የሠልፉ አስተባባሪዎች እየወጡ ያሉትን ባነሮች እንደማያውቋቸው ገለጹ የዐማራ ልዩ ኃይል ፖሊስ አጋርነቱን እየገለጸ ነው
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
የሠልፉ አስተባባሪዎች እየወጡ ያሉትን ባነሮች እንደማያውቋቸው ገለጹ Muluken Tesfaw
ሴቶችና ሕጻናት በሰልፉ ላይ እንዲገኙ ጥሪ አቅርበዋል፤ የዐማራ ልዩ ኃይል ፖሊስ አጋርነቱን እየገለጸ ነው
ሐምሌ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ በሚካሔደው ሰልፍ ላይ ይያዛሉ ተብለው የሚወጡትን ባነሮች ሰልፉን የሚያዘጋጁ አካላት እንደማያውቋቸው ገልጸዋል፡፡ ሰልፉ ላይ የሚንጸባረቀው በዐማራው ሕዝብ ላይ የሚደርሱ በደሎችንና የወልቃይት ጠገዴ የዐማራ ማንነት ጥያቄ ላይ ያተኮረ ብቻ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
እየወጡ ስላሉት ባነሮችና ባለቤትነታቸው ላነሳንላቸው ጥያቄ ‹‹ምንም እንኳ አንተ ያነሳሃቸው ሀሳቦች ትክክለኛ ቢሆኑም እንደዚህ ያለ ሐሳብ እኛ አላነሳነም፡፡ ይህ የወልቃይት ጠገዴን የዐማራ ማንነት ጥያቄን በሌላ ሀሳብ ሸፋፍኖ ለማለፍ የሚደረግ ነው፤ ይህም ሕወሓት የመልካም አስተዳደር ችግር ነው ብሎ እንዲያልፈው መንገድ ማዘጋጀት እንዲሁም የ‹‹ጸረ ሰላም›› ኃይሎች እጅ አለበት የሚለውን የሕወሓት ሀሳብ ለመደገፍ ጎን ለጎን እየተሰራ ያለ ደባ እንዳይሆን ጥርጣሬ አለን›› ሲሉ ለባነር ዝግጅት የተመደቡት አካላት ገልጸዋል፡፡
በዚህ መረጃ መሠረት ጎን ለጎን ሌላ ኮሚቴ ተዋቅሮ እያዘጋጀው ያለ ባነር ካለ እርምት እንዲወስድ ብሎም መሠረታዊውን ጥያቄ ብቻ እንዲያንጸባርቅ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ገለጻ እንዳደረጉት አካላት ማንም ሰው እስካሁን ድረስ እንዳላገኛቸው እነርሱ ያዘጋጇቸው ባነሮችም ይፋ እንዳልሆኑ ገልጸዋል፡፡ እነዚህን ባነሮች ይዘው በመምጣት ችግር እንዳይፈጥሩም አሳስበዋል፡፡
ሰላማዊ ሰልፉን የሚያዘጋጁት አካላት ሴቶችና አዛውንቶች በሕብረት ወደ ሰልፉ እንዲመጡ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ በየመንገዱ ያሉ የዐማራ ልዩ ኃይል ፖሊስ አባለት በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለዐማራው ሕዝብ ድጋፍ እየሰጡ እንዳሉ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ‹‹እኛ እኮ ከእናንተ ጋር ነን›› ሚሉ መልእክቶችን እያስተላለፉ ይገኛል፡፡
ሰላማዊ ሰልፉን በተመለከተ የመንግሥት አካላት ፈቅደናል አልፈቀድንም የሚል ንትርክ መፍጠራቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በጎንደር በሚገኙ በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ‹‹የፋሲል ደመወዝና የሻንበል በላይነህ›› ሙዚቃዎች እንደሚሰሙም ከቦታው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