በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለችንን መጠነኛ ተሳትፎ ለማቀጨጭ የሚደረገው ጥረት እንዲሰምር አንፈቅድም!!! ህዝባዊ ጥሪ ድምፃችን ይሰማ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ህዝባዊ ጥሪ ድምፃችን ይሰማ
#EthioMuslims #EthioMuslimPeacefulStruggle
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለችንን መጠነኛ ተሳትፎ ለማቀጨጭ የሚደረገው ጥረት እንዲሰምር አንፈቅድም!!!
,

ዲሞክራሲያዊ መንግስታት በህዝብ ፈቃድ ላይ የተመሰረቱ ከመሆናቸው የተነሳ ህዝብ ጥያቄ እስከሚጠይቅ ሳይጠብቁ ፓሊሲያቸውን እና ውሳኔያቸውን የህዝብን ፍላጎት እና እምነት ያማከለ በሚያደርግ ባህሪያቸው ይታወቃሉ። ከስም ባለፈ ዲሞክራሲያዊነትን የማያውቀው ኢህአዴግ ግን ይህን የሕዝባዊነት ባህሪ አልተላበሰም። በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ጉዞ እያደር ቁልቁል ከሆነ እነሆ አስር ዓመታት አለፉ። በተለይ ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ከየአቅጣጫው ደጋግመው የተሰሙ የሕዝብ ድምጾች ከመበርከታቸው ጋር የስርዓቱ ኢ-ዴሞክራሲያዊነት አፍጥጦ ገሐድ ወጥቷል። ከ2008 የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ጋር ተያይዞ የያዘው አቋም የገዥውን ፓርቲ አምባገነናዊነትና ህዝባዊ መሰረቱን ማጣቱን ከማሳየት አልፎ ራሱን ከሕዝብ የነጠለ ስርዓት መሆኑን እያስመሰከረ ይገኛል።
,

በትምህርት ሚኒስቴር በኩል የተወሰነው አዲስ የፈተና ሳምንት የሙስሊሙን ህብረተሰብ ብሄራዊ ማንነት የሚክድ እና የህዝባችንን ባህል ያላገናዘበ እንደሆነ በማሳወቅ መንግስት ውሳኔውን ዘወር ብሎ እንዲያይ እና ማስተካከያም ያደርግ ዘንድ ማሳሰባችን የሚታወስ ነው። የሙስሊሙን ህብረተሰብ በመወከል የተላያዩ የህብረተሰቡ ክፍሎች እና ሽማግሌዎችም ይህንኑ ጉዳይ በማስመልከት ለተለያዩ የመንግስት አካላት አቤቱታ በማሰማት ላይ ይገኛሉ። በህዝበ ሙስሊሙ እየቀረበ ላለው አገራዊ ቅሬታ እስካሁን መንግስት ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በእምቢተኝነቱ የጸና ይመስላል። በዚህም መንግስት ለህዝበ ሙስሊሙ ያለውን ንቀት ከማሳየቱም በላይ የስርዓቱን እብሪተኝነት እና በሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ የተከፈተው ብሄራዊ ጭቆና ደርጃ ከፍ ማለቱን የሚያመላክት ነው።
,
በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት ሙስሊሙን ህብረተሰብ ከትምህርት ለማግለል የወሰዳቸው እርምጃዎች በርካታ ናቸው። ከመለስተኛ ትምህርት ቤቶች አንስቶ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ ሙስሊም ተማሪዎች ከትምህርታቸው እና ከእምነታቸው አንዱን እንዲመርጡ የሚያስገድዱ መመሪያዎችን በማውጣት መሰረታዊ የዜግነት መብታቸው የሆነውን የትምህርት እድል መንፈግ፣ በፈተና ወቅቶች ውጥረቶችን በመፍጠር የተጋረጠባቸውን ኢ-ሰብዓዊ እርምጃ በመቋቋም ለፈተና የተዘጋጁ ተማሪዎች አጥጋቢ ውጤት እንዳያመጡ ማድረግ እና ከአገር አቀፉ ተፎካካሪነት ማስወጣት የእስካሁን የጭቆና ማስፈጸሚያ መንገድ ሆነው ቆይተዋል። ይህም ለዘመናት ከትምህርትና ሌሎች ማሕበረ-ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ሲገለል ለኖረው ህዝባችን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ መሆኑ አልቀረም።
,
የሙስሊሙ ተማሪ ድርሻ አናሳ በሆነባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለንን መጠነኛ ተሳትፎ ለማቀጨጭ የሚደረገው ጥረት እንዲሰምር የማንፈቅድ መሆናችን ሊታወቅ ይገባል። በመሆኑም ፈተናው ዳግም ተራዝሞ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን እንደሌሎች የአገራችን ተማሪዎች በቂ ዝግጅት አድርገው እኩል ተወዳዳሪ የሚሆኑበት እድል እንዲፈጠር አበክረን እንገልጻለን። ይህንን ስንል ከህገ መንግስታዊ የዜግነት መብታችን የተለየ ተጠቃሚነት እየጠየቅን እንዳልሆነ ማወቅ ያሻል። ይልቁንም ፈተናው ተሰርዞ የተራዘመው በመንግስት እልኸኝነት የተነሳ መሆኑ ታውቆ ጥያቄያችን የሚያጠነጥነው ተቀያሪው ፈተና በሰኔ ወር መገባደጃ እንዲሆን ሲወሰን የሕዝበ ሙስሊሙን ተጨባጭ ያላማከለ በመሆኑ ላይ ነው።
,
በተለይ ይህ የፈተና ጊዜ በክረምቱ ወራት ሙቀታቸው የሚጨምሩ ሙስሊም-በዝ የአርሶ አደር ክልሎችን ግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑን ልናስታውስ እንወዳለን። የተለየ ድጋፍ በሚያሻቸው ታዳጊ ክልሎች የሚገኙ ሙስሊም ተማሪዎች የድርቁን ጠኔ እና የበረሐውን ሐሩር ተቋቁመው ከመጾም ባለፈ ለፈተና የሚዘጋጁበት አሰራር ሰብዓዊነት የጎደለው ነው። ካገራችን የባህል ተጨባጭ በመነሳትም ልጆች በበአላት ወቅት ከሚኖራቸው ሚና አንጻር ካየነው ከጾምና የተለያዩ ኃላፊነቶች በተረፈች አናሳ ጊዜያቸው ለፈተና መዘጋጀት ለእኩል ስኬት እንደማያበቃቸው እሙን ነው።
,
በመሆኑም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌደራልና የአርብቶ አደር ጉዳዮች፣ ሙስሊሙ በብዛት ሰፍሮ የሚገኝባቸው ታዳጊ ክልሎች፣ ሙስሊሙን ማህበረሰብ ወክለው በፓርላማ የተቀመጡ ሙስሊም ወኪሎች፣ ሙስሊም በዝ የሆኑ ዞኖች እና ወረዳዎች፣ በተለይም የትምህርት ዴስክ እና ጽ/ቤቶች፣ የሴቶች፣ ወጣቶችና ባህል ሚኒስትር የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድተው በመንግስት ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
,
ህዝበ ሙስሊሙ በተለይ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ ሙስሊም ምሁራን እና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ይህን የሙስሊሙን ማንነት ለመፋቅ የዳዳው የመንግስት ሂደት ላይ ድምጻቸውን የማሰማት ታሪካዊ ሃላፊነት አለባቸው፡፡ በመሆኑም በፈተናው ዳግም መራዘም ላይ ያላቸውን ቁርጠኛ አቋም በመግለጽ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ እናሳስባለን።
,

ለከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና በዝግጅት ላይ ያሉ ተማሪዎችም በበኩላቸው ከጾም ጎን ለጎን ትምህርታቸውን በርትተው እያጠኑ ከትምህርት ቤታቸው አስተዳደር ጋር በቡድን ተገናኝተው የፈተናውን መራዘም ጉዳይ እንዲወያዩ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን።

ወላጆች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት ምሁራን እና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት መንግስት የሙስሊሙን ማንነት በሚፈታተን ሂደት ከቀጠለ የሚከተለውን አገራዊ ጦስ ከማሳሰብ አንጻር የራሳቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ በአላህ ስም እንጠይቃለን። ሙስሊም አክቲቪስቶችም በጉዳዩ ላይ የሙስሊሙን አቋም በማብራራት፣ የመንግስትን እብሪተኝነትና ህዝባችን ላይ በተጋረጠው አደጋ ላይ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በቅርበት ምክክር በማድረግ ስርዓቱ እየተጓዘበት ካለው አደገኛ ሂደት ይመለስ ዘንድ ርብርቦሽ እንዲያደርጉ እናሳስባለን።

ከምንም በላይ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ፊት ለፊታችን በተደቀነው የፈተና ቀን ጉዳይም ሆነ መንግስት በሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ ያወጀውን ብሄራዊ ጭቆና ግዝፈቱን እና ጥልቀቱን በትክክል ተረድቶ ከመቸውም በላይ አንድነቱን እንዲያጠናክር፣ በተለያየ መልኩ የሚያደርጋቸውን ጥረቶች የግል ፍላቶቶችን ወደጎን በማድረግ አንድ አቅጣጫ ላይ እንዲያደርግ እናሳስባለን።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ሙስሊሙ ያለውን መጠነኛ ተሳትፎ ለማቀጨጭ የሚደረገው ጥረት እንዲሰምር አንፈቅድም!!
ህልውናችንን ለመፋቅ የዳዳው የመንግስት አብሪተኛ እርምጃ ላይ ድምጻችንን የማሰማት እና እስከመጨረሻው የመቃወም ታሪካዊ ሃላፊነት አለብን!
የዜግነት መብታችንን ለበደለኞች አሳልፈን አንሰጥም!
አላሁ አክበር!