ጂንካ ህዝባዊ እምቢተኝነቱ – የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት /ኦህዲኅ/ ም/ሊቀመንበር ‹ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ› ተሰጣቸው


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የኦህዲኅ ም/ሊቀመንበር ‹ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ› ተሰጣቸው // ዛሬ ነሃሴ 14/2008 ዓ.ም ከሰዓት በፊት የድርጅታችን የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት /ኦህዲኅ/ ም/ሊቀመንበርና የዞኑ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዓለማሁ መኮንን በዞኑ ፖሊስ አዛዥ ቢሮ ተጠርተው ዘጠኝ የሲቪልና ሚሊቴሪ ባለሥልጣናት በተገተኙበት የማስፈራራት ሙከራ እንደተፈጸመባቸውና ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ታውቋል ፡፡ የማስፈራራቱና ማስጠንቀቂያው ጭብጥ ‹‹ በሌሎች አካባቢዎች እንደሚደረገው በዞናችን አንዳች ነውጥ ቢከሰት ከአንተ ራስ አንወርድም፤ ይህን ለማድረግ አቅም ያለው ከአንተ ሌላ የምናውቀው በወረዳዎች መዋቅር ያለው ማንም የለም፡፡ ስለዞናችንም የተለያዩ መረጃዎች የሚወጣው በአንተ በኩል ነው፡፡ ስለዚህ ደግመን ደጋግመን የምናስጠነቅቅህ በዞናችን አንዳች ብጥብጥ ቢነሳ ከአንተ ራስ እንደማይወርድ ነው፡፡›› የሚል ነው፡፡ ከነዚህ ባለሥልጣናት የዞኑ ፖሊስ አዛዥ- ኮ/ር ሸጎሌ ሾዴ፣ የዞኑ ሚሊሺያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ አርገው፣ የከተማው ፀጥታና ፍትህ ተጠሪ አቶ ካሣሁን አባይነህ፣ የከተማው ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ሹም ኮ/ር ተፈራ ሥዩም፣ የዞኑ – ደህንነት ተጠሪ፣ – ልዩ ኃይል ሃላፊ ኮማንደር፣ እንዲሁም በቅርቡ ወደዞኑ የመጣው የፌደራል ፖሊስ ቺፍ፣ ይገኙበታል፡፡ አቶ ዓለማዬሁም ፡- ‹‹ በድርጅቴም ሆነ በግሌ በነውጥና በሃይል የሚመጣ የመንግስት ለውጥ አናምንም፡፡ ድርጅታችን በአደባባይ ‹‹ ይህ የአገዛዝ ሥርዓት በአገሪቱ ያለውን ምስቅልቅል ፖለቲካዊና ማኅበረ-ኢኮኖሚ ጥያቄዎች ሊሸከም አልቻለም፣ አይችልም፡፡ ላለንበት ተጨባጭ ሁኔታና ከህዝብ ለሚነሱ ህገመንግስታዊ የመብት ጥያቄዎች የተለመደው አፈናና የኃይል እርምጃ መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡ ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሄው በሰላማዊ ህዝባዊ ትግላችን የብሄራዊ መግባባትና ዕርቅ አውርዶ በአካታች የሽግግር መንግስት መመስረት ነው፡ ›› ብለን ግልጽ አቋማችንን በተደጋጋሚ አሳውቀናል፡፡ በህዝቡ የሚደርሰውን በደልና የመብት ረገጣ በምናገኘው መገናኛ ብዙሃን መግለጽ፣ ህዝቡ ለህገመንግስታዊ መብቱ እንዲታገል ማደራጀት፣ ማንቃት ፣ ለህዝብ መረጃ ማቅረብ፣ ከህዝብ ለሚቀርብ ጥያቄ የድርጅታችንን አቋምና መደረግ ስላለበት ምላሽ መስጠት የመሪዎች ብቻ ሳይሆን የአባላትም የየዕለት ተግባራችን ነው ፤ በዚህም እንቀጥልበታለን ፡፡ ከዚህ ውጪ ለመብት መታገልና ጭቆናን መቃወምም ሆነ በፈጠራ ውንጀላ መታሰር የጀመርኩት ገና በወጣትነት ዕድሜዬ ነው፤ አሁን በቅርቡ በዚሁ መንገድ በታሰርኩበት ወቅት ከፌደራል ለመጡ መርማሪዎችና ደህንነቶችም ይህን ግልጽ አድርጌ ነግሬአቼዋለሁ፡፡ እናንተ የህዝብን ሠላማዊ ጥያቄ መመለስ ሲያቅታችሁ ለአፈና የቱንም እርምጃ እንደምትወስዱ አውቃለሁና ይህ እኔን አያስፈራኝም፣ የምታገለውም ይህ ኢህገመንስታዊ የአፈና አካሄድ እንዲስተካከል፣ ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ነውና ከሰላማዊ ትግላችን ወደኋላ አያደርገንም፡፡ ለማስጠንቀቂያውም ከስጋታችሁ ውጪ በተጨባጭ የነገራችሁኝ ነገር የለም፡፡ ›› በማለት መልሰዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በቅርቡ የሚታየውን የባለሥልጣናት ስጋትና ለዚህም አፈናን እንደመፍትሄ መውሰድ አስመልክቶ በዞኑ ዋና ከተማ በጂንካ ከምሽቱ 3 ሰዓት እስከንጋት 12 ሰዓት የባጃጅ እንቅስቃሴ መታገዱን ከህዝብ የተደበቀው ሥጋትና የህገመንግስት ጭፍለቃ በደቡብ ኦሞ፤ እንዲሁም የተወካዮች ም/ቤት አባል የጠሩትን ስብሰባ አብዛኛው ተሰብሳቢ ረግጦ መውጣቱን በሚመለከት በደቡብ ኦሞ–ጂንካ ህዝባዊ እምቢተኝነቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል // በሚል ርዕስ በመገናኛ ብዙሃንና በማኅበራዊ ድረገጽ መገለጹ ይታወሳል፡፡ ስለአጠቃላይ የዞኑ ጸጥታና በህዝቡ እየተነሱ ስላሉ ጥያቄዎችና ስለህዝቡ ስሜት እንዲሁም በድርጅቱ መሪ/ዎች ላይ እየተፈጸመ ስላለው ሁኔታ ፣ የጠየቅናቸው የኦህዲኅ ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ ‹‹ ይህ ኢህአዴግ በውስጡ ችግር ሲከሰት፣ የህዝብ ሰላማዊ ጥያቄዎች በየመድረኩ ሲያጨናንቁት፣ ህዝቡ ለመብቱ ሲነሳ፣ህዝባዊ እምቢተኝነቱ ሲጠናከር … የሚፈጠርበትን ድንጋጤና ስጋት ለማፈን የሚጠቀመው የተለመደው የአፈና አካሄድ ነው፡፡ የዞናችን ህዝብ የሚፈጸምበትን ኢህገመንግስታዊ የመብት ጥሰትና አፈና በቃኝ ካለ ቆይቷል፡፡ ይህ በሌሎች የአገራችን ክፍሎች በተለይም በኦሮሚያና አማራ ህዝብ እየታየ ያለው የተባበረ አደባባይ የዋለ ህዝባዊ እምቢተኝነት ወደ ዞናችን እንዳይገባ ብለው የሚፈጽሙት የማዋከብ ህገወጥ ተግባር ነው፡፡ ይህን በዞናችን ያለው ህዝብም ሆነ የድርጅታችን አባላት በሙሉ የነቁበትና ጆሮ የማይሰጡት ነው፡፡በየመድረኩ የሚንጸባረቀውና አስተዳደሩን መቆሚያና መቀመጫ ያሳጣው ተቃውሞ/ የህዝቡ እምቢተኝነትም ትግሉ ወደ ህዝቡ መድረሱንና ህዝብ ባለቤትነቱን መቀበሉን የሚያመለክት ነው፡፡ ስለዚህ የተያያዝነው ሰላማዊ የህገመንግስታዊነት ትግል – በቅድሚያ ህገመንግስቱን ማክበርና ማስከበር ያለበት መንግስት ህገመንግስቱን መጨፍለቁን እንዲያቆምና ለህዝቡ ጥያቄዎች ጆሮ እንዲሰጥ … በመሆኑ ከምናደርገው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ይህ ዓይነቱ ህገወጥ ማስፈራሪያ፣ ማስጠንቀቂያና ወከባ ህዝባዊ ትግሉን አይቀለብሰውም፣ አያስቆመውም፡፡ ድርጅታችንን ከሰላማዊ ትግሉ ቅንጣት ወደኋላ እንዲያፈገፍግ አያደርግምና ከህዝባችን ጋር ያለንን ግንኙነት አጠናክረን፣ ከሌሎች ድርጀጅቶች ጋር ተባብሮ ለመስራት በተጀመሩ ጥረቶች በንቃት በመሳተፍና ባለን አቅም ሁሉ የድርሻችንን አስተዋጽኦ በማበርከት ህዝባዊ ትግሉን ወደፊት ከመግፋት ለዚህ ማስፈራሪያ የምናባክነው ጊዜ የለም፡፡ ይልቁንም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ራሳቸውን ከህወኃት ተላላኪነት ነጻ ስለሚወጡበት፣ የህወኃት አምባገነኖችም የከፋፍለህ ግዛ ሴራቸው ያለመስራቱን ተቀብለው ቆም ብለው ለማሰብ የሚያስገድድ ወቅት ላይ መሆናቸውን መረዳት ከእኛ በላይ እነርሱኑ ተጠቃሚ ስለሚያደርግ ልብ ያለው ልብ ይበል እንላለን፡፡ ›› በማለት አስረድተዋል ፡፡