ከዚህ ወዲያ ሽብር? “አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል!”
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
Yohanes Molla – “በኢንተርኔት አማካይነት የድምፅና የምሥል ጥሪዎችና መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ አፕሊኬሽኖች፣ ኢትዮ ቴሌኮም ከውጭ ጥሪዎች ማግኘት የሚችለውን ከፍተኛ ገቢ እንዳስቀሩበት ተገልጿል።” ብሎ ተራ ንግግር ከየትም አይገኝም። አገልግሎት ሰጪ ከሚሰጠው አገልግሎት ጋር እንጂ፥ “እንዲህ ባይሆን ይሄን ያህል አገኝ ነበር” የሚል ‘opportunity cost’ ያሰላል እንዴ? ይሄ እኮ፥ “የዓለም የቴሌኮም አገልግሎት በእኛ ስር ቢሆን ኖሮኮ ከዓለም አንደኛ ሀብታሞች እንሆን ነበር።” እንደማለት ያለ ነውር ሀሳብ ነው።
“አሜሪካዊ ብንሆን ኖሮ እኮ ይህን ያህል ሰው አይራብም ነበር!!”
“በአሁኑ ወቅት ክፍያ ለማስከፈልም ሆነ በማጭበርበር ተግባር ላይ የተሰማሩትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂ ባለቤት ነን፡፡ ነገር ግን ክፍያ ለመጣል አልወሰንም፤” ብሎ ንግግርም ሌላ የሚያሳፍር ነው። እንዴት ነው ነገሩ? ቴክኖሎጂውን መጠቀም/አለመጠቀማቸውን ሳያውቁ ነው እንዴ በሚሊዮኖች ከፍለው የቴክኖሎጂው ባለቤት የሆኑት? መንግስት ሳያውቀው ነው እንዴ ግዢ የሚፈጸመው?
“ከአፕሊኬሽኖቹ ባለቤቶች ጋር መደራደርና ከዓመታዊ የትርፍ ድርሻቸው ክፍያ እንዲፈጽሙ መግባባት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ብቸኛው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ኢትዮ ቴሌኮም በመሆኑ፣ ከአፕሊኬሽን ባለቤቶች ጋር የክፍያ ድርድር ማድረግ ለኢትዮ ቴሌኮም ጠቀሜታዊ ፋይዳው የተሻለ ከሆነ ቀላል አማራጭ እንደሚሆን አቶ አንዱዓለም ጠቁመዋል፡፡” ከዚህ ወዲያ ገዳይ ዜናስ መቼም አይገኝም። ሃሃሃ… ደግሞ ብቸኛ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪነት የሚያኮራ ሆኖ ነው?
ደግነቱ ነውራችን ሁሉ በአማርኛ ነው።
“ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የወጣበትን የቴሌኮም መሠረተ ልማት ያለባለቤቱ ዕውቅናና ተጠቃሚነት የሚገለገሉና ከፍተኛ ትርፍ ለራሳቸው የሚያካብቱ ናቸው፤”
ኧረ ሼ! ኢንቨስትመንቱ ከሕዝብ ኪስ አይደለም እንዴ?? እቁብ ገብተው፣ ቆጥበው የከፈቱት ካምፓኒ አስመሰሉት እኮ። ከፍተኛ ትርፉን የሚያገኘውና ለራሱ የሚያካብተውስ “የሚታለበው ላም” ቴሌ አይደለም?? የቴሌኮም አገልግሎቱ አልበቃ ብሏቸው ስልክ ወደ መቸርቸር የገቡት እነሱ አይደሉም እንዴ?? አዳዲስ የኢንተርኔት አገልግሎቶችን በመቀየር ሰበብ የapparatus ወጪ የሚያስወጡን (ለምሳሌ ከEVDO ወደ 3G ሲያሻግሩን) እነሱ አይደሉም?? ደግሞ በፈለጉት መንገድ ለሚቆርጡትና አሁን ተሞልቶ አሁን ለሚያልቅ ካርድ።
የዚህን ምስኪን ነዋሪ ኑሮን በግንኙነት ወጪዎች (communication cost) መደጎም ማሰብ ቢቀር፥ ከፍተኛውን ወጪ ለግንኙነት እያወጣን ባለበት ሁኔታ እንዲህ ያለ ነገር ግፍ አይሆንም? ደግሞ ግንኙነት ሲቀላጠፍ እና ሕዝብ የግንኙነት ወጪ ሲቀንስ ገንዘቡን ቀቅሎ አይበላው ነገር፤ …ስራ ይሰራል እንጂ?! ዓለማቀፍ የነዳጅ ዋጋ በጣም ወርዶ ባለበት ሁኔታ፥ “በፊት ስንደጉም የነበርነውን እያወራረድን ነው” በሚል ተልካሻ ምክንያት፥ በየወሩ ዋጋ እየቀያየሩ ሕዝቡን ማሸበርስ ምን ይባላል?
መንግስቱ ኃይለማርያምም መጥቶ “በፊት ስደጉም የኖርኩትን ሂሳብ አስልታችሁ ቁረጡልኝ” ይበላ!?
በmacro economics ጽንሰ ሀሳብስ ብናስበው ዓለማቀፍ የግንኙነት ወጪዎችን መቀነስ ማለት፥ ስራዎችን ከማቀላጠፍ ባሻገር፣ የዲያስፖራውን ወጪ በመቀነስ ሀገር ውስጥ የሚላከውን ገንዘብ (remittance) ማሳደግና የአገር ውስጥ እንቅስቃሴን መደገፍ ማለት አይደለምን? ታዲያ ይሄ “ከውጭ ከሚገኝ ገቢ ከ50 በመቶ በላዩ ዲያስፖራ የሚልከው ነው።” የተባለለትን የሀገር ሀብት ማሳደግ እንጂ ሌላ ምን ነገር አለው? ደግሞ ምን ያህሉ የስልክ ተጠቃሚ ኢንተርኔት ይጠቀማል?
“ኢኪዩፕመንት አይደንቲቲ ሬጂስተር” ደግሞ ሌላ ገዳይ ነገር ናት። አሁን እንደው የተሰረቁ ስልኮች ቴሌን አሳስበውት? ሴንሰርሺፕ እና ስግብግብነት ሲቀሸሩ እንጂ።
“አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል!”