የብአዴን ጉዞ የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄና የአማራ ብሔርተኛነት
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
በአሸናፊ ድጋፌነህ ([email protected])
መንደርደሪያ፤
በ1970ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በኢህአፓ ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈል አንድ አካል የሆነው የበለሳው ንቅናቄ ህዳር 11 ቀን 1973 ዓ.ም የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን (ኢህዴን) ወለደ። ኢህዴን ከመሰረቱ ጀምሮ ከተሓህት (ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ) በኋላ ላይም ህወሓት (ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ) ጋር የተያያዘና የተሳሰረ ድርጅት ነበር። በኋላ ላይ ሀይላቸውን አጠናክረው ወደ ዋግ ከመግባታቸው በፊት የመንቀሳቀሻ “ነጻ መሬት” እንዲሁም የሎጀስቲክስና የፕሮፖጋንዳ ስንቅ ድጋፍ ከህወሓት ይደረግላቸው ነበር። በ1980 ዓ.ም ህወሓት “ሰላም በትግል” ብሎ በሰየመው ኦፕሬሽን ደርግ ሽሬ ላይ ስለተሸነፈና ትግራይን ለቆ ስለወጣ ትግራይ የህወሓት ነጻ መሬት ሆነ። ህወሓት በማኒፌስቶው የከተበው የታላቋ ትግራይ ሪፐብሊክ ምስረታ ግን ትግራይን ከደርግ አገዛዝ ነጻ በማውጣት ብቻ ሊከናወን አይችልም ነበር። በመሆኑም ህወሓት በአጠቃላይ መላውን ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ያስችለው ዘንድ የግድ ኢትዮጵያዊ የሆነ ቅርጽ ያለው ድርጅት መፍጠር ነበረበት። ለዚህ ዓላማ ይረዳው ዘንድ በ1981 ዓ.ም ከኢህዴን ጋር “በመተባበር” ኢህአዴግን መሰረተ። ኢህአዴግ በተመሰረተ በአንድ ዓመት ውስጥ የህወሓትና የሻዕቢያ ምርኮኛ ወታደሮችን በማሰባሰብና “የፖለቲካ ንቃት” በመስጠት መኮንን የሆኑትን በማሰባሰብ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ መኮንኖች አብዮታዊ ንቅናቄን (ኢዴመአን) በሚል አደራጃቸው። ምርኮኛ የኦሮሞ ተወላጆችን ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) እንዲያቋቁሙ በማድረግ የዘመቻ “ቢልሱማ ውልቂጡማ” መንገድ ጠረጋውን በ1982 ዓ.ም ጀመረ። የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) የተመሰረተው ከደርግ ወድቀት በኋላ በ1984 ዓ.ም ነው።
ረጅሙ የህወሓት እጅና የብአዴን ጥገኝነት፤
የኢህአዴግ የውስጥ መተዳደሪያ ህገድንብ አባል ድርጅቶቹ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ የአመራር ውክልና እንደሚኖራቸው ይደነግጋል። ይሁንና በኢህአዴግ ውስጥ ህወሓት የአንበሳውን ድርሻ ይዞ እንደኖረ የአደባባይ ሚስጥር ነው። በኢህአዴግ ውስጥ የሚታየውን የህወሓት የበላይነት በተበታተነ ሁኔታም ቢሆን አንዳንድ የኢህዴን ነባር ታጋዮች ከጅምሩም ይቃወሙ ነበር። ኢህዴን (ብአዴን) እንደ ድርጅት በአጠቃላይ አብዛኛው የድርጅቱ ከፍተኛ የአመራር አባላት ደግሞ በተለይ በህወሓት ጥብቅ ቁጥጥር ስር የተያዘ በመሆናቸው በተበታተነ ሁኔታ የሚነሱ ተቃውሞዎች ፍሬ ሊያፈሩ አልቻሉም።
