሩት የቁልምጫ፣ የቅጽልና የብርቅዬ፣ እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች የሚያወጡት የክርስትና ስሞች፣ በተጨማሪ ሊሰጡ ይችላሉ። ግለሰቡም ቢሆን፣ ከነዚህ ስሞች መካከል ባንዱ ወይንም በሁለቱ ስም ሊታወቅ ይችላል። በመንግሥት ደረጃ ግን ጸንቶ የሚቈየው ያው ሲወለድ ያገኘው ስም ነው። በኢትዮጵያ በወላጅ የተሰጠ ስም፣ እንደሁናቴውና እንደኅብረተሰቡ በየጊዜው ይቀየራል። ደብተሮች ብዙዉን ጊዜ በየሄዱበት ትምህርት ቤት፣ ራሳቸውን በተለያየ ስም የማስተዋወቅ ልማድ እንደነበራቸው አስተማሮቼ ነግረውኛል። ለምሳሌ ያህል፣ በዋድላ የቅኔ ትምህርትቤት ሳለ፣ ስሙ ወልደብርሃን የነበረው፣ ወደደብረ ዐባይ መዝገበ ቅዳሴ ሊያጠና ቢሄድ፣ ስሜ ገብረክርስቶስ ይል ነበር። በተቀረ፣ በወላጅ የተሰጠው ስም፣ በተለያየ በግለሰቡ የሕይወት ደረጃ በሚገጥሙት ሁናቴዎችም ሆነ፣ በአገልግሎቱ ምክንያት ባካበተው የኅብረተሰቡ ዕውቅና ሊቀየር ይችላል። ማለትም በቤተክህነት ከሆነ፣ ሲቄስስ፣ ሲመነኲስ፣ ሲጳጵስ፣ በመንግሥት በኩል ደግሞ ሲሾም ወይንም ሲነግሥ፣ እንዲሁም በማኅበረሰቡ እንደየባህሉና እንደየቦታው፣ ሲገረዝ፣ ሲያገባ፣ ሲወልድና፣ ሸምግሎ ከአካባቢው በነገር ዐዋቂነት፣ በዕውቀቱና በፍርዱ ብስለትና አለማዳላት፣ ጉምቱ ሁኖ በመገኘቱ፣ የክብር ቦታ ሲሰጠው። ይኸ ሁሉ እንግዴህ በግለሰብ ደረጃ ነው።

ባገርና በብሔረሰብ አኳያ ደግሞ፣ እነሱ ከሚጠሩበት ከግል መጠርያቸው ውጭ፣ ሌሎችም ጐረቤቶቻቸው የሚሰጡት ስሞች አሉ። መጠርያችን ነው የሚሉት ስም ራሱ፣ ያመጣጡ ጥንተመሠረቱ ከሌላ የተሰጣቸው እንጂ፣ ራሳቸው በዚህ ስም እንጠራ ብለው በስምምነት የወሰኑት እንዳልሆነ ግልጥ ነው። ስለዚህ ብዙዎች ራሳቸውን የሚጠሩት፣ ጐረቤቶቻቸው በሰጧቸው ስም ነው። ለምሳሌ፣ በአገራችን ሲዳማ የተባለ ሕዝብ ክልልም ሆነ፣ በውስጡ የሚኖሩት የተለያዩ ጐሣዎች የሚጠሩት በወረራቸው ወቅት ጋሎች በሰጧቸው “ሲዳማ” በሚል መጠርያ ስም ነው። በማኅበረሰባቸው መኻል ግን አንድም ሲዳማ ተብሎ የሚጠራ ጐሣ የለም። ብዙውን ጊዜ ግን አንድ ብሔረሰብም፣ አገርም ራሳቸውን የሚጠሩበት ስምና፣ ጐረቤቶቻቸው የሚሰጧቸው ስም አይመሳሰሉም። ለምሳሌ ያህል፣ ጀርመኖችን የወሰድን እንደሆነ፣ ራሳቸውን የሚጠሩበት ስም ሌላ ሲሆን፣ የጐረቤታቸው አገሮች የሚጠሯቸው እንደየቋንቋቸው የተለያየ ነው። ከፈቀዱልኝ እስኪ እዚህ ላይ ጥቂቶቹን ልዘርዝርልዎት። በአኳኋንዎ የላቲኖች ፊደላት አድናቂ ስለሚመስሉ፣ በዚያው ልጻፍልዎት።

