• “ጠላትም ሆነ አውሬ ከአንገት በታች መትቼ አላውቅም”
• ዛሬ ኩንታል እየተሸከሙ ኑሯቸውን ይመራሉ
ወደ ጦር ሜዳ ከመግባታችን በፊት—–ስለ አዳኝነትዎ ያጫውቱኝ —
አባቴ… አጎቶቼ … ጠቅላላ ዘር ማንዘራችን … የተዋጣላቸው አውሬ አዳኞች ነበሩ፡፡ “የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ” እንደሚባለው፣ እኔም አባቴንና አጎቶቼን ተከትዬ ነው አውሬ ለማደን በልጅነቴ ጫካ የገባሁት፡፡ በእኛ አካባቢ ባህል አውሬ አድኖ ያልገደለ፣ አንበሳን፣ ነብርን፣ ዝሆንና ጎሽን አልሞ በመተኮስ ያላጋደመ ወንድ አይባልም፡፡ ከወንዶች ጎራም አይሰለፍም፡፡ ሚስቱ ውሃ ልትቀዳ ምንጭ ብትወርድ፣ ቅድሚያ አግኝታ በኩራት ውሃ አትቀዳም፡፡ አንበሳ ገዳይ … ጎበዝ አዳኝ ተሰሚነት ያገኛል፡፡ ክብርና ሞገስ አለው፡፡ ይዘፈንላታል፤ ይጨፈርለታል፡፡ በዚህ ምክንያት ከአውሬ ጋር ነው ያደግነው፡፡ አውሬ ለማደን ከቤታችን ወጥተን፣ ሁለት ሳምንትና ከዚያ በላይ ጫካ ድንጋይ ስር ነበር የምንኖረው፡፡
በወቅቱ ለአደን የምትጠቀሙበትን ጥይት ከየት ነበር የምታገኙት?
እንገዛለና! ግን በዚያን ወቅት ጥይት በጣም ውድ ነበር፡፡ አንዷን ጥይት በ19 ብር ነበር የምንገዛው። አንድ ጥይት ተኩሰን ሳትን ማለት ኪሳራ ውስጥ ወደቅን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ስንመታ አንድ ጥይት፣ አንድ አውሬ እንዲገድል አድርገን ነው፡፡ ገንዘብ ደግሞ ከመንዲና ከአካባቢው እስከ አምቦ ድረስ አውሬ ማደን ለመለማመድ ከሚመጡ ሰዎች እናገኛለን፡፡ ጎሽ ካስገደልን 40 ብር፣ ዝሆን ካስገደልን 80 ብር እንቀበላለን፡፡ ይሄ ገንዘብ በወቅቱ ብዙ ነበር፡፡ በዚያ ገንዘብ ጥይት እንገዛለን፡፡ ያው እነሱም እኛ ድረስ መጥተው አውሬ ማደንና መግደል የሚለማመዱት፣ በአካባቢያቸው ክብርና ዝና ለማግኘት ስለሆነ ሲከፍሉ ቅር አይላቸውም፡፡
የአገራችንን ብርቅዬ የዱር እንስሳት የጨረሳችሁት እናንተ ናችሁ ማለት ነዋ?
አዎ ጨርሰናል፤ ምንም የሚዋሽ ነገር የለውም። ጨፍጭፈን ጨርሰናል፡፡ ያልገደለ ሰው ለሚስትም ለሌላ ክብርም አይታጭም ነበር፡፡ ምን እናድርግ ብለሽ ነው! ለፖሊስ እንኳን አንመችም ነበር፡፡ በእኛ አካባቢ ጠብመንጃ በፖሊስ ተቀማን ማለት፣ በቁመናችን ሞትን ማለት ነው፡፡
በ1969 ዓ.ም ሶማሊያ ኢትዮጵያን ስትወርር፣ ከዘመቱት 300 ሺህ ሚሊሺያዎች አንዱ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ እንዴት ተመለመሉ? ያኔ እድሜዎ ስንት ነበር?
