ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ በወቅታዊው የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያስተላለፉት እጅግ ጠቃሚ መልዕክት


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ካፈራቻቸው በአሁን ጊዜ በሕይወት ከሚገኙት እጅግ በጣም ጥቂት ሊቃውንት አንዱ የሆኑት ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ በተለያዩ ርዕሶች በተለይም በቤተክርስቲያናችን ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ አስመልክተው የተለያዩ ጦማሮችንና መጣጥፎችን ለንባብ እንዳበቁልንና እንዳስተማሩን ይታወቃል። ቀሲስ አስተርአየ በቤተክርስቲያንና በምዕመናን ላይ በአጠቃላይም በአገር ላይ እየደረሰ ያለው ፍጅትና ውድመት እንዲገታ ከመጮህና ከመማጸን ወደ ኋላ ብለው አያውቁም።

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ውስጥ በአሁን ዘመን ቁጥራቸው እጅግ በጣም ጥቂት የሆነ እውነተኛ መምህራንና ካህናት መኖራቸው አይካድም። ሆኖም አብዛኛው ለወያኔ “ይደልዎ” የሚል፣ ነፍሱን ለስጋው የሸጠ፣ ለመንግስተ ሰማያት ሳይሆን ለህንጻ፣ ለገንዘብና ለጥቅም ያደረ አስመሳይና አወናባጅ “ካህንና መምህር” ነኝ ባይ ብቻ ነው።  ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አባ ገብረመድኅን (አቡነ ጳውሎስ) የወያኔንን የበላይነትና ገዥነትን አስጠብቀው ለማቆየት በጎሳ በሽታ ተለክፈው”መንፈሳዊ ኮሌጅ” ከሚባለው ማሰልጠኛ ጣቢያ “መምህር” የሚል የሃሰት ታርጋ እየለጠፉ በመላው ዓለም ማዕዘናት በሚገኙ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ውስጥ አሰርገው ያገቧቸው ቁጥራቸው በቀላሉ ለመገመት አዳጋች የሆነ ካድሬዎች፤ የምዕመናንን ህሊና በማደንዘዝ ከቤተክርስቲያኒቷ እምነት በተጻረረ መልክ በሚረጩት መርዝ ሁሉቆ መሳፍርት የሌላቸውን ምዕመናን ወደ ገደል ይዘው እየነጎዱ ይገኛሉ። በአባ ገብረ መድኅን የተጀመረው ካድሬዎችን በቤተክርስቲያን ውስጥ መሰግሰግ አሁንም በአባ ማቲያስ ዘመንም ቀጥሏል።

እነዚህ መምህራን ነን ባዮች ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል” እንደሚባለው ካህንና መምህር ለመሆን ንጽህናው፣ዕወቀቱና ብቃቱ ሳይኖራቸው በድፍረትና በንቀት ቤተክርስቲያንን እያረከሱና እያዋረዱ ይገኛሉ። ንጽህናውና ብቃቱ ስለሌላቸው ነው እንጅ የዕወቀት ራቁትነታቸውን አንኳ በትምህርት ሊሸፍኑት በቻሉ ነበር ። በተለይም የቤተክርስቲያኒቷ ቋንቋ የሆነውን ግዕዝን ከጥራዝ ነጠቅነት ባለፈ ሁኔታ መናገርና መጻፍ የማይችሉ ደፋሮችንና አታላዮችን ምዕመናን ተሸክመው እንዲሄዱ በወያኔ ተፈርዶባቸዋል። ሳይማር የጠመጠና ማዕረጉን፣ጥቅሙንና ክብሩን አለይሉኝታ ሲቀበል የነበረ ካድሬ እንዴት አድርጎ ጉድለቱና ጥፋቱ ይታየዋል? በአሁን ሰዓት ለአገርና ለወገን መጸለይ፣ “በግፍ የታሰሩ ይፈቱ” ብሎ መጮህ፣ በጎሳቸውና በማንነታቸው ምክንያት የጥይት እራት ለሚሆኑት መቆርቆር፣ “ንጹሃን ወንድምና እህቶቻችን ላይ የሚፈጸመው ሰቆቃ ይቁም” ብሎ መናገር እንዲሁም “ስደት መፍትሄ ይሰጠው” ብሎ መማጸን በዘመኑ ካድሬ መምህራን አንደበትፖለቲካ” የሚል ጥላሸት እየተቀባ ሰው ለራሱ ብቻ እንደ ጅብ ሆዱን ብቻ እንዲመለከት እየተሰበከና እየተቀሰቀሰ ይገኛል።

ይህንን መርዘኛ የሆነና ህጸጽ የሞላበትን ወያኔን ስልጣን ላይ ለማቆየት በካድሬ መምህራን አንደበት የሚሰራጨውን የክህደና የእርግማን ቅስቀሳ በማጋለጥና አጸፋውን በመስጠት ምዕመናንን ከጥፋት ለመታደግ ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ግምባር ቀደሙን አስተዋጽኦ እየበረከቱ ይገኛሉ። አሁንም ወቅታዊ የቤተክርስቲያናችንን ሁኔታ አስመልክተው የሰጡትን ትምህርት አቅርበንላችኋልና ልብ ብላችሁ ተከታተሉት።