“ቃና” ወይስ ቃታ? (ይታገሱ ጌትነት )


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


“ቃና” ( Kana Tv )የሚባል የቴሌቪዥን ጣቢያ በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምር ለወራት ሲያስታውቅ መቆየቱ ይታወሳል። ይሄን ተንተርሶ በርካቶች ተስፋ ሲያደርጉ ሌሎች ደግሞ በስጋት ተከበዋል፡፡ ተስፋ አድራጊዎቹ ተጨማሪ የመዝናኛ አማራጭ ልናይ ነው የሚል ሲሆን ባለስጋቶቹ ደግሞ ከቀደሙት በምን ይሻል ይሆን? ከገባንበት የመደንዘዝ ባሕር ሊያላቅቀን የሚችል ምን አዲስ ነገር ይዞ ይመጣ ይሆን? ከተዘፈቅንበት የዘቀጠ የኮፒራይት ጥሰት ምን ይለውጥ፣ ምን ይጨምር ይሆን? የሚል ይመስላል፡፡

“ቃና” ወይስ ቃታ?
በእውነቱ ከ90 ሚሊዮን በላይ ለሆነ ህዝብ ያሉት የቴሌቪዥን አማራጮች በቂ ናቸው ተብሎ አይታመንም፤ ገና ብዙ ብዙ ያስፈልገናል፡፡ እንደ ጫጩት ቅርጫት ተደፍቶብን ሌላው ዓለም የደረሰበትን ጸጋ ማየት አልቻልንም፡፡ እድሜ ለዲሽ ያሉትን አማራጮች በጥቂቱም ቢሆን ለማስተዋል ችለናል፡፡ የኢቲቪ (ኢቢሲ) ደረቅ ፕሮፓጋንዳ ያበሳጨው ከተሜ፣የቤቱን ጣራ ከዲሽ የተሠራ አስመስሎታል፡፡ ይሄንንም አጋጣሚ ለመጠቀም በፈራ ተባ ኮምጠጥና ፈታ ያሉ በዲሽ የሚሠራጩ የቲቪ ጣቢያዎች ከመንግስት ውጪ ያሉ አማራጭ ሆነው ብቅ ብለዋል፡፡
የተረፉትና አዲስ ተቀላቀሉ የተባሉት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣እግሮቻቸውን በደጅ አድርገው ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞቻቸውን ሊያስጠብቅ የሚችለውን ቤዝ በሀገር ውስጥ በማድረግ ገራገር ጭብጦችን፣ በኮፒራይት ዘረፋ የበለጸጉና አጓጉል ሙዚቃዎቻቸውን ለተመልካቾቻቸው በመጋት እየተንገታገቱ ይገኛሉ፡፡ (በርግጥ እግራቸውን ሀገር ውስጥ ያላደረጉት የመንግስት የልጅ ጨዋታ የመሰለ የመከልከል አዚም መሆኑን ማንም አያጣውም) በዚህም መሰረት ኢ.ቢ.ኤስ በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢቲቪን የተመልካችም ሆነ የማስታወቂያ ሞኖፖሊ መስበር የቻለ መሆኑን አሳይቶናል፡፡ አብዛኛው ፕሮግራሙ በግብር ይውጣ አንዳንዴም ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ የሚሠራ ቢሆንም ቢያንስ መሰረቱንና ተመልካቹን ያገናዘበ፣ ኢትዮጵያውያንንና የኢትዮጵያውያንን ጉዳይ በኢትዮጵያውያን ለማንሳት ውስን ሥራዎችን ሠርቷል። (ኢቢኤስ በርካታ ስህተቶችን ሲሠራ የቆየ ጣቢያ መሆኑን አልዘነጋሁትም፡፡ የፍቅር ምርጫዬን የመሰሉ ከባኅላችን ያፈነገጡ ፕሮግራሞችን በማቅረቡ የደረሰበትን ቁጣ ማንሳት አንዱ ማሳያ ነው) ያም ቢሆን በእያንዳንዷ ዝግጅት ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች ቢያንስ በአንድ የ1 ሰዓት ዝግጅት ላይ ከ10 ያላነሱ ኢትዮጵያውያን ሥራ በመሥራት ኑሯቸውን መደጎም እንዲሁም በነርሱ ግንዛቤ ልክ ቢሆንም ህዝቡን ለማገልገል ሞክረዋል፡፡