በወቅቱ ሶማሊያ በምስራቅ ኢትዮጵያ 700 ኪ. ሜትር፣ በምዕራብ 300 ኪ. ሜትር ወደ አገራችን ዘልቃ ገብታ ነበር፡፡ ወንድ ልጅ እንዴት አገሩን ለጠላት ሰጥቶ ይቀመጣል የሚል የቅስቀሳ ዘመቻ ነበር፡፡ በወቅቱ ልጅ ነበርኩኝ፡፡ ከአውሬ በስተቀር ሰው ላይ ተኩሼ አላውቅም፡፡ እርግጥ አውሬ በምናድንበት በኩል ሱዳኖች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ሲገቡ እንመልሳቸው ነበር፡፡ እኛ ሳንተኩስ እነሱ ይሸሻሉ፡፡ እኛም የጥይቱ ውድነት ስለሚያሳሳን ቶሎ አንተኩስም ነበር፡፡ እና ያ ቅስቀሳ ሲደረግ ለመዝመት ወደ አውራጃ መጣሁ፡፡ ወቅቱ እንዳልሺው 1969 ዓ.ም ነው፡፡ “አንተ ልጅ ነህ አትሄድም” ተባልኩኝ። “ከኔ በላይ አትተኩስም፤ ስለዚህ ተወኝ” አልኩት አዛዡን፡፡ “አትሄድም” ሲለኝ ዘልዬ ኤኔትሬ ላይ ወጣሁ፤ ጎትተው አወረዱኝ፡፡ እንደገና በትግል ወጣሁና አብሬ ሄድኩኝ፡፡ ያኔ እድሜዬ 15 ዓመት ቢሆን ነው፡፡
ከዚያ ወደ ታጠቅ ጦር ማሰልጠኛ ነው የመጣችሁት?
እውነት ነው፤ወደ ታጠቅ ጦር ማሰልጠኛ ነው የገባነው፡፡ ወቅቱ ዝናብ ስለነበር ታጠቅ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ጭቃው ያስቸግራል፤ በቂ የምግብ አቅርቦትም አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት ከታጠቅ ማዶ መንደር አለ፤ እዚያ እየሄድኩ ቂጣ እየነጠቅኩ እሮጥ ነበር። ብር የለማ—ምን ልክፈል?! ዛሬ የነጠኩበት ቤት ደግሜ አልሄድም፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልን፣ ሶስት ወር ሰልጥነን ቀጥታ ወደ ጦር ግንባር ተላክን፡፡ ግንባሩ ሀረር ቢል ሲዲሞ ይባላል፡፡ ሀረርና ባቢሌ መሀል ነው፡፡ በመጨረሻ ውጊያው ተጀመረ፤ ሰው ዝም ብሎ ይተኩሳል፤ እኔ ግን አልተኩስም ነበር፡፡
ለምን ነበር የማይተኩሱት?
ምን አይቼ ነው የምተኩሰው? ሌሎች አለቆቼም ለምን አትተኩስም ይሉኛል፡፡ በእኔ እምነትና ልምድ፣ያለ ኢላማ አንድም ጥይት መተኮስ ኪሳራ ነው፡፡ “ዝም ብለህ ተኩስ አትበሉኝ፤ ስተኩስ ግን የእኔ ጥይት መሬት ካረፈ ወደ አገሬ መልሱኝ፣ ያለ ኢላማ ግን አልተኩስም” አልኩኝ፡፡ ከዚያ ቢል ሲዲሞ ስንገባ፣ ሶማሊያ የአካባቢውን ት/ቤት አቃጥላ፣ በታንክና በመድፍ ታጅባ እየገፋች መጣች። ውጊያ ላይ የሆነች ጥይት ወደኔ ጩ…ጩ…ጩ… እያለች ትመጣለች፡፡ እኛ ተኝተናል፡፡ “የታለች? እንዴትስ ልተኩስ?” አልኩኝ፡፡ አለቃዬ ኮ/ል ገበየሁ አበበ ይባላሉ፡፡ በቀደምም በኔ ህይወት ላይ በተፃፈው መፅሐፍ ምርቃት ላይ ተገኝተው ስለኔ ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡ “እንዴት ዛሬም አልተኮስክም” ብለው ተቆጡኝ፡፡ “እኔ አላየሁም፤ ጠላት ወደ ሰማይም ወደ ምድርም ይተኩስ፣ሳላይ ጥይት አላባክንም” ብዬ እምቢ አልኩኝ፡፡ በነጋታው ጠዋት ሁለት ሰዓት ላይ፣አንድ የእኛን ወታደር እጁን በምስማር ግራና ቀኝ ቸንክረው፣ በቁመናው ስጋውን ዘልዝለውታል። ቦታው ላይ ስደርስ፤ “ወገኔ ነህ፤ እንዲህ ከምሰቃይ ጨርሰኝ” አለኝ፡፡ “አልጨርስህም” አልኩት፡፡
ለምን?
