በብሪታኒያ ሕዝበ ውሳኔ ላይ ጥቂት ሀሳቦች (Tadesse Biru Kersmo)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በብሪታኒያ ሕዝበ ውሳኔ ላይ ጥቂት ሀሳቦች (Tadesse Biru Kersmo)

የዛሬ የብሪታኒያ ሕዝበ ውሳኔ ውጤት ኣስገርሞኛል። ከኢኮኖሚም ከደህነነትም አንፃር ብሪታኒያ በአውሮፓ ኅብረት ብትቆይ ኖሮ ይሻላት ነበር ብዬ በግሌ አምናለሁ፤ እኔ የብሪታኒያ ዜግነት ቢኖረኝ ኖሮ በኅብረቱ እንድትቆይ ነበር ድምጽ የምሰጠው። ታላቅዋ ብሪታኒያ እያነሰች የመጣች አገር ናት፤ ይህ ሕዝበ ውሳኔ የቁልቅለት ጉዞዎን ያፈጥነዋል የሚል ስጋት አለኝ።

የኔን የግል እይታ እዚህ ላይ እናብቃና ለምንድነው አብዛኛውን የብሪታኒያ ሕዝብ የአውሮፓ ኅብረት ያንገፈገፈው? ይህ ውሳኔ ለእኛ አገር ፓለቲካ ያለው አንድምታ ምንድነው? ለእነዚህ ጥቃቄዎች በቂ ምላሽ ባይኖረኝም ጥቂት ነገሮችን ልበል።

በአሁኑ ወቅት በዓለም ፓለቲካ ጽንፈኝነት የብዙዎችን አዕምሮ መማረኩ አሳሳቢ ጉዳይ ይመስለኛል። በብዙ የአውሮፓ አገሮች የግራ ፓርቲዎች ይበልጥ ወደግራ፣ የቀኞቹ ደግሞ ይበልጥ ወደ ቀኝ እየተጠጉ የመሀከለኛው – ለዘብተኛውን – የፓለቲካ መስመር ባዶ እያደረጉት ነው። በብርታኒያ ፓለቲካ ውስጥ እየታየ ያለው ነገር ይኸ ይመስለኛል። ዴቪድ ካሜሮን የቀኝ ክንፍ የፓርቲ አባላቱን ለማባበል ሲል ይህን መጥፊያው የሆነውን ሕዝበ ውሳኔ በመደራደሪያነት አቀረበ፤ አሁን ደግሞ ከዚህም በላይ ወደ ቀኝ የመሳብ አደጋ ተደቅኖበታል። ሌበር ፓርቲ ደግሞ ጀረሚ ኮርብን በመምረጥ ከቀድሞው አንፃር ወደ ግራ ተንሸራቷል። በዚህም ምክንያት የብሪታኒያ የመሀል ሜዳ ፓለቲካ እየጠፋ ነው። በፈረንሳይ፣ በስፔንና ሌሎችም የአውሮፓ አገሮች ተመሳሳይ ነገር ይስተዋላል። በአሜሪካም የዲሞክራቱ በርኒ ሳንደርስ (በጣም ግራ) እና የሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ (በጣም ቀኝ) ወደ መድረክ መምጣት ከዚሁ ዓለም ዓቀፍ የስነልቦና ለውጥ ጋር ይያዛል ብዬ አስባለሁ። ሂላሪ ክሊንተን በሳንደርስ ብትተካም ውድድሩ ውስጥ የምትኖረው የድሮዋ ሂላሪ ሳትሆን ወደ ሳንደርስ የተጠጋችዋን ሂላሪ ነው። መሀል ባዶ ሲሆን አደጋ ነው፤ ዓለም ይህ አደጋ ያንዣበበባት ይመስላል።

