በሱዳን በ“ጫት መቃም” ወንጀል እስከ 20 ዓመት የተፈረደባቸው ኢትዮጵያውያን ተማጽኖ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
መንግስት ወደ አገራቸው እንዲመልሳቸው ተማፅነዋል ከ10-20 ዓመት እስር ተፈርዶባቸዋል
ከሶስት ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ በሱዳን አቋርጠው ሊቢያ ለመግባት ሲጓዙ የነበሩ ከ20 በላይ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ጫት ሲቅሙ በፖሊስ ተይዘው በተመሰረተባቸው ክስ፣ ከ10 እስከ 20 ዓመት እስር ተፈርዶባቸው በወህኒ ቤት እንደሚማቅቁ በተለይ ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ወደ አገራቸው እንዲመልሳቸው እስረኞቹ ተማፅነዋል፡፡
በካርቱም እስር ቤት ከሶስት ዓመት በላይ እንዳሳለፉ የተናገሩት ወጣቶቹ፤ ቤተሰቦቻቸው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በሱዳን ኤምባሲ በኩል ለማስፈታት ጥረት ቢያደርጉም እንዳልተሳካላቸው ከእስር ቤት በላኩት ቪዲዮ ጠቁመዋል፡፡ ኑርሁሴን በሪሁ የተባለው የ30 ዓመት ወጣት፤ ሰርቶ የመለወጥ ዓላማ ሰንቆ ሊቢያ ለመግባት በሱዳን በኩል ሲጓዝ፣ ጫት ሲቅም ተይዞ ክስ እንደተመሰረተበትና ጫት በመቃም ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ 20 ዓመት እንደተፈረደበት ይገልፃል፡፡ በኤምባሲ በኩል ፍትህ ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን የጠቀሰው ኑሩሁሴን፤ በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሃላፊዎች፤ “ሀሺሽ ይዘው ለተገኙት ሃላፊነቱን አንወስድም፤ በጫት ለታሰራችሁት ግን መፍትሔ እንሰጣለን” ብለዋቸው እንደነበር ይናገራል፡፡ ሆኖም በዓመት አንድ ጊዜ መጥተው ከመጐብኘት በስተቀር ያመጡልን መፍትሔ የለም ብሏል፡፡
የኑሩሁሴን በካይሮ መታሰር ከራሱ አልፎ በቤተሰቡ ላይ ከፍተኛ ቀውስ አስከትሏል፡፡ ታናሽ እህቱ ወ/ሮ ስትኑር በሪሁ ለአዲስ አድማስ እንደገለፀችው፤ አባታቸው የልጃቸውን መታሰር ሲሰሙ በተፈጠረባቸው ድንጋጤ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን ሱዳን ይኖር የነበረው የኑሩሁሴን ታላቅ ወንድም ሙስጠፋ በሪሁም ወንድሙን ለማስፈታት ቀን ከሌት ሲሮጥ፣ በባጃጅ አደጋ ህይወቱን እንዳጣ ተናግራለች፡፡ “ወንድሜ አገሩ ላይ በመጋረጃ ሙያ ስራ ይተዳደር ስለነበር ከአገር እንዳይወጣ ተማፅኜዋለሁ፤ ምክሬን አልሰማ በማለቱና ለዚህ በመብቃቱ አዝኛለሁ” ብላለች፤ ታናሽ እህቱ፡፡
ሌላው ታሳሪ ወጣት ይድነቃቸው ካሳ በቪዲዮ ባስተላለፈው መልዕክት፤ “ሰርቼ ራሴንና ቤተሰቤን ለመለወጥ ከአገሬ ብወጣም፣ ጫት ቃምክ ተብዬ የ10 ዓመት እስር ተከናንቤያለሁ” ብሏል፡፡
የይድነቃቸው ቤተሰቦችም ላለፉት ሶስት ዓመታት ልጃቸውን ለማስፈታት ላይ ታች ቢሉም ያተረፉት ድካም ብቻ መሆኑን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ከአማራ ክልል ወደ ሱዳን የተሰደደው ሌላው የ21 ዓመት ወጣት፤ ሱዳን ውስጥ ጫት መቃም ወንጀል እንደሆነ ባለማወቃቸው ተከሰው የ10 ዓመት እስር እንደተፈረደበት ገልፆ፣ “ጎረቤት አገር ሱዳን አስተምራ ልትምረን ሲገባ፣ ሰርተን የምንለውጥበትን እድሜ በእስር እንድናሳልፍ መደረጉ ከፍተኛ ሀዘን ውስጥ ከቶናል ብሏል፡፡
የወጣቱ አያት በበኩላቸው፤ “ይጦረኛል ያልኩት የልጄ ልጅ፤ በመጥፎ አጋጣሚ ካገሩ ወጥቶ፣ በሰው አገር እስር ቤት መማቀቁ ሞቴን እንድመኝ አድርጎኛል” ብለዋል፤ በእንባ ታጅበው፡፡
ከወሎ የተሰደዱት ጀማል መሀመድ ኢማም፣ እንድሪስ አብዱ መሐመድ፤ ከጅማ ወደ ሱዳን ሄደው ለእስራት የተዳረጉት አደም ኢሳ፣ ሀሰን ጀማል ከድርና ከጉራጌ ዞን የተሰደደው ሙክታር ከድር፤ ከካርቱም ወህኒ ቤት በላኩት ቪዲዮ፤ “ቢያንስ ጥፋተኛ ከተባልን እንኳን እስራቱን አገራችን ገብተን እንድንጨርስ መንግስት ጥረት ያድርግልን፤ እዚህ ያሉት የእስር ቤት አለቆች ለእኛ ካላቸው ጥላቻ የተነሳ፣ ብዙ መከራ እያደረሱብን በችግር ላይ እንገኛለን” ሲሉ መንግስት እንዲደርስላቸው ተማፅነዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ፤ ሱዳን ውስጥ ስለታሰሩት ዜጎች መረጃው እንደሌላቸው ጠቁመው፤ ሆኖም መንግስትና በየአገራቱ ያሉት ኤምባሲዎቻቸው ዜጎቻቸውን ችላ እንደማይሉ ገልፀዋል፡፡
በየመንና በማላዊ በችግር ውስጥ የነበሩ ዜጎችን፤ መንግስት እንዴት በትጋት ወደ አገራቸው እንደመለሳቸውም ቃል አቀባዩ በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡
Addis Admass