“እኔ አንተን አልጨርስህም፤ አንተን እንዲህ ያደረገህን ጠላት ግን እጨርስልሃለሁ” ብዬ ቃል ገብቼለት አልፌው ሄድኩኝ፡፡ ከዚያ መቶ አለቃ ሙለታ ደልሳ የሚባል አለ፡፡ “ያውልህ ጠላት፤ እንጨቱ ስር” አለኝ፡፡ “አይቼዋለሁ ዝም በል” አልኩትና ሳልንበረከክ፣ ቁጭ ብዬ ግንባሩን አፈረስኩት፡፡ በነገራችን ላይ እኔ አንድም ቀን አውሬም ይሁን ሰው ከአንገት በታች መትቼ አላውቅም። በፊት ስናድን ቆቅ ለመብላት ስጋዋ እንዳይበላሽ አልመን የምንመታት ራሷን ነው፡፡ ከአንገት በታች የተመታ ጠላት ካለ፣የእኔ አይደለም፡፡ እናም ያንን መትረየስ ተኳሽ ግንባሩን ካልኩት በኋላ “ያው ሰውየው ወድቋል” አልኩት ለመቶ አለቃ፡፡ ይህን እያልኩ እያለ የሟቹ ረዳት መጥቶ መትረየስ ላይ ጉብ አለና ቦታ ሊቀይር ሲል፣አየር ላይ ነው ግንባሩን ብዬ ያነሳሁት፡፡ ከዚያ “ረዳቱን ጣልከው?” አለኝ። “አዎ” አልኩት፡፡ “ሂድና መትረየሱን አምጣልኝ” ጎትቼ አመጣሁለት፡፡ RP 47 ይባላል መትረየሱ። “ስንት ጥይት ተኮስክ?” ሲለኝ “ሁለት” “ስንት ሰው ገደልክ?” ሲለኝ “ሁለት” ብዬ መለስኩለት፡፡ እንግዲያውስ ጠብመንጃ ይቀየርለት ተባለና ረጅም ተቀየረልኝ፡፡ ከእኔ ጋር ጠብመንጃ ይዞ የሚሄድ ቱታ የሚባል ጓደኛዬ ነበረ፡፡ ድሮ አብረን እናድን ነበር። ጎበዝ ሆኖ ዒላማ ላይ ትንሽ ይቀረው ነበር፡፡ እኔን አያጠግበኝም፤ ሌሎች ግን ያደንቁታል፡፡ ከዚያ ሱማሌ ድሬደዋን ወርራ፣ አውሮፕላን ማረፊያውን ከደበደበች በኋላ የኢትዮጵያን ወታደር አባረረች፡፡ እኛ በአንድ በኩል ስንገባ፣ የሱማሌ ወታደር እንደልብ ተገኘ፡፡ መቶ አለቃ ሙለታ “እንደልብ ከተገኘ፣ አውቶማቲክ ተኩስ” አለኝ፡፡ እኔ “አውቶማቲክ አልተኩስም” አልኩኝ፡፡
ለምን ነበር አውቶማቲክ መተኮሱን የጠሉት?
