በጸረ-ወያኔ ስም ዘረኝነትን መርጨት ወያኔያዊነት ነው – ‪#‎ግርማ_ካሳ‬


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


12778986_10208493380322780_8820881662972165283_o

“ለኔ ህወሓት ማለት ህዝብ ነው፣ ሌላ አይደለም። እኔ የሚገባኝ ህወሓት የለችም ማለት የትግራይ ህዝብ የለም ማለት ነው፤ ስለዚህ ህወሓት ማለት ህዝብ ነው”

ይሄን የተናገረው በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚያ፣ በአማራው ክልል እና በአዲስ አበባ ቀጥታ መመሪያና ትእዛዝ እየሰጡ የሚያስገድሉ ጥቂት የሕወሃት ሰዎችን ካቀፈው፣ ራሱን የአገር ደህንነት እና የጸረ-ሽብር ግብረ ሃይል ብሎ ከሚጠራው አሸባሪ ቡድን መካከል በቀንደኝነት የሚጠቀሰው ሳሞራ (መሐመድ) የኑስ ነው።

የቀድሞ የአየር ሃይል አዛዥ ፣ ጀነራል አበበ ተክለሃይማኖት፣ “ ህወሃት ማለት የትግራይ ህዝብ ነው የሚለው አነጋገር ፀረ ህዝብነቱ የሚጎላው ፀረ ሕገ መንግስታዊ ይዘቱ ስንረዳ ነው …… አንድ ኢታማዦር ብድግ ብሎ ህወሓት ማለት የትግራይ ህዝብ ነው ሲል ያሳፍራል” ሲሉ ለሳሞራ ምላሽ ሰጥተዋል።

ህወሃትን እና የትግራይ ህዝብን በተመለከተ፣ ሰሞኑን በሶሻል ሜዲያዎች ብዙ እየተባለ ነው። ሕወሃት በጎንደር እና በኦሮሚያ እየፈጸመ ያለውን ፍጹም አረመኔያዊ የጭካኔ ተግባራትን በመመልከት ፣ በዉጭ አገር ያሉ የህወሃት አገዛዝ የጥቅም ተጋሪዎች የሚናገሩትን እና የሚጽፉትን ጸያፍና ዘረኛ አባባሎችን በማየት ከመናደዳችን የተነሳ፣ አንዳንዶቻችን ማሰብ የማንፈልገውን ወደ ማሰብ የደረሰን ወገኖች አለን።

ስሜቱን በሚገባ እረዳዋለሁ። ይገባኛል። ግን መናደዳችን፣ መበሳጨታችንን መቆጣታችን ወደ ማያስፈለግ ጥግ እንዲወስድን ልንፈቅድለት አይገባም። መናደዳችን የበለጠ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የዘረኝነትን እና የጥላቻን ስር ለመንቀል ትግሉን እንድናጠናክር ሊገፋፋን ይገባል እንጂ፣ ለችግራችን እና ለመከራችን መጀመሪያዉኑ ምክንያት ወደ ሆነው ወደ ዘረኝነት ሊወስድን አይገባም። በሕወሃትና ጀሌዎቹ በአንድ ብኩል በጭቁኑ የትግራይ ሕዝብ በሌላው በኩል ያለዉን ልዩነት መረዳት ካልቻልን፣ ወገኖቼ አረመኔው ሶሞራ የተናገረውን ተቀብለናል፣ እንደርሱ ሆነናል ማለት ነው።

ጀነራል አበባ አንድ ነገር አልካዱም። የትግራይ ሕዝብ እና ህወሃት አንድ አለመሆናቸዉን ካስረዱ በኋላ፣ “ የትግራይ ህዝብ ህወሓትን ፈጠረ እንጂ ህወሓት የትግራይ ህዝብን አልፈጠረችዉም” በማለት ሕወህት የመጣው ከትግራይ ህዝብ እንደሆነ ይገልጻሉ።

ልክ ነው ነው ሕወሃቶች የትግራይ ሰዎች ናቸው። ግን የትግራይ ሰዎች በሙሉ ግን ሕወሃቶች አይደሉም። ስለዚህ የጅምላ ፍረጃ ደካማነት ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነው። በአስቸኳይ መቆም አለበት። ዘረኛዉን ሕወሃት ስንታገል የሕወሃት ትሬድ ማርክ (መለያ) የሆነውን ዘረኝነትንም አብረን መመከትና መዋጋት አለብን። ራሳችንን ለበሽታ አናጋልጥ። በሽታ ለሚያስራጩትም ጆሯችንን እንስጥ።

ይሄን ብዬ በኦሮሚያ ወደ ዘጠኝ መቶ ሰዎች በሕወሃቶች በጭካኔ ሲጨፈጨፉ፣ በባህር ዳር በአንድ ቀን ብቻ ከ70 በላይ ዜጎች እንደቅጠል ሲረግፍ ፣ አሁንም በሕወሃቶች፣ ምንም ያልመሰላቸውና ምንም ያላሉ፣ ሰሞኑን የሕወሃት ታጣቂዎች ላይ እርምጃ በመወሰዱ ትግሬ ላይ ጥቃት ደረሰ ብለው ጩከት ያበዙ አሉ።

ለነዚህ አንድ መልእክት አለኝ። በርግጥ ለትግሬው ማህበረሰብ የምታስቡ ከሆነ ሕወሃትን ታገሉ። አብርሃ ደስታ በግልጽ አስቀምጥቶታል። ለትግራይ ሕዝብ ባስተላለፈው መልእክት “እመነኝ ባንተ ስም የሚነግዱ ኤርትራውያን የህወሓት መሪዎች፣ መጀመሪያ አገሪትዋን ካለ ወደብ እንድትቀር፣ ቀጥሎም በኢትዮጵያን መካከል መፈቃቀር እንዳይኖር በጎጥና ባከባቢ በመከፋፈል የዘረኝነት መርዝ ሲረጩ ቆይተው፣ በመጨረሻው ሰኣትም የትግራይ ህዝብ በሁሉም እንዲጠላና እንዲገለለ ኣበክሮ እየሰሩ ይገኛሉ” ሲል ነው የትግራይ ሕዝብን ከመቼዉም ጊዜ በላይ በኦሮሚያና በአማራው ክልል ካለው ሕዝብ ጋር በመቆም ሕወሃትን መታገል እንዳለበት ያስገነዘበው።

የሕወሃት ዘረኛ ስርዓት የኦሮሞዎች ጠላት ነው። የአማራዉም ጠላት ነው። የጉራጌው ጠላት ነው። የጋማቤላው ፣ የወላይታው ፣ የቅይጡ፣ በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ መታወቅ የሚፈለገው ጠላት ነው። የትግሬዉም ጠላት ነው። የኢትዮጵያዊ ሁሉ ጠላት ነው። የሕመማችን፣ የችግራችን፣ የደም መፋሰሳች፣ የመከፋፈላችን መንስኤው ሕወሃት ነው። ሕወሃት እስካለ ድረስ ሰላም የለም። ሕወህቶች መሄድ አለባቸው። ለዚህ ሁልችንም በጋራ፣ በአንድነት፣ እናንተና እኛ ሳንባባል እንነሳ። አራት ነጥብ።