ኢትዮጵያ – አረብ – እስራኤል (ትንሽ ረዘም የሚል ፅሑፍ) (አዲስ ከድሬዳዋ)
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ኢትዮጵያ – አረብ – እስራኤል (ትንሽ ረዘም የሚል ፅሑፍ)
(አዲስ ከድሬዳዋ)
ሰሞኑን የገልፍ የጋራ ትብብር አባል የሆኑት እነየተባበሩት አረብ ኢሚሬቶችና ሳዑዲ የኤርትራን አሰብ ወደብ መከራየታቸውንና ቀይባህርንም የአረብ ባህር የማድረግ የዘመናት ውጥናቸውን ሊያሳኩ እየመሰለ እንደሆነ በተለያዩ ሚዲያዎች እየተነገረ ነው፡፡ ከእነሱ ቀድሞ ኳታር ጦሯን በኤርትራ እንዳሰፈረች ይታወቃል፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት ኢትዮጵያዊ ደም ያለው በዜግነት ግን ኳታራዊ የሆነ የኳታር ወታደር ኤርትራ እንደነበረ አዲስአበባ ያሉ ዘመዶቹ ሲያወሩ አስታውሳለሁ፡፡ ይህንን የገልፍ ሃገራት እንቅስቃሴ ደግሞ ግብፅ በደስታ እያየችው እንደሆነ ነው የሚነገረው፡፡
ይህንን የሚያደርጉት ለምንድን ነው
ሃገራቱ በቀይ ባህር ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ ሙሉ ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ እስከዛሬ የምዕራብ ሀገራትም የምስራቅ ሀገራትም በአካባቢው ከትመዋል፡፡ በርካታ ሀገሮች በጂቡቲ የጦር ቤዝ ወይም ቃኚ ሀይል አላቸው፡፡ አረቦቹ ሶማሊያን ለመያዝ አስቸጋሪ እንደማይሆንባቸው ያስባሉ፤ የኤርትራ ጉያቸው ውስጥ የመሸጎጥ ጥያቄ ግን በእልልታ የሚቀበሉት ነገር ነው፡፡ ደስታቸውን ድርብ የሚያደርገው ደግሞ ተለዋዋጭ ባህሪይ ያለው ኢሳይያስ ነገ ይገለበጥብናል ብለው እንዳይሰጉ ወደቡን በሊዝ አከራይቷቸዋል፡፡ ኢሱ ቢገለበጥም ወደቡን አይለቁም፡፡
ኢትዮጵያ ለነሱ ምንድን ነች
ብዙዎቻችን ከልጅነት ጀምሮ ስንሰማ የኖርነው የግብፅ የኢትዮጵያን መልማት ያለመፈለግ ጉዳይ አንዱ ነጥብ ነው፡፡ ልብ በሉ የአሁኑ የግብፅ አስተዳደር ስጋቱ የህዳሴው ግድብ ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ ነገ ይቺ ሀገር ባደገች ቁጥር የአባይ ተፋሰስ አካባቢዎች፣ በተለይ አማራና ትግራይ ዋነኛ የምግብ እጥረት ተጋላጭ በመሆናቸው ወንዙን ወይም የወንዙን ገባሮች እየጠለፉ ለመስኖ እንጠቀም ማለታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ይህንን ባንድ ወቅት የቀድሞው ጠ.ሚ. በይፋ ተናግሮታል፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ኮስምኖ መቅረት በእጅጉ ይፈለጋል፡፡
