የመድረክ 12ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ የአቋም መግለጫ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የመድረክ 12ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ የአቋም መግለጫ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ/መድረክ በሀገራችን የፓርቲዎች ማቋቋሚያና ምዝገባ ሕግ መሠረት በግንባር አደረጃጀት ተደራጅቶና ተመዝግቦ በሀገራችን ሰፍኖ በሚገኘው አስቸጋሪና ጠባብ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ አባል ድርጅቶቹንና ሕዝባችንን ከጎኑ በማሰለፍ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ማካሄዱን ቀጥሎአል፡፡ እኛ የመደረክ ጠቅላላ ጉባኤ አባላት በግንባራችን መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በዛሬው ዕለት 12ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ያካሄደን ሲሆን በዚሁ ስብሰባችን የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታዎችና የድርጀታችንን እንቅስቃሴዎች በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አካሄደን የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡

1ኛ፡- መድረክ ሰላማዊ የትግል ስልትን መርጦ የሕዝባችንን የሥልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የምርጫ ሥርዓት በሀገራችን ተግባራዊ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋጽዖ ለማድረግ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በ2002 ዓ ም እና በ2007 ዓ ም በተካሄዱት ሁለት ምርጫዎች ከፍተኛ ተሳትፎ አድርጎአል፡፡ ይሁን እንጂ በሕዝብ ፈቃድ ሳይሆን በጉልበቱ በስልጣን ለይ ለመቆየት ቆርጦ የተነሳው የኢህአዴግ አገዛዝ ምርጫዎቹን ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የሚውል የይስሙላ ምርጫ ብቻ እንዲሆኑና የሕዝባችን ነፃ የመምረጥ መብትና የሥልጣን ባለቤትነት ተግባራዊ እንዳይሆን በምርጫው በሚሳተፉ አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን ላይ ዘግናኝ የሆኑ የአፈና እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቶአል፡፡ በተላይም በ2007 ዓ ም በተደረገው ምርጫ በንቃት ከተሳተፉ አባሎቻችን ውስጥ በአምስት አባሎቻችን ላይ የግዲያ ወንጀል የተፈጸመ ሲሆን ገዳዮቻቸውም ለሕግ ቀርበው ፍትሐዊ ውሳኔ ያገኙበት ሁኔታ የለም፡፡ ብዙ አባሎቻችንም ለእስራትና ለተለያዩ እንግልቶች ተዳርገዋል፡፡ ስለዚህም ገዥው ፓርቲ በአገዛዝ ዘመኑ ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌዎችን በመተላለፍ ፍትሐዊ፣ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ታአማኒነት ያለው ምርጫ በሀገራችን እንዳይካሄድ አድረጎ ሀገራችንን በማን አለብኝነት በጉልበት ለመግዛት የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በጥብቅ እናወግዛለን፡፡

2ኛ፡- በሕገመንግሥቱ የተረጋገጠውን መብት በመጠቀም ወቅታዊ የሀገራችንን ጉዳዮች በሚመለከት መድረክ በዚህ ዓ ም ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎችን ለማዘጋጀት ያደረጋቸው ሙከራዎች በገዥው ፓርቲ ክልከላዎች ምክንያት ሊካሄዱ አልቻሉም፡፡ በብዙ አከባቢዎች የአባል ድርጅቶች ጽ/ቤቶችም በገዥው ፓርቲ ካድሬዎች ስለተዘጉ ድርጅታዊ ሥራዎችን በአግባቡ ማከናወን አልተቻለም፡፡ ስለዚህም እነዚህን የኢህአዴግ የአፈና እርምጃዎች የፖለቲካ ምህዳሩ በከፋ መልኩ መጥበቡን የሚያረጋግጡ ስለሆኑ በአሰቸኳ የሚቆሙበት ተጨባጭ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

3ኛ፡- በዓመቱ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል በተነሳው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ምክንያት በሰላማዊ ሕዝብ ላይ የተወሰደው አግባብ ያልሆነ የኃይል እርምጃ ከ300 በላይ ለሆኑ ዜጎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሊሆን ችሎአል፡፡ ከዚህም ሌላ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች በገፍ ታስረው በመንገላታት ላይ ይገኛሉ፡፡ በርካታ የመድረክ አባላትም በግፍ ታስረው በመሰቃየተ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህም ገዥው ፓርቲ እራሱ ባመነበት ብልሹ አስተዳደር ምክንያት የተነሳውን ሰላማዊ የሕዝብ ተቃውሞ በኃይል ለመጨፍለቅ የወሰደው የግፍ እርምጃ በመሆኑ አጥብቀን እንኮንነዋለን፡፡

4ኛ፡- ሀሳብን በነፃ ከመግለጽ አኳያም በአንድ በኩል ነፃ የግል ፕሬሶች ላይ ኢህአዴግ በሚፈጽመው አፈና ምክንያት ብዙዎቹ እንዲዳከሙና ከገበያ እንዲጠፉ በማድረግና በሕዝብ ንብረት የሚንቀሳቀሱ የመንግሥት ሚዲያዎችም የተቃዋሚ ፓርቲ መግለጫዎችን በፍጹም እንዳያስተላልፉና የገዥውን ፓርቲ ፕሮፓጋንዳ ብቻ እንዲያሰራጩ በማድረግ የተለያዩ ሀሳቦችን በሚዛናዊነት እንዲያስተላልፉ የተደነገገውን ግልጽ የሆነ ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌ በመጣስ የሕዝቡን ሚዛናዊ መረጃ የማግኘት መብት እያፈነ በመሆኑ ይህንን ፀረ-ሕገመንግሥታዊ ተግባሩንም አጥብቀን እናወግዛለን፡፡

5ኛ፡- በአሁኑ ወቅት የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰቶች፣ ታቃውሞን ለማፈን የሚወሰዱ አምባገነናዊ የኃይል እርምጃዎች፣ ሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦት ችግሮችና የዜጎች በገፍ ሥራ ማጣትና መሰደድ የሀገራችን ተጨባጭ መገለጫዎች በሆኑበት ሁኔታ የኢህአደግ አገዛዝ በልማታዊ መንግሥትነት እየተመጻደቀ ከመሆኑም በላይ ባሉት ተጨባጭ ችግሮች ላይ ለመወያየትና በሀገራችን የሕግ የበላይነት የሚሰፍንበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እንዲቻል መድረክ በተደጋጋሚ ያቀረበቸውን የሰላማዊ ውይይት ጥያቄዎችን ኃላፊነት በጎደለ ሁኔታ በማንአለብኝነት ውድቅ ሲያደርግ ቆይቶአል፡፡ በዚህም ተግባሩ የሀገራችን ችግሮች ሰላማዊ መፍትሔ የሚያገኙበትን እድል ዘግቶ ይገኛል፡፡ ጉባኤው ይህ የኢህአዴግ አምባገነናዊ ባሕሪይ በሀገራችን ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደገኛ ሁኔታ በጥሞና የገመገመው ሲሆን ኢህአዴግ ከዚህ አደገኛ ባሕሪው በአስቸኳይ ታርሞ በአሁኑ ወቅት ዘግቶ የሚገኘውን የሰላማዊ መፍትሔ በር በአስቸኳይ እንዲከፍትና ለሰላማዊ ውይይት ዝግጁ እንዲሆን አጥብቆ ይጠይቃል፡፡

6ኛ፡- በአሁኑ ወቅት የኢህአዴግ አገዛዝ በማንአለብኝነት ዜጎችን በየሰበብ አስባቡ ማሰሩን ቀጥሎአል፡፡ ዛሬም በሀገራችን በአጠቃላይና በተለይም በኦሮሚያ ክልል እስሩ ተባብሶአል፡፡ ስለሆነም በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት በየቦታው ታስረው የሚገኙት እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ጉባኤው አጥብቆ ይጠይቃል፡፡
በመጨረሻም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና የዓለም ማሕበረሰብም ኢህአዴግ ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እየፈጠረ ያለውን አሳሳቢ ሁኔታ በወቅቱ ለማረም እንዲቻል መድረክ እያደረገው ያለውን ሰላማዊ የመፍትሔ ጥረቶች በአግባቡ ተረድቶ ከጎኑ በመሰለፍ የበኩሉን አስተዋጾ እንዲያበረክት ጉባኤው ጥሪ ያቀርባል፡፡

ድል ለሕዝባዊ ትግላችን!!
የኢትዮጵያ ፈዴራለዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ
12ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ፣
ግንቦት 27 ቀን 2008 ዓ ም
አዲስ አበባ