ዛሬ ደግሞ የኢ.ቢ.ኤስ ትርፋማነት ያስጎመጃቸው አሊያም ሌላ መልክና ደርዝ ያለው ያሉት ሀሳብ ብልጭ ያለላቸው ጣቢያዎች መጣን መጣን እያሉ ነው፡፡ ከነዚህ መካከል አንዱ “የሀገሪቱ ባኅል እና ጉዳይ ጉዳዬ ነው” ያለ መሆኑን ለማስተዋወቅ እየሞከረ ነው፡፡ አረረም መረረም አድካሚውንና ማገዶ የሚፈጀውን የቴሌቪዥን ፕሮዳክሽን ሥራ ወስደው የሚሠሩ የዜጎችን ድምጽ ለማሰማት መንገድ መጀመሩን ታዝበናል፡፡ ሌላው አዲስ ጣቢያ “ቃና ቲቪ” በአንጻሩ አቋራጩንና ከምድሪቱ ላይ ያልበቀለውን ከውጭ በማምጣት ለመትከል ሀሳብ አለኝ፣ 70 እጅ የውጭ ሀገር ፊልሞችንና የቴሌቪዥን ምርቶችን 30 እጅ የሀገር ውስጥ ዘፈኖችን በማስተላለፍ ከሀገር ውስጥ ተቋማት ከትርፋቸው ማስታወቂያና ስፖንሰር ሰብስቤ ንግዴን አስፋፋለሁ ሲል ለመገናኛ ብዙኃን ገልጧል፡፡ (በርግጥ ከውጭ ሀገር ብር እንደማይደገፉ ማረጋገጥ አይቻልም) ፊልሞችን ከበቀሉበት ቀዳሚ ቋንቋ ወደ ሌሎች ቋንቋዎች የመተርጎም አሠራር በሌላው ዓለም የተለመደ አካሄድ ነው፣ ብዙውን ጊዜ ግን ትርጉሙን የሚያሰሩትና ለትርጉሙ ንዋይ የሚመድቡት ተቀባዮቹ ጣቢያዎች ሳይሆኑ አምራቾቹ ናቸው። ይሄም ያላቸውን የገበያ ስፋት በመፍጠር ትርፋማ ለመሆንና ለተቋቋሙበት አላማ ስኬት የሚያከናውኑት አካሄድ ነው፡፡ በዚህ መሰረት አዲሱ “የቃና ቲቪ” የጣቢያው ዋና ግብም እኛን ማዝናናት ሳይሆን ትርፋማ የመሆንና ያለመሆን ጉዳይ ነውና ዜጎችም ትርፋቸውን ማስላት ስለሚገባቸው ሂሳባችንን ልንሠራ ይገባናል፡፡ እውነት ለመናገር እቺ ሀገር የችግር ሀብታም ናት፡፡ ስለዚህ ያለንን ሀብት በትክክልና ተገቢ በሆነ መንገድ ልንጠቀም ይገባናል። የቴሌቪዥን የገቢ ምንጭ የማስታወቂያ ክፍያ መሆኑ ይታወቃል። የነዚህ ማስታወቂያ ምንጮች ደግሞ በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ተቋማት ናቸው። እነዚህ ተቋማት የመኖር ህልውናቸው ደግሞ ህዝቡ ነው፡፡ በመሆኑም የሚከፍሉት ማስታወቂያ እንዲጠቀምበት የሚታሰበው ማስታወቂያውን የሚያሠራጨው ጣቢያ ብቻ ሳይሆን በጣቢያው አማካይነት ተጠቃሚ የሚሆኑ ባለሙያዎችና አጠቃላይ አወንታዊ መልእክት የሚተላለፍለት ህዝብ ጭምር ነው፡፡
ባለንበት ተጨባጭ አውድ ሁሉም ነገሮች ነጻ የሆነ ሀሳብና ውድድር ይመራዋል ማለት ምኞት እንጂ እውነት ሊሆን አይችልም፡፡ ጣቢያዎቹ መከፈታቸው ብቻ ሳይሆን ያለንን አጋጣሚ ጠቃሚ በሆነ መንገድ እንዴት ተጠቅመንበታል? ምን ገንቢ ምን አሉታዊ ነገሮች አሉት? በማለት መመዘን ይገባናል፡፡ በእኔ እምነት የ“ቃና ቲቪ” ካሉት ውስን ጥቅሞች ባሻገር ያለው ወቅታዊና ዘለቄታዊ እንከኖቹ ጎልተው ይታዩኛል፡፡ ሀሳቤን በጥቂት ነጥቦች ላይ በማተኮር ላጽና፡፡