ሳዑዲና ኳታር አጀንዳቸው ሌላ ነው፡፡ በሃገራቸው ያለው አምባገነናዊ ስርዓት ያለተቃውሞ በሀገራቱ ላይ ንግስናውን ሊያስቀጥል የሚችለው ዴሞክራሲና ዴሞክራሲዊ አስተሳሰብ በሀገራቱ እስካልደረሰ ድረስ ብቻ ነው፡፡ በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነትና ከዚያም በኋላ በነበሩት ዓመታት የሰሜን አፍሪካና ጥቂት የመካከለኛው ምስራቅ አረብ ሀገራት ስልጣኔንና ዴሞክራሲያዊ ባህልን በተለየ ደረጃ ባህላቸው ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ እነኚህ ሃገራት እየበዙ በመጡ ቁጥር በጎረቤቶቻቸው ላይ የሚፈጥሩት የአስተሳሰብ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ ለሳዑዲና ኳታር አምባገነኖች ህልውና ስጋት የሆነ አስተሳሰብን የሚፈጥር ነው፡፡ ለምሳሌ በ1960ዎቹ በሺ የሚቆጠሩ የግብፅ ሴቶች ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው ሂጃብ እኛ ለራሳችን ብለን ሳይሆን ለወንዶች ብለን እንድንለብስ የተገደድነው ልብስ ነው ብለው በአደባባይ ላይ በጅምላ ያቃጠሉ ሲሆን በዘመኑም ሂጃብ መልበስ ነውር የመሰለበት ሁኔታ ሁሉ ተፈጥሮ ነበር፡፡
ከ1980ዎቹ ጀምሮ ግን እነሳዑዲ ይህንን ለህልውናቸው ስጋት የሆነውን ዘመናዊ አስተሳሰብ ወደሃገራቸው እንዳይስፋፋ ለመዋጋት ዋናው ስልት በቤታቸው ጋሻና ጦር ይዞ መጠበቅ ሳይሆን ይህንን ዘመናዊ አስተሳሰብ የሚፀየፍ አስተምህሮ የሚከተለውን አክራሪ የእስልምና ሴክት(ዋሃቢዝም ወይም ሰለፊ) ኤክስፖርት በማድረግ እነሱ ጋር ያለው ልማድ የመላው ሙስሊም ልማድ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ጀምረዋል፡፡ በዚህም በተለይ በድሃ ሃገራት የማይናቅ ውጤት እያመጡ ናቸው፡፡ ባጠቃላይ የሰለፊ እምነትን ማስፋፋት የመንግስታቱ ቁልፍ ፖለቲካዊ አጀንዳ ሆኖ እየተሰራበት ነው፡፡ ይ ለእነሱ ፖለቲካ እንጂ የሐይማኖት ጉዳይ አይደለም፡፡
ለሃገራቱ ቅርብ የሆነችውና ከሳዑዲ አረቢያ የበለጠ ሙስሊም የሚኖርባት ኢትዮጵያም ይሄንኑ ገፈት እንድትቀምስ ከተወሰነባት ሀገራት አንዷነች፡፡
እነአልጀዚራ ከ90 ፐርሰንት በላይ የኦሮሚያ ህዝብ ሙስሊም ነው እያሉ የሚዘግቡት(በተጨባጭ ግን በኦሮሚያ 50 ፐርሰንት ገደማ ነው ሙስሊሙ)፣ ራሳቸው አፈላልገው ለአክቲቪስቶች የሚዲያ ሽፋን የሚሰጡት (ጃዋር ለመጀመሪያ ጊዜ ኦሮሞ ፈርስት ብሎ በአልጀዚራ የተናገረው ራሳቸው አልጀዚራዎች ስለኦሮሞ ኮዝ የሚናገር ሰው እንዲቀርብላቸው በጠየቁት መሰረት የአሁኑ ኦኤምኤን መስራቾች ተወያይተው ጃዋር በሚዲያው እንዲቀርብ ወስነው ሊቀርብ እንደበቃ ዶክተር ሶሎሞን ኡንጋሼ ሲናገር አስታውሳለሁ)፣ ከኳታር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የተቀዳ ነው፡፡
በግብፅ በርከት ያለ የኦሮሞ ኮሚዩኒቲ መኖሩ፣ የጃዋር ተደጋጋሚ የግብፅ ጉብኝት፣ በሌሎች አረብ ሃገራት ከሚኖሩት ኦሮሞዎች ይልቅ በግብፅ ያሉ የኦሮሞ ኮሚዩኒቲዎች ፖለቲካ ላይ ንቁ መሆናቸው እንዲሁ በአጋጣሚ አይመስልም፡፡ በግልፅ አፍጥጦ የሚታዬው እንደዚህ ከሆነ ከመጋረጃ በስተጀርባስ ስንት ይኖራል ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል)፡፡