ጀርመኖች ራሳቸውን የሚጠሩት Deutschen ሲሆን፣ እንግሊዞች (ከሮማውያን ጌቶቻቸው በወሰዱት) Germans፣ ኢጣሊያኖች tedeschi፣ ፈረንሳዮች allemands፣ ዳቾች duitsers፣ ዳንሾች tyskerne፣ እስዊድኖች tyskarna, የፊን ምድር ሰዎች saksalaiset፣ ሁንጋሮች nemetek፣ ሩሲያኖች Hemubi ይሉዋቸዋል። ከነዚህ መካከል ጥቂት የሚቀራረበው ስም ቢኖር፣ የደንሾቹና የእስዊድኖቹ ነው። እንግዴህ እያንዳንዱ የየራሱን ሰም ያወጣው፣ ካንድ በጀርመኖች ላይ ካየው ግንዛቤ ወይንም በመጀመርያ ከተገናኘው ካንዱ የጀርመን ጐሣዎች ተነሥቶ ነው። እኛን ኢትዮጵያውያንንም የቅርብ ጐረቤቶቻችን የሆኑት፣ ከቀይ ባሕር ማዶ ያሉት ዐረቦች፣ ካንድ ለየት ካለ ግንዛቤ ተነሥተው “ሐበሻ” ይሉናል፤ ፈረንጆችም “Abyssinians” የሚሉን፣ ቃሉን ከነሱ ወስደው ነው። ልክ እኛ ከዐረቦች ተበድረን፣ ከጽርዖች {ማለትም ከዛሬው ግሪኮች] በስተቀር፣ ሌሎቹን አውሮጳውያን በድፍኑ ፈረንጅ [ከFrance/Frank] እንደምንል ማለት ነው። ኢትዮጵያውያንን ለማመልከት “ሐበሻ” ወይንም “አበሻ” የሚል ቃል በየትም የኢትዮጵያ ታሪክ የለም። ያለው ኢትዮጵያ የሚል ቃል ብቻ ነው። ዐረቦች “ሐበሻ” የምትለውን ቃል ከየት እንዳመጧት አናውቅም። ግን ቃሉ በኛም መኻል ተዛምቶ፣ ክርስቲያን ለሆኑት ለሰሜኖቹ ብቻ የተሰጠ አስመስለን፣ እነዚህን የጠላቸውና ያኰረፈባቸው ሁሉ፣ ቁጭቱንና ብሶቱን ሊወጣ ሲፈልግ፣ ቃሉን ስድብነት አለባብሶ፣ “እናንተ አበሾች” ሲባል ይሰማል። እንዳልክሁዎት ስድብ አድርጎ የሚገምተው ተናጋሪው ነው እንጂ፣ ቃሉ ገለልተኛ ነው። መጥፎነቱና ጥሩነቱ የሚወሰነው ካጠቃቀሙ እንጂ ከቃሉ አይደለም። ከዚህ በላይ ስም በዐዋጅ አይቀየርም ያልክሁዎት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት አውሮጳውያንንና ሌላውን ዓለም “አበሻ” አትበሉን፤ በስማችን ኢትዮጵያ ብላችሁ ጥሩን ሲል ቢያስታውቃቸው፣ አውሮጳውያን የተቀበሉት ቢመስሉም፣ ዐረቦቹ ግን ገና አበሻ እያሉን ነው።

“ጋላ”ም የሚለው ቃል እንግዴህ አመጣጡ በዚያ መልክ ስለሆነ፣ ስድብ አድርጎ መውሰዱ አያዋጣም። ለመጀመርያ ስሙ የተሰጠው በሱማሌዎች ስለሆነ፣ እነሱም አለምክንያት ከመሬት ብድግ ብለው ሳይሆን፣ ባንድ ግንዛቤ ተመሥርተው ነው። ልክ ጋሎች ሌላውን በአካባቢያቸው ያለውን የደቡብ ኢትዮጵያን ሕዝብ “ሲዳማ” ብለው ይጠሩ እንደነበር ማለት ነው። “ሲዳማ” አሁንም ሆነ፣ ስሙን በሰጡት ጋሎችም ዘንድ ስድብ አይደለም። ሰጪዎቹ ራሳቸውንና ቡድናቸውን፣ በባህልም በቋንቋም ከማይመሳሰሏቸው ለመለየት ሲሉ የሠየሙት “ሌላ” እንደማለታቸው ነው። እንዲሁም እርግጠኛ ነኝ ሱማሌዎችም ‘ጋላ” የሚለውን ቃል ሲሰጡ፣ በዚያው መልክ መሆን አለበት። ሱማሌዎቹ ራሳቸው፣ እንደጋላው ሕዝብ እረኞች ቢሆኑም፣ እስላሞች በመሆናቸው፣ በቋንቋም በእምነትም፣ ክጐረቤታቸው “ጋላ” የሚል ስያሜ ከሰጡት ጐሣ ይለያሉ። እንግዴህ ለሱማሌ “ጋላ” ማለት “ሱማሌ” ያልሆነ፣ የሱማሌን ባህልና የእስልምናን እምነት የማይከተል “ሌላ” የተለየ ጐረቤታችን ማለት ነው።

“ጋላ” ስድብ ከሆነ፣ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መከሰስ ይኖርባታል እላለሁ። ይህቺ፣ የሰው ዘር በሙሉ በእግዜር ምስል ነው የተፈጠረው፣ ሁሉም እኩል ነው የምትለው ቤተክርስቲያን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሏት ከዋናዎቹ ሰበካዎች መካከል “የጋላ ሐዋርያዊ ሰበካ [በእንግሊዝኛ The Apostolic Vicariate of the Galla፣ በኢጣሊንኛ ደግሞ Vicariato Apostolico di Galla”] ይገኝበታል። ስድብ ቢሆን እንግዴህ፣ እንዴት ይህቺ ከቅድሳትም ይበልጥ ቅድስት ናት የሚትባል ቤተክርስቲያን፣ የራሷን ታማኞች ምእመናን በስድብ ስም “ጋላ” ብላ ትጠራቸዋለች። የማይታሰብ ነው። ዝቅተኝነት የሚያጠቃውና የእእምሮ ችግር ያለው ካልሆነ በስተቀር፣ ማንም ሰው መጠርያ ስምን እንደስድብ አያስብም። ስለዚህ ጋላ የሚለው ቃል ችግር ባለባቸው በፓለቲከኞች ጭንቅላት ካልሆነ በስተቀር፣ መጥፎነትን የማያመለክት ገለልተኛ መጠርያ ነው። ልክ ጋሎች ከእረኝነት ኑሯቸውና፣ ከሚያምኑበት እምነት የተለየ ኑሮና ሃይማኖት ያላቸውን፣ የጐረቤታቸውን ሕዝብ “ሲዳማ” ብለው ሲጠሯቸው፣ ተጠሪዎቹ እንዳልተቀየሙ ሁሉ፣ ሌሎችም እነሱን ጋላ ቢሏቸው የሚቀየሙበት ምክንያት አይታየኝም። እነሱም “ጋላ” ያሏቸው፣ ከባህላቸውና ከቋንቋቸው ጋር የማይጣጣም “ሌላ” ዐይነት ሕዝብ ስለሆኑ እንጂ፣ መሳደብ ፈልገው አይመስለኝም። እንደማንኛውም ሕዝብ፣ እነሱም ጐረቤታቸውን በቋንቋቸው ስም የመሰየም መብታቸው የተጠበቀ ነው። እብድ ካልሆነ በስተቀር ቀይሩ ብሎ የሚያስገድዳቸው የለም። እርስዎ ከመሳደብ ውጭ፣ ለምን “ጋላ” የሚለውን ቃል መጠቀም ከጥላቻ እንደሚቈጠር፣ ምንም ዐይነት ማስረጃ ስላላቀረቡልኝ፣ የኔን ትንተና በጸጋ እንደሚቀበሉልኝ ተስፋ አደርጋለሁ።

