ቤተል ቲቺንግ ጠቅላላ ሆስፒታል የሕመምተኞችን ኩላሊት በመስረቅ ተከሰሰ፤4,590,000 የጉዳት ካሳ ተጠይቋል


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የገጠማቸውን ሕመም ለማወቅ ባደረጉት ምርመራ በግራ ኩላሊታቸው ላይ ጠጠር መኖሩ የተነገራቸው የ37 ዓመት ሴት፣ ጠጠሩን በቀዶ ሕክምና ለማስወገድ በቤተል ቲቺንግ አጠቃላይ ሆስፒታል የተኙ ቢሆንም፣ ሕክምናው ተደርጎላቸው በሰላም ከተጠናቀቀ ከአራት ዓመታት በኋላ ባደረጉት የአልትራ ሳውንድ ምርመራ የግራ ኩላሊታቸው ሙሉ በሙሉ ተነጥሎ መውጣቱን በማወቃቸው የፍትሐ ብሔር ክስ መሠረቱ፡፡

ያለፈቃዳቸውና ያለዕውቀታቸው የግራ ኩላሊታቸው መውጣቱን ካረጋገጡ በኋላ ክስ የመሠረቱት የ37 ዓመቷ ወጣት ወ/ሪት ወርቅነሽ ደበላ የሚባሉ ግለሰብ ሲሆኑ፣ ክሱን የመሠረቱት በቤተል ቲቺንግ አጠቃላይ ሆስፒታልና ቀዶ ጥገናውን አድርገዋል በተባሉት እንግሊዛዊው ሐኪም ፕሮፌሰር ጎርደን ዊሊያም ላይ መሆኑን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀጥተኛ ስምንተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ያቀረቡት የክስ ቻርጅ ይገልጻል፡፡ ተጎጂዋ በጠበቃቸው አቶ ሰለሞን ጓንጉል አማካይነት ያቀረቡት የፍትሐ ብሔር ክስ እንደሚያብራራው፣ በሐምሌ ወር 2004 ዓ.ም. በሚሠሩበት ተቋም ክሊኒክ ተመርምረው፣ በሪፈራል ወደ ቤተል ቲቺንግ ጠቅላላ ሆስፒታል ተልከዋል፡፡

በሆስፒታሉ የላብራቶሪና የአልትራሳውንድ ምርመራ ታዞላቸው ውጤቱ በሌላ አካላቸው ላይ ውኃ መኖሩንና በግራ ኩላሊታቸው ላይ ጠጠር እንደሚታይ ተገልጾላቸዋል፡፡ ጠጠሩን በቀዶ ሕክምና ካስወጡ በኦቫሪ ላይ የታየው ውኃ እንደሚጠፋ ተነግሯቸው ወደ ፕሮፌሰሩ መላካቸውን ክሱ ያብራራል፡፡ ፕሮፌሰሩ ድጋሚ ምርመራ አድርገው ጠጠር መኖሩን ካረጋገጡ በኋላ፣ ግለሰቧ አልጋ እንዲይዙ አድርገው ጠጠሩን ለማስወገድ ሌሎች አማራጮች እንዳሉ ሳይገለጹላቸው፣ የኩላሊት ጠጠሩን በቀዶ ሕክምና አውጥተው ለከሳሿም እንዳሳዩዋቸው ክሱ ይገልጻል፡፡ የስድስት ሳምንታት እረፍትና የተኝቶ ታካሚዎች የምስክር ወረቀት ፈርመው ሰጥዋቸው፣ ታካሚዋ ሐምሌ 24 ቀን 2004 ዓ.ም. ከሆስፒታሉ እንደወጡም ያክላል፡፡ የሕክምና ተቋሙ ከመሥሪያ ቤታቸው ጋር ባለው የሕክምና ስምምነት መሠረት ከሳሿ በሆስፒታሉ ለተለያዩ ሕክምናዎች ክትትል ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን፣ ለሌሎች ሕመሞች የሚታዘዙላቸው መድኃኒቶች አልስማማ እንዳላቸው ክሱ ይገልጻል፡፡

በሌላ አካል ላይ ታይቷል የተባለው ውኃ መጥፋት አለመጥፋቱን ለማረጋገጥ ከሦስት ዓመታት ቆይታ በኋላ በጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም. አልትራሳውንድ ሲነሱ፣ የግራ ኩላሊታቸው እንደማይታይ ባለሙያዎች እንደነገሯቸው ክሱ ይጠቁማል፡፡ ግለሰቧ በባለሙያ የተነገራቸውን ባለማመንና በመደናገጥ ክትትል ወደ ሚያደርጉላቸው የቤተል ሆስፒታል ሠራተኛ ዶክተር ሄደው የተነገራቸውን ሲያስረዷቸው፣ ቀደም ብለው የቀዶ ሕክምና ባደረጉበት ወቅት የነበራቸውን የሕክምና ማስረጃ እንዲያገኙ ነግረዋቸው፣ በብዙ ውጣ ውረድ ማስረጃቸውን ማግኘታቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ ኩላሊታቸው መኖር አለመኖሩን በድጋሚ በቤተዛታ ሆስፒታል ባደረጉት ምርመራ፣ የግራ ኩላሊታቸው እንደማይታይ ማረጋገጣቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