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ
በአሁኑ ወቅት ባለው የሉላዊነት (globalization) እንቅስቃሴ ሳቢያ በኢኮኖሚ ጠንካራ የሆኑና የራሳቸውን አቅም ቀድመው መሥራት የቻሉ አገሮች በሁሉም መስክ አሸናፊ ሆነው ለመውጣት የሚያስችላቸውን ስልት ይቀይሳሉ፡፡ አንድን ማኅበረሰብ መርታት የሚቻለው አስቀድሞ ህሊናውንና ሞራሉን መስለብ ሲቻል ነው። ለዚህም እንዲረዳ ታሪክና ባኅላቸውን በማስተዋወቅ ያለምዱታል፡፡ በዚህም በቀጣይነት ለሚያከናውኑት ኢኮኖሚያዊ የበላይነት ድልዳል ይፈጥራሉ፡፡ በዚህም ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ውስጥ በሀገራችን የተፈጠረውን ግራ የተጋባ ቅይጥ ማንነት (confused Identity) መመልከት ከበቂ በላይ የነገዋ ኢትዮጵያን መልክ ያሳየናል፡፡ ይሄን ለመረዳት የከተማችንን የሆቴሎችና የንግድ ቤቶች ስያሜን አሊያም በስልጣኔ ስም የራሳቸውን ቋንቋ “የረሱትን” አፋቸውን ከፈቱበት አማርኛ፣ ትግሪኛ፣ ኦሮምኛ ይልቅ የባእዱ ቋንቋ የሚቀድማቸው ወጣቶችን ማየት በቂ ነው፡፡
ዛሬ የበርሀ ንዳድ፣ የአስገድዶ መደፈር፣ የሻርክ እራት መሆን ከጉዳይ ሳይቆጠር ራሳችንን ለስደት ጋብዘን ለሞት እንድንገብር ያደረገን አንዱ ነጥብ ይሄው የተሳከረ ማንነትና የባዕዳን ተረኮች ናቸው፡፡ (ተሰዳጁም አሰዳጁንም ይመለከታል)፡፡ እንደነ “ቃና” አይነት ለባዕድ ሀሳብ ገባሪ መሰል ጣቢያዎች ይሄው ችግራንን የሚያስፋፉና መዋጣችንን የሚያለማምዱ የማደንዘዣ ኪኒን በመሆን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆናሉ የሚል ስጋት አለኝ። በርግጥ በቁንጽሉ ጣቢያው የሚያሠራጫቸው ፊልሞች ለእንዲህ አይነት ችግር የሚያጋልጡን መሆን አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ ስርጭቱን መከታተል ይቀድማል የሚሉ የዋሃን መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ በቀን ውስጥ ካሉት 24 ሰዓታት ስርጭቶቹ ውስጥ ወደ 17 ሰዓት በውጭ ቋንቋዎች የተሰሩ ፊልሞችን አስተላልፋለሁ የሚል ተቋም፤ዓለምን ከከደኗት ፊልሞች ምን ያህሉን በልዩ አይን ተጠንቅቆ መርጦ ያቀርብልናል ብሎ መጠየቅና የቀድሞ ልምዳችንን መመልከት በቂ ይመስለኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ 30 እጁም ቢሆን የሀገር ውስጥ ሙዚቃ በሚል ኮፒራይታቸው ያልተጠበቀ በዘመናዊነት ስም ዲቃላ ማንነትን የሚሰብኩ የሙዚቃ ክሊፖችን እንደሚሆን ለመገመት ነብይ መሆን አይጠበቅም፡፡
አሳሳቢው ችግራችን ምንድን ነው?
አስቀድሜ ለማንሳት እንደሞከርኩት፤ ሀገራችን ባለ ብዙ ችግር ናት፡፡ ብዙ የሚያስፈልጉን ጉዳዮች አሉብን፡፡ እነዚህ ችግሮቻችን ሊቀረፉ የሚችሉት ደግሞ የሚያጋጥሙንን ጸጋዎች በአግባቡ መጠቀም ስንችል ነው፡፡ ከዚህ ህዝብ የተሰበሰቡ ገንዘቦች የማኅበረሰቡን አሳሳቢና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ችግሮች ለመቅረፍ ካልዋሉ የግፍ ግፍ እየሠራን መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡ የጥቂቶችን የቅንጦት ጥማት ለማርካት የሚስኪኑን መሰረታዊ ጥቅም የምንሰዋ ከሆንን፣ ባቋረጥነው የእሾህ መንገድ ዳግመኛ መመለስ የፈለግን ምስኪኖች ያስመስለናል። በተቻለን አቅም የባለሙያዎቻችንን አቅም፣ የተቋሞቻችንን እሴት፣ የምሁራኖቻችንን ሀሳብ በማስፋት በድንቁርና እና እውቀት ማጣት ውስጥ ላለው ማኅበረሰባችን አንዳች ብርሃን ልንፈነጥቅ ይገባል፡፡ የጥቂት ግለሰቦች መክበርና መጠቀም እንደሀገር ጥቅምና ትርፍ ማሰብ የምንችልበት እውነታ ላይ አይደለንም፡፡
ስለዚህ ከፍላጎቶቻችን ከችግሮቻችን ውስጥ መርጠን ቅድሚያ ልንሰጥ የሚገባው ነገር ምንድን ነው? አዎ የሰው ልጅ መዝናናት አንዱ ጥያቄው ሊሆን ይችላል፤ ይገባልም፡፡ ሆኖም ለመዝናናት የምስኪን ህጻናትን ነፍስንና የሀገር ህልውናን መስዋዕት ማድረግን ለድርድር ሊያቀርቡት አይገባም፡፡ ከማስታወቂያ የሚሰበሰበው ገንዘብ በቀጥታ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ተመልሶ ወደ ህዝቡ መግባት አለበት። በእያንዳንዱ ፕሮዳክሽን ውስጥ በሚሳተፈው ባለሙያ አማካይነት ለልጆቹ ለጎረቤቶቹ እንዲሁም በሸመታ ወቅትም መልሶ ስፖንሰር ላደረገው አካል መተላለፍ መቻል አለበት። እንዲህ ሲሆን ነው በጋራ ማደግ የሚመጣው። በመሆኑም አሳሳቢውን የሀገራችንን ችግር በመንቀስ ማረቅ የሚችል ዝግጅት መሥራት (ሲፈልግ በፊልም ሲሻው በመዝናናት ስበብ አውዱን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት በመሥራት ሊሆን ይችላል)፣ በተጨማሪም በጥቂቶች ኪስ ውስጥ የሚከማችን ሀብት በማሠራጨት የጋራ ሀገራዊ ጥቅምን መፍጠር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።
የሀብት ክፍፍልና ታክስ
