ትግሉ የህዝብ ነው ፣ «ከተጋድሎው ጀርባ እኛ አለንበት» ለሚሉ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ይድረስ በአንድነት ስም እየተንቀሳቀሳችሁ ላላችሁ አገር አቀፍ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪል ተቋማት ባላችሁበት

ከአቻምየለህ ታምሩና ከሙሉቀን ተስፋው

እንደምታውቁት ከሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የአማራ ህዝብ ከፋሽስት ጥሊያን በላይ የከፋ ከሆነው ጨካኙ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር ጋር ፊት ለፊት ገጥሞ እየተጋደለ ይገኛል። ባሁኑ ሰዓት አማራው እያደረገ ያለው ተጋድሎ ወደኋላ ላፍታ እንኳ ቢመለስ ህዝባችን የከፋ ግፍና መከራ ላይ በእርግጠኛነት ሊወድቅ እንደሚችል ቂመኛውን ወያኔ የሚያውቅ ሁሉ ያውቀዋል። ስለሆነም እየተካሄደው ያለው የአማራ ተጋድሎ የተከፈለው መስዕዋትነት ተከፍሎ ወደፊት መሄድና ማደግ አለበት እንጂ ወደኋላ ሊመለስ አይገባም።

የአገራችንን ሁኔታ ለሚከታተል ሁሉ ግልጽ እንደሆነው በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ በሳልሳዊ ቴዎድሮስ ወይንም በኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ችቦ ለኳሽነት የተጀመረው ይፋዊ የአማራ ተጋድሎ በአሁኑ ሰዓት ጎጃምን አዳርሶ ወደ ሸዋና ወሎ ተሸጋግሯል። ትናንትና በወልቃይት አማሮች የተለኮሰው የአማራ ተጋድሎ ችቦ አድማሱን አስፋፍቶ ዛሬ ላይ መላውን የአማራ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር አነቃንቋል።

ባለፉት ሶስት ሳምንታት በጎጃምና በጎንደር የተካሄደው የአማራ ተጋድሎ በቅርበት ለተመለከተ ተጋድሎው አላማውን እያሳካ፤ ህዝባዊነትን ተላብሶ እንደሰደድ እሳት እየተስፋፋ ስለመሆኑ ነጋሪ አያሻውም። ይህ ታሪካዊ ተጋድሎ በዚህ ፍትነት ሲስፋፋና ውጤታማ ሊሆን የቻለው የአማራው ህዝብ እያካሄደ ያለው የፖለቲካ ሳይሆን የህልውና ትግል በመሆኑ ነው። በዚህ የአማራ የህልውና ተጋድሎ ጀርባ የተሰለፉም ሆነ ተጋድሎውን ከፊት ሆነው እየመሩ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሆኑ ግለሰቦች የሉም። ከትግሉ ጀርባ የተሰለፈውም ሆነ የትግሉ መሪ ራሱ ተጋዳዩ ጀግናው የአማራ ህዝብ ነው።

ሆኖም ግን የአማራው የህልውና ተጋድሎ የፖለቲካ ትግል እየመሰላቸው የህልውና ተጋድሎውን ወደ ፖለቲካ ትግል ደረጃ ለማሳነስ የሚሞክሩ የፖለቲካ ድርጅቶች አልጠፉም። በተጋድሎው ወቅት የታዩት የፖለቲካ ድርጅቶች መፈክሮችም ሆኑ ከተጋድሎው በኋላ የተስተጋቡት «ከትግሉ ጀርባ እኛ አለንበት» ወይንም « ትግሉ የእኛ ነው» በሚል የቀረቡት የድርጅት መግለጫዎችና ዲስኩሮች የአማራው ተጋድሎ ከእውነተኛው የህዝቡ የህልውና ተጋድሎ ከፍታ ወደ ፖለቲካ ትግል ደረጃ ወርዶ ህዝባዊ ተጋድሎው የፖለቲካ ትግል እንዲመስል ጣልቃ በመግባት ለማሳነስ ተሞክሮ እንደነበር ማሳያዎች ናቸው።

