በክፉ ምክራቸው ለበርካታ የውስጥ አለመግባባት መንሥኤ የነበሩት የመዝባሪዎች አለቃ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ ከሓላፊነታቸው ተወገዱ!!


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በክፉ ምክራቸው ለበርካታ የውስጥ አለመግባባት መንሥኤ የነበሩት የመዝባሪዎች አለቃ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ ከሓላፊነታቸው ተወገዱ!!

ድምጻችን ይሰማ ዘኦርቶዶክስ's photo.

በፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የልዩ ጸሐፊነት ሥልጣናቸው ተገን፣ የሙስና ሰንሰለት ዘርግተው ሕገ ወጥ ሀብት በማካበትና በክፉ ምክራቸው ለበርካታ የውስጥ አለመግባባት መንሥኤ የነበሩት የመዝባሪዎች አለቃ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ ከሓላፊነታቸው ተወገዱ!!

ልዩ ጸሐፊው፣ በእጃቸው የሚገኘውን ንብረት፣ ዛሬ፣ ሰኞ፣ ሰኔ 27 ቀን 2008 ዓ.ም.፣ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አቡነ ቀሲስ፣ አባ ኪዳነ ማርያም ደስታ አስረክበው፣ ልዩ ጽ/ቤቱን እንዲለቁ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከቅዱስነታቸው በተላለፈ ትእዛዝ መሠረት ነው፣ ዛሬ ከቀትር በኋላ ከሓላፊነታቸው ከልዩ ጽ/ቤት ሓላፊነታቸው የተወገዱት፡፡

ንቡረ እድ ኤልያስ፣ ከሓላፊነታቸው ከተወገዱ በኋላ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ከሚገኙት ድርጅቶች አልያም መምሪያዎች በአንዱ፣ በዋና ሓላፊነት ሊመደቡ እንደሚችሉ ቀደም ብሎ ቢዘገብም፣ ምንም ዓይነት ምደባ እንዳልተሰጣቸውና በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቦታ ተገኝቶላቸው እስኪመደቡ ድረስ እንዲጠባበቁ በፓትርያርኩ ከተጻፈላቸው የማሰናበቻ ደብዳቤ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ የንቡረ እዱን ተለዋጭ ምደባ አስመልክቶ ከፓትርያርኩ እንደተጠየቁና፣ “ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ውጭ ካልኾነ፤ ቦታ የለኝም፤” ማለታቸውን የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ምንጮች ጠቅሰዋል፡፡

ንቡረ እዱ፣ በአስተሳሰባቸው ይኹን በተግባራቸው ያሉበት ብልሹ ተክለ ሰብእና፣ ከመንበረ ፓትርያርኩም ኾነ ከልዩ ጽ/ቤቱ ደረጃ እና ክብር ጋር በመሠረቱ የማይጣጣምና የቅዱስነታቸውም ልዩ ረዳት ሊኾኑ እንደማይገባ በመጥቀስ ከቦታው እንዲርቁ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ በምልአተ ጉባኤ ደረጃ፤ ቋሚ ሲኖዶሱም በመደበኛ ስብሰባዎቹ እንዲኹም፣ ብፁዓን አባቶችና የፓትርያርኩ የቅርብ ወዳጆች እንደ ግለሰብ፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ሲመክሩና ሲያሳስቡ ቆይተዋል፡፡

በግንቦቱ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ልዩ ጸሐፊው ሳይገባቸው ከያዙት ቦታ በአጭር ጊዜ እንዲነሡ፣ ምልአተ ጉባኤው ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጥብቅ ማሳሰቢያ እንደሰጣቸውና ቅዱስነታቸውም፣ ይህንኑ እንደሚፈጽሙ ማረጋገጣቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡

“አንዴ፣ ምልአተ ጉባኤው ሳያልቅ አያንሡኝ፤ ሌላ ጊዜ ትምህርቴን እስክጨርስ ይታገሡኝ” የሚለው የንቡረ እዱ ተማኅፅኖ፣ ፓትርያርኩን እስከ አኹን ድረስ እንዳዘገያቸው ቢገለጽም፤ ዋናው መንሥኤ፣ በቦታው የሚተካና የፓትርያርኩ ምርጫ የኾነ ሰው አለመገኘቱ ነው፤ ይላሉ የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች፡፡