የአንድ ጠንካራ ሀገር መሰረት ከሚባሉ ጉዳዮች መካከል የታክስ ስርአቱ አንዱ ነው፡፡ ታክስ መሰብሰብ ሁሌም ግብ አይደለም፡፡ ይልቁንም በታክስ አሰባሰብ ጊዜና በኋላ ባሉ አካሄዶች ላይ የሀብት ክፍፍልን ማረጋገጥ አንዱ ጉዳይ ነው። ምናልባት መንግስት ከሀብታሞች ላይ በዛ ያለ ታክስ በአንዴ መሰብሰብ መቻሉን እንደ መልካም አጋጣሚ ሊቆጥረው ይችላል፡፡ ሆኖም ሁለተኛውን መሰረታዊ ነጥብ ግን ይስተዋል፡፡ በርካታ ባለሙያዎች በአንድ የቴሌቪዥን ፕሮዳክሽን ላይ ሲሳተፉ መሰረታዊ የሀብት ክፍፍል ከማምጣቱ ባሻገር ከብዙዎች የተሻለ ታክስ መሰብሰብ የሚያስችለውን አጋጣሚ ያገኛል፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ሁሌም ታክስ የሚሰበሰበው የተቋማቱ የገቢና የወጪ ስሌቶች ተካተው ነው፡፡ ከነዚህ የተቋማት ወጪዎች ውስጥ የማስታወቂያ ወጪ አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም ተቋማቱ ትርፋቸውን ለእንደነዚህ አይነት ፋይዳቸው እዚህ ግባ ለማይባሉ ጣቢያዎች አሳልፈው የሚሰጡ በመሆኑ መንግስት ሊያገኝ የሚገባውን የትርፍ ግብር ያጣል፡፡ በርግጥ ሰንሰለቱን ተከትሎ ከተከፋይ ላይ የሚሰበሰብ ቢሆንም ዋና መሰረታቸውን በሀገር ውስጥ ካላደረጉ፣ ተቋማት የተጣራ ታክስ የሚሰበስብበት ሁኔታ በጥያቄ ውስጥ ይወድቃል፡፡ ከዚህም በላይ ለሳተላይትና ለሌሎች ቴክኒካዊ ክፍያ ወደ ውጭ የሚፈሰውን የውጭ ምንዛሪን ሀገሪቱ ከምታገኘው ሁሉ አቀፍ ጥቅም አንጻር መፈተሽ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡
ማኅበረ ባኅላዊ ቀውስ
የሀገሪቱ ህግ ከለላ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የባህሎች የመጠበቅ ጉዳይ አንዱ ነው። ባኅል ግዘፍ የነሳ ተጨባጭ ጉዳይ አለመሆኑ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ቋንቋው፣ ፍልስፍናው፣ አኗኗሩ፣ ሙዚቃው፣ ጭፈራው፣ አስተሳሰቡ፣ የሚፈቅደው ጉዳይ፣ የሚከለክለው ጉዳይ . . . ወዘተ ጭምር ናቸው። እነዚህ ስም ያወጣንላቸውና ልንጠቅስ የቻልናቸው ነገረ ሃሳቦች ናቸው እንጂ ባኅል እጅግ ጥልቅና ሰፊ ጉዳይ ነው። ባኅል ሲበረዝም ሆነ ሲለወጥ በቀላሉ ማወቅ አይቻልም፡፡
ይልቁንም ከጊዜ በኋላ በነበር ሲወሳ እንባንን ካልሆነ፡፡ የባህል ለውጥና ሞት እንደሚታሰበው በፋሽን የመተካትና የመከለስ ጉዳይ ብቻ አይደለም። በአንድ ቋንቋ ሞት ውስጥ የሰው ልጆች አስተሳሰብ፣ ፍልስፍና፣ ጥበብ፣ ስልጣኔ፣ ወዘተ ሞት አለ፡፡ ይሄ ሀሳብ ከዳቦ አይበልጥም የሚል የዋህ እንዳለ ሁሉ ይሄ ሀሳብ ዳቦ መጋገሪያ የዳቦ ምንጭ መሆኑን የተረዱ ሀገራት፣ የራሳቸውን ባኅል ቋንቋና ፍልስፍና በሌሎች ላይ ይጭናሉ፡፡ ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል እንዲባል ደሀዎችና ቸልተኞች የዚህ ሰለባ ይሆናሉ፡፡