የባህርዳሩ ህዝባዊ ተጋድሎ ከፍተኛ መስዕዋትነት ያስከፈለን የህዝባዊ ተጋድሎው መሪም ሆነ ስልት ነዳፊ ሰፊው የአማራው ህዝብ ራሱ ሆኖ ሳለ «የአማራ ችግር የፖለቲካ ችግርና የአስተዳደር ጉድለት እንጂ የህልውና አደጋ አይደለም» ብለው የሚያምኑና «በአንድነት» ስም «እንታገላለን» የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች በፈጠሩት ጣልቃ ገብነት ነው። ይህ የድርጅቶች ጣልቃ ገብነት ወያኔ «አሸባሪ» በሚላቸው ድርጅቶች አስታኮ ህዝቡን እንዲጨፈጭፍ ሰበብ ሆኖታል።

የዚህ ተማጽኖ አላማም ወደፊት የአማራ ህዝብ በሚያደርጋቸው ተጋድሎዎች ዙሪያ ከአማራው የህልውና አደጋዎች በላይ የድርጅታቸውን አጀንዳ ቀዳሚ የሚያደርጉ ድርጅቶች ከድርጊታቸው ይቆጠቡና ወያኔ ህዝባችንን እንዲጨርስ ሰበብ እንዳይሆኑ ወገናዊ ልመናችንን ለማቅረብ ነው።

የፖለቲካና የሲቪል ድርጅቶች ተጋዳዩን የአማራ ህዝብ ከድርጅታቸው ሳጥን በመውጣት ከህዝቡ ጋር ሆነው እንደ ድርጅት ሳይሆን እንደ ህዝብ፤ የድርጅታቸውን አጀንዳ አንግበው ሳይሆን ህዝቡ ያነሳውን የህልውና አደጋ እንደ ህዝብ በማንሳት በድርጅት ደረጃ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ተሳታፊ በመሆን የአማራውን ተጋድሎው ማገዝ ይችላሉ። ይህን የሚያደርጉት ታዲያ «ከተጋድሎው ጀርባ እኛ አለንበት» ወይንም «ተጋድሎው የእኛ ነው» የሚል የሰለቸ የመግለጫ ጋጋታ ለማውጣት አይደለም።

በአማራው ተጋድሎ ሂደት ህዝቡን ወክሎ መግለጫ የሚሰጥ፣ የሚደራደርም ሆነ ጥሪ የሚያቀርብ ራሱ ተጋዳዩ ህዝብና የአማራ በደል የወለዳቸው ልጆቹ ብቻ ናቸው እንጂ የድርጅት አጀንዳ የያዙ ግለሰቦችና የፓርቲ ስብስቦች አይደሉም።

የፖለቲካ ፕሮግራማቸው በዋናነት የአማራውን ህዝብ ህልውና ማዕከል ያላደረጉ የፖለቲካና የሲቪል ድርጅቶች መፈክርና መግለጫ እያወጡ አማራው ከተጫነበት የህልውና አደጋ በላይ የራሳቸውን አጀንዳ በማስቀደም «ከተጋድሎው ጀርባ እኛ አለንበት» ወይንም «ተጋድሎው የእኛ ነው» ቢሉ ጨካኙ ወያኔ የሚጠላውንና ሊያጠፋው የተነሳውን የአማራ ህዝብ እንዲጨርስ፤ በአሳው አሳቦ ባህሩን እንዲያደርቅ ሰበብ መሆናቸውን መገንዘብ አለባቸው።

ስለዚህ «ህዝባዊ ነኝ» የሚል ማንኛውም የፖለቲካና የሲቪል ድርጅት ሁሉ ወያኔ አማራውን ሰበብ ፈጥሮ እንዳይጨፈጭፈው «ከትግሉ ጀርባ እኛ አለንበት» ወይንም « ትግሉ የእኛ ነው» ከሚል ህዝባዊ ያልሆነ የድርጅት መግለጫ ራሱን በመቆጠብ ህዝባዊ ተጋድሎውን በህዝቡ አጀናዳዎች ዙሪያ ብቻ እንደ ህዝብ የሚችለውን አስተዋጽኦ በማድረግ የአማራን ተጋድሎ ያግዝ ዘንድ በታላቅ አክብሮት ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ድል ለአማራ ህዝብ!
ድል ለኦሮሞ ህዝብ!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!
የአማራ ተጋድሎ ይቀጥላል።