የግብጽ ፕሬዝዳንት ተፈረደባቸዉ።


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ዶክተር ሙሐመድ ሙርሲ ተፈረደባቸዉ
የፍርድ ሒደቶቹ በሙሉ ይግባኝ ሊባሉ ይችላሉ። በ ስር ሺዎች የሚቆጠሩ የሙስሊም ወንድማማቾች አባላት እስር ላይ ናቸዉ።የወደፊት እጣ ፈንታቸዉ አልታወቀም።
ቢቢኤን ሰኔ 12/2008
ከሰላሳ አመት አምባገነናዊ አገዛዝ በኋላ በዲሞክራሲ የተመረጡት የመጀመሪያዉ የግብጽ ፕሬዝዳንት ተፈረደባቸዉ። ዶክተር ሙሐመድ ሙርሲ እራሳቸዉ በሾሟቸዉ ጠቅላይ ጦር አዛዥ ጀኔራል አብዱልፈታህ አልሲሲ መፈንቅለ መንግስት ከተደረገባቸዉ በኋላ እራሳቸዉና ሌሎች የሙስሊም ወንድማማቾች አባላት በቁጥጥር ስር ዉለዉ ግብጽ ዳግም ወደ አምባገነናዊና ወታደራዊ አመራር መመለሷ የሚታወቅ ነዉ።
በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡት የግብጹ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙሐመድ ሙርሲ አገራቸዉ ላይ የስለላ ተግባር ፈጽመዋል፤ ወሳኝ የሆኑ ምስጢራዊ መረጃዎችን ለኳታር አሳልፈዉ ሰጥተዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዉ ነበር። “በአገር ላይ ክህደትን ፈጸሙ” የሚለዉ ክስ ቢጸና ኖሮ የሞት ፍርድ ሊፈረድባቸው እንደሚችል የመገናኛ ብዙኋን ዘግበዋል። ዶክተር ሙርሲ “ህገወጥ የሆነ ድርጅት በመምራት” የሚል የእድሜ ልክ እስራት በግብጹ ፍርድ ቤት ቢፈረድባቸዉም ፍርድ ቤቱ ገለልተኛ አይደለም ወታደራዊዉን የመፈንቅለ መንግስት የሚያገለግል ነዉ የሚል ክስ ይቀርብበታል።
አንድ አመት ከሶስት ቀን በስልጣን ላይ የቆዩት ዶከተር ሙርሲ ለፍልስጤማዉያን መብት ጥብቅና የቆሙ፣ በየመድረኩና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ንግግር ሲያደርጉ በፈጣሪ ስም በመጀመር ሰላምን በነብዩ ላይ በማዉረድ የሚታወቁ የአገር መሪ ነበሩ። አገሪቷ ዉስጥ ከአርባ አመት በላይ ተንሰራፍቶ የነበረዉን የጦር መኮንኖች በስልጣን መባለግ ለመናድ በመሞከራቸዉና የሙስናዉ ተባባሪ ባለመሆናቸዉ የመፈንቅለ መንግስት ሰለባ እንደሆኑ አስተያየት የሚሰጡ አሉ።
ከአረብ አገራት በሙሉ በህዝብ ቁጥር አንደኛ የሆነችዋ ግብጽ ዲሞክራሲያዊ ከሆነች ሌሎች የአረብ አገራት የራሳቸዉን እድል ወደ መወስን ሊሔድ ይችላሉ የሚለዉ የአረብ አምባገነናዉያን መሪዎች ስጋትና ፍልስጤማዉያንን በሐይል ደፍጥጣ መሬታቸዉን የነጠቀችዉ እስራኤል አጠገቧ ያለቸዉ ግብጽ ህዝቧነጻነትን ከተጎናጸፈ የፍልስጤማዉያን ነጻነት እሙን ይሆናል በሚል ፍራቻና ሴራ ግብጽን ለማዳከም በዉጭ ሐይሎች የተደረገ መፈንቅለመንግስት መሆኑን የአረብ አገራት የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ።
ዶከተር ሙርሲ ቀደም ሲል ሌላ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸዉ ነበር። ሌሎች የሙስሊም ወንድማቾች አባላት በሞት ፍርድ ቢቀጡም ባለዉ አለም አቀፍ ጫና የርሳቸዉ ተፈጻሚ ሳይሆን ዳግም የእድሜ ልክ እስራት ተበይኖባቸዋል። ሌሎች ስድስት ሰዎች በትላንታናዉ እለት በሌሉበት የሞት ፍርድ የተፈረደባቸዉ ሲሆን ከስድስቱ መካከል ሁለቱ የአልጀዚራህ ጋዜጠኞች መሆናቸዉ ታዉቋል።
ለዲሞክራሲ ቆመናል የሚሉ ሐያላንና አገራት እይታ በላተሰወረ መልኩ፤ በዲሞክራሲ የተመረጠ መንግስት በዲሞክራሲ ሊወርድ ሲገባዉ የመፈንቅለ መንግስት ሰለባ ሆኗል። የሞት ፍርድ ለፖለቲካዉ ጥቅም ሲባል በበርካታ ግብጻዉያን ላይ ሲበየን መንግስታቱ ዝምታን መርጠዋል። ዲሞክራሲ መድሎ ያለበትና ለሶስተኛዉ አለም የማይሰራ እስኪመስል ድረስ ምእራባዉያኑ ደንታ-ቢስ መሆናቸዉን አሳይተዋል የሚል የመረረ ሒስ እየተሰጠ ነዉ።
የዶክተር ሙሐመድ ሙርሲ የፍርድ ሒደት ጸንቶ ተፈጻሚ ይሆናልን? ወይስ በሌላ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ለዉጥ ይቀለበሳል? በሒደት የሚታይ ይሆናል።

Abdurehim Ahmed's photo.