በመጨረሻ ላነሣ የምፈልገው፣ እርስዎ በንቀት መልክ አቡጊዳ የሚሉትን የአማርኛ ፊደል ነው። ላቲን ይበልጣል ማለትዎ ብቻ የሚያጠግብ መልስ ሊሆን አይችልም። ከላቲን በምን መልክ እንደሚተናነስም ከነማስረጃው ማቅረብ ይጠበቅብዎታል። ባያውቁት ይሆናል እንጂ፣ የላቲን ፊደል ራሱ ምንጩ ከአፍሪቃ ነው። ላቲንንም እንደቋንቋ እንዲገንን ያደረጉት የአፍሪቃ ጸሓፊዎች ናቸው። አዲስ ኪዳን ሲጻፍ፣ ሮማውያን የአይሁድን አገር ብቻ ሳይሆን አብዛኛውን ዓለም ይገዙ ነበር። ግን እነሱ ገዢዎች ቢሆኑም፣ በቋንቋቸው የተጻፈ የክርስቲያኖች ቅዱስ መጽሐፍ የለም። ክርስቶስ በዘመናቸው ኖረ ቢባልም፣ አዲስ ኪዳን ግን በቋንቋቸው አልተጻፈም። ታዲያ የተጻፈው በአረማይስጥና ያኔ ዓለም ይናገር በነበረው፣ ግን በሮማዉያን ሥር በነበሩት፣ በግሪኮች ቋንቋ ነው። ታላላቆቹ የአፍሪቃ ሊቃውንት እንደነጠርጡሊያኖስ፣ እንደነአውጉስጢኖስ ያሉት ናቸው እንግዴህ፣ ላቲንን በኋላ ለክብርና ለማዕርግ ያበቁት።

የአማርኛ ፊደል፣ ከማንኛውም አሁን ባለም ካሉት ፊደላት እንደሚሻል በጽሑፌ አሳይቻለሁ። ቫወል እያሉ በሁለት ፊደል ከመጻፍ፣ ባንድ ፊደል መገላገሉ እንደሚሻል፣ ዓለም በሙሉ ያውቃል። የተጻፈውን ፊደል አለአገባቡ ከማንበብ፣ እንደተጻፈው ማንበቡ እንደሚበልጥም አስረድቻለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ብሔራዊ ክብርና ኩራት አለ። በፊደል ብዛት የሺኖች (ቻይናውያን) ከማንም ይበልጣል። ሲቀለድ እንኳን ሺኖች ፊደላቸውን ሕይወታቸውን በሙሉ አጥንተው ሳይጨርሱት ነው የሚሞቱ ይባላል። በአውሮጳ ተማሪ ሳለሁ፣ መደጐሚያዬ በትርፍ ጊዜዬ አስተምር ከነበርሁት የቋንቋ ትምህርት ነበር። የክፍያው ልክ በቋንቋው አስቸጋሪነት መጠን ስለነበር፣ ከሁላችንም ዕጥፍ የሚያገኝ የነበረው የሺኑ አስተማሪ ነበርና በጣም እንቀናበት ነበር። ታዲያ፣ ይኸንን ያነሣሁልዎት አንድ ነገር ላሳስብዎት ነው። በቅርብ ጊዜ፣ የአውሮጳ ጋዜጠኞች የጃፓንን መሪ፣ ለምን አገርዎ ውስብስቡንና አስቸጋሪውን የሺንን ፊደል ትቶ፣ ቀላሉንንና ለሥራ ቀልጣፋ የሆነውን የላቲንን ፊደል አይጠቀምም ብለው ሲጠይቋቸው የሰጡት መልስ፣ የሺን ፊደል አስቸጋሪ መሆኑ ጠፍቶብን አይደለም፤ በደምብ እናውቃለን። ሺን የእስያ ሥልጣኔ ነው፤ ጃፓንም የእስያ አካል ናት። ስለዚህ እኛም እስያዉያን ነንና የእስያን ሥልጣኔ እንጂ የአውሮጳውያንን ሥልጣኔ የምንጠቀምበት ምክንያት አይታየኝም” የሚል ነበር።