በሌላ በኩል ኦብነግ እና አልሸባብ ከኳታር እና ሌሎች የገልፍ ሃገራት ያገኙ የነበረው ድጋፍ በአንድ ወቅት የቀድሞው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዲፕሎማሲው ከተለመደው ወጣ ብለው በይፋ ኳታር ይሄንን ነገር ካላቆመች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችንን እናቋርጣለን ብለው የዛቻ መግለጫ እስከማውጣት አድርሷቸው ነበር፡፡ ከሚዲያ እይታ ውጪ የአረብ ዲፕሎማቶች (ለምሳሌ የፒኤልኦ የቀድሞ ዲፕሎማት ከኦሮሞ አክቲቪስቶች ጋር እንደሚገናኝ በአንዳንድ ሚዲያዎች መዘገቡን እዚሁ ፌስቡክ ላይ አንብበናል፡፡ ከሌሎች እስላማዊ ወይም ወደፊት እስላማዊ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ከሚታሰቡ ሀይሎች ጋር ግንኙነቶች ሊኖሩ እንደሚችሉም ለመገመት አይከብድም፡፡
ልብ በሉ በሀገር ቤት የተቀጣጠለው የኦሮሞ ፕሮቴስት የአረቦች የእጅ ስራ ነው የሚል አቋም የለኝም፡፡ እያንዳንዱ በዚህ እንቅስቃሴ የተሳተፈ የኦሮሞ ወጣት የራሱ ሀይማኖታዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ምክንያቶችን አስቀምጦ ነው እየተቃወመ ያለው፡፡ ግን የተቃውሞ እንቅስቃሴውን ለራሳቸው ጥቅም ሊያውሉ የተዘጋጁ/ ጥረት የሚያደረጉ የአረብ ሀገራት የሉም ማለት ይከብዳል፡፡ የኢትዮጵያ መከፋፈል ወይም መዳከም ጥረታቸውን ቀላል እንደሚያደርግላቸው ግልፅ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ ኦትዮጵያን በጅምላ እስላማዊ ለማድረግ ከመሞከር የተከፋፈሉ ግዛቶችን፣ ለምሳሌ ኦሮሚያን እስላማዊ ለማድረግ መሞከር ቀላል እንደሆነ ነው የሚታሰበው)፡፡
በዚህ ሂደት ከአለማችን እጅግ ውድ ከሚባሉ ወደቦች አንዱ የሆነውን የጂቡቲ ወደብን የምትጠቀመው ሃገራችን ነገ የኤርትራ አምባገነናዊ መንግስት ከተቀየረ በሊዝ ልጠቀምበት እችላለሁ ብላ ያመነችበት የአሰብ ወደብ አይኗ እያዬ ተስፋዋን የሚያጨልም ለውጦች እየተካሄዱበት ነው፡፡ የሱዳን ወደብ ለጥቂት የሐገሪቱ አካባቢዎች ካልሆነ ለአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል አዋጪ ወደብ አይደለም፡፡ በፖለቲካዊ እውቅና እና የፋይናንስ እጦት የምትሰቃየው ሶማሊላንድም ሆነች መላዋ ሶማሊያ ወደቦቻቸው የጂቡቲ ወይም የአሰብን ያህል የረጂም ጊዜ እቅድ ሊታቀድባቸው የሚችሉ አይመስሉም፡፡ በማንኛውም ጊዜ ፖለቲካዊ የአቋም ለውጥ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ በእነኳታር ተፅዕኖ ስር ላለመውደቃቸው እርግጠኛ መሆን የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ሰላሟን የአፍሪካ ህብረት እያስከበረላት የምትገኘው ሶማሊያ ለህብረቱ ወታደሮች ክብር እንኳ ሳታስብ የገና በዓልን ማክበርን በይፋ የሚከለክል ህግ አውጥታለች፡፡ ወደፊት በሁለት እግሯ የቆመች ቀን ቅልጥ ያለች የኢትዮጵያ ወዳጅ ወይም የለየላት ጠላት ልትሆን ትችላለች፡፡ ሶማሊያ እንደሃገር ከመስረታ ጥቂት አመታት በፊት የነበሩ የሶማሊያ ኤሊቶች ከኢትዮጵያ ጋር መዋሃድን እንደአንድ አማራጭ ያስቡ የነበሩ ሲሆን ሉዓላዊነቷ በተረጋገጠ በጥቂት አመታት ውስጥ ግን የኢትዮጵያ ቁጥር 1 ጠላት ነበር የሆነችው፡፡ በዚህ ደረጃ መገለባበጥ ይቻላል፡፡
የኢትዮ – እስራኤል ነገር
እያደገ የሚሄደውን ኢኮኖሚ የወደብ ፍላጎት ማስተናገድ የሚችል የአስተማማኝ ወደብ ጥያቄ እና የእስልምና አክራሪነት ስጋት በተደቀኑበት ሰዓት ነው የእስራኤሉ ጠ.ሚ. ኢትዮጵያን የጎበኙት፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ከኢትዮጵያ ጋር እዚህ ግባ የሚባል ግንኙነት የሌላት እስራኤል አለች፡፡ በንጉሱ ጊዜ ከነበረው የተወሰነ ወዳጅነት በስተቀር የኢትዮ እስራኤል ግንኙነት ሁለቱ ሃገራት ካላቸው ታሪካዊ ትስስር አንጻር ኢትዮጵያውያን በሚያስቡት ደረጃ አይደለም፡፡
አሁን እስራኤል እና ግብፅ ሁለቱም ከአሜሪካ የ1.5 ቢሊዮን ዓመታዊ የጦር መሳሪያ ድጋፍ የሚያገኙ ሃገራት ናቸው፡፡ እስራኤል በሲናይ በረሃ ያሉ አሸባሪዎችን ለመቆጣጠር፣ የአረቦችን ገደብ የለሽ ፀረእስራኤል ጥላቻ ለማለዘብ/ ለመከፋፈል፣ በዋናነት የምትጠቀመው ግብፅን በመያዝ ነው፡፡ የግብፅ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም ቀላል አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር እስራኤል ለኢትዮጵያ ስትል ይህንን በምንም የማይተካ ግንኙነት ስጋት ላይ የሚጥል ግንኙነት ታደርጋለች ተብሎ አይታሰብም፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የመስኖ ልማትን በተመለከተ ድጋፍ የምታደርግ ከሆነ እንደእስከዛሬው ከአባይ ተፋሰስ ውጭ በሆኑ አካባቢዎች በውስን ደረጃ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ በኢንቨስትመንት ረገድም ከሰለጠነችው እና እጅግ የሰለጠነ(ሌበር ኤክስቴንሲቭ) ቴክኖሎጂን ከምትጠቀመው እስራኤል ይልቅ የታዳጊዋ የግብፅ ባለሃብቶች ኢንቨስትመንት ይበልጥ ተስፋ የሚጣልበት ይመስለኛል፡፡ መሬት ላይ ያለው እውነታም ይሄንኑ የሚያሳይ ነው፡፡ እስራኤል ቅርባችን ስለሆነች ወይም ታሪካዊ ትስስር ስላለን ከሌሎች ሀገራት የተለዬ ነገር መጠበቅ የዋህነት ይመስለኛል፡፡