የእኩልነት ጥያቄ የሚያነሱትን የኢህዴን (ብአዴን) ታጋዮች በሰበብ አስባቡ ከድርጅቱ ማሰናበት ወይም ከነአካቴው ማጥፋት ካመሰራረቱ ጀምሮ ድርጅቱን አልተለየውም። የመጀመሪያው የድርጅቱ መሪ አቶ ያሬድ ጥበቡ (ጌታቸው ጀቤሳ) እንዴት ለስደት እንደበቁና በምትካቸው አቶ ታምራት ላይኔ መሪ ሊሆኑ እንደበቁ ሁለቱም በህይዎት ስላሉ ዘርዘር አድርገው ሊያስረዱን ይችላሉ። በ1983 ዓ.ም ከዘመቻ ቴዎድሮስ ክንውን በኋላ እነ አውጃኖ (የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበረ) በቦንብ እንዲገደሉ ያበቃቸውን ምክንያት አቶ ህላዊ ዮሴፍ ላስረዱን ይችላሉ። በ1985 ዓ.ም ክረምት ላይ በደሴ ከተማ ከነባር ታጋዩ ጋር ከተደረገው ኮንፈረስ መልስ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ (በወቅቱ የክልል 14 ዋና ፀሃፊ የነበሩ) ድርጅቱንና አገራቸውን ለቀው ዳግም ለስደት የተዳረጉት ለምን እንደነበር ይታወቃል። በተመሳሳይ ወቅት አቶ ሙሉዓለም አበበ (የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የምስራቅ ጎጃም አስተዳዳሪ የነበሩ) ደብረማርቆስ ላይ በቢሮአቸው ውስጥ እንዴት ለምንና በማን እንደተገደሉ የአደባባይ ሚስጥር ነው። በ1989 ዓ.ም አቶ ታምራት ላይኔን ከድርጅት ሊቀመንበርነትና ከመከላከያ ሚንስትርነት አስፈንጥሮ ቃሊቲ ቤተኛ ያደረጋቸው ነገረ-ጉዳይ “ስኳር” ነው ብሎ የሚያምን የዋህ የሚገኝ አይመስለኝም። (በዚህ አጋጣሚ አቶ ታምራት ከስር ከተፈቱ በኋላ እንኳን አብዝተው ዝም የማለታቸው ጉዳይ ሲታሰሩ ፓርላማ ፊት ቀርበው “በተደጋጋሚ ተመክሬ ነበር፤ አልሰማ ብየ ነው” ካሉት የበለጠ ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት ይመስለኛል።) ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ፍጻሜ በኋላ አቶ ዮሴፍ ረታን (ገይድ) ከብአዴን አመራርነትና ከአማራ ክልል ፕሬዝዳንትነት ያፈናቀላቸው የህወሓት (አቶ መለስ) ቀጭን ትዕዛዝ እንደሆነ ተዘግቧል። አቶ አያሌው ጎበዜንም ከአማራ ክልል ፕሬዝዳንትነት ለቱርክ አምባሳደርነት የዳረጋቸውን “ሹመት” እንዴትነት ህወሓትና የሱዳን መንግስት ብቻ ሳይሆኑ የክልሉ ህዝብም ጠንቅቆ ያውቃል። ኮሚሽኑ የተቋቋመበትን አዋጅ በሻረ ሁኔታ ወ/ሮ እንወይ ገብረመድህንን ከፀረ-ሙስና ኮሚሽነርነትና ከድርጀት አመራርነት ያፈናቀለው የህወሓትና አቶ መለስ ረጅም እጅ እንደነበር ይታወቃል። አቶ መላኩ ፈንቴም ከገቢዎች ጉዳይ ዋና ዳይሬክተርነት ምክትላቸውን አስከትለው ቃሊቲ ያወረዳቸው ጉዳይ በተለያዩ ጊዜያት ተዘግቧል።
ከላይ በተደጋጋሚ እንደተገለፀው የብአዴን አመራሮች በህወሓት የተሰመረላቸውን ቀይ መስመር እስካላከበሩ ድረስ ያለምንም ርህራሄ በቀይ ካርድ ከጨዋታ ውጭ ይደረጋሉ። ሐምሌ (ነሐሴ) 2004 ዓ.ም ይህን የተለመደ አካሄድ የቀየረ የሚመስል አዲስ ሁኔታ ተፈጠረ – የአቶ መለስ ሞት።
ድኅረ መለስ ኢህአዴግና የአባል ድርጅቶች ውስጠ-ትግል፤
አቶ መለስ በተለይ ከ2001 ዓ.ም የህወሓት ውስጣዊ ክፍፍል (እንፍሽፍሽ) በኋላ ፍጹም አምባገነን ሆነው ወጡ። በጋራ አመራር ሂደት ምክንያት ሊፈጽሟቸው ያልቻሏቸውን አጀንዳዎች ያለአንዳች ተቃውሞ የፈለጉትን ማድረግ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ተፈጠረላቸው። የእርሳቸው ሀሳብ የሆነ ነገር ሁሉ ለየድርጅቶችና ለህዝቡ በሙሉ የግዴታ መመሪያ ሆኖ ቆይቷል። ሲፈልጉ ድርጀት ይፈጥራሉ፤ ካልፈለጉ ያፈርሳሉ። ሲፈልጉ አንዱን የራሳቸው ሰው ከሜዳ ላይ አንስተው ባንድ ጀንበር ሚሊኒየር ያደርጋሉ፤ ካልፈለጉ ሚሊኒየሩን አክስረው ወደ ጎዳና ያወጣሉ። የፈለጉትን ይሾማሉ፤ ያልፈለጉትን ያስገድላሉ፣ ያስራሉ፣ ተንበርክካችሁ ይቅርታ ለምኑኝ ይላሉ… ወዘተ ወዘተ በአጭሩ በእግዚአብሔር እስከተጠሩበት ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ አምላኳ ነኝ ብለው በተግባር የታበዩ መሪ ነበሩ።
የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ ማን የኢህአዴግ ሊቀመንበር (የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር) ይሁን በሚለው ጥያቄ ዙሪያ በአባል ድርጅቶች መካከል የነበረው መሳሳብና መገፋፋት የሚታወስ ነው። ህወሓት የአንበሳ ድርሻውን ይዞ ለመቀጠል ያደረገው የሞት ሽረት ትግል፤ ብአዴንና ኦህዴድ ደግሞ ከእንግዲህስ የበታችነት ይብቃን፣ እኩልነት ይስፈን ያሉበት የውስጥ ትንቅንቅ ባሕርዳር ከተማ ላይ ባካሄዱት የኢህአዴግ ጉባኤ ላይም ሳይቀር ተስተውሏል። በወቅቱ የተጀመረው የውስጥ ትግል እያደገ ሄዶ በተለይ ብአዴንና ኦህዴድ ለህወሓት አገልጋይ ሆነን አንቀጥልም በሚለው የገፉበት ይመስላሉ፤ በሁሉቱም ድርጅቶች ዛሬም ለህወሓት የሚሰሩ “የህወሓት ተክሎች” የሉም ማለት ግን አይደለም። ህወሓት በይፋ ባይቀበለውም ከአቶ መለስ ሞት በኋላ እንደገና ድርጅቱ (መከላከያውና ደህንነቱም ጭምር) የመቀሌና አዲስ አበባ ቡድን ተብሎ ውስጥ ለውስጥ እንደተከፋፈለ ይነገራል። መቀሌ ላይ በተደረገው ያለፈው የህወሓት ጉባኤ ላይ ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴና ፖሊት ቢሮ አባልነት የራስን ወገን ለማስገባት የነበረው መቆራቆስ መከፋፈላቸውን የሚያረጋግጥ ሆኗል። የህወሓት መከፋፈል ደግሞ ብአዴንና ኦህዴድ ለጀመሩት ውስጠ ተቃውሞ ተጨማሪ አቅም የፈጠረላቸው ይመስላል። ላለፉት ዘጠኝ ወራት በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ አመጽ ሊቆም ያልቻለው የህዝቡ ቁርጠኝነት እንደተጠበቀ ሆኖ የኦህዴድም የዝምታ ድጋፍ (passive support) ስለተጨመረበት እንደሆነ ይገመታል። አቶ አባይ ፀሐየ ካድሬውን ሰብስበው “ህዝቡን ልክ እናስገባዋለን” ያሉበትን ዲስኩር በድምጽ ቀርጾ ለህዝቡ እንዲደርስ ያደረጉት የኦህዴድ ካድሬዎች እንደሚሆኑ ይታመናል። በአማራ ክልልም ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። የህዝቡ ንቁ ተሳትፎና እስከ መሰዕዋትነት ለዓላማው መሰለፉ እንደተጠበቀ ሆኖ በወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄና በቅማንት ጥያቄ አፈታት ዙሪያ በህወሓትና ብአዴን መካከል ያለው ድርጅታዊ መገፋፋት የበለጠ ግልጽ እየሆነ መጥቷል።
ብአዴንና የአማራው ህዝብ ብሔርተኝነት ትላንትና ዛሬ፤
ኢህአዴግ መራሹ ስብስብ በሰኔ 1983 ዓ.ም ለሁለት ዓመት የሚፀና የሽግግር መንግስት ም/ቤት ሲያቋቁምና ም/ቤቱ የሚመራበትን ቻርተር ሲያፀድቅ በሂደቱ አማራው እንደ ብሔረሰብ አልተወከለም ነበር። የሽግግር መንግስቱ በተቋቋመ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ ኢዴመአን እንዲከስም ተደረገ፤ የኢዴመአን አባላት የነበሩት መኮንኖችም በሌሎች አባል ድርጅቶች እንዲታቀፉ ተደረገ። በ1984 ዓ.