ልዩ ጸሐፊው፣ ልዩ ጽ/ቤቱን ዛሬ ከቀትር በኋላ ለአቡነ ቀሲሱ ሲያስረክቡ፣ የካህናት አስተዳደር መምሪያው ዋና ሓላፊ መጋቤ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዘማርያም፣ የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ዋና ሓላፊ ቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል እና የውጭ ግንኙነት መምሪያ ዋና ሓላፊ መልአከ ሰላም ‘አባ’ ቃለ ጽድቅ ሙሉጌታ በእማኝነት ተገኝተዋል፤ ተብሏል፡፡

የኒውዮርክ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅና በአሜሪካ ስለ ጤና አገልግሎት አስተዳደር በሚያማክር ብሔራዊ ኩባንያ ውስጥ በፕሬዝዳንትነት የሚሠሩ የፓትርያርኩ የቅርብ ወዳጅ፣ ዶ/ር ሙሴ ሐረገ ወይን ቦታውን እንደሚይዙና ጥሪም እንደተላለፈላቸው ሲገለጽ ቢቆይም፣ ፓትርያርኩ ለኤጲስ ቆጶስነት ከጠቆሟቸው ቆሞሳት መካከል አንዱ የኾኑት፣ አወዛጋቢው ቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን ሊተኩ እንደሚችሉ ከወዲኹ ተገምቷል፡፡

በሌላ በኩል፣ የግንቦቱ የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ፣ የልዩ ጽ/ቤቱ አወቃቀር፣ ተግባርና ሓላፊነት በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረቱን ይዞ፤ በአስፈላጊው የሰው ኃይል ተደራጅቶ በሊቀ ጳጳስ እንዲመራ የወሰነው ተግባራዊ እስኪኾን፤ ቀጣዩ ልዩ ጸሐፊ፣ ከብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ዲዮስቆሮስ ጋር በመመካከር እንደሚመደብ ነው፣ እየተገለጸ የሚገኘው፡፡

በአቋቋም የመዘምርነት ሞያ እንዳላቸው የሚነገርላቸው ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ መስፍን፣ ከአንድ ዓመት በፊት ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በማታው መርሐ ግብር በሥነ መለኰት በዲፕሎማ፣ ዘንድሮ ደግሞ በዲግሪ “በከፍተኛ ማዕርግ” ተመርቀዋል፤ ከአልፋ ዩኒቨርስቲ በማኔጅመንት በርቀት የወሰዱት ሌላ ዲፕሎማ እንዳላቸውም ተገልጧል፡፡

ንቡረ እዱ በልዩ ጸሐፊነት ልዩ ጽ/ቤት ከተቆጣጠሩበት ካለፈው ዓመት ወዲኽ ያለው ጊዜ አጭር ቢኾንም፣ የሚሰጡትን ክፉ ምክርና የሚያረቋቸውን ደብዳቤዎች ተከትሎ፣ ፓትርያርኩ በሚያራምዷቸው ሕግንና ምክረ አበውን የሚጥሱ አቋሞች የቤተ ክርስቲያናችንን መልካም ስም እና ዝና የሚጎዱ በርካታ ውዝግቦች ተፈጥረዋል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎችንና የቋሚ ሲኖዶስ መመሪያዎችን በቸልታ እየተላለፉ፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱንና የአህጉረ ስብከትን ሥልጣንና ተግባር እየተሻሙ፣ ከብፁዓን አባቶችና ሌሎች አስፈጻሚ አካላት ጋር ከፍተኛ አለመግባባቶች ተከሥተዋል፡፡ ፓትርያርኩ ራሳቸው፣ በየመድረኩ በቃለ ነቢብ የሚገልጿቸው፤ ትክክለኛውን ሰው በትክክለኛው ቦታ የሚያስቀምጡ፤ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን የሚያሰፍኑ፣ የተቋማዊ ለውጥ ጅምሮችና ተስፋዎች በከንቱ መክነዋል፡፡ በዚኽም ፓትርያርኩ ንቡረ እዱን መልሰው የወቀሱባቸው ጥቂት አጋጣሚዎች የነበሩ ቢኾንም፣ በአብዛኛው ግን የማይተኩ አለኝታ ተደርገው ሲታዩ እንደነበር ነው የሚታመነው፡፡

