ጸ በቃን!
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ከአስቻለው ከበደ አበበ – ቶረንቶ፣ ካናዳ
ስሞኑን ለአንድ ጉዳይ ዳውን ታዎን ደርሼ ስመለስ የባህል ምግብ መአዛው ናፍቆኝ ከአንድ የኢትዮጵያኖች ቅመማ ቅመም መሸጪያ ቤት ጎራ አልኩኝ፡፡የምሸምተውን ሸምቼ ከሱቁ ስውጣ አንድ ጎለማሳ ሰው አቆመኝና ጃማካዊ ነህ ብሎ ጠየቀኝ፡፡አይደለሁም አልኩት፡፡ ቀጠለና ኤርትራዊ፣ሩዋንዳዊ…ኢትዮጵያዊ የሚለው ጋር ሲደርስ፣ መሆኔን አረጋገጥኩለት፡፡ለካስ ሰውዬው የሀገር ልጅ ኖሮ፣ ቋንቋ ቀይረን ስለሀገር ቤት ሁኔታ ማውራት ቀጠልን፡፡
የሚያጨሰውን ሲጋራ እንደጨረሰ፡፡ ሲጋራ ሊያጨስ እንደወጣ እንጂ ከአውራ ጎዳናው ማዶ ያለው የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ውስጥ ቢራ አስከፍቶ እንደመጣ ነግሮኝ ፣ከብዙ ማግባባት በኋላ አንድ ቢራ ሊጋብዘኝ ተስማምቼ ወደ ሬስቶራንቱ አመራን፡፡ መግቢው ላይ አሱ የሚጠጣውን ቢራ እንዲያዝልኝ ነግሬው ወደ መታጠቢያ ቤት ሄድኩ፡፡
ይዞ ይጠብቀኝ የነበረው ቦታ ላይ ተደላድዬ እነደተቀመጥኩ፣ ከቢራው አንድ ሁለት ተጎነጨሁና ትንፋሽ ወስጄ ዙሪያ ገባውን ማስተዋል ጀመርኩ፡፡ቡና ቤቱ ውስጥ ያሉ ወንበሮች ሁሉ፣ የባልኮኒዎቹ እንኳን ሳይቀሩ በግማሽ ቅርጽ ተደርድረው ቤቱ አምፊ ቲያትር መስሏል፡፡
ታዳሚዎቹ በእጃቸው የሚጠጣ ነገር ቢይዙም ስብሰባ ላይ እንደሆኑ ያስታውቃል፡፡ አጠገቤ ወደ ነበረው ስው ጠጋ ብዬ ስብሰባው ስለምንድን ነው ብዬ ጠየቅኩት፡፡ “ ፀ በቃን !” ነው ብሎ በኃይለ ቃል መለሰልኝ፡፡ ንግግሩን በቃ ዝም በል እንደ ማለት ነው ብዬ በመውሰድ ታዳሚዎቹን ማጤን ጀመርኩ፡፡
ከሁለቱ ሰብሳቢዎች ጎልማሳው የውይቱን ሃሳብ ባህረ መዝገብ ላይ ያሰፍራል፡፡ ሌላኛው ፀጉረ መላጣው ሸበታም ሰውዬ አወያይ ሳይሆን አይቀርም ስብሰባውን ለመምራት ይሞክራል፡፡ ነገር ግን ታዳሚዎቹ ሲናገሩ ተራ አይጠብቁም፤ ድብልቅልቅ ያለ ንግግር ነበር የሚሰማኝ፡፡
“በቃ ፀ በቃን! ነው የምንለው፡፡” ሽማግሌው ሰውዬ በመኃል ገባና “ፀ ብሎ ፀሓይ ይጻፋል፡፡ እንዴት ነው ፀ በቃን የምንለው? ”
“እኛ ይሄኛውን ፀ አላልንም፡፡ ባለ ሁለት እግሩን ነው የምንለው፡፡” ቤቱ ድምጹን ተቀብሎ አስተጋባ“ ስንት አመት ሙሉ ጺውጺውታ ዘፍን ከፍቶ የእናት ኢትዮጵያን ሆድ መመጥመጥ፣ ከዚያም በክንፎቿ ጥላ ስር እያደሩ አንቺ ዶሮ ነሽ፤ የእኔ እናት እንቁላል ናት ማለት! አረ በቃን! አረ በቃን! ጎተና አውጥቶ እንደ ጫጩት መጮኽ፡፡ ጸ በቃን ይህ ፊደል ከ ፊደል ገበታ ላይ ይሰረዝ!” ንግግሩን ተከትሎ አብዛኞቹ ታዳሚዎች ቤቱን በፉጨትና በጭብጭባ አደበላለቁት፡፡
