በጎንደር እሁድ አስተዳደሩ አወቆት ሐምሌ 17 ሰላማዊ ሰልፍ ሊኖር ይችላል (ግርማ ካሳ)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ከሕዝቡ የተወጣጡ የአገር ሽማግሌዎች ከክልሉ የብአዴን አመራሮች ጋር በመነጋገር በጎንደር አንጻራዊ መረጋጋት እንዳመጡ በስፋት የተዘገበ ጉዳይ ነው። ከትግራይ የመጡ የሕወሃት ታጣቂዎች፣ ከክልሉ አስተዳደር እና የጸጥታ ሃይሎች እውቅና ዉጭ፣ እንደ ወንበዴ በሌሊት በመምጣት፣ በሰላም ይኖሩ የነበሩ ወገኖችን አፍነው ለመዉሰድ ባደረጉት ሙከራ፣ በጎንደር ደባርቅ በመሳሰሉ ቦታዎች ለብዙ ዜጎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው ቀዉስ መከሰቱ ይታወቃል።

ይሄን ሕወሃት ያመጣዉን ቀዉስ የአገር ሽማግሌዎች ከብአዴን ጋር በመሆን ለጊዜዉ እንዲረግብ በማድረጋቸውም በጎንደር ስታዲየም ብዙ ስው በተገኘበት የእግር ኳስ ጨዋታ በሰላም ተጠናቋል። የጎንደር ሕዝብ ካልተነካ የማይነካ፣ ካልተደፈረ የማይደፍር ጨዋና የሰለጠነ ህዝብ መሆኑንም አረጋግጧል።

ይህ ማለት ግን የሕዝቡ መሰረታዊ የመብትና የፍትህ ጥያቄዎች ተመልሰዋል ማለት አይደለም። አሁን በወልቃይት የማንነት ጥያቄ ዙሪያ ታፍነው የተወሰዱ ዜጎች በማእከላዊ ቶርቸር እየተደረጉ ነው። ቤተሰቦቻቸው እንዳይጎበኟቸው ተከልክለዋል። ለጊዜው የአጋዚ ጦር ከከተማዋ ቢወጣም ተመልሶ ላለመምጣቱ ምንም ማስተማምኛ የለም ። ከጎንደር ዉጭ ሕወሃት አሁንም ግፍና በደል በኢትዮጵያዉያን ላይ እየፈጸመ ነው። በመሆንኑም ሕዝብን ወክለው የተፈጠረዉን ቀዉስ ለማረጋጋት፣ ከብአዴን ጋር የሰሩ ሽማግሌዎች፣ በሕገ መንግስቱ የተደነገገዉን ሀሳብን በነጻነት የመገልጽ መብት በመጠቀም፣ ትግሉ እንዲቀጥል፣ ሕዝቡ በሰላም ድምጹን እንዲያሰማ ለእሁድ ሐመሌ 17 ቀን ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ እንደጠሩ ዘገዎች ይጠቁማሉ። ሰልፉ እንደሚደረግ፣ በሕጉ መስረት ለከተማዋ ጽ/ቤት የእውቅና ደብዳቤ የገባ ሲሆን፣ አስተዳደሩ ነገ አርብ ሐምሌ 15 ቀን አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ይጠብቃል።

ሕወሃት፣ ሕገ መንግስቱን በመጻረር፣ የሕዝብ ድምጽ እንዳይሰማ፣ ብአዴን “ሰልፍ ማድረግ አይቻልም” ብሎ ሰልፉን እንዲከለከል ግፊት ማድረጉ አይቀርም። በክልሉ ያሉ የብአዴን አመራሮች ግን ፣ ሕወሃትን ለማስደሰት ለመብቱና ለነጻነቱ ከቆረጠ ህዝብ ጋር ይጋጫሉ ተብሎ አይጠበቅም። ከሆነም ብአዴን ላለፉት አንድ ሳምንታታ ከአገር ሽማግሌዎችና ክሕዝብ ጋር በመነጋገር ያመጣዉን መረጋጋት መልሶ አደፈረሰው ማለት ነው። በሰላም ድምጽን ማሰማት ካልተቻለ ወደ አላስፈላጊ መንገድ መኬዱ አየቀርምና። ደግሞ ሕወሃት ደጋፊዎችን ሰብስበ ጠመንጃ ስልፍ ሲጠራ ብአዴን ለምን ሰልፍ ጠራህ ብሎት ያወቃል ወይ ? ታዲያ በአማራው ክልል ስለሚሆነው ነገር ሕወሃት ምን አገባው ?

በጎንደር ቢያንስ ወደ ሶስት መቶ ሺህ ህዝብ ይኖራል ተብሎ ይገመታል። ሆኖም በጎንደር ዙሪያ ካሉ የተለያዩ ከተሞች ሰዎች ከተሰባሰቡ ፣ አገዛዙ ሰዉ ወደ ጎንንደር ከተማ እንዳይገባ መንገዶችን ካልዘጋና የትራንስፖርት እንቅስቅሴ እንዳይኖር ካላደረገ፣ በመቶ ሺሆች ምናልባት ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ሊሰለፍ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል። ቁጥሩን በትክክለልመገመት አሁን ቢያስሸግርም፣ ሰልፉ ከተካሄደ ግን ያለ ምንም ጥርጥር በጎንደር ታሪክ የመጀመሪያው የሆነ የሰላማዊ ህዝብ ማዕበል ሊታይ ይችላል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በባህርር ዳር፣ በደሴንና በደብር ብሃርና ተመሳይ ሰልፎችን ለማድረግ ዘጅቶች እየተጠናቀቁ ነው።

ህዝብ በዚህ መልኩ አንገቱን ቀና አድርጎ ሲነሳ ከማየት የበለጠ ደግሞ ደስታና ኩራት የለም።ጎንደር አልተወለድኩም። ጎንደርን በአካል አይቼ አላውቅም። ግን አሁን ጎንደር ዉስጤ ገብታለች። በመንፈስ እኔም አሁን ጎንደሬ ነኝ !!!!!

(ሳተናው ድረገጽ)