እንደርስዎ ያለ ግን ወደሰባ ዓመት ገደማ፣ ባገኙት በዘመናዊ መሣርያ ኀይል ከሰው ዘር በሙሉ የበላይ ነን በማለት በድፍኑ ዓለም እንደልባቸው እየፈነጩ ነጭ ያልሆነውን የሰውን ዘር ያተራምሱ በነበሩበት ጊዜ፣ እርስዎን የመሰለውን ጥቁር ሕዝብ በሙሉ፣ ከዝንጀሮየማይሻሉ ፍጥረት ናቸው፤ ለሰው ዘር ሥልጣኔ ያደረጉት ምንም ዐይነት አስተዋፅዖ የለምና መጥፋት ያለባቸው የጐሦች ጥርቅምቅም ናቸው፣ ይሉ የነበሩትን ነጮች ከሚያደንቁት ጥቁሮች አንዱ ይመስሉኛል። “ላም ካራጇ ጋር ትውላለች” የሚለው ያገራችን ተረት ለርስዎ ዐይነቱ የተተረተ ይመስለኛል። የጃፓኑ መሪ ግን ይኸንን ታሪክ አብጠርጥረው ስለሚያውቁና፣ የሳቸውም አገር የነጮች ዕብሪትና ምንአለብኝነት ሰለባ እንደነበረች ስለተማሩ፣ የበቀል ስሜት ሳያሳዩ፣ ለጠያቂዎቻቸው የአውሮጳውያን ጋዜጠኞች፣ በጣም ጨዋ መልስ ነው የሰጧቸው። ከነቃና ከተማረ የሚጠበቀውም ይኸ ዐይነት ተግባር ነው።

እርስዎም በጥቁርነትዎ ክብርና ኩራት እንደሚሰማዎት አልጠራጠርም። በአገርዎና በሕዝብዎ ግን የሚኰሩ አይመስለኝም። እንግዴህ ነጮች ጥቁሮች አፍሪቃውያንን፣ ጊዜአቸው ያለፈባቸው የጐሦች ጥርቅምቅም እንጂ፣ ሕዝብ ስላልሆኑ፣ ቀይ ህንዶች የሚባሉትን የአሜሪቃን ተወላጆች እንዳደረጉ ሁሉ፣ አፍሪቃውያንንም አጥፍተው በነጭ ሕዝብ ለመተካት ሲሉ ነው ክፍለ አገሩን በሙሉ የቅኝ ግዛት ያደረጉት። ዓላማቸውን ያከሸፈችባቸው ኢትዮጵያ በልጆቿ ትብብር በአድዋ ላይ ባደረገችው ድል ነው። ያሸነፈችውም እንደሌላው የአፍሪቃ አገሮች የጐሣ ጥርቅምቅም ጦር ሁና ተዋግታ አይደለም። ሁሉም ተባብረው በኢትዮጵያዊነታቸው ብቻ ባንድ መሪና ሰንደቅ ዓላማ ሥር ተሰልፈው፣ እንዳንድ አገርና ሕዝብ በመዋጋት ነው። እንደሌሎቹ አፍሪቃውያን እያንዳንዱ ጐሣ በተናጠል ቢዋጋ ኖሮማ፣ የእኛም ዕጣ የመላዪቷ አፍሪቃ በሆነ ነበር። የጐሣና ያንድ አካባቢ ጦር ዋጋቢስ መሆኑን በትግራይ መሪዎች አይተናል። አንድ ጭብጥ የማይሞላ የኢጣልያን ጦር፣ ያኔ የትግራይ የበላይ ገዢ የነበሩትን የራስ መንገሻ ዮሐንስን ጦር ሠራዊት፣ ባንዳፍታ ድምጥማጡን አጠፋው። የኢጣሊያን ጦር በዚህ ቀላል ድል ልቡ ደንድኖ፣ የኢትዮጵያም ብሔራዊ ጦር ቢመጣብኝ፣ ጽዋው ከዚያ የከፋ ይሆናል ብሎ እየደነፋ ቈየ። ብሔራዊ ጦሩ ሲደርስ፣ በመጀመርያ የገጠመው ይኸንን ነበር።  