አልሜ ግንባር ግንባሩን ለማለት ነዋ! አውቶማቲክ ከሆነ ጥይት ሊባክንና ኢላማ ሊስት ይችላል፡፡ ከዚያ አሁንም ጣ አሁንም ጣ እያደረግኩኝ ብዙ ሶማሌ እረፈረፍኩኝ፡፡ ጦሩ ወደ ኋላ ሲሄድ እኔ እዛው ቀረሁ፡፡ ወደ እኛ ሊመጡ የነበሩትን በሙሉ ለቃቀምኳቸው፡፡ ሙለታ፤ “ያ አለቃቸው ነው፤ ምታ ምን ትጠብቃለህ” አለኝ፡፡ ርቀቱ በወታደራዊ ግምት 300 ሜትር ይሆናል፡፡ ከዚያ ርቀት አለቃቸውን ጣልኩት፡፡ በዚህ ግዜ ጦርነቱ ከሸፈ፡፡ ኮሎኔል ገበየሁም መቶ አለቃ ሙለታም በደስታ አቅፈው ሳሙኝና፤ “በቃ አባረናቸዋል” ብለን ስንሄድ ከኋላችን ተከትለውናል፡፡ እኔና ቱታ ያልኩሽ ጓደኛዬ፤ ዞረን በደንብ ለቀምናቸው፡፡ በ1969 ነው ይሄን የማወራሽ። በዚህ ወቅት ነው ድሬደዋ የተደበደበው። ከላይ በአውሮፕላን፣ በመሬት ታንክና መድፍ ይርመሰመሳል፡፡ ትልቅ ውጊያ ነበር ያካሄድነው። ይህን ስናጠናቅቅ ባቢሌ ተይዟልና ወደዚያ ሂዱ ተባለ፡፡ ማታ ማታ ምሽግ ላይ “ስንት ገደልክ… ስንት ጣልክ?” እየተባለ ቀረርቶና ሽለላ ሁሉ ነበረ፡፡ ልጆች ተሰብስበው ይጨፍሩልኛል፡፡
ከዚያ ባቢሌ አቡሸሪፍ ወደሚባል ግንባር ሄዳችሁ…
አዎ ኮ/ል ገበየሁ፤ “አንተ ብቻ መሪ መሪዎቹን፣ አለቆቹን ልቀምልኝ” አለኝ፡፡ “ቃል እገባለሁ፤ ያልከውን አደርጋለሁ” አልኩኝ፡፡ አንድ ቀን ታላቅ ውጊያ አድርገን፣ ለቅመን ለቅመን ከጣልናቸው በኋላ አምስት ታንኮች መጡ፡፡ “በቃ ተከበናል ከምሽግ እንዳትንቀሳቀሱ” አልኳቸው፡፡ አዛዡ በጣም ወፍራም ነው፤ ስድስትና ሰባት ሬዲዮ አስይዞ ያወራል፤ በቅርብ ርቀት ላይ ነበርኩኝና እሱን ግንባሩን ስመታ፣ ታንኩ ፊት ወደቀና ታንኩ በላዩ ላይ ሄደበት፡፡ ሌሎቹ ታንኩን እየነዱ ሲሄዱ፤ ብተኩስ አይሞቱም፤ ብተኩስ አይሞቱም፤ “ኮ/ል ገበየሁ፤ ይሄ ነገር ምንድን ነው?” አልኩት፡፡ “ቆይ ለዚህ መድሀኒቱ ቦምብ ነው” አለና እየገጠመ እየገጠመ ሰጠኝ፡፡ ታንኩ ላይ ያንን ቦንብ ማዝነብ ጀመርኩኝ፡፡ ነደዱ፡፡
ከዚያስ?