ሽማግሌው “አረ የለም፣ አረ ሗላ አይሆንም፡፡ሁሉም ፊደሎች የሚወክሉትን ድምጽ ብዛት ይዘው መቀመጥ አለባቸው ፡፡ ጸ ብሎ ጸሎት፣ ጸ ብሎ ጽድቅ አለ እኮ፣ ታዲ እነዚህ ሃሳቦች በምን ፊደል ይገለጹ?” ጉባኤተኛውን ጠየቁ፡፡ድንገት አንዱ ከመሃል ተነስቶ “በቃ እነዚህ ሁለት ፊደላት በ ፊደል ጠ ይተኩ” ብሎ ተቀመጠ፡፡ሌላኛው ደግሞ ተነስቶ“ በቃ እነዚህ ፊደላት ይጥፉ፣ የሚጽፍባቸውም አይገኘ፡፡ ከፊደላቱ ጋር የተነካካ ሁሉ የተረገመ ይሁን! ” እርግማኑን አወረደው፡፡
ይህን ጊዜ ከጎኑ ከተቀመጠው በኋላ በሹክሽታ ወንድሙ ነው ሲሉ ከሰማሁት ሰው ጋር የሁለቱ ሰዎች ንግግር ከጉባኤተኛው ጩኸት በልጦ እስኪሰማ ድረስ ተጨቃጨቁ፡፡
“ስማ ዱሮ አምስተኛ ክፍል እያለህ በእንግሊዝኛ “the” ተብሎ የተጻፈውን “ተለሮ” ብለህ በአማርኛ ካነበብክ ጀምረህ ለዚህ ሁሉ ያበቃኝ የኢትዬጵያ ፊደል ነው በማለት ጥላቻ እንዳደረብህ አውቃለው፡፡ ስትናገር ምክነያታዊ ሁን እንጂ በስሜት የምትነዳ አትሁን” አለው ፊደላቱን ረግሞ ለተቀመጠው ሰው፡፡
ጉባኤተኛውም “ተለሮ፣ ተለሮ፣ተለሮ…” እያለ ወንበር ይደበድብ ጀመር፡፡ እኔም ምን አይነቱ ጉባኤ አብዳን ላይ ነው እግር የጣለኝ ብዬ እራሴን ጠየቅኩ፡፡ ሽበታሙ ሰውዬ በመሃል ገባ፡፡ ሰውዬው ሰብሳቢ ሳይሆን ሃሳብ በማቀረጥ አቃቢ ሰዓት እንደሆነ እየተገለጠልኝ መጣ፡፡
“አክሱማውያኑ ከአንድ ሺህ አመታት በፊት ከላይ ከሰሜን ኢትዮጵያ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ፈልሰው በድንጋይ ሐውልታት የጥቁር ህዝብ ታሪክን ሲጽፉ ብዙ አልጮሁም፣ ስራቸው ነው እስካሁን ድረስ ምስክር ሆኖ እየተናገረ ያለው፡፡ አንድ ጊዜ ጨጨብሳ የሚባል ጠፋጭ ምግብ አጋጠማቸውና ከነባሩ ህዝብ ጋር ለመግባባት ጠ ከሚለው ፊደል ጨ ን ፈጠሩ፡፡
ልክ እንደነሱ ከቦታ ቦታ እየዞረ የሚሰፍር ደፋር፤ጀግናና ኩሩ ህዝብ ስላጋጠማቸው በአለም ታሪክ እንደሆነው ሁሉ በነበረው መስተጋብር ቃላት መዋዋስ ሲጀምሩ ጀብደኛ የሚለውን ቃል ለመጻፍ ከፊደል ደ ፊደል ጀ ን ፈጠሩ፡፡ ታሪክን በነባራዊው ሁኔታ በጊዜውና በቦታው ላይ ሆነን በአለማቀፋዊ መስፈርት መመዘን ብቻ ነው መጪውን ጊዜ ብሩህ የሚያደርግልን፡፡ ”የሽማግሌውን ዲስኩር ተከትሎ በቤቱ ውስጥ ለጥቂት ጊዜ ፀጥታ ከሰፈነ በኋላ ሌላ ትርምስ ተነሳ፡፡
“አይገርማችሁም፣ ንጉሱ ሠ የሚባል ፊደል አለ፡፡ የአብሲኒያ ነገስታት ብቻ ናቸው የሚጠቀሙበት፡፡ደግሞ ኃይለመለኮት፣ ኃይለስላሴ ለሚባል መጠሪያቸው ነገስታቱ ንጉሱ ኃ የተባለ ፊደል አስፈጥረው ነበር፡፡ አሁን ሦስት ሀ ፊደላት ምን ይሰራሉ፣ አንድ አይበቃም? ወቼ ጉድ ደርግ መጥቶ ነጻ ባያወጣን ኖሮ እኮ አማርኛ እራሱ የጭሰኛ፣የቀጥቀጭና የፈላጭ ቆራጭ ፊውዳል ሆኖ ሶስት ቦታ ይከፈል ነበር፡፡ ” አለ በደር ጊዜ ከድሬ የነበረው ሻምበል ባሻ፡፡ ከግራ ጥግ በኩል የተነሱት ሁለት ሰዎች ደግሞ ከኛ በፊት የተናገሩት ምሁር እንደገለጹት በማለት የሻምበል ባሻ ሀሳብ ላይ በመመርኮዝ አስተያት አቀረቡ፡፡