ስለዚህ ከኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አንጻር ትንሽም ቢሆን ከእስራኤልም ሆነ ከአረብ ሃገራት የሚገኘውን ኢንቨስትመንት አሟጦ መጠቀም የተሻለ እና ሃገራችንም ተግባራዊ የምታደርገው አቅጣጫ ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ የአረብ ሃገራት ፖለቲካዊና ማህበራዊ ግንኙነታቸው ላይ እንከኖች ቢኖሩም ሃገራችን የምታገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ግን ጉልህ ነው፡፡
የወታደራዊ ጥቃት ስጋትን በተመለከተ አረቦች አሰብ ጦር ሰፈር ካቋቋሙ ኢትዮጵያ በኤርትራ ልትወስድ የምትችለው ወታደራዊ እርምጃ ሁሉ ከእነኚህ ሃገራት ጋር ሊያጋጫት ይችላል ማለት ነው፡፡ ይህንን ስጋት በመቀነስ ረገድ እስራኤል ልታበረክት የምትችለው እገዛ እዚህ ግባ የሚባል አይመስለኝም፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ እጇን እንድታስገባ የሚያስገድዳት ሁኔታ የለም፡፡ በስልጠናና ማማከር ሊደግፉን ከሚችሉት በስተቀር የደህንነታችን ዋስትና በራሳችን መከላከያ ላይ ነው የሚወድቀው፡፡ ከሩሲያና እንግሊዝ በላይ ወታደራዊ በጀት ያላት ሳዑዲ የምትጠቀማቸውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች መቋቋም የሚችል ቴክኖሎጂ ባለቤት መሆን የሐገራችን ብቸኛው ክፍተት ይመስለኛል፡፡
አክራሪነት
በህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱም የአክራሪነት አመለካከትን በማስፋፋት ረገድ የተሳካ ስራ እየሰሩብን ነው፡፡ ፀጉሯን በሂጃብ ሰውነቷን በኩታ ትሸፍን የነበረች የወሎ እናት ኩታዋን ጥላ ጅልባብ መልበስ ጀምራለች፡፡ የከሚሴ ዙሪያ አመራሮች አርሶ አደሮች በአመት እስከመቶሺ ብር ገቢ የሚያገኙበትን የትምባሆ እርሻ ምርት እንዳያመርቱ እየከለከሏቸው ነው፡፡ ወንድና ሴት ለየብቻ የሚስተናገዱባቸው ሆቴሎች ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ አብያተ ክርስትያናት ክፍተት በተፈጠረ ቁጥር እየተቃጠሉ ነው፡፡ የራሱን የእስልምና ሃይማኖት ከመውደድና ከማክበር ውጭ ምንም የማያውቀው አማኝ ዛሬ ክርስትያን ከማለት ይልቅ ካፊር ማለት እየቀለለው ነው፣ በእስራኤል እና በሺዓዎች ጥላቻ እየተናጠ ነው፡፡ ባጠቃላይ በጎ ስነምግባርን ሳይሆን አረባዊ አስተሳሰብን እያሰረፁብን ነው፡፡ በዚህ በኩል መንግስታችንም፣ በመቻቻልና መተሳሰብ የሚታወቀው ኢትዮጵያዊው እስልምናም እየተሸነፉ ናቸው፡፡
በዚህ ረገድ ቀድሞ የተሸለ ኑሮን የለመደውና አሁን በአክራሪነት ስጋት ውስጥ የሚኖሩ የአረብ ሃገራት ነዋሪዎች ወደፊት መፈናፈኛ የሚያሳጣው አክራሪነት ቋቅ ብሏቸው ሰለፊን ያለፈበት ሴክት (ሰለፊነትን የድሮ ፋሽን) እስከሚያደርጉት ድረስ ለተወሰኑ አስርት ዓመታት ይህ ስጋት እንዳዣበበብን የሚቆይ ይሆናል፡፡ የሙስሊም – ክርስትያን ማህበራዊ ትስስርም መልኩን እየቀየረ መሄዱ አይቀርም፡፡