ስለነገው የአዲስአበባ ሰልፍ ሳስብ የቻይና ባምቡ ወይም ቀርከሃ ዛፍ ታወሰኝ (ያሬድ ጥበቡ)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


yared 3ያሬድ ጥበቡ

የቀርከሃ ዛፍ ፍሬ ከተተከለ በኋላ ለአራት አመታት ከትንሽ እምቡጥ ቅጠል በቀር ምንም እድገት አያሳይም ። ተካዩ እነዚያን ሁሉ አመታት በተስፋ መጠባበቅ አለበት ። አንድ ቀን ሳይታሰብ ያቺ እምቡጥ ወደሰማይ መመዘዝ ትጀምራለች ። እነዚያን ከአፈር በላይ ያላደገችባቸውን አራት አመታት ከአፈር በታች ስታድግ፣ ስትመነደግ፣ ስትስፋፋ ስለኖረች እድገቷ እጅግ ፈጣን ነው ። በአማካይ 80 ጫማ ከፍታ ወይም 24 ሜትር ሽቅብ ትመነደጋለች ። ለካስ 4 አመት ሙሉ 24 ሜትር ቁመት ያለው ዛፍ ለመሸከም የሚያስችል ሥር ስትገምድ ነው የከረመችው ።

በቃ! ለኔም የአዲስ አበባ ሰልፍ እንደ ቻይና የባምቡ ዛፍ እድገት መስሎ ተሰማኝ ። ልዩነቱ አራት አመታት ሳይሆን የጠበቅነው 25 አመታትን ነው፣ ሩብ ክፍለዘመን ነው ። ታላቅ ቧጋችነትና ቻይነት ለአለምም ሆነ ለራሳችንም አሳይተናል ። ዝግጅቱ 25 አመታትም የወሰደብን ያለምክንያት አልነበረም ። በመሃላችን የነበረውን የኢትዮጵያዊነት ድልድይ ሰብሮ፣ እርስ በርስ በጥርጣሬ እንድንተያይ ያደረገን ዘረኛ ሥርአት መንግስታዊ ስልጣኑን ጨብጦ ስላዳከመን ነበር ። የጥርጥሬንና የፍርሃትን ገደል ተሻግረን ለመተማመንና ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈን አብረን ለመቆም ብዙ ጭንቀት፣ ብዙ እንቅልፍ አልባ ሌሊቶች፣ ብዙ እርስ በርስ ያለመተማመን አመታት አሳልፈን ይሄው ከዚህ ደርሰናል ። በዳያስፖራ ያሉ ወገኖቻችን የኢትዮጵያንና የገዳ ኦሮሞን ሰንደቅ ጎን ለጎን ተሸክመው፣ በአለም ህዝብ ፊት ሲሰለፉ አኩርተውናል ። የክፍፍልና ጥርጥሬ ዘመን አከተመ፣ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ተደገመ ሲሉን ጆሮ ሰጥተን አድምጠናቸዋል ። አዲስ አበባም የሚሆነው እንደዚያው ነው ። ተከፋፍለን ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዜግነት የወረድነበትን የ25አመታት የውርደት ህይወት ላንመለስበት ቆርጠን ተነስተናል ።

አለመተማመን፣ ጥርጣሬና ፍርሃታችን ሁላችንንም ለሁለተኛ ደረጃ ዜግነት እንደዳረገን ተረድተናል ። በሃገራችን ላይ የበይ ተመልካች ሆነናል ። በዘመናዊነት ስም ከቀዬአችን ነቅለውን ከከተማው ጥግ ሲወረውሩንና እነርሱ በመሬታችን ላይ ሰማይጠቀስ ሲሰሩበት፣ በአርምሞ ተመልክተናል ። ሆኖም ቤታችንን ብቻ ሳይሆን የደረመሱት፣ ማህበራዊ ትስስሮቻችንን ጭምር ነበር ። የዘመናት ጎረቤቶች አብረን እንዳንኖር ተበትነናል ። ይህ ሁሉ አበሳ የደረሰብን በ1997 ምርጫ ለቅንጅት ባደረግነው ድጋፍ መሆኑንም እናውቃለን ። ሊበትኑንና ማህበራዊ ኢንጂነሪንግ ሊያካሂዱብን ወሰኑ ። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አዲስ ሰፋሪዎች አምጥተው አሰፈሩብን ። በሎተሪ በሚያድሉን ፎቆች ውስጥ ተጠቃሚዎቹ መጤዎቹ ከመሆናቸው አልፎ፣ ከአጋዚ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው አስተኳሾች ሆነው ተሾሙብን ። ከተማህን በመሰረተ ልማት ስላሳደግናት አሜን ብለህ ተቀበለን ፣ ሆድህ ባይሞላም ዓይንህ የኛን ፎቆችና የሴቶቻችን ሹሩባ ላይ የተነሰነሰውን የወርቅ እንክብል እያየ ይደሰት ፣ አትመቅኝ ብለው አላገጡብን ።