የስብሰባው አቅጣጫና ኢሳይንሳዊ አካሄድ መጨረሻ ያሰጋቸው ሽማግሌው ሰው “እሺ እንግዲህ ሰው ሲፈጠር ቃልና ቃልን የሚወክል ፊደል ይዞ አልተፈጠረም፣ የሚናገርበትን አካል ብቻ እንጂ፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮን አሸንፎ ህይወትን ቀጣይ ለማድረግ ባህልን ፈጠረ፡፡የዚህ ሁሉ ማሳረጊያው ሰውን መግቦ ደህንነቱን በመጠበቅ ድህነትን አሸንፎ ማኖር ነው፡፡ ታዲያ ፤ ድህነትን ፀጥ ጭጭ እናደርጋለን ብለን ለመፎከር ብንፈልግ እንዴት እንጻፈው?” አቃቢ ሰዓቱ ወይም ሰብሳቢው ከሻምበል ባሻ ጀምረው ጉባኤተኛውን በአይናቸው ቃኙ፡፡
ሁለት ሶስተኛው የሚሆነው ተሰብሳቢ ”“ድህነትን ጠጥ ጥጥ እናደርጋለን!” ብሎ ፎከረ፡፡
“ይህማ ድህነትን ጭራሽኑ አስክረን እላያችን ላይ ጣልነው ማለት ነው፡፡” የሽማግሌው የመጨረሻ ቃላቸው ነበር፡፡ ይህን ተናግረው ወደ ሰማይ ይውጡ ወይም ወደ መሬት ይስረጉ ሳይታወቅ ከመድረኩ ላይ ተሰወሩ፡፡ እኔም በቃለ ጉባኤ ጸሐፊ ብቻ የሚመራ ስብሰባ የትም እንደማይደርስ ሰለተረዳሁ ከቡናቤቱ ለመውጣት ወደ ኃለኛው በር አመራሁ፡፡
በሩ ጋር እንደደረስኩ አስተናጋጇ ተከትላኝ መጥታ እጄን ያዝ አድርጋ አቆመችኝ፡፡
እጄን ወደ ኪሴ እየከተትኩ “ሂሳብ ስንት አለብኝ?” አልኳት፡፡
“ቢራውን እኮ የጋበዘህ እሱ ነው፡፡” ጋበዘህ ያለቺኝን ሰውዬ ዞር ብዬ ተመለከትኩት፡፡ ትንሽ ትንሽ መልኩ ትዝ አለኝ፤ የት እንደማውቅው ግን አልከሰትልህ አለኝ፡፡ በጥያቄ አስተያየት መልሼ ተመለከትኩት፡፡ ፈራ ተባ እያለች፣
“ከመታጠቢያ ቤት ተመልሰህ ስትመጣ፣ ተሳስተህ እሱ የቀዳውን ቢራ ነበር የጠጣህው፡፡ ዶዲ ደግሞ ሁል ግዜ ምናምን ቢራው ውስጥ ጨምሮ ነው የሚጠጣው” ደህንነቴን በማጠየቅ አመለካከት ዓይኖቿን በመላ አከላቴ ላይ አሯሯጠቻቸው፡፡
“ዶዲ የምትይው ዳዲ ለማለት ፈልገሽ ነው ወይስ… ” አላስጨረሰችኝም፣
“ዶክተር ዲፕሬሽን ወይንም ድብርት ብለን ነው የምንጠራው፡፡ ሩስያ ሃገር ቋንቋ ተምሮ ነበር ሲሉ ሰምቼአለሁ፡፡ የድብርት በሽታ ሰላለበት እራሱን ዘና ለማድረግ ቢራው ውስጥ ዕጠ ምናምኑ ይከታል፡፡ ሰውዬው የሚታወቀው ከማንም ወገን የተጠራ ስብሰባ ላይ በመገኘት ነው፡፡ ለአንድ ሰዓት ያህል ነትርኮሃል እኮ፡፡”
ዶዲን ዞር ብዬ ተመለከትኩት፡፡ መልኩ ቀስ ብሎ መጣልኝ፡፡ ስብሰባው ላይ ቃለ ጉባኤ ያዢው እሱ ነበር፡፡ ልከፍለው የነበርውን ብር ለአስተናጋጁ ሰጥቼ ዕጠ ፋሪስ በቢራ ያስጠጣኝን ዕድሌን ረገምኩ፡፡ ቡናቤቱን ለቅቄ ከመውጣቴ በፊት ዶዲን ለመጨረሻ ጊዜ ተመለከትኩት፡፡ ቦታ ቀይሮ ሶስት ሰዎች መሃል ተቀምጦ ያወራል፤ ምናልባትም ከቀናው ከዚህም ከዚያም የሰበሰበውን በዕጠፋሪስ ቢራ ያንሾካሽክባቸው ይሆናል፡፡ ዶዲስ ቢሆን ለህመሙ መድሃኒት ያጣ የተሳከረ ዘመን ውጤት አይደል? ቅብብሎሹ ግን ይገርማል፡፡ እኔም ከዕጠፋሪስ ፈረስ ተቀብሎ ቤቴ የሚያደርሰኝን ባቡር ለመያዝ ወደ ሰብዌይ አመራሁ፡፡