በባህር ዳር ሰልፍ አስተዳደሩ እውቅና ሊሰጥ መሆኑ ታወቀ – ግርማ ካሳ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
በባህር ዳር ሰልፍ አስተዳደሩ እውቅና ሊሰጥ መሆኑ ታወቀ – ግርማ ካሳ
ነሐሴ 1 ቀን በባህር ድፋር ከተማ ሰልፍ እንደሚደረግ የሰማያዊ ፓርቲ እና በጎንደር ሰልፍ እንዲደረግ ያደረጉ የአገር ሽምጋሌዎች፣ ለአስተዳደሩ አሳውቀዋል።
የብአዴን አስተዳደር ከአገር ሽማግሌዎች ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ በይፋ መግለጽ አይፈለግም። የአገር ሽማግሌዎቹ የሚያነሱት ጥያቄዎች ከምንም በላይ ሕወሃትን የሚያበሳጩ ጥያቄዎችን ናቸው። ወልቃይት ጠገዴ ወደ አማራው ክልል መቀላቀል አለባት የሚል።
በነዚህ የአገር ሽማግሌዎችም የቀረበ ለሰልፍ እወቁልኝ ጥሪም፣ ይፋዊ መልስ ለመመለስ እንደተቸገረ አይተናል። በጎንደሩ ሰልፍም በመጀመሪያ ለ10 ቀናት እንዲራዘም አስተዳደሩ ጠየቀ። 10 ቀናት አለፉ። ለሰልፉ እውቅና ሳይሰጥ ቀረ።
ማሳወቅ እንጂ ፍቃድ ማግኘት የለብንም በሚል አስተዳደሩ እውቅና ባይሰጥም ሰልፉ ተካሄደ።በሚያስደነቅ ሁኔታ ጎንደር ተነቃነቀች። ከስምንት መቶ ቪህ በላይ የሚሆን ህዝብ የፋሲልን ከተማ በኮከብ አልባ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ አሸበረቃት።
በተመሳሳይ ሁኔታ ደቡብ ጎንደር ዞን ዋና ከተማ በሆነቸው በደብረ ታቦር፣ እንዲሁም በክልሉ ዋና ከተማ በባህር ዳር፣ በዋናነት በወልቃይት የማንነት ጥያቄ ዙሪያ ሰልፍ እንደሚደረግ ተገለጸ። አስተዳደሩ እስከ አሁን እውቅና አልሰጠም።
በተጓዳኝ ሰማያዊ ፓርቲ ተመሳሳይ የሰልፍ ጥያቄ በባህር ዳር አቅርቦ ነበር። ሰማያዊ በቅርብ ጊዜ በባህር ዳር ስብሰባ ለማድረግ አስቦ፣ አስተዳደሩ እውቅና ሰጦ፣ ነገር ግን ለስብሰባ ሲቀሰቅሱ አባላቱ በመታሰራቸው ስብሰባው ለመሰረዝ ተገዶ እንደነበረ የሚታወቅ ነው። ሰብሰባ ማድረግ አልቻልኩም በሚል ስብሰባውን ወደ ሰልፍ በማዞር ለነሐሴ 1 ቀን ሰልፍ እንደሚደረግ፣ የጎንደሩ ሰልፍ ከመደረጉ በፊት አሳወቀ።
ከብዙ ደብዳቤ ምልልሶች በኋላ የባህር ዳር አስተዳደር ሰልፉ እንዲደረግ ወደ መፍቀድ የደረሰበት ሁኔታ እንዳለ ነው እየተዘገበ ያለው። “ሰማያዊ ፓርቲ የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሄድ ያቀረበውን ጥያቄ ተመልክቶ ዝርዝር መረጃዎችን እንድንሰጥ በተጠየቅነው መሰረት መረጃዎችን የገለፅን ሲሆን የከተማ አስተዳደሩ የከንቲባ ፅ/ቤት ሀላፊና የሰማያዊ ፓርቲ የዞኑ አስተባባሪዎች ጋር በመነጋገር ሰልፉን ማካሄድ እንደሚቻል ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ የውል ስምምነት ለመፈራረም ዛሬ 10 ሰዓት ላይ ቀጠሮ ተይዟል፡፡የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፉ እሁድ ነሐሴ 1 ቀን 2008 ዓ/ም ስለሚካሄድ መላው የባህርዳርና አካባቢው ነዎሪዎች በሰልፉ እንዲገኙ ፓርቲያችን ጥሪውን ያስተላልፋል” ይላል የሰማያዊ መግለጫ።
የሰማያዊ ፓርቲ በዚህ ረገድ ደብዳቤ በመለዋወጥ አስተዳደሩ ለባህር ዳሩ ሰልፍ እውቅና እንዲሰጥ በማድረጉ ትልቅ ሥራ ነው የሰሩት። ሆኖም ግን ለሰማያዊ ፓርቲ እውቅና ሰጥተው ከሕዝቡ ለተወጣጡ የአገር ሽማግሌዎች እውቅና አለመስጠታቸው ግን በራሱ አጠያያቂ ነው። አስተዳደሩ ለነጻነትና ለመብት የሚታገሉ መካከል መከፋፈልን ለመፍጠር ሆን ብሎ እየተጠቀመበት ያለ ስትራቴጂ ሊሆን እንደሚችልም መዘንጋት አያስፈለግም።
ሆኖም ግን ግልጽ መሆን ያለባቸው ነገሮች አሉ። የሰማያዊ የምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ይድነቃቸው “ህዝባዊ ትግል ማገዝ እንጂ ማደናቀፍ የሃቀኛ ፓርቲ መገለጫ አይደለም” እንዳልው በአሁኑ ጊዜ ትግሉን እየመራ ያለው ህዝቡ ራሱ መሆኑን አሳይተዋል። ሰማያዊ ፓርቲ የ”እወቁልን” ደብዳቤ አስገባ ማለት እንቅስቃሴው የፓርቲ እንቅስቃሴ ነው ማለት አይደለም።
በዚህ አጋጣሚ ለሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ እውቅና ስለተሰጠ፣ የባህር ዳር ህዝብ በነቂስ በመውጣት በጎንደር የተነሱ የወልቃይት ጥያቄን በማንሳት፣ ኮከብ አልባ ሰንደቃችንን በማውለብለብ ድምጹን በማሰማት፣ በጎንደር የተጀመረውን ማቀጣጠል ያስፈለጋል። ማንም ጠራው ማንም ቁም ነገሩ ያ አይደለም። ቁም ነገሩ ህዝብ በነቂስ መዉጣቱና ድምጹን ማሰማቱ ነው። በመሆኑም በትናንሽ ነገሮች በመካከላችን ክፍተት ባንፈትር ጥሩ ነው። ሕዝብ የተለያዩ ጥያቄዎች አሉት። እነርሱን ይዞ አደባባይ ይወጣል። ለዚህ የሕወሃት ዘረኛና አፋኝ አገዛዝ ያለዉን ምሬትና ተቃዉሞ ይገልጻል።
ለማጠቃለል አስተዳደሩ እውቅና ሊሰጥ እንደሆነ እንጂ ሰጠ ማለት እንዳልሆነ ግን ከወዲሁ ይሰመርበት። የሰማያዊ ፓርቲ በደብዳቤ አስተዳደሩ እውቅና የሰጣቸው ከሆነ የእውቅና ደብዳቤዉን እና ሰልፉ የሚደረግበትን አቅጣጫ በቶሎ ማሳወቅ ያለባቸው መሰለኝ።