አዲስ አበባ የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት ከመኾኑም ጋር ተያይዞ፣ ንቡረ እዱ ቀደም ሲል በሥራ አስኪያጅነት ሲያገለግሉ በዘረጉትና በልዩ ጸሐፊነታቸው ተገን ባጠናከሩት የምዝበራ ሰንሰለት፤ ከጉዳይ ማስፈጸም፣ ከአለቆችና ሠራተኞች ዕድገትና ዝውውር ተቀማጫቸውን በማድለብ በተለያዩ ይዞታዎቻቸው ለከፍተኛ ‘ኢንቨስትመንት’ መዘጋጀታቸው ይነገራል፡፡

በቤተሰባዊነት የሚዛመዷቸውን የወቅቱ የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅ በማስመደብ፤ እንዲኹም፣ በቅርቡ፣ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ በሌሉበት ከአስተዳደር ጉባኤው ዕውቅና ውጭ አልቆ በመጣው ከደርዘን በሚልቁ የአድባራት አለቆችና ጸሐፊዎች ዝውውርና ምደባ የነበራቸው ወሳኝ ሚናና ያተረፉበት ኹኔታ ይጠቀሳል፡፡

በሀገረ ስብከቱ፣ በሥራ አስኪያጅነት በሠሩበት 2003 ዓ.ም.፣ በምዝበራ ሰንሰለቱ ያሉ ግለሰቦች በልማት ጉብኝት ስም አጥንተው በሚያመቻቹት የዘረፋ ስልት፣ በየአድባራቱ በሚዘዋወሩበት ወቅት፣ “የኮቴ” የተሰኘና በእያንዳንዱ ከ25ሺሕ ያላነሰ ብር የሚቀበሉበት አማሳኝነት በንቡረ እዱ የተጀመረ ውርስ እንደኾነ ዛሬም የሚነገር እውነታ ነው፡፡

ከመናፍስት ጋር በተያያዙ ክፉ ልማዶች ጭምር ስማቸው የሚነሣው የቀድሞው መሪጌታ ኤልያስ ኣብርሃ፣ ንቡረ እድ ከተባሉበት የርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ካቴድራል በሕዝብ እንዲባረሩ ያደረጋቸው ይኸው የምዝበራ አመላቸው ነው፡፡ ከአዲስ አበባ አድባራት ራሱን ችሎ በሙዳየ ምጽዋት በሚሰበሰብ ገንዘብ የሚሠራው የካቴድራሉ ሙዝየም ግንባታ ውል፣ በተፈጸመበት ኹኔታም መወቀሳቸው አልቀረም፡፡

ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እና በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በዲንነት፤ በጠቅላይ ቤተ ክህነት መንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅነትም ሠርተዋል፡፡

ብልጡ መለኛ ንቡረ እድ ኤልያስ፣ ከፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የመወገዳቸው ጉዳይ፣ ለረጅም ጊዜ በተለያየ መልክ ሲገለጽ ቢቆይም፣ ዛሬ ተጨባጭ እስኪኾን ድረስ፣ ብዙዎችን፣ “ካላየን አናምንም” አሰኝቷቸዋል፤ ምትሃዊ አድርገው የሚያዩዋቸውም አልጠፉም፡፡

ንቡረ እዱ፣ በተማሪ ቤት ሥልጥንናቸውን ያሳዩበትን የአቋቋም ሞያ ይዘው፣ ወደ አዲስ አበባ በ1980ዎቹ አጋማሽ ሲገቡ፣ አገልግሎታቸውን የጀመሩት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በመዘምርነት ነበር፡፡ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ቦታ ይፈለግላቸው ቢባልም፣ ትክክለኛ ምደባቸው እንዲኹ ከመዋቅራዊ ሓላፊነት ውጭ እንዲኾን ብዙዎች ይሻሉ፤ መቼም ለተጠያቂነቱ አላደለንምና!!
Source Hara Tewahdo

ድምጻችን ይሰማ ዘኦርቶዶክስ's photo.