የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በ“ቃና” ቴሌቪዥን ላይ ተቃውሞ እንደሌለው ገለፀ::
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በ“ቃና” ቴሌቪዥን ላይ ተቃውሞ እንደሌለው ገልፆ ከኪነጥበብ ሙያ ማህበራቱ የሚቀርቡት ተቃውሞዎች የሳንሱር ባህሪ ያላቸው በመሆኑ አልደግፈውም ብሏል፡፡ ባለፈው ሳምንት የተለያዩ የኪነ ጥበብ ማህበራት የ“ቃና” ቴሌቪዥን 70 በመቶ ወደ አማርኛ ቋንቋ የተተረጎሙ የውጭ ፊልሞችን አሰራጫለሁ ማለቱን በመቃወም፣ መግለጫ መስጠታቸውን ያስታወሰው ማህበሩ፤ በመግለጫው ላይ የደራሲያን ማህበሩ ተወካይ የተገኙት በጣቢያው ላይ ተቃውሞ ለማሰማት ሳይሆን መግለጫውን ለመከታተል መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡ እነ በዓሉ ግርማን የመሳሰሉ ፀሃፍት በሳንሱር ምክንያት የህይወት መስዋዕትነት ጭምር መክፈላቸውን የጠቆሙት ዶ/ር ሙሴ፤ ማህበሩ ይህን መርህ በማስጠበቅ፤ የኪነ ጥበብ ስራዎችን የማገድና የማሳገድ ስራ ውስጥ አይገባም ብለዋል፡፡ የሳንሱር ባህሪ ላላቸው ጉዳዮችም ድጋፍ አይሰጥም ሲሉ አክለዋል፡፡ “የቴሌቪዥን ፕሮግራሞቹን ተመልክቶ መፍረድ ያለበት ህዝብ ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ “ማህበሩ በዚህ ጉዳይ እጁን አያስገባም፤ የሳንሱር ባህሪ ያላቸውን አመለካከቶችም አይቀበልም” ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፊልም ፕሮዲውሰሮች፣ የቲያትር ባለሙያዎች፣ የሙዚቀኞችና የሰአሊያን ማህበራት እንዲሁም አላቲኖስ የፊልም ሰሪዎች ማህበር በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ “ቃና ቴሌቪዥን” የሚያስተላልፈው ፕሮግራም የሀገሪቱን የሲኒማ ጥበብ አደጋ ላይ የሚጥልና የባህል ወረራን
የሚያስፋፋ ነው በማለት፤ መንግስት ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ መጠየቃቸው አይዘነጋም፡፡ Addis Admass