ከ14 ዓመታት በላይ በኃላፊነት የከተማውን መንገዶች ባለሥልጣን ሲመሩ የቆዩት ከነምክትላቸው ተሰናበቱ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣንን በዋና ሥራ አስኪያጅነት ለ14 ዓመታት ሲመሩ የቆዩት ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌና ምክትላቸው አቶ ግደይ እሸ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተሰማ፡፡
የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ከፍተኛ ኃላፊዎች እንደሚነሱ ሲነገር ቢቆይም ከኃላፊነታቸው መሰናበታቸውን የሚገልጸው ደብዳቤ ሰሞኑን ደርሷቸዋል፡፡
ሁለቱም ባለሥልጣናት ከኃላፊነት እንዲነሱ የተደረገበት ምክንያት በይፋ ባይገለጽም፣ በባለሥልጣኑ ውስጥ ታይተዋል ከተባሉ ችግሮች ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ አስተዳደር ባካሄደው ግምገማ እንደሆነ ታውቋል፡፡
በተለይ ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌ ከኃላፊነት እንደሚነሱ እየተነገረ በነበረበት ወቅት፣ ቦታውን ተክቶ የሚሠራ ኃላፊ ለመመደብ አስተዳደሩ ሲያፈላልግ መቆየቱንም ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ኢንጂነር ፍቃዱን በመተካት የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ይሆናሉ ተብለው ከታጩትና ጥያቄ ከቀረበላቸው መካከል ቀደም ሲል የኢትዮጵያ መንገድ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ በኋላም የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ እንደሚገኙበት ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ የአዲስ አበባ ከንቲባ በነበሩበት ወቅት በአስተዳደሩ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ከተመደቡት ባለሙያዎች መካከል አንዱ የነበሩት ኢንጂነር ፍቃዱ፣ ከ14 ዓመታት በላይ በኃላፊነት የከተማውን መንገዶች ባለሥልጣን ሲመሩ ቆይተዋል፡፡
እስካሁን ድረስ ከኃላፊነት የተነሱበት ምክንያት ባይታወቅም መልቀቃቸው ግን አይቀሬ ነበር ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል ኢንጂነር ፍቃዱ ከኃላፊነታቸው የሚሰናበቱት በፈቃዳቸው ነው የሚሉ አስተያየቶችም እየተደመጡ ነው፡፡