ም በሽግግር መንግስት ምስረታው ከክልል 7 – 11 የተካለሉ አምስት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎችን በቀላሉ “ለመጠርነፍ” እንዲያስችል ደኢህዴን እንዲመሰረትና የኢህአዴግ አባል ድርጅት እንዲሆን ተደረገ። ደኢህዴን ሲመሰረት በኢትዮጵያዊነታቸው በኢህዴን ውስጥ ይታገሉ የነበሩ የደቡብ ክልል ተወላጆች ከኢህዴን ተነስተው ለደኢህዴን በእርሾነት ተሰጡ። የሌላ ብሄር ተወላጆች ወደ ብሄራቸው ስለሄዱ አገራዊ ተልዕኮውን ጨርሷል የተባለው ኢህዴን ደግሞ በ1985 ዓ.ም ባህርዳር ላይ ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ ከስሞ ብአዴን ሆኖ ወጣ። የአዲሱ ድርጅት መሪ መፈክርም “የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔረተኛነት ይለምልም” የሚል ነበር።
ከሕዳር 1985 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል በሚገኙት 138 የምርጫ ክልሎች ሁሉ ህዝቡ እየተሰበሰበ መፈክሩን እንዲያስተጋባ ይደረግ ነበር። የክልሉ ህዝብ ግን በክልሉ ውስጥ ኢትዮጵያዊነቱን እንደያዘ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር የቆየውን መተሳሰርና መከባበር አጠናክሮ ቀጠለ። በኢትዮጵያ ካሉት ዘጠኝ ብሄር ተኮር ክልሎች ውስጥ የሌሎች ብሄረሰቦችን እውቅና መስጠት ብቻ ሳይሆን እራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ የሚፈቅድ የክልል ህገመንግስት ያለው የአማራ ክልል ብቻ ነው። በአማራ ክልል ውስጥ የአዊ፣ ህምራና ኦሮሞ ብሄረሰቦች የየራሳቸው የሆነ የዞን አስተዳደር ም/ቤት ሲኖራቸው የአርጎባና በቅርቡ ደግሞ የቅማንት ብሄረሰቦች እራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት የልዩ ወረዳ ም/ቤት ተቋቁሟል። ይህ በዞንና በወረዳ ተደራጅቶ እራስን የማስተዳደር መብት የተለያዩ ብሄረሰቦች አብረው በሚኖሩበት የትግራይ ክልል ውስጥ ክልክል ነው፤ በኦሮሚያም የተፈቀደ አይደለም። በአንፃሩ አማራው በሚኖርባቸው ሌሎች ክልሎች እንኳን የራሱ ዞን ወይም ወረዳ ም/ቤት ሊቋቋምለት ይቅርና ከየክልሉ እየተፈናቀለ ለአያሌ ተደጋጋሚ ጥቃት መዳረጉ ይታወቃል። ከአርባጉጉ ጀምሮ እስከ ቤንሻጉልና ጉራፈርዳ ድረስ በህወሓትና ተባባሪዎቹ የደረሰበት ሰቆቃ በታሪክ የተመዘገበ ነው።
የአማራው ከየክልሉ የመፈናቀል ሁኔታና በአማራ ክልልም ያለው ህዝብ የበይ ተመልካች እንዲሆን መደረጉ በአማራ ህዝብ ላይ እየፈጠረ የመጣው የመገፋትና የነፃነት ማጣት ስሜት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሄደ። ይህ የህዝቡ ስሜትም ቀስ በቀስ ለህዝቡ ቅርብ ወደ ሆነው ዝቅተኛና መካከለኛ የብአዴን አመራር መጋባቱ አልቀረም። ከአቶ መለስ ሞት በኋላ እስካሁንም ድረስ በድርጅቶች መካከል የሚካሄደው የውስጥ ፍትጊያ ብአዴንን ሳይወድ በግድ ወደ ህዝቡ እንዲቀርብ የገፋውም ይመስላል። የብአዴን ስልታዊ ለውጥ ማድረግ (ስትራቴጅካዊም ሊሆን ይችላል) በህዝቡ ላይ የሚደረገውን አፈና በተወሰነ ደረጃ በመቀነሱ የአማራው ህዝብ በተለይም ወጣቶች በአማራነታቸው ከምንጊዜውም በላይ መነቃቃት ፈጥረዋል። በወጣቶች የተፈጠረው አዲስ መነቃቃትም ብአዴንና አንዳንድ የድርጅቱ አመራሮች እንደከዚህ በፊቱ በማን አለብኝነት ህዝቡን እያዋረዱ ሊቀጥሉ እንደማይችሉ ያመላከተ ሆነ። በ2006 ዓ.