ይሄ ከማላቆመው መልክቶቼ ውስጥ አንዱ ነው ! ( ሄኖክ የሺጥላ )


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ይሄ ከማላቆመው መልክቶቼ ውስጥ አንዱ ነው ! ( ሄኖክ የሺጥላ )

የሃገራችን ፖለቲካ ፥ ትችት እና ዘለፋ እንደ ርችት እያብረቀረቀ የሚዘንብበት የነገር ሸራተን ነው ። ትናንት ወዳጅህ የነበረ ፥ ዛሬ እንደ አማዞን እባብ ቆዳውን ሸልቅቆ ሙልጭ አድርጎ ሊሰድብህ ይችላል ፥ ሃሳብህን ሳይሆን ሱሪህን ሊያወልቅ ይፈልጋል ፥ እሱ ራሱ የወጣለት ጠንጋራ ብሄርተኛ ሆኖ ፥ ኣይኑን በጨው አጥቦ « ለምን ስለ አንድነት አትሰብክም ይልሃል » ፥የሌሎችን ቁመና ሲያፍረጠርጥ ከርሞ ፥ የሱ ቁመና ሲነካ ፥ ኣደለም ቁመናዬን እዳሪዬን እንኳ መተቸት ( መንካት ) መብትህ አይደለም ሲል አያፍርም ፥ ዲሞክራሲ አቅም የሚኖረው እና ጥያቄ ሆኖ የሚቀርበው እሱ ለሚፈልገው አላማ ሲውል ብቻ ነው ፥ ኢ ፍትሃዊነት ትርጉም የሚኖረው እሱ ሲናገረው ብቻ ነው ፥ የነፃነት ጥያቄ በሱ ልሳን ካልሆነ በሌሎች ሰዎች ልሳን መነገር የማይችል የመለኮት ቃል አስመስሎ ይቀርፅልሃል ። ሃሳቡን ፥ አካሄዱን ፥ መንገዱን እና መድረሻውን እንደ አንድ ተቆርቋሪ ዜጋ « ይህ እንዳይሆን እንዲህ ይሁን » ብለህ ስታመለክት ፥ ከግንዛቤህ ከመማር ፥ የተሳሳትከውን በጨዋ መንገድ ከማረም እና ከማስተማር ይልቅ ከ የ ፓል ቶኩና እና መሰል ቦታዎች በጋራዥ ሴል ( በብላሽ ይለዋል ጉራጌ ) የተገዙ የሳይበር ወታደሮቹን ጥቃት እንዲፈጥሙ መረጃ ይሰጣል ።

እርግጥ ይህ አካሄድ እነ ዶ/ር ታዬ ወ/ሰማትን ከሜዳ ኣስወጥቶ ሊሆን ይችላል ፥ እነ ሳይንቲስት ጥላሁን ይልማን አስደንግጦ ( ወይም ተስፋ አስቆርጦ) ይሆናል ፥ ግን ለሁሉም ይሰራል ማለት አይደለም ። ፖለቲካው ምህዋሩን በማይረቡ ሰዎች ዙሪያ ሊቀልስ ና ሲሽከረከር ስናይ ዛሬ አዲስ ኣይደለም ፥ ትናንት አዲስ ኣልነበረም ፥ ነገም አዲስ አይሆንም ። እነ አባ መላ በአንድ ጊዜ የግሎባል አሊያንስ እና መሰል ድርጅቶች ወግ ከዋኒ ሆነው ወደፊት የመጡት በእውቀታቸው ሳይሆን ባላቸው ገደብ አልባ የመባለግ ብቃታቸው ነበር ። ከነሱ የብልግና እውቀት መጠቀም የሚሻ ፥ በደካሞች መሃል ትልቅ ሆኖ መታየት የሚሻ ትንኞችን ኢየመረጠ የደረቀ ባሊ ላይ ማሰማርቱ የምንነቱ መገለጫ ነው ። እርግጥ እንደዚህ አይነት ሰዎችን ከላይ እንደገለጥኩት «በርካሽ ከጋራጅ ሴል ላይ» ልታገኛቸው ትችላለህ ፥ ግን እንደዚህ አይነት ደካማ ፥ ነውረኛ እና አሳፋሪ ሰዎችን ወደፊት በማምጣት ለውጥ ማምጣት እንችላለን የሚል ተቋም ይሁን ኣቋቋም ለምን ተተቸሁ ብሎ አካኪ ዘራፍ ሲል ብትሰማው « ማነው ልክ » ብለህ ራስህን ትጠይቅ ይሆናል እንጂ አካኪ ዘራፉ የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል እውነት ኖሮት ያንተን የእምነት ተራራ በፍርሃት ጨረሩ ሊገፋ እያስችለውም ።