ለቊርሱ እንኳን አልበቃም። የሞት ሽረት ፍልሚያ ቢገጥምም፣ ከመሪያቸው ጭምር አንድ ሳይቀር ተደመሰሰ። ቀጥሎም ዋናው ጦር ራሱ ልክ እንደዚያው ወደመ። አንድነታችን እኛን አኰራን፤ ከሁሉም ይበልጥ ደግሞ በዳርዊን የዘገም ለውጥ ሂደት እምነቱን ጥሎ፣ የላዕላይነት ስሜት በማራጋብ ጥቊርን ከአፍሪቃ ገጸ ምድር ሊደመስስ ያልም የነበረው የነጭ ዘር ቅዠት በነነ። አፍሪቃ ከጥፋት ዳነች፤ ኢትዮጵያም አለኝታዋና የነፃነት ተስፋዋ ጭላንጭል፣ የድሏ አረቦን ሆነች። ድሉ በእውነት የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ነጭ ያልሆነ የድፍኑ ዓለም ሕዝብ ሁሉ አርኬሳ ነበር።

አሜሪቃ የነጮች ሰለባ ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ ተሸንፎ የማያውቀው የነጮች የቅኝ ግዛት ጦር፣ አውሮጳዊ ባልሆነ ሕዝብ ለመጀመርያ ጊዜ በማያዳግም መልኩ ድል የሆነው በኢትዮጵያ ብቻ ነው። ቀጥላ ጃፓን ደገመችው። የእንደዚህ ዐይነት አስደናቂ ድል ፊታውራሪዎች እንደመሆናችን፣ በዚህ መኩራት አለብን። ይበልጥ ደግሞ የምንኰራው ሠራዊቱን እንደአንድ አገር ሕዝብ የሚያስተባብር አንድ ቋንቋ ባይኖር ኖሮ፣ የኢትዮጵያም ድል አጠያያቂ ሁኖ በቀረ። ስለዚህ አማርኛና የአማርኛችን ፊደል የአንድነታችን መግለጫ፣ የሥልጣኔአችን መለዮ፣ የታሪካችን ኩራት፣ የምንነታችን ክብር ነው። እንደሺኖች ፊደላት አስቸጋሪ አይደለም። እንደሮማውያን ደግሞ ከሌሎች አልተበደርንም። ጽሑፌ ሊያስረዳዎት የሞከረው እንግዴህ፣ ለዕድገቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አስተዋፅዖ ያደረገበት አገርበቀል ፊደል ስለሆነ፣ ካስፈለገ አሻሽለነው መጠቀም አለብን እንጂ መናቅ የለብንም ነው። የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ የመላ አፍሪቃ ሀብት ነው። ስለዚህም ነው እርስዎና እንደርስዎ የመሰሉት የጐሣ ታሪክ አቀንቃኞች ለነጭ ፊደል ሲያጐበጉቡ፣ ንቃት ያለው እንደየአፍሪቃ-ጠቅል ገናናው የጋና መሪ ንክሩማ መሰሎች፣ ከዋና ዕቅዶቻቸው ከነበሩት አንዱ፣ የአፍሪቃን አንድነት ለማጠናከር የአማርኛን ፊደል በመላ ጥቊር አፍሪቃ እንዲሰራጭና፣ በላቲን ፊደል ምትክ እንዲጠቀም የፈለጉት። የሥልጣናቸው ዘመን ባጭሩ ባይቀጭ ኖሮ፣ ፍላጎታቸውን በግብር እንደሚተረጒሙ አይጠረጠርም።