ከዚያማ እነዛ ታንኮች ተመቱ፡፡ አዛዦቼ ሀረርም ድሬደዋም ወሰዱኝ፡፡ ልዩ አክብሮትና ቦታ ሰጡኝ። “ውጊያ ሲጀመር ብቻ ይምጣልን፤ ከዚያ ውጭ እንደፈለገ…ያሻበት ቦታ ይሂድ” ተባልኩኝ፡፡ እኔ ግን አልሄድኩም፤ ከጦር ሜዳ ዞር ማለት አልፈልግም- አልኩኝ፡፡ ነገር ግን 16 ቀናት ሙሉ ውጊያ ቆሞ አንድም ጥይት ሳይተኮስ ቀረ፡፡ ምክንያቱም የሶማሊያ ጦር በደንብ ነበር የተመታው፡፡ ከዚያ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በኮሎኔል ገበየሁ የሚመራ ጦር ነበር፡፡ ሶማሌዎች በታንክና በመድፍ ተጠናክረው መጡና፣ በአንድ ሰዓት ውስጥ አራት ሺህ የእኛ ወታደር አለቀ፡፡ አቡ ሸሪፍ የሚባለው ቦታ ላይ ነው ይህ የሆነው፡፡ በወቅቱ ኮ/ል ገበየሁ፤ “ለአገሬ በጣም አዝናለሁ፤ በአንድ ሰዓት ውስጥ ይህን ካደረጉ፣ በቃ አዲስ አበባ ገቡ ማለት ነው” አለ፡፡ “በምንም አይነት አይገቡም፤ እኛ ተራራ ላይ ቦታ ይዘን እንመክታቸዋለን” አልኩት፡፡
እርስዎ አራት ሺህ ሰው ሲያልቅ የት ነበሩ?
እዛው ውጊያው ውስጥ ነበርኩኝ፡፡ ከዚያ በኋላ እኮ ሶማሌዎቹ የልብ ልብ ተሰምቷቸው በቁምጣ መጡ። እነዚህ ኢራን ውስጥ ሰልጥነው የመጡ ናቸው አሉኝ። “እንኳን ኢራን የትም ቢሰለጥኑ አልፈራቸውም፤ ለእኔ ተውት” ብዬ መከታተል ጀመርኩ፡፡ መሪያቸው ኢራቃዊ ነው፤ እየመራ ሲመጣ በርቀት ግንባሩን አፈረስኩት። እሱ ሲወድቅ ሌሎቹ ቁምጣ የለበሱት ፈረጠጡ፡፡ እኔና ቱታ የሚባለው ጓደኛዬ ብዙዎቹን ከጥቅም ውጭ አደረግናቸው፡፡
ከሱማሌ ጋር እስከ መቼ ተዋጉ?
እስከ 1976 ዓ.ም ድረስ ተዋግተናል፡፡ በላምበል ላይ ውጊያ ነበር፡፡ ከዚያም እኔ የነበርኩበት 94ኛ ብርጌድ ወደ ሰሜን ሲዞር፣ እኔ እዚያው ምስራቅ ቀረሁ፡፡ ጦርነቱም በዛብኝ፡፡ ብዙ ጫና ደረሰብኝ፡፡
በጦርነቱ አልቆሰሉም?
ወይ ጉድ! ከዘጠኝ ጊዜ በላይ ተመትቼ ነው የተረፍኩት፡፡ የጨበጣ ውጊያ ሁሉ ገብቼ በሳንጃ ወግተውኛል፡፡ በተዓምር ነው የተረፍኩት፡፡
ከኮሎኔል መንግስቱ የላቀ የጦር ሜዳ ኒሻን ተሸልመዋል አይደል?
መንጌ በጣም ይወደኝ ነበር፡፡ “እኔን እንዴት ታየኛለህ?” ሲለኝ፤ “አገርህን ስለምትወድ እወድሀለሁ” አልኩት፡፡ ሽልማቱ የላቀ የጦር ሜዳ ሜዳሊያ ነው፡፡ ብዙ መብቶችን ያጎናፅፋል፡፡ አውሮፕላን ነፃ ነው፣ ትልልቅ ሆቴሎች ቅድሚያና ነፃ ተጠቃሚ ያደርጋል፣ ሆስፒታልና ትምህርትም ነፃ ነው፡፡ ነፃ ብቻ ሳይሆን ቅድሚያም ነው። ያ ሜዳሊያ አሁን ጠፍቶብኛል፤ በግርግር የት እንደገባ አላውቅም፡፡
ከድቶ ለሶማሊያ ጦር ስለገባውና በእጅዎ ስለወደቀው አንድ ባለስልጣን ይንገሩኝ?
