ዲሞክራሲ፣ሰብዓዊ መብትና ፍትህ – በ25 ዓመት
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ባለፉት 25 ዓመታት ከምርጫ ጋር ተያይዞ፣ ከተቃውሞ ሰልፍና ውጤታቸው፣ ከፕሬስ ነፃነትና ከጋዜጠኞች ስደት እና እስራት፣ ከብሄር ጎሳዉ ጥቃት እና ከመሳሰሉት ዲሞክራሲያዊ፣ፍትሃዊና፣ ሰብአዊ ጊዳዮች ጋር በተያያዘ በርካታ አሉታዊ ሪፖርቶች በአለማቀፍ ተቋማት ቀርበዋል፡፡ መንግስት በበኩሉ የሚወጡትን ሪፖርቶች በሙሉ እንደማይቀበላቸው እየተከታተለይፋ ሲያደርግ ከርሟል፡፡ ዲሞክራሲን ስናነሳ ሰብአዊ መብትን ሰብአዊ መብትን ስናነሳ የህግ የበላይነትን፣ የህግ የበላይነትን ስናነሳ ፍትህን እናነሳለን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ የህግ ባለሙያዎችን በዲሞክራሲ፣ በሰብአዊ መብትና በፍትህ ላይ ባለፉት 25 ዓታት ሀገሪቴ ምን ያህል ተራምዳለች ሲል ጠይቋቸዋል፡፡
“ዲሞክራሲ በሌለበት ነፃ ፍ/ቤት ሊኖር አይችልም” (ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም፤አለማቀፍ የህግ ባለሙያ)
በሀገራችን እንደ ሰማይ ከራቁ የሰብዓዊ መብቶች ዋነኛው ፍትህ ነው፡፡ አንድ የመንግስት ባለስልጣን ለሰራው ወንጀል ተጠያቂ ያለመሆን በሀገራች ስር የሰደደ ባህል ሆኗል፡፡
ተጠያቂ ያለመሆን ደግሞ ከፍተኛ የፍትህ ጥሰት እንደመሆኑ መጠን፣ በአለማቀፍ ህግ ከፍተኛ አፅንኦት የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ዘ ሄግ የሚገኘው አለማቀፍ የህግ ፅ/ቤት የተቋቋመው በዋናነት ተጠያቂነትን ለማስፈን ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ያቋቋመው የሩዋንዳው ፍ/ቤት የተመሰረተው በዋናነት ሩዋንዳ ውስጥ ተንሰራፍቶ የነበረው የመንግስት ባለስልጣናት ለሰሯቸው ወንጀሎች ተጠያቂ ያለመሆን ባህልን ለመስበር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ስንገመግመው፣ በሀገራችን አንዳንድ ባለስልጣናት ለሰሯቸው ወንጀሎች ተጠያቂ አልሆኑም፡፡ በኢህአዴግ ዘመን ከተቃዋሚዎቹ በስተቀር ከኢህአዴግ ሰዎች ለሰሯቸው ወንጀሎች ተጠያቂ የሆነ የለም፡፡ በወንጀል ተጠያቂ ሊያደርጉ የሚችሉ 3 ምሳሌዎችን መጥቀስ ይችላል፡፡ አንደኛ፤ በ1997 ዓ.ም 300 ሰላማዊ ሰልፈኞች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን መንግስት አምኗል፡፡ በጊዜው የደህንነትና የፖሊስ ኃይል፣ በቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ቁጥጥርና እዝ ሥር ስለነበረ፣እነዚህ የፀጥታ ኃይሎች ለፈፀሙት ድርጊት አቶ መለስ ተጠያቂ ሲሆኑ አላየንም፡፡
ሁለተኛው፤ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረበት ጊዜ አንስቶ ምናልባትም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በጎሳቸው ወይም በቋንቋቸው ምክንያት ለዘመናት ከኖሩበት አካባቢ ተፈናቅለው ለከፍተኛ እንግልትና ስቃይ ተዳርገዋል፡፡ ቤኒሻንጉል – ጉራፈርዳን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ከነዚህ አካባቢዎች የተፈናቀሉት በአብዛኛው አማርኛ ተናጋሪዎች መውደቂያ አጥተው ተንገላተዋል፡፡ አንድን ሰው በዘሩ፣ በሃይማኖቱ፣ በጎሳው ምክንያት ከኖረበት ቦታ ማፈናቀል አለማቀፍ ወንጀል ነው፡፡ በትውልድ ሃገሩ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ሀገር ሆኖ ይህ በደል የደረሰበት ሰው መንግስት ላይ ክስ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ይህ ወንጀል በሰው ፍጡር ላይ የሚፈፀም ወንጀል እንደመሆኑ ክሱ በይርጋ አይታገድም፡፡ ከ20ም ሆነ ከ30 ዓመት በኋላም ቢሆን ክሱን ማንቀሳቀስ ወይም ክስ መመስረት ይቻላል፡፡ ቅጣቱ ብዙ ጊዜ እድሜ ልክ እስራት ነው፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት ለዚህ ቅጣት የሚዳርጉ በርካታ ኢ-ሰብአዊ ተግባራት ተፈፅመዋል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ በቅርቡ ወደ 400 የሚጠጉ የኦሮሞ ሰላማዊ ወጣቶች ህይወት መጥፋት ተዘግቧል፡፡
ለዚህ ተጠያቂ የሆነ አካል የለም፡፡ መንግስት ለወንጀሉ ሳይሆን ለድርጊቱ ኃላፊነት ወስዷል፡፡ ለተፈፀመ ድርጊት ይቅርታን በመጠየቅ ወንጀል አይታለፍም፡፡ መንግስት ከተጠያቂነት አሁንም አይድንም፡፡
ለፍትህ ትልቅ ስንቅ የሆኑት አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን የሚንዱ አዋጆች በኢህአዴግ ተደንግገዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ በዋናነት ሊጠቀስ የሚችለው የፀረ-ሽብር አዋጅ ነው፡፡ ይህ አዋጅ የሚደነግጋቸው አንቀፆች ህገ-ወጥ ናቸው፡፡ እንደ ብዙ አውሮፓና አፍሪካ አገሮች፣ ከህገ-መንግስቱ ጋር የሚጣረሱ ህጐችን የሚሽር ነፃ የህገ-መንግስት ፍ/ቤት ቢኖር ኖሮ ይህ አዋጅ በቀጥታ በተሻረ ነበር፡፡ በሀገራችን ይህ ኃላፊነት የተሰጠው የፌደሬሽን ም/ቤት፣ የህገ-መንግስት አጣሪ ጉባኤ ነው፡፡ ይህ አካል የፖለቲካ አካል ስለሆነ ነፃ ነው ለማለት አይቻልም፡፡
ለምሣሌ በ1997 ዓ.ም ተሠናባቹ ፓርላማ፣ ቅንጅት አሸንፎ ሊቆጣጠር ይችላል በሚል ፍራቻ፣ ተተኪውን ፓርላማ ዋጋ ቢስ ያደረገው አዋጅ ይሻርልን ብለን ዶ/ር ሃይሉ አርአያና እኔ ላቀረብነው አቤቱታ መልስ ሳይሰጠን ፋይሉ ተዘግቷል፡፡ ስለዚህ ዲሞክራሲ በሌለበት፣በአንድ ፓርቲ አምባገነንነት በሚተዳደር ሀገር ነፃ ፍርድ ቤት ሊኖር አይችልም፡፡ እስካሁንም ህብረተሰቡ የሚያምነው ነፃ የፍትህ ስርአት አልተገነባም፡፡
ፕሬስን በተመለከተ በአንዲት ቃል ልጠቅልለው፡፡ በኛ ዘመን የትግሉና የለውጡ ጀግኖች፣ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ አሁን ግን ጋዜጠኞች ናቸው፡፡
===========================
“የሰብአዊ መብት ጥሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት ነው”
(አቶ ተማም አባቡልጉ፤የህግ ባለሙያ
የፍትህ ሥርአቱ ተመስርቷል ወይ ብለን ስንጠይቅ፣ለኔ ገና አልተመሰረተም፡፡ የፍትህ ስርአት ማለት የፖሊስ፣ የፍ/ቤት የአቃቤ ህግና ከነዚህ ጋር ተያያዥ ነው፡፡ የፍትህ ስርአት ተመስርቷል ብለን ስናስብ፣ እነዚህ ተቋማት መኖራቸውን ብቻ ካሰብን ስህተት ነው፡፡ ድሮም ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ እነዚህ ተቋማት ነበሩ፡፡ ፖሊስም ሆነ ፍርድ ቤት ድሮም ነበሩ፡፡ አሁን ማየት ያለብን ከዲሞክራሲ መስፈንና ከህግ የበላይነት አንፃር ነው፡፡