አዲስ በሚጫንብን መጤ የባኅል ወረራዎች ውስጥ ከነባሩ ማንነታችን ጋር የማይወዳጁ አዲስ እሳቤዎች የሚያመጡት ማኅበረሰባዊ ምስቅልቅሎሽ እንዲህ እንደዘበት የሚታለፉ ነጥቦች አይደሉም፡፡ በተለይ የነዚህ ተጽዕኖዎች ዳፋ የሚያርፍባቸው ለጋ ህጻናትና ወጣቶች እንዲሁም በትምህርትም ሆነ በንባብ የግንዛቤ ውሱኑነት ያለባቸው የማኅበረሰባችን ክፍሎች መሆናቸውን ስንረዳ፣ የጥፋቱ ስፋትና ዘለቄታዊነትን እንረዳለን። ይሄን ለመገንዘብ መጣን ባሉት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚተላለፉትን ዲቃላና የተወዛገበ መልእክት የሚያሰርጹትን በራፕ፣ በሂፖፕ፣ በሬጌና ሌሎች ስልቶች የተሞሉትን ጫጫታዎች መመልከት ብቻ ይበቃል።
ከዚህም ባሻገር የሚተረጎሙት ፊልሞችና መልእክቶች የህዝቦች ማንነት ላይ አሉታዊ ትርጉም በመስጠት ለሀገራዊ መግባባት እንቅፋት እንዲሁም ለግጭቶች መስፋፋት ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለዚህም ቃና ቲቪ በአማርኛ ተርጉሞ ካዘጋጃቸው ፊልሞች ውስጥ አንዱን በማየት አስተያየት እንድሰጥ እድሉ በገጠመኝ ወቅት ፊት ለፊት ሀሳቤን ገልጫለሁ፡፡ በወቅቱ የተተረጎመው ፊልም ምናልባትም በአንድ ብሄር ላይ አሉታዊ የሆነ ተጽዕኖን በማምጣት አደጋው ከፍተኛ ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡ በመሆኑም ነገም ከዚህ አይነት ቁርሾን ከሚያስፋፉ ስብከቶች እንዴት ልንጠበቅ እንችላለን? የሚለው ከፍተኛው ስጋቴ ነው፡፡
የሥራ እድል
የአንድ ሀገር ሀብት ለዜጎቿ በፍትሃዊ መንገድ ከሚሠራጭባቸው መንገዶች አንዱ እና ዋንኛው ንዋዩ በፈሰሰበት አቅም ልክ ዘለቄታ ያለው ሥራ እድል መፍጠር መቻሉ ነው፡፡
በሌላም መንገድ አንድ ሀገር ንዋይ አፍስሳ ጌዜ አባክና በርካታ ባለሙያዎችንንና ተቋማትን ትሠራለች። የእነርሱም ምላሽ በሙያቸው የሚያበረክቱት አስተዋጽዖና ለማኅበረሰቡ የሚሰጡት አገልግሎት ነው፡፡ ሆኖም የሚጨምሩት እሴትና የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ ከወጣባቸው ወጪ በታች በሚሆንበት ጊዜ እንዲሁም አበርክቷቸው ሀገሪቱ ከሚያስፈልጋትና ቅደሚያ ከምትሰጣቸው ጉዳዮች በተቃራኒ በሚሆንበት ወቅት የተደራረበ ኪሳራ ሆኖ ይቆጣጠራል፡፡ ሮኬት ሳይንስ ያሰለጠነችው ምሁር የብስኪሌት ጠጋኝ ሆኖ የርሱን ኑሮ መደጎም ቢችልም ለሀገርና ለህዝብ ግን ኪሳራ ነው፡፡ የቲያትር አርት ሰልጥኖ “ሊፕ ሲንክ” በመሥራት ሆዱን መሙላት ከወጣበት ወጪ በታች መሥራት ነው፡፡