ቶዶባ ይባላል፡፡ የአንድ አውራጃ አስተዳዳሪ ነበር። ድንገት ጠፍቶ የሶማሊያን ጦር እየመራ መጣ፡፡ ሀሳቡ አንድ ነዳጅ ማደያን ለመምታት ነበር፡፡ እሱን እጄ ላይ ጣለው፡፡ ግንባሩን ነድዬ ጣልኩት፡፡ ቁጭት ነበረኝ። እንዴት ሰው ሀገሩን … አፈሩን … እናቱን … ይክዳል የሚል ቁጭቴን ተወጥቻለሁ፡፡ እሱ ቢያመልጠኝ ኖሮ እስከ ዛሬ ይቆጨኝ ነበር፡፡ መንጌ በዚህ በዚህ ይወደኝ ነበር። ከኦጋዴን ተጠርቼ ቀጥታ ቤተመንግስት መጣሁ። ቤተ መንግስት ጠዋትና ማታ መግባት ትችላለህ አለኝ። ከዚያም “አሊ በርኪ፤ አንተ በዚህ ግንባር ካለህ ጠላት እንኳን ኢትዮጵያን ሊወርርና ሊቀራመት ቀርቶ አንዲት ቅጠል በጥሶ መሄድ አይችልም” አለኝ “አይዞህ አላሳፍርህም” አልኩት፡፡ የጦር ግንባሩ ደግሞ በአጋጣሚ እኔ አውሬ እያደንኩ ያደግኩበት ቦታ ነበር፡፡ አንድ መግቢያ መንገድ ብቻ ነው ያለው፡፡ በዚህ ቦታ “ቡቃ” የሚባል ጦር ሄደና ተመታ፡፡ “ንብ” የሚባል ጦር ዘመተ፤ እሱም ተመታ፡፡ በቃ እኔ ልሂድ አልኩና ሱዳንን በስተቀኝ ትቼ፣ ሶስቱን ትንንሽ ከተሞች መታሁ፡፡ ይሄ የኢትዮጵያ ግዛት ነው ብዬ ባንዲራ አውለበለብኩበት፡፡ መንጌ ጠራኝና፤ “እንዴት ነው?” አለኝ፡፡ “ተመትቷል” አልኩት፡፡
በጦርነቱ በግምት ምን ያህል ጠላት ገድለዋል?
(በጣም እየሳቁ …) አልቆጠርኩም፤መገመት አልችልም፡፡ አሊ በርኬ ተኮሰ ማለት… በአንድ ጥይት፣ አንድ ሰው ገደለ ማለት ነው፤ ጥይት አላባክንም፡፡
መቼ ነው ውጊያ ያቆሙት?
ኢህአዴግ ሲገባ ነዋ! በ1983 ነው ያቆምኩት፡፡ ሻዕቢያንም በደንብ ገርፌያታለሁ፡፡
ከሻዕቢያ ጋር የት ተገናኛችሁ?
ሰሜን የሚባል ግንባር አልዘመትኩም፤ ግን እኔ ባለሁበት ግንባር ከሱዳኖች ጋር ተቀላቅለው ይመጡ ነበር፤ በአሶሳ በኩል ማለት ነው፡፡ እዚያ ሳገኛቸው በደንብ ቀጥቻቸዋለሁ፡፡
ከ1983 ዓ.ም በኋላ የት ሄዱ?
ኬኒያ ቲካ የሚባል የስደተኞች ካምፕ ገባሁ፡፡ የመጨረሻው ጦርነት አካባቢ የኢህአዴግን ሰራዊት ወደ ላይም ወደ ታችም አላስኬድ አልኩት፡፡ ሆኖም ሌላውን አካባቢ ስለተቆጣጠሩት “ግዛትህ የሞተ ነውና ኬንያ ግባ” የሚል መልዕክት ደረሰኝ፡፡ የምመራውን ጦር ይዤ በእግር ተጉዘን፣ መንገድ ላይ ያጋጠሙንን ሽፍቶች ሰብረን ቲካ ካምፕ ገባን፡፡
እንዴት ነው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ሊታሰሩ የቻሉት?
በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አታልሎኝ ነው፤ እዚህ መጥቼ ወህኒ የተወረወርኩት፡፡
እንዴት?
የኤምባሲው ሰዎች፤“አሊ በርኪ በሰራው ጀብዱ በስሙ መንገድ፣ ት/ቤትና ሆስፒታል ይገነባለታል፤ በፍፁም አይታሰርም አገሩ ይግባ ተብለሀል” ብለው ሽምግልና መጡ፡፡ በወቅቱ ብር አልነበረኝም፤ እራሳቸው ገንዘብ አዋጥተው “ወደ አገርህ ሂድ፤ የሰው አገር ይብቃህ” አሉኝ፡፡ መጣሁና መርካቶ ገባሁ፡፡ “እጅ ወደ ላይ” ተባልኩ “ምንድን ነው?!” ስል “በቁጥጥር ስር ውለሀል” አሉኝ፡፡ ከዚያ የት ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዱኝ አሁንም አላስታውስም፤ ግን 19 ቀን በስቃይ ቆየሁ፡፡ በዚህ ፖሊስ ጣቢያ ያሳለፍኩት ስቃይ፣ በጦርነት ካሳለፍኩት ይበልጣል፡፡ እጅ እግሬ በሰንሰለት ታስሮ፤ በረሀብና በውሃ ጥም ተሰቃየሁ፡፡ ከሰው አልገናኝም ነበር፡፡ ከዚያ ልደታ ከፍተኛ ፍ/ቤት ቀረብኩ፡፡ ዳኛው፤ “ይሄ የኢትዮጵያ ባለውለታ ነው፤ እኔ አላስረውም፤ እናንተ ብትፈልጉ እቤታችሁ ወስዳችሁ እሰሩት” አላቸው፤ ፖሊሶቹን። ከዚያ ፍ/ቤት ሊለቀው ነው አሉና ያለ ፍርድ ቃሊቲ ወስደው ወረወሩኝ፡፡ ዘጠኝ ዓመት ከሁለት ወር ጠጥቼ ወጣሁ እልሻለሁ፡፡ ከእስር የወጣሁት በ1992 ዓ.ም ላይ ነው፡፡ አልተከሰስኩ፤አልተፈረደብኝ፤ እዛ ተጣልኩ ተረሳሁ፡፡ ከዚያ ወጣሁ፡፡
የሞራል ካሳ አልጠየቁም?
ማንን ነው የምጠይቀው? እንኳን የሞራል ካሳ ልጠይቅ … ጡረታዬ እንኳን አልተከበረልኝም፡፡ ጡረታዬ ቢከበርልኝ በእዚህ እድሜዬ ኩንታል እሸከም ነበር፡፡ ወይ አንቺ… አገሬ ለከፈልኩት ውለታ ፊት ነስታኛለች፡፡ ጡረታ እኮ የለኝም፡፡ ውሃ በሞተር ካልሆነ በስተቀር ወደ ላይ ይፈሳል እንዴ? በቃ እንዲህ ነው የሆነው፡፡
ልጆች አልወለዱም እንዴ?
ኡጋዴን ውጊያ ላይ እያለሁ ነው የወለድኩት፡፡ ወደ ስምንት ልጆች አሉኝ፡፡ እንዳሉ አልቆጥራቸውም፤ አይፈልጉኝም፡፡ በየቦታው ነው የወለድኩት፡፡ አሁን ሁለቱ ብቻ ናቸው ከእኔ ጋር ያሉት፡፡ ውጭም የሚኖሩ አሉ፡፡ በየሄድኩበት መውለድ ነው፡፡ ኡጋዴን ወልጃለሁ፤ ወለጋም ወልጃለሁ፡፡
በቅርቡ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተዘጋጀ ሽልማት ከተመረጡ ሶስት የጦር ሜዳ ጀግኖች አንዱ እንደነበሩ ሰምቻለሁ፡፡ ነገር ግን እርስዎ ለሽልማቱ አልሄዱም፡፡ ለምንድን ነው ያልሄዱት?