ከጽሑፍዎ እንደምረዳ ከሆነ፣ እርስዎ እንደጐረቤቶቻችን እንደኤርትራ መሪዎች፣ ትላንት ከአውሬ እንጂ ከሰው የማይቈጥርዎት የነበረውን ነጭ እንደሚያመልኩ፣ ግን ከነጭ ጨቋኝ እጅ ታድጋዎት ለወግና ለማዕርግ ያበቃችዎትን፣ አገርዎን ኢትዮጵያን እንደጨቋኝ በመቊጠር እንደሚሳደቡና እንደሚያዋርዱ ነው። ተረት የሚባለው እንደዚህ ዐይነቱ አስተሳሰብ እንጂ፣ በሐቅ ላይ የተመሠረተ የኔ ትንተና አይደለም። ሮም አውሮጳውያንን ከአረመኔነት አወጥታ ለሥልጣኔ እንዳበቃቻቸው ሁሉ፣ ኢትዮጵያም ከሮም በምንም መልኩ በማያንስ ሥልጣኔዋ፣ አብዛኛውን ሕዝብ ለታላቅ ሥልጣኔ አብቅታለች። እረኛ የነበረውን እርስ በርሱ ይፋጅ የነበረውን የጐሦች ጥርቅምቅም፣ በማእከላዊ መንግሥት ሥር አደራጅታ፣ ለታላቅ ማዕርግና ወግ እንዲደርሱ አድርጋለች። እንደዚህ ዐይነቱን እውነት የጐሣ ሥርዐት አራማጆች ሊውጡት የማይችሉት፣ ሊናገሩት የማይወዱት ሐቅ ነው። ግን ምን ይደረግ። ቀናቸው ሁኖ እንደድሮ ባላባቶች ሕዝባችንን እየከፋፈሉና እያወናበዱ፣ አንድነታችንን እያላሉ፣ ኩሩ ታሪካችንን እያንቋሸሹ፣ በቋንቋችንና በፊደላችን እያላገጡ ይገኛሉ። ወራዳ አቋማቸውን ለሚፋለም ግን ከመጮህና ከመሳደብ ውጭ ሌላ ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር የለም።

እርስዎ ከድፍረትዎ የተነሣ የትምህርቴንና የሙያዬን ብቃትንም እጥያቄ ውስጥ እስከማስገባት ደርሰዋል። ማወቅ ያቃተዎት ነገር ቢኖር፣ ከተወለድህበት አገር ወጥተህ በተማርከው መስክና ሙያ መቀጠር የትም ቢሆን አስቸጋሪ መሆኑን ነው። በምዕራብ ዓለም ከሆነ ደግሞ፣ ያገሩን ተወላጅ ቢያንስ በዐምስት እጅ ካልበለጥህ ዞር ብሎ የሚያይዎት እንደሌለ ማንም የውጭ አገር ምሁር ያውቀዋል። እንግዴህ እኔንም ማየት የሚገባዎት በዚያ መልክ መስሎኝ ነበር። እርስዎ ከሚያደንቁት ከጐሣዎ ምሁራን ስማቸውን ባልነግርዎትም፣ ጥቂቶቹን አሁን ወዳሉበት ደረጃ እንዲደርሱ በማድረግ የኔም እጅ እንዳለበት ይኸንን ዕድል በመጠቀም ልናዘዝልዎት እወዳለሁ። እንደርስዎና እንደአብዛኞቹ እርስዎን ከመሰሉት ስሜን በብርዕ ስም ሽፋን ሳልደብቅ በግልጽ የምጽፈው ደግሞ፣ በዕውቀቴና በሙያዬ ስለምተማመን ነው። ዕውቀቴና ድግሬዬ መስፈርቶቹን በማትረፍረፍ አልፈው አሟልተው የተገኙ እንጂ፣ እንደብዙዎቹ፣ በተለይም እንደአብዛኞቹ የአሁኑ መንግሥት ባለሥልጣኖችና ምሁራን ነን ባዮች፣ ከሸቀጥ ቤት የተገዙ አይደሉም። በዚህ አይጠራጠሩ። ምስክሮቼ የሠለጠንኩባቸው ተቋሞች ብቻ ሳይሆኑ፣ በየሄድሁበት የሠራኋዋቸው ሥራዎቼም ስላሉ፣ የርስዎን ስድብ ከምንም እንደማልቈጥር ይረዱልኝ።