የኛ ፖለቲካ ከሞላ ጎደል እውነትን በመፍራት እና የተናገረንን በማስፈራራት ላይ የተመሰረተ ነው ። ለራሱ ክብር የሌለው ሰው ሁለቱንም ሲያደርግ ልታየው ትችላለሁ ፥ ከዚህ ለራሱ ክብር ከሌለው ሰው ያነሰው ሰው ደሞ በዚህ ክብረ ነክ የሚደርስበትን ዘለፋ ፥ ዛቻ እና ማስፈራሪያ በመፍራት እንደ ቀንድ አውጣ ብርድልብሱ ውስጥ ተደብቆ « ፖለቲካ ለምኔ » ሲል ልታገኘው ( ልታየው) ትችላለህ ። በዚህ የመፍራት እና የማስፈራራት ትብታብ የተጠመዱት ፥ የወደቁት እና መነሳት ያቃታቸው ፥ በግሩፕ ዘለፋ ፥ በህዝባዊ ዛቻ እና በግብረ ሃይል ጥላቻ ከሜዳ እንዲወጡ የተደረጉት እና እጅ ሰጥተው የወጡት ( የወደቁት ) ፥ በኔ እይታ የአሸናፊነት ስነ ልቦና ምን እንደሆነ የማያውቁ ናቸው ፥ በኔ ግንዛቤ « ተሳዳቢው » ከኔ በኢትዮጵያዊነት ይበልጣል ብለው ያመኑ ናቸው ፥ ተቀጣሪው ወይም አቃጣሪው የተሻለ የሰውነት አቅም አለው ብለው ሽንፈትን የተቀበሉ ደካሞች ናቸው ። ይህ ግን ልክ አይደለም ።

በሃገራችንም ሆነ ከሃገራችን ውጭ ፥ ሀገራችንን በተመለከተ የሚደረግ ማንኛቸውም ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳባችንን የመሰንዘርም ሆነ ቢሆን ጥሩ ነው ብለን የምናስበውን ነገር የመናገር መብት አለን ። ይህንን መብት መለስ ዜናዊ አልሰጠኝ ፥ አያስጠብቅልኝም ፥ ይህንን መብት ብርሃኑ ነጋ አልሰጠኝም ፥ ታግሎም ኣያጎናፅፈኝም!! ይህንን መብት ከማንም ሳይሆን እንደ ሰው ከእግዚያብሄር ያገኘሁት ምንነት ነው ፥ ማንነት ነው ። ብርሃኑ ቢሳካለት ምናልባት ለተፈጥሮ መብቴ እውቅና ይሰጥ ይሆናል ፥ ባይሰጥ ግን እሱ እነ መለስን እንደተቃወመው እኔ ደሞ በተራዬ እሱን እቃወመዋለሁ ። ያንን ያህልም ተራ የምጠብቅ አይመስለኝም እንደውም !

ለሃገራቸው በየ በርሃው መስዕዋት እየከፈሉ የሚገኙ ታጋዮች በመጀመሪያ ነፃ የሚያወጡት ራሳቸውን ነው ብዬ ነው የማስበው ። የወያኔም ትልቁ ክሽፈት ራሱ ነፃ ሳይወጣ ሌሎችን ነፃ ለማውጣት መታገሉ ላይ ይመስለኛል ። የሃሳብ ነፃነትም ሆነ የመሰብሰብ መብት በድህረ ወያኔ ስርዓት የተነፈግነው ፥ እኛ ሳንሆን ወያኔ ራሱ ነፃ ስላልሆነ ነው ። እኛማ ነፃ ነን ፥ ነፃም ስለሆንን ነው የነፃ ሰው ባህሪ ያሳየነው ። የመናገርም ሆነ የመፃፍ ነፃነት የነፃ ሰው ባህሪ ነው ። ያንን ማድረግ አትችልም የሚልህ አካል ግን ያንን ነፃነት የማያውቅ እስረኛ ስለሆነ ነው ። ለዚህም ይመስለኛል ካርል ማርክስ የዘመናዊ ሰው መነጠል ( The Alienation of Modern Man ) በተባለው መጥሃፉ