እንዴት እንዲህ ይሆናል የአንድ ሃገር ዜጎች ሆነን? ብለን ስንጠይቅ፣ “የባሰ ይጠብቅሃል፣ ለኦሮሞ አስረክበንህ ነው ወደመጣንበት የምንመለሰው” እያሉ ሲያስፈራሩን ኖረዋል ። አምነናቸው ነበር፣ ሆኖም የበታችነቱ ሲበዛብን፣ የነርሱም ዘረኝነትና ጥጋብ ልንሸከመው ከምንችለው በላይ ሲሆን አንድ ጥያቄ አበክረን ራሳችንን ጠየቅን ። “ኦሮሞ ቢመጣ ከሁለተኛ ደረጃ ዜግነት ባነሰ ምን እንዳያደርገን ነው ፣ እንዲህ በፍርሃት ተዋርደን የምንኖረው?” ብለን ። መልሳችንም እምቢ ለፍርሃት ሆነ ።

የኦሮሞ ህዝብ ባለፉት 25 አመታት በወያኔ አገዛዝ ሲቀጠቀጥ የኖረ ህዝብ ነው ። ታላቅ መስዋእትነትም ከፍሏል ። የትግሉም ዋነኛ መንስኤ “ሁለተኛ ደረጃ ዜግነት አልቀበልም” ማለቱ ነው ። የመሬቴ ባለቤትና ተጠቃሚ እኔው ልሆን ይገባል ነው ። ከቀዬ አልነቀልም ነው ። ከኦሮሞ ህዝባችን ጋር በደላችን ተመሳሳይ ጥያቄአችንም አንድ ነው ።እኛም በሃገራችን ላይ ሁለተኛ ደረጃ ዜግነትን ወይም ውርደትን አንቀበልም ነው የምንለው ። ይህንንም በፍፁም ሰላማዊነት ለማስከበር ቆርጠን ተነስተናል ። ባትተኩሱብንም እንወዳለን ።

የህዝብን ሰላማዊ ጥያቄ ግን በግድያ እናቆማለን ካላችሁ ምርጫው የናንተ ነው ። ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ ሆነን ከምንኖር፣ በጥይታችሁ ልንሞት ቆርጠናል ። ለሞት የቆረጠ ህዝብ ደግሞ ተሸንፎ አያውቅም ። ማሸነፉም አይቀሬ ነው ። ሰላማዊን ህዘብ በጨፈጨፋችሁ ቁጥር ግን ችግሩን በሰላምና በእርቅ የመጨረስ እድሉን ግን እያጠፋችሁ መሆኑን እንድትገነዘቡት እንፈልጋለን ። መጨረሻችሁ ያማረ አይሆንም ። ለልጆቻችሁ ስትሉ የሰላምና የእርቅን መንገድ ተከተሉ ። በሰላም ጥያቄዎቻችንን የማቅረብ መብታችንን ተቀበሉ ። የመፍትሄው አካል የመሆን እድል አላችሁ ። አታበላሹት ። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በሰላማዊ ህዝብ ላይ ተኩሳችሁ እልቂት ብትፈጥሩ ተኳሽ፣ አስተኳሽ፣ እዝ ሰጪ፣ ፖሊሲ አርቃቂ ወዘተ ለፍርድ የምትቀርቡበት ቀን ሩቅ አይሆንም ። ግን እዚያ ጋ መዳረስ የለብንም ። ራሳችሁን አስተካክላችሁ የመፍትሄው አካል ሁኑ ። ከዘረኝነት ፣ ከጥጋብ፣ ከእብሪት የሚገኝ ምንም ደግ ትሩፋት የለም ። በዚህ የፍፃሜው መጀመሪያ ደቂቅ ላይ ፣ ፈጣሪ ቀናውን እንዲያሳያችሁ ፀሎታችን ነው ። እባካችሁ ተለመኑ ።