ም በተለይ በባሕርዳር ከተማ ወደ 100ሺ የሚገመት የከተማውና የአካባቢው ነዋሪ አደባባይ ወጥቶ “ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር ይሻላል!” በማለት የክልሉ ም/ፕሬዝዳንት የሆኑትን አቶ አለምነውንና ደርጅታቸውን ማውገዙ ያሳየውም ይህንኑ ነው። የአማራ ብሔርተኛነት ሌላ ክስተት የሆነው ደግሞ የቤተ-አማራ መፈጠር ነው። ቤተ-አማራ የተባለው ስብሰብ ባለፉት ሁለት ዓመታት በማህበራዊ ሚድያው የአማራ ብሔርተኝነትን በህዝቡ ዘንድ መሰረት ለማስያዝ ያካሄደውን የፕሮፖጋንዳና ቅስቀሳ ስራ የስብስቡ ም/ሊቀመንበር አቶ መሳፍንት ባዘዘው በቅርቡ ያካሄዱት ቃለ ምልልስ ያሳያል። ከማህበራዊ ሚድያው እንቅስቃሴ አኳያ ሲታይ ቤተ-አማራ በተለይ ወጣቱን በመድረስና በማነቃነቅ ረገድ ከፍተኛ ግብዓት ሆኗል። በአጠቃላይ በህዝቡ ዘንድ ከመቸውም ጊዜ በላይ አማራ ነኝ የሚለው ስሜት እያደገ መምጣት፣ ዝቅተኛና መካከለኛ ካድሬዎቹ ከህዝቡ ጋር መወገን፣ ይህም በብአዴን ከፍተኛ አመራሮች ላይ ያሳደረው ተጽእኖ በኢህአዴግ ውስጥ ካለው ድርጅታዊ መገፋፋት ጋር ተደማምሮ በአሁኑ ጊዜ ብአዴን ክህዝቡ ጋር እንዲቆም እየተገደደ የመጣ ይመስላል።
የብአዴንና ህወሓት ውስጠ-ነቆራ፤
ብአዴን ወደ ህዝብ ለመጠጋት እያሳየ የመጣው ዝንባሌና በኢህአዴግ ውስጥ የሚያሳየው ስልጣን ተገዳዳሪነቱ ያልተዋጠለት ህወሓት፤ ብአዴንን ለማዳከምና የክልሉንም ህዝብ ለማበጣበጥ ስትራቴጅ ነድፎ መንቀሳቀስ ነበረበት። ይህንኑ ለመረዳት ያስችለን ዘንድ ከሱዳን ጋር ስለሚካለለው ድንበር፣ የቅማንት ጥያቄና የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ የሆነውን እንመልከት።
ከሱዳን ጋር ስላለው ድንበር፦ ህወሓት ከጎንደር ሰሜን ጫፍ እስከ ጋምቤላ ድረስ 1600 በ30 ካሬ ኪሎሜትር ስፋት ያለው መሬት ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት ተስማምቷል። ከዚህ መሬት ውስጥ አብዛኛው የሚገኘው የአማራ ክልል በሚባለው ውስጥ እንደመሆኑ መጠን መሬቱ ለሱዳን ተላልፎ ቢሰጥ ምናልባትም በሚልዮኖች የሚቆጠሩ የአማራ ገበሬዎች ቀጥተኛ ተጎጅ ይሆናሉ። ይህም በክልሉ ህዝብና በክልሉ መንግስት መካከል ቀላል የማይባል ቀውስ መፍጠሩ አይቀሬ ይሆናል። ህወሓት በዚህ ሂደት የክልሉ መንግስትና መሪዎቹ ፈርመዋል በማለት ብአዴንንና የክልሉን አመራሮች ከህዝብ ነጥሎ በቀላሉ ለመምታት ሊጠቀምበት ያሰበ ይመስላል። በሱዳን ድንበር ጉዳይ ህወሓት ከታላቋ ትግራይ ምስረታ አንፃር የሚተነተን ሌላ የመልከዓምድር ፖለቲካ ስሌትም (geopolitical calculation) እንዳለው ይታወቃል፤ ለጊዜው እርሱ ይቆየን።
የቅማንት ጥያቄ ጉዳይ፦ የቅማንት ህዝብ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄን በየደረጃው ከሚመለከተው ህዝብ ጋር ውይይት ካደረገና ጉዳዩን በባለሙያ ካስጠና በኋላ የክልሉ መንግስት በሐምሌ 2007 ዓ.ም ባካሄደው ጉባኤ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄውን የተቀበለው ሲሆን ለአፈጻጸሙም ም/ቤቱ አዋጅ አውጥቶለታል። የፌደሬሽን ም/ቤትም የክልሉን ም/ቤት ወሳኔ ተቀብሎ አጽድቆታል። የቅማንት ብሄረሰብ እንደ ብሄረሰብ እውቅና ተሰጥቶት በአማራ ክልል ም/ቤትም ሆነ በፌደሬሽን ም/ቤት ተወካይ እንዲኖረው ተደርጓል። ብሄረሰቡ 42 ቀበሌዎችን በሚያቅፍ ልዩ የወረዳ ም/ቤት አቋቁሞ እራሱን በርሱ እንዲያስተዳድር በአዋጅ ፀድቆለታል። ከላይ እንደተገለፀው በትግራይ ክልል የተለያዩ ብሄረሰቦች ቢኖሩም (አብነት ኩናማና ኢሮብ) ህወሓት ከትግራዋይነት ውጭ ሌላ ማንነት በክልሉ እንዲኖር አልፈቀደም። የኩናማ ወይም የኢሮብ የብሄረሰብ ዞን ወይም ወረዳ ም/ቤት አልተቋቋመም። ይሁንና በአማራ ክልል ውስጠ ጉዳይ ህወሓት አስርጎ ባሰማራቸው የተወሰኑ የቅማንት ኮሚቴ አባላት ተጠቅሞ ህዝቡን ለመከፋፈል ከፍተኛ የሆነ ቅስቀሳ ሲያደርግ ይስተዋላል። ህወሓት ተላላኪ የኮሚቴ አባላትን በመጠቀም በማህበራዊ ሚድያው በኩል በአጠቃላይ በአማራው ህዝብ ላይ በተለይ ደግሞ በብአዴንና በተወሰኑት አመራሮቹ ላይ ከፍተኛ የሆነ የማጥላላት ቅስቀሳ ያደርጋል። በተቃራኒው ደግሞ እነዚህ የኮሚቴ አባላት ነን የሚሉ ሰዎች ለህወሓት ያላቸውን ወገናዊነት በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በግልጽ ይናገራሉ። ሌላው ቀርቶ በሐምሌ 24ቱ ታሪካዊ የጎንደር ሰላማዊ ሰልፍ ዋዜማ በማህበራዊ ሚድያ መወያያ ገጾቻቸው ላይ የአማራ ጉዳይ እኛን አይመለከተንም፣ ሰልፍ እንዳትወጡ፤ ብአዴን የትምክህት ድርጅት፣ የግንቦት 7 አጋር፣ የቤተ-አማራ ልሳንና የጎንደር ሕብረት ማህበርተኛ ነው በማለት አራግበዋል። ይሄ በብአዴን ላይ ያካሄዱት ቅስቀሳና ማጥላላት በፌስቡክ በተመሳሳይ ስራቸው ከሚታወቁ የህወሓት ካድሬዎች ጋር አንድ አድርጓቸዋል። ህወሓት የቅማንት ጥያቄን የራሱን ግዛት የማስፋፊያ አማራጭ አድርጎ እየሰራበት ያለ ጉዳይ ነው። ይሁንና በታሪካዊው የጎንደር ሰላማዊ ሰልፍ እንደታየው አማራና ቅማንቱ በጋራና በአንድነት አብሮ በመወጣት ተላላኪዎችን አሳፍሯቸዋል።
የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ፦ የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄውን ማንሳት የጀመረው አንዳንድ የህወሓት ካድሬዎች ደጋግመው ሊነግሩን እንደሚሞክሩት የዛሬ ሁለት ዓመት አይደለም። የወልቃይት ህዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄውን ማቅረብ የጀመረው በመሰረቱ ሳይጠይቅ ያለፍላጎቱ ወደ ትግራይ እንዲካለል በህወሓት ከተወሰነበት 1983 ዓ.ም ጀምሮ ነው። የሽግግር መንግስት እንደተቋቋመ ወልቃይት ወደ ክልል 1 (በኋላ ላይ ክልል ትግራይ) መከለሉ ሲታወቅ ወልቃይቴዎች ተሰባስበው እኛ አማራዎች እንጅ ትግሬዎች አይደለንም በማለት የመጀመሪያ የተቃውሞ ማመልከቻቸውን በወቅቱ የሽግግር መንግስቱ የሰሜን ጎንደር አስተዳዳሪ ለነበሩት ለአቶ አስማማው የሱፍ ማቅረባቸው ይታወሳል። ከዚያም ተቃውሞአቸውን በመቀጠል ጥያቄያቸውን በየጊዜው ለተሾሙ የጎንደር አስተዳዳሪዎች ማቅረባቸውን ቀጥለው ለአቶ አድጎአይቸው ፀጋ፣ ለአቶ አቡኔ መንገሻ፣ ለአቶ ተሰማ ገ/ሕይወት፣ ለአቶ ሙሌ ታረቀኝ፣ ለአቶ አገኘሁ ተሻገር፣ ለአቶ ግዛት አቡየ ያቀረቡ ሲሆን አሁንም ለአቶ ሙሉጌታ ወርቁ ማቅረባቸው አልቀረም። ለፍትህና አስተዳደር አቤቱታ ለማቅረብ ወደ ትግራይ አንሄድም በማለት ወደ ጎንደር ከተማ እየተመላለሱ መፍትሄ ለማግኘት ቢጥሩም በህወሓት ረጅም እጅ ጎንደር ላይ በተቀመጡ አስተዳዳሪዎች ክልላችሁ ትግራይ ስለሆነ በዚያው ተዳኙ እየተባሉ ሲገፉ መቆየታቸው ይታወቃል። በመሆኑም የወልቃይት ጠገዴ አማራዎች በህወሓትና ብአዴን የጋራ ትብብር ማንነታቸው ተረግጦና ታሪካዊ የአስተዳደር ግዛታቸው በግዳጅ ተለውጦ እንዲኖሩ ተገደው ቆይተዋል።
