ሰሚት አካባቢ የተደረመሰው ባለአምስት ፎቅ ሕንፃ በጥራት ችግር መሆኑ ተጠቆመ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ሰሚት ለስላሳ መጠጦች ፋብሪካ በተለምዶ እንዶዴ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፣ ሚያዝያ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ከንጋቱ 12፡30 ሰዓት ላይ የተደረመሰው ባለአምስት ፎቅ ሕንፃ ምክንያቱ የጥራት ችግር መሆኑ ተጠቆመ፡፡

ሕንፃው አቶ ዓለማየሁ ታዬ የሚባሉ ግለሰብ ንብረት መሆኑን ከተጀመረ ዓመታትን ማስቆጠሩን የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎች፣ ግንባታው ሳይጠናቀቅ የታችኛው ወለል ለሁለት ድርጅቶች፣ አንደኛ ፎቅ ደግሞ ለማምለኪያ ተከራይቶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

የሕንፃ አዋጅ አንድ ሕንፃ ተገንብቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ለአገልግሎት ብቁ መሆኑን የሚያረጋግጥ የአገልግሎት መስጫ ፈቃድ ሳያገኝ ማከራየት እንደማይቻል የሚደነግግ ቢሆንም፣ በተግባር እየተሠራበት ያለው በተቃራኒው መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ይናገራሉ፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ሚያዝያ 19 ቀን ከንጋቱ 12፡30 ሰዓት ላይ በተደረመሰው ሕንፃ ሥር አቢሲኒያና ዳሸን ባንኮች ተከራይተው ይሠሩ ነበር፡፡ በመሆኑም የሕንፃው ግንባታ በአግባቡ ቁጥጥር ስላልተደረገለት ተገንብቶ ሳይጠናቀቅ ሊደረመስ መቻሉን አክለዋል፡፡

የሕንፃውን ምድር አቢሲኒያ ባንክ ከዓመት በፊት በካሬ ሜትር 200 ብር ሒሳብ 120 ካሬ ሜትር ተከራይቶ የሚሠራ ሲሆን፣ ለአምስት ዓመት ኮንትራት ተፈራርሞና ክፍያ ፈጽሞ እንደነበር ታውቋል፡፡

ዳሸን ባንክ ከሁለት ወራት በፊት ከፍተኛ የኪራይ ዋጋ በመክፈል መከራየቱ የታወቀ ሲሆን፣ ሁለቱም ባንኮች ሙሉ ዕቃቸውና አዳሪ ገንዘብ በካዝና እንዳስቀመጡ የመደርመስ አደጋው መከሰቱን ሪፖርተር በሥፍራው ካገኛቸው የባንኩ ባለሙያዎች መረዳት ችሏል፡፡

የሕንፃ አዋጅ ቁጥር 624/2001 አንቀጽ 18፣ ‹‹የተገነባ ሕንፃ መሥፈርቱን ማሟላቱ በፍተሻ ካልተረጋገጠና የመጠቀሚያ ፈቃድ ካልተሰጠ በስተቀር ሕንፃው ጥቅም ላይ ሊውል አይችልም፤›› ይላል፡፡

ነገር ግን ሁሉም በመገንባት ላይ ያሉ ሕንፃዎች ገና መሠረታቸው ብቅ ሲል እንደሚከራዩ የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎች፣ ምክንያቱ ደግሞ ሕንፃ ገንቢዎቹ ገንዘብ ሲያጡ ከባንክ ሰዎች ጋር በመደራደርና መደለያ በመክፈል አከራይተው በገንዘቡ ሌላ ሥራ እንደሚሠሩ ጠቁመዋል፡፡

በተለይ በአሁኑ ጊዜ በርካታ ሕንፃዎች እየተገነቡ ከመሆኑ አንፃር ሕጉ ተግባራዊ የማይደረግ ከሆነ አደጋቸው እየተባባሰ ስለሚሄድ፣ ሕጉን የሚያስፈጽመው የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ሊያስብበት እንደሚገባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሰሚት አካባቢ የተደረመሰው ሕንፃ በሰው ሕይወት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አለማድረሱ ታውቋል፡፡ ባለቤቱ አቶ ዓለማየሁ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ ላይ በመሆናቸው ሪፖርተር ሊያነጋግራቸው ካለመቻሉም በላይ፣ ከፖሊስ መረጃ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