<< The Germans toured us, used a poison gas to massacre us and even put us in a furnace, it is only because we are free>> ። የምንታሰረው ፥ ስንጥፍ የምንነቀፈው ፥ ስንናገር የምንፎተተው ፥ ስንደፍር « ኩም » አድራጊው የበዛብን እኛ ነፃ ስለሆንን ነው ። ለምን ፥ እንዴት ፥ እንዲህ ባይሆንስ ፥ ይሄ ቢሆንስ የሚል ሁል ጊዜም በእንቅልፍ ልቡ የሚኖር ስላለመሆኑ ማሳያ ነው ። ስለዚህ ሰድባችሁ የምታቆሙት ፥ አብራችሁ የምታስበረግጉት ፥ አሲራችሁ የምትጥሉት ፥ ወጥናችሁ የምታሰናክሉት ማንነት ትከሻችን አይሸከምም ። የተወሰነ ደረጃ መሄድ ትችሉ ይሆናል ፥ አራት ወይም አስር ሰዎችን አሳፍሮ ከጫወታ ውጭ ማድረግ ይቻል ይሆናል ፥ ሁሉንም ግን በአንድ አይነት መንገድ ማሸነፍ አይቻልም ። እንዲህ ያለውን ሰው ለማሸነፍ ብቸኛ መንገዱ ግን መብቱን ማክበር ብቻ ነው ።

መልክቴ ከወንዚያ ወዲህ ማዶም ወዲያ ማዶም ላላችሁት ነው ። መፃፍ ፥ ማጋለጥ ፥ ማስተማር ፥ ክርክር መፍጠር ፥ ጠያቂ እና መሪማሪ ትውልድ እንዲፈጠር የአቅማችንን ማድረግ እንቀጥላለን ። ከዚያ እኩል ተንኮሉ ፥ ሴራው ፥ ደባው እንደሚኖርም እናውቃለን ። ያፈቀሩን ለምን ጠሉን ብለን አይደለም የምንታገለው ፥ ወይም እንደ አንዳንድ ግብዞች በግሩፕ ፍቅር ሰክሮ ፥ በጋርድ እና በ ከበባ ለመሄድም አይደለም ። አላደግንበትም ። ከሊስትሮ ጋ ኳስ ተጫውተን ፥ ከቆሎ አዟሪ ጋ ተጋፍተን ነው ያደግነው ። የህዝብ ልጆች ነን ! አስተዳደጋችን አድር ባይነትን አይፈቅድም ! ማስመሰልን ደባል አድርጎ መኖር አይችልም ። ለድሃ መቆምህን ለማሳየት ስለ ድሃ ኣታውራ ፤ ከድሃ ጋ ኑር! ከድሃ ጋ ተዋለድ ፥ ከድሃ ጋ ብላ ፥ ከድሃ ጋ ጠጣ። ስለ ነፃነት መቆምህን ለማሳየት ጥቅስ አትጥቀስ ፥ አንተን ጠቅሰው ፥ ስህተትህን ነቅሰው የሚናገሩትን የማድመጥ ልምድ ይኑርህ ። ሃቀኝነትህን በምታገኘው ላይክ እና በያዝከው ማይክ ልክ አትለካው ፥ ሃቀኝነትህን ሌሎችን ለማዳመጥ ባለህ ቅንነት ልክ ለካው ! ይሄ ከማላቆመው መልክቶቼ ውስጥ አንዱ ነው !

ቸር እንሰንብት ( ሄኖክ የሺጥላ )

Henoke Yeshetlla's photo.