እኔ ከእስር እንደወጣሁ ብሄረ ፅጌ አካባቢ ነበርኩኝ። ከዚያ ጉርድ ሾላ መጣሁ፡፡ ከጉርድ ሾላ ካራ፣ ከዚያ ኮተቤ—እያልኩ ነው የኖርኩት፡፡
ለምንድን ነው መኖሪያ የሚቀያይሩት?
በወቅቱ ስራና የገቢ ምንጭ ስላልነበረኝ ከመብራት – ኩራዝ ወዳለበት፤ ከሊሾ – አፈር ወለል ወደሆነበት ቅናሽ ፍለጋ ስዞር … ከተማው በሰፋ ቁጥር እየሸሸሁ እየሸሸሁ አሁን ለገጣፎ ላይ አርፌያለሁ፡፡ አንዱ ሲቀልድብኝ፤ “አንተ ደብረ ብርሃን ልትገባ ነው እንዴ?” አለኝ “አቅሜ ካልፈቀደ ደብረ ብርሃንንም ማለፌ አይቀርም” አልኩት። በዚህ ምክንያት ለሽልማቱ አሜሪካ ልወሰድ ስፈለግ አድራሻዬ ጠፋ፡፡ እናም ሳልሄድ ቀረሁ፡፡
አሁን ኩንታል ችለው ይሸከማሉ?
/ቆፍጠን ብለው/ ለምን አልሸከምም…፡፡ ህይወት እኮ ነው፡፡
ከማን ጋር ነው የሚኖሩት?
ሚስት አግብቼ ሁለት ልጆች ወልጄ፣ ከእነሱ ጋር ነው የምኖረው፡፡
የሽልማቱ መጨረሻ ምን ሆነ?
ያኔ በቤት መቀያየር ተፈልጌ ተፈልጌ ጠፋሁና ሁለቱ ሄደው ተሸለሙ፡፡ አንድ ጊዜ ከሆነ ቦታ ገንዘብ ተልኮልኝ ሁለት ሰዎች አታልለው 100 ሺህ ብር ወሰዱብኝ፡፡ የአሜሪካኑም ሽልማት ገንዘብ ነበር፡፡ የሽልማቱን ብር ወሰድኩና አርቡጉያ ሰፈራ የሚባል ቦታ ቤት ሰራሁ፡፡ አሁን ኩንታል እየተሸከምኩ ከቤተሰቤ ጋር እኖራለሁ፡፡
ከሽልማቱ ምን ያህል አገኙ?
ሌቦቹ የቀናነሱትን ቀናንሰው ወደ 400 ሺህ ብር እጄ ደርሷል፤ ቦታ ገዝቼ ቤት ሰራሁበት፡፡ ካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አንዲት ሴት በምትመራው ሬዲዮ ጣቢያ፤ “እኛ የጄነራልነት ማዕረግ ሰጥተንሃል፤ ለሀገርህ ባለውለታ ነህ” ብለው የጀነራልነት ማዕረግ ሰጥተውኛል። አልፎ አልፎ በሰው በኩልም በባንክም ትንሽ ትንሽ ብር ይልኩልኛል፡፡ እነሱ እየጦሩኝ ነው፡፡ ተቋቁሜያለሁ። አገሬ ግን ውለታዬን አልከፈለችኝም፤ ጡረታዬን አልጠበቀችልኝም፡፡
በማዕረግ ደረጃ እስከ ሻለቃ ባሻ ነው የደረሱት?
አዎ፡፡ ካናዳ ያሉት በራሳቸው ፈቃድ ነው የጄነራልነት ማዕረግ የሰጡኝ፡፡
የላቀ የጦር ሜዳ ኒሻን ተሸላሚው፤ “አገሬ ፊት ነስታኛለች” ይላሉ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
Addis admass