በዚህ ሕዝበ ውሳኔ ሰበብ ላነሳው የምፈልገው ሌላው ነጥብ ስለኅብረት ያለን ግንዛቤ ነው። ኅብረት ጠቀሜታ የሚኖረው (1) የሚፈለገው ውጤት በግል ማምጣት የማይቻል ሲሆን ወይም (2) በመተባበር ምክንያት የሚገኝ ተጨማሪ ጥቅም ሲኖር ነው። 1ኛ ምክንያት በተመለከተ ለጦር ውርወራ ኅብረት ዋጋ እንደሌለው ለእግር ኳስ ጨዋታ ግን ግዴታ መሆኑን ማስተዋል በቂ ነው። 2ኛው ምክንያት ትንሽ ውስብስብ ነው። በኅብረት ሳቢያ ጊዜን፣ ሰውን፣ ገንዘብን፣ እውቀትን፣ መረጃን፣ ሁኔታዎችንና እና ኔትዎርክን በተሻለ ስልጠት /efficiency/ መጠቀም ሲቻል፤ እና/ወይም ውጤቶች የተሻሉ ሲሆኑ (effectiveness)፤ እና/ወይም ተባባሪ ድርጅቶች በግልም በጋራም ያላቸው ሕዝባዊ ተቀባይነት /legitimacy/ ከቀድሞው የተሻለ ማድረግ ከተቻለ ኅብረት ጥሩ ነው፤እነዚህ በሌሉበት ግን መተባበር ዋጋ የለውም። በሕዝበ ውሳኔው ክርክር ወቅት አንዷ የእንውጣ ተሟጋች የኅብረቱ የሥራ መንዛዛት “28 የአውሮፓ አገሮች የረባ የምግብ ቋጠሮ (takeaway)መስራት አይችሉም” በማለት ነበር የገለፀችው። ኅብረቱ ቢመሰረትም አባላቱን በሚያረካ መጠን ውጤታማ አለመሆኑ ብርታኒያ በጀመረችውና ሌሎች ሊከተሉት በሚችሉት ማፈንገጥ ተገልጿል። ይህ መተባበር ሳንችል ስለኅብረት ጥቅም አብዝተን ማውራት ለምንወድ ኢትዮጵያዊያን ትልቅ ትምህርት ነው።

ዛሬ ብርታኒያ የደረችበት ውሳኔ በርካታ መዘዞችን የሚያስከትል አቢይ ጉዳይ ቢሆንም የውሳኔው አሰጣጥ ሂደት ግን የሚያስቀና ነው። እንዲህ ዓይነቱ ከባድ ውሳኔ ሲወሰን ድምጽ ተጭበረበረብኝ የሚል አንድም ሰው አለመኖሩ የሚገርም ነው። የተቋማት ሚና የታየበት ሕዝበ ውሳኔ! በውሳኔው ይፋ መሆን በኃላ ዴቢድ ካሜሮን ስልጣን ለመልቀቅ መወሰኑ ደግሞ ሌላ አኩሪ ዲሞክራሲያዊ ባህል ነው። ካሜሩን ስልጣኑን እንዲለቅ ባህል እንጂ ህግ አያስገድደውም ነበር።

በኔ ግምት ሕዝበ ውሳኔው ብሪታኒያን የሚጎዳ ቢሆንም እንኳን ካወቅንበት ኢትዮጵያን የሚጠቅም ይመስለኛል። ብርታኒያ የአሜሪካና የህወሓት አገዛዝ ሸሪክ በመሆኗ በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ የነበራት ሚና ኢትዮጵያን የሚጠቅም አልነበረም፤ ይህ ሁኔታ በመጠኑም ቢሆን ይቀየራል የሚል ግምት አለኝ። ከአሁን በኋላ ብርታኒያ ራሷ ችግር ውስጥ መግባቷ አይቀሬ ይመስላል፤ በዚህም ምክንያት ጊዜዋን የምታጠፋው ራስዋን በማስታመም ይሆናል፤ አለበለዚያ ብርታኒያ ከዚህም በታች አንሳ እንግሊዝ ብቻ ልትቀር ትችላለች። ብሪታኒያ ወደራስዋ መመልከት ስትጀምር የኛንም መከራ የመረዳት እድሏ ከፍ ይል ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ።

በመጨረሻም የማነሳው ነጥብ የብርታኒያው ሕዝበ ውሳኔ ከአሜሪካው ምርጫ ጋር የተያያዙ መሆናቸው ነው። ዶናልድ ትራምፕ እዚያ ማዶ፤ ናይጅል ፋራዥ እዚህ ማዶ የሚወረውሯቸውን ቃላት ስናዳምጥ በቀድሞ ታሪክ ናፋቂነት፣ በስደተኞች ጥላቻ፣ በማንነት ጥያቄ፣ በሉዓላዊነት …. ወዘተ ረገድ ከአንድ የአስተሳሰብ ጅረት የተቀዱ መሆናቸውን እንረዳለን። የዚህ ድል ያንን ያጠናክራል። ስለሆነም አሜሪካ ውስጥ ትራምፕ ቢመረጥስ በእኛ ትግል ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ምንድነው ተብሎ በጥልቀት ሊታሰብበት ይገባል።