ነገር ግን ቀደም ብለው በቤተል ቲቺንግ ጠቅላላ ሆስፒታል ባደረጉት ምርመራ፣ ሁለቱም ኩላሊታቸው እንደነበር በሰነድ መረጋገጡን ክሱ ጠቁሞ፣ በሆስፒታል ቀዶ ሕክምና ካደረጉ በኋላ ኩላሊታቸው እንዴት ላይታይ እንዳልቻለ ተጎጂ ማብራርያ ጠይቀው፣ ፕሮፌሰሩ ማብራርያ መስጠታቸውንም ክሱ አካቷል፡፡ ፕሮፌሰሩ በሰጡት ማብራርያ ግለሰቧ የቀኝ ኩላሊታቸው ጤነኛ እንደነበርና የግራ ኩላሊታቸው ግን ጠጠር እንደነበረበት መናገራቸው በክሱ ተገልጿል፡፡ እንዲሁም የግራ ኩላሊታቸው መኮማተሩንና ሌሎችም ምርመራ አክለው ከቀዶ ሕክምና በፊት የታካሚዋ ኩላሊት መወገድ እንዳለበት በመወሰን ማስወገዳቸውን፣ በጽሑፍ ማብራርያ መስጠታቸውን ክሱ ያብራራል፡፡ ፕሮፌሰሩ የራሳቸውን ውሳኔ ለታካሚዋ የማሳወቅና የማስፈረም ግዴታ ቢኖርባቸውም አለማድረጋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

ፕሮፌሰሩ ለታካሚዋ በሰጡት የሕክምና ሰርተፊኬት ላይ የጠቀሱት የኩላሊት ጠጠር ቀዶ ሕክምና ማድረጋቸውን እንጂ፣ ስለኩላሊቱ መወገድ የጠቀሱት ነገር እንደሌለም ያብራራል፡፡ ፕሮፌሰሩ ማብራርያ ሲሰጡ ከግራ ኩላሊታቸው ላይ ጠጠር እንዳወጡ የገለጹ ቢሆንም፣ ተኝተው ታክመው ሲወጡ በሰጡት ሰርተፍኬት ላይ ግን ከቀኝ ኩላሊታቸው ላይ ጠጠሩ እንደወጣ መግለጻቸውንና ይህም የተለያየ መረጃ መሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡ ግለሰቧ በመጀመርያ ሕክምና ሲያደርጉ ምንም ዓይነት የኩላሊት ሕምም እንደሌለባቸውና ጤነኛ መሆናቸውን የሚያስረዳው ክሱ፣ ቀዶ ሕክምና ተደርጎላቸው ከሦስት ዓመታት በላይ ሌላ ሕክምና ሲከታተሉ ምንም የሚያውቁት ነገር እንዳልነበረና ፕሮፌሰሩ በራሳቸው ውሳኔ አካላቸውን ከሚያሳጧቸው ሊያማክሯቸው፣ ሊስማሙና ሊፈርሙ ይገባ እንደነበር ያክላል፡፡

በአንድ ኩላሊት ሲኖሩ ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸው እንደበርም ሊገለጽላቸውና ሙያዊ ምክር ሊደረግላቸው ይገባ እንደነበርም ግለሰቧ በክሱ ገልጸዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ በእንግሊዝ በመምህርነትና በሆስፒታል አስተዳዳሪነት መሥራታቸውን፣ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ፕሮግራሞችን በተለያዩየ የአፍሪካ፣ አውሮፓና ሌሎች አገሮች የጀመሩት እሳቸው መሆናቸው በክሱ ተዘርዝሯል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የእንግሊዝ መንግሥት በሚያስተዳድረው ብሪትሽ ካውንስል አማካይነት መሆኑን ጠቁመው፣ ከፍ ያለ የሥራ ልምድና ዕውቀት ያላቸው ከመሆኑ አንፃር የተጎጂን ፈቃድ ማግኘት እንደሚገባቸው ይጠፋቸዋል የሚል ግምት እንደሌላቸው በክሱ ገልጸዋል፡፡

የግራ ኩላሊታቸውን ያወጡትም ሆን ብለው ነው የሚል ግምት እንዳላቸውም አክለዋል፡፡ በመሆኑም ፕሮፌሰሩ የተጎጂን የግራ ኩላሊት ያለፈቃዳቸው በማውጣታቸው ላደረሱት ጉዳት ኃላፊነት እንዳለባቸው በክሱ ገልጸዋል፡፡ ተጎጂዋ የኩላሊታቸው መውጣትን ካወቁ ጀምሮ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ችግር እንዳጋጠማቸውም በክሱ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ስምንተኛ ቀጥተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት 4,590,000 ብር ተከሳሾች የጉዳት ካሳ እንዲከፍሏቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ ግለሰቡ የዳኝነት መክፈል እንደማይችሉ ለፍርድ ቤቱ በማመልከት በደሃ ደንብ እንዲታይላቸው ጠይቀዋል፡፡ ክሱ መታየት ያለበት በደሃ ደንብ ነው ወይስ አይደለም በሚለው ላይ ለመወሰን ቤተል ቲቺንግ አጠቃላይ ሆስፒታል መልሱን በጽሑፍ እንዲያቀርብ ለሐምሌ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ፍርድ ቤቱ መጥሪያ ልኮለታል፡፡