ጽሑፍዎ ብዙ አላስፈላጊ ስድብ አዝሏል። እኔ ግን ሙያዬም አስተዳደጌም የርስዎን ዐይነት የብልግና ንግግር ስለማይፈቅዱልኝ፣ ከርስዎ ከፍ ብዬ እንጂ፣ እኩል ሁኜ ወይንም ዝቅ ብዬ ለመታየት ፍላጎትም ዝንባሌም የለኝም። በኛ አገር እንደርስዎ ዐይነቱን አሳዳጊ የበደለው ብለን እንደምናፍርበት ያስታውሱ ይሆናል። በፈረንጅ አገርም ቢሆን፣ የርስዎ ዐይነቱ ንግግር ከወሽከሬ እንጂ ከተራም ሰው እንኳን የማይጠበቅ አጸያፊ ነው። በነሱ ዘንድ፣ ይልቅስ እያንዳንዱ ሰው እንደየዝንባሌውና እንደየሙያ ብቃቱ የሚሠራበትና የሚወዳደርበት መስክ አለው። ለሁሉም ዕድል የሚሰጥ የሚደነቅ አገር ነው። መማታትና ጡንቻ የሚያምረው ወደBoxing ያመራል። ቊጣ ለሚያጠቃው ደግሞ የቊጣ መቈጣጠርያ ሰፈር አለ፤ ባልሳሳት በእንግሊዝኛ ቋንቋ “Anger Management” ይሉታል። እዚያ ሄዶ ቊጣውን እንዴት መወጣትና መቈጣጠር እንደሚገባው ይማራል። ከባዶ ተነሥቶ ተሳዳቢም ቢሆን፣ ወይ ስድብ እየተጠቀመ ሌላውን ለማዝናናት ወደሚችልበት ወደኮሚክነት ሙያ ይገባል፤ ካልሆነለት ደግሞ እንደአዲስ አበባው የአማኑኤል ሆስፒታል ወደመሰለ የአእምሮ ቀውሶች መታከሚያ ቤት ያመራል። ለርስዎም ስድብ ዐመልዎ ከሆነ፣ ከነዚህ አንዱ ሳይስማማዎት አይቀርም ይሆናል። ምርጫው የርስዎ ነውና ቢያስቡበት መልካም ነው።

ይሁንና ከላይ እንደገለጽክሁልዎት ድረገጾች የተቋቋሙት፣ ባገር ጉዳይ አሳብ እንድንለዋወጥ፣ እንድንማማር፣ እንድንተናነፅ እንጂ ለመሰዳደብ አይደለም። ስድብ የደደቦች መሣርያ መሆኑን እንደሚያውቁት አልጠራጠርም። ጅሎች ከዝቅተኝነት ስሜታቸው የሚመጣባቸውን ፍራቻቸውንና የብቃት ጉድለታቸውን የሚወጡበት በስድብ ስለሆነ፣ ርሱም የተሳዳቢውን የብቃትና የችሎታ ማነስ ነው የሚያመለክተው። ለማዳ ያልሆኑ የዱር አውሬዎች የሚፈሩትን በጉልበታቸው ለማጥቃት፣ አፋቸውን ከፍተው፣ ሊነክሱም ሊገድሉም እንደሚሮጡ ሁሉ፣ ደደቦችም የሚያደርጉት ልክ እንደነሱ ነው። ጭንቅላትና በትምህርት የተገራ አእምሮ ያለው ግን፣ መልሱን በጨዋነትና በብልሃት ይሰጣል። ካልመሰለውና ዐቅም ቢያንሰው፣ ታዝቦ ያልፋል እንጂ ከቶ አይሳደብም።

ቸር ይግጠመን።