በእነዚህ የፍትህ ተቋማት የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዴት እየተከበሩ ነው የሚለው ነው መታየት ያለበት፡፡ የፍትህ ስርአቱ ተቋቁሟል ወይ ስንል፣ ከነዚህ አንፃር ከነጭራሹ አልተቋቋመም፣ የለም፡፡
ድሮ የነበሩ ስርአቶች አያያዛቸውና መሰረታቸው ይለያያል እንጂ ሁሉም ጨቋኝ ናቸው የሚል ድምዳሜ ነው ያለው፡፡ እነዚህ ስርአቶች በሌላ መልኩ እንዲቀጥሉ ተደረገ እንጂ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ከማስከበር አንፃር ብዙ ርቀት አልተሄደም፡፡ ነባሩን ከማስቀጠል በዘለለ አዲስ የፍትህ ስርአት አልተቋቋመም፡፡ የዲሞክራሲ መሰረት የሆነው መድብለ ፓርቲ የሚባለውም በተግባር የለም፡፡ ኢህአዴግ መንግስት ሲሆን ኢትዮጵያን በዘር ነው የከፋፈላት፡፡
ክልሎቹ በዚህ መንገድ ተሰርተው ካበቁ በኋላ ነው ክልሎቹን ሊያስተዳድሩለት የሚችሉ የብሄር ፓርቲዎችን ያዋቀረው፡፡ የዚህ መሃንዲስ ደግሞ ህወኃት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የመጡ ፓርቲዎች አጃቢዎች ናቸው፡፡ በእኔ ግንዛቤ መድብለ ፓርቲ በኢትዮጵያ እስከ ዛሬ አልተቋቋመም፡፡ የፍትህ ስርአቱም ድሮ ከነበሩት አልተለየም፡፡
ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ፣ ገለልተኛ ፍርድ ቤት በሌሉበት መድብለ ፓርቲ ስርአት ሊኖር አይችልም፡፡ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት በሌለበት ስለ ዲሞክራሲ ማውራት አይቻልም፡፡ ኢህአዴግ ከህብረ ብሄራዊ ፓርቲዎች ይልቅ የዘር ፓርቲዎች ነው የሚፈልገው፡፡ የመድብለ ፓርቲ ስርአት በኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን አልተፈጠረም፡፡
የህግ የበላይነት አልሰፈነም የምለው በንጉሱ ዘመን ህግ ነበረ፤ነገር ግን የህግ የበላይነት ከንጉሱ በታች ነው፡፡ ዛሬም ያ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ፍትህ ተአማኒነት እንዲያጣ፣ ሰው ሁሉ የህግ የበላይነት ስህተት እንደሆነ ቆጥሮ፣ ለህግ ክብር እንዲያጣ የተደረገው በዚህ 25 ዓመት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
የሰብአዊ መብት ጉዳይን ካየን፣ ጥሰቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት ነው፡፡ ደርግ በግልፅ ይገድላል፣ ያስራል፡፡ አሁን ደግሞ ፍርድ ቤት እንደ ሽፋን ያገለግላል፡፡ በእስር ወቅትም ሰላም የለም፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ላይ ስርአቱን የነካ ሰው ከሁሉም አቅጣጫ ዱላ ይበዛበታል፡፡ መጠጊያ የለውም፡፡ ፖሊሱ ይጣላዋል፣ አቃቤ ህግ ይጣላዋል፤ ሁሉም ይጣላዋል፡፡ የአባት ገዳይ ተደርጎ ነው የሚታየው፡፡
እንደ ህግ ጠባቂነቴ ያስተዋልኩት፤ዛሬ አንድ ተጠርጣሪ በፖሊስ ሲያዝ መደብደብ፣ መዋከብ የመሳሰሉት ይቅሩ የተባሉ ተግባርት ሁሉ ይፈፀሙበታል፡፡ የድሮው ባህል አልተቀረፈም፤ ድሮም ፖሊስ ሰው ይደበድባል፤ዛሬም ይደበድባል፡፡ ድሮም ተጠርጣሪ በፖሊስ ይመናጨቃል፤ዛሬም ክብሩ አይጠበቅም ይመናጨቃል፡፡
እነዚህን ነገሮች አንስተን ከገመገምን፣ በፍትህና በሰብአዊ እንዲሁም ዲሞክራሲ መመዘኛዎች ኢህአዴግን የሚያህል ፈላጭ ቆራጭ መንግስት ያስተናገድን አይመስለኝም፡፡ ደርግ ወታደራዊ አምባገነን ነበር፡፡ ኃይለሥላሴ ግለሰባዊ አምባገነን ነበሩ፡፡ ኢህአዴግም አምባገነን መንግስት ነው፡፡