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን በወልቃይት አማራዎች ላይ በሚኖሩበት አካባቢ በተስፋፊዎች እየደረሰባቸው ያለው የመሬት ነጠቃ መባባስ፣ የአማራው ብሔርተኝነት እየጎለበተ መምጣት፣ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ በድርጅቶች መካከል የተፈጠረው መገፋፋት ተጨምሮበት ጥያቄው በማይቀለበስ ሁኔታ የአማራው ህዝብ መሪ አታጋይ አጀንዳ ለመሆን በቅቷል። በኮለኔል ደመቀ ዘውዱ የሚመራውና በወልቃይት ባህል በህዝቡ የተመረጠው የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ኮሚቴ ጥያቄውን ለፌደሬሽን ም/ቤትም ያቀረበ ቢሆንም አፈ ጉባኤው አቶ ያለው አባተ (የአማራ ክልል ም/ቤት የቀድሞው አፈጉባኤ) የማንነት ጥያቄው በትግራይ ክልል ም/ቤት እንዲወሰን ለትግራይ ክልል መርተውታል። በአቶ አባይ ወልዱ የሚመራው ህወሓትና የትግራይ ክልል ም/ቤት የችግሩ አካል እንደመሆኑ መጠን የኮሚቴውን ጥያቄ በአወንታ ሊመልሰው አይችልም። አቶ አባይ ወልዱ በየካቲትና መጋቢት 2008 ዓ.ም “ምዕራባዊ ትግራይ” በሚሉት ዞን እየተዘዋወሩ ለትግራዋይ ምን ይቀሰቅሱ እንደነበር የትግራይ ቴለቭዥንን የሚከታተል ሰው ያውቃል።
የብአዴን ከፍተኛ መሪዎችም በዚህ ጥያቄ ዙሪያ የተከፋፈሉ እንደሆኑ አንዳንድ ምልክቶች እየታዩ ነው። በክልል ደረጃ ካሉት ከፍተኛ አመራሮች አቶ ገዱ አንዳርጋቸው (የብአዴን ም/ ሊቀመንበርና የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት) ጥያቄው ከታሪክ ማእቀፍ አንፃር ታይቶ በፍትሃዊ ሁኔታ እንዲፈታ እንደሚፈልጉና ህወሓትና የትግራይ ክልል እየሄዱበት ያለው ችግር አፈታት እንዳላስደሰታቸው ይነገራል። ለማሳያነትም በኢህአዴግ አመራር ስብሰባ ላይ ከአቶ አባይ ወልዱ ጋር የተመላለሱት ስድብ ቀረሽ ምልልስ ይቀርባል። አብዛኛው በዝቅተኛና መካከለኛ አመራር ላይ ያለው ካድሬም የአቶ ገዱን ሃሳብ እንደሚደግፍ ይነገራል። አቶ ገዱ ከፌደራል መዋቅሩም ደጋፊዎች እንደሚኖራቸው ይታመናል። ይህ በእንዲህ እያለ ሰሞኑን በተለያዩ የክልሉ የተለያዩ ከተሞች ከህወሓት አግዓዚዎች ጋር በተደረገው ትንቅንቅ በክልሉ ውስጥ ያሉ አብዛኛው የብአዴን ካድሬዎችና የየአካባቢው ፖሊሶች ከህዝቡ ጋር አብረው መቆማቸው ተስተውሏል። በሌላ በኩል ደግሞ አቶ ብናልፍ አንዷለም (የብአዴን አመራር አባል፣ የክልሉ ም/ፕሬዝዳንትና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ) ጎንደር ላይ ከህዝብ ጋር በተካሄደ ስብሰባ ላይ ህወሓት ደርግን በማስወገድ ላበረከተው የትግል አስተዋጽኦ ለትግራዋይ “ወልቃይት ብቻ ሳይሆን ደባርቅም ሊሰጣቸው ይገባል” ማለታቸው በቅርቡ ተዘግቧል። በስብሰባው የተሳተፈው ህዝብም ንግግራቸውን ሳይጨርሱ እንዲያቋርጡ አስገድዷቸዋል። በፌደራል ደረጃ በአመራርነት ከተቀመጡት የብአዴን ስዎች ውስጥ የወልቃይትን ጥያቄ በተመለከተ እስካሁን በአደባባይ የተናገሩት የፌደሬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር የሆኑት አቶ ካሳ ተክለብርሐን ናቸው። አቶ ካሳ ባህርዳር ከተማ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው 2ኛ የዲያስፖራ ጉባኤ ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ “ወልቃይት የትግራይ ነው” ማለታቸውን በቪድዮ ተመልክተናል። እሁድ በባህርዳር በተካሄደው ታሪካዊ የአማራነት ተጋድሎ የአማራ ወጣቶች ይዘውት ከወጡት መፈክሮች ውስጥ “… ካሳ ተክለብርሐን ወልቃይት የትግራይ ናት ማለታቸው በአማራ ህዝብ ላይ ጦርነት አውጀናል ከማለት አይለይም!” የሚል ይገኝበታል። በእለቱ የአማራ ወጣቶች የአቶ ካሳ ተክለብርሐንን ፎቶም ቀዳደዋል፤ አቃጥለዋል። አቶ ካሳና መሰሎቻቸው አሰላለፋቸውን እንዲያስተካክሉ አማራው ቁጣ የታከለበት መልዕክቱን በአደባባይ አቅርቦላቸዋል። ምርጫው የእርሳቸው ነው።
የብአዴን ቀጣይ ጉዞ ወዴት ይሆን?
ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው ከአቶ መለስ ሞት በኋላ የህወሓትን ስልጣን ለመገዳደር ብልጭ ድርግም እያለ እዚህ የደረሰው ብአዴን መስቀለኛ መንገድ ላይ የደረሰ ይመስላል። ብአዴን ሁለት አበይት ምርጫዎች ከፊቱ ተጋርጠዋል።
- የመጀመሪያው አማራጭ የክልሉ አመራሮች የጀመሩትን ከህዝቡ ጋር የመቀራረብ መልካም ጅምር ማጠናከር፤ በክልሉ ወጣቶች ተቀባይነት እያገኘና እያበበ የመጣው የአማራ ብሔርተኝነት ለክልሉ ህዝብ ሁለንተናዊ መብቶች መረጋገጥ ዋስትና የሚሰጥ የላቀ ኃይል እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፤ የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄን ጨምሮ ህዝቡ ባነሳቸውና ወደፊትም በሚያነሳቸው ህዝባዊ ጥያቄዎች ከህዝቡ ጋር አብሮ መቆም፤ ድርጅቱንም ሆነ የክልሉን ህዝብ በላዩ ላይ ከተጫነበት የህወሓት የአፈናና ጭቆና ቀንበር አላቆ ሁሉም የአገራችን ህዝቦች በእኩልነት የሚሳተፉበትና ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሀቀኛ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትመሰረት ድርሻውን ለመወጣት መዘጋጀትና በእርግጥም “ያልተንበረከከ” ድርጅት መሆኑን በተግባር ማሳየት ነው።
- ሌላው አማራጭ ከ35 ዓመታት በኋላም ዛሬም እንደትላንቱ ህወሓት የተሻለ ልምድ ያለው ድርጅት ስለሆነ በሚል አንካሳ ምክንያት በአገራችንና በህዝቡ ላይ የመወሰንን ሙሉ ስልጣን ለህወሓት አስረክቦ “እንደተንበረከከ” መቀጠል፤ አቶ ያሬድ ጥበቡን (ጌታቸው ጀቤሳ)፣ አቶ አውጃኖን፣ አቶ ሙሉዓለም አበበን፣ አቶ ታምራት ላይኔን፣አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን፣ አቶ ዮሴፍ ረታን (ገይድ)፣አቶ አያሌው ጎበዜን፣ አቶ ተፈራ ዋልዋን፣ ወ/ሮ እንወይ ገ/መድህንን፣ አቶ መላኩ ፈንቴን፣ አቶ ተሰማ ገ/ህይዎትን፣ አቶ መለስ ጥላሁንን፣ አቶ ዮሃንስ ቧያለውን፣ ጀኔራል ሐይሌ ጥላሁንን፣ ጀኔራል አለሙ አየለን (ጡንች)፣ ጀኔራል አሳምነው ጽጌን፣ ጀኔራል ተፈራ ማሞን፣ ጀኔራል አበባው ታደሰን፣ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን… ወዘተ ወዘተ በህወሓት የበላይነት ላይ ጥያቄ ያነሱ አያሌ መካከለኛና ከፍተኛ አመራሮችን ተራ በተራ እንዳስበላ ሁሉ እነአቶ ገዱ አንዳርጋቸውንም አስቆርጥመው ጊዜያዊ የህወሓት ሹመት ለራሳቸው እየሰበሰቡ እነርሱም በተራችሁ የሚቆረጠሙበትን ጊዜ መጠበቅ ነው።
ማጠቃለያ፤
ምርጫው አሁንም የብአዴኖች ነው። የትኛውን እንደሚመርጡ በሂደት የምናየው ይሆናል። ህዝብን ማክበርና እወክለዋለሁ ከሚሉት ህዝብ ጋር አብሮ መቆም የተሻለው ምርጫ እንደሚሆን የሚያጠራጥር አይደለም። የፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ አስተዳደራዊ፣ ወታደራዊና የደህንነት ተቋማት ከህወሓት የግል መጠቀሚያነት ተላቀው በሁሉም ተቋማት ውስጥ እኩልነትንና ፍትሀዊ ውክልናን ማረጋገጥ የሚያስችል ለውጥ እንዲመጣ መትጋት ያስፈልጋል። ይህን ቆራጥነት ያለው ትግል ለማካሄድ ደግሞ ከሁሉ አስቀድሞ ውስጥን ማጥራት ይጠይቃል። ብአዴን አሰላለፉን ከህዝቡ ጋር ለማስተካከል ያለው የመጨረሻ እድል አሁን ነው። እድሉን ከተጠቀመበት እርሱንም ከውድቀት ያድናል፤ ህዝቡ ለነጻነቱ የሚከፍለውን መስዋዕትነትን ይቀንሰዋል። አሰላለፉን በጊዜ ካላስተካከለ ግን ውድቀቱና ኪሳራው ለድርጅቱና ለአመራሮቹ ብቻ ይሆናል። የአማራው ብሔርተኝነት በምንም ሁኔታ ወደኋላ የማይመለስበት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ሰሞኑን በጎንደርና ጎጃም የተለያዩ ከተሞች በመካሄድ ላይ ያለው የአማራ ተጋድሎ ዋቢ ነው። ተጋድሎው በወሎና ሰሜን ሽዋ የተለያዩ ከተማዎች እንደሚቀጥል ይጠበቃል። የአማራው ተጋድሎ በየፈርጁ ይቀጥላል፤ ነፃነቱ በግዛቱ እስኪታወጅ ድረስ። ቸር እንሰንብት።