በመሆኑም አንድ ሀገር ለምታሰለጥናቸውና አቅሟን ለምታፈስባቸው ልጆቿ በበቂ ሁኔታ እንዲያገለግሏትና ያላትን ሀብት እንዲያበለጽጉላት ከለላ ትሰጣቸዋለች፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉት ያላደጉ ኢንዱስትሪዎችን መደገፍ እንዲቻል በተለያየ ስልት ከውጭ ወደሀገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጫና በማድረግ እንዲሁም ለሀገር ውስጥ ምርቶች የተለየ ድጋፍ መስጠት የተለመደ አሠራር ነው። አንዳንዴም አልፎ ተርፎ እንዳይገቡም እስከ መከልከል የሚደርሱ ምርቶችና ሀሳቦች አሉ፡፡ እነዚህ ፍትሀዊ የመሆንና ያለመሆን ጉዳይ ሳይሆን ለራስን ዜጋ ምቹ የሥራ መደላድል የመፍጠርና የሀገር ውስጥ አቅምን የማሳደግ ስትራቴጂ ነው፡፡
በዚህች ሀገር ውስጥ ኮምፒዩተር እንደ ቅንጦት እቃ ተቆጥሮ ታክስ እንደሚደረግ የምንረዳ ስንቶች ነን? የመማሪያ ወረቀትና ስክርቢቶ፣ መጽሐፍ ታክስ የሚደረግባት ሀገር መሆኗን ስንቶቻችን እናውቃለን? በሀገር ውስጥ የተጻፉ መጻሕፍትን ውጭ ወስዶ ለመሸጥ ታክስ መክፈል ግዴታ መሆኑን ስንቶቻችን እንረዳለን? አይደለም የሲኒማ ጥራትን ማገዝ የሚችሉ ካሜራዎችን ቀርቶ ስለ ሲኒማ የተጻፉ መጻሕፍትን ከታክስ ነጻ ማግኘት በማይቻልበት ሀገር፣ በግል ጥረታቸው ለሚደክሙ ዘርፈ ብዙ ወጣት ተስፈኛ የሲኒማ፣ የክዋኔ፣ የጋዜጠኝነት ባለሙያዎችን የሥራ እድል ማሳጣትና ማጥበብ እንዲሁም የሀገራቸውን ሀብት የሚቀራመትባቸው ባዕድ አምላኪ ብልጣብልጥ ህጋዊ አድርጎ ማኖር የሚደፍር መንግስት፣ የማን ሀገር መንግስት እንደሆነ መጠየቅ ተገቢነት ያለው ይመስለኛል፡፡
የተጀመረው የአቋራጭ መንገድ በሀገሪቷ ውስጥ እየተስፋፋ ካለው የዘቀጠ ሙሰኝነት ጋር ተደማምሮ ፍትሀዊ ባልሆነ መንገድ ገንዘብን መሥራት ለሚሹ ባለጊዜዎች ውሻ የቀደደው መንገድ የማይሆንላቸው ይመስለናልን? ሰደን ማሳደድ ልማዳችን ነውና ከጸጸት ለመዳን ዛሬ አይናችንን ገልጠን ልንሟገት ይገባል፡፡ በ1990ዎቹ መጀመሪያ አስቀድሞ የተሠሩና አሬንጅመንታቸው ዜማና ግጥማቸው የተጠናቀቁ የውጭ ሀገርና የሀገር ውስጥ ዘፈኖችን በመገልበጥ በቀላሉ በአንድ ኪቦርድ ወደማቀናበር ያወረደን ስህተት በሙዚቃ ባለሙያውና የሙዚቃ ቅጂ ዘርፉ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ምን እንደሆነ መናገር ጅልን ማርዳት ይሆናል፡፡
ዛሬ ደግሞ ፊት ለፊታችን ይሄው የሰነፍ አቋራጭ ከፊታችን ቆሟል፡፡ የቃና ቃታ ከጥቂት ቀናት በኋላ በይፋ ሥራውን ይጀምራል፡፡ እቺ ሀገር ሀገሬ ናት የሚል ሁሉ ትርጉም ያለው ድምጹን ማሰማት መቻል አለበት፡፡ ቢያንስ ቃና ቲቪም ሆነ የንግድ ፍቃዱን የሰጠው አካል ሁኔታውን ዳግመኛ በማጤን ፊልሞችን በመተርጎም ልናገኘው የምንችለውን ውስን በጎ ጥቅም በማያሳጣ ደረጃ 70 እጁን ሀገር በቀል ለሆኑ ጥበባዊና አስተማሪ ጉዳዮች፣ 30 እጁን አሁን ላቀዱት ቢያደርጉት ለሀገሪቱ ካለው ጥቅም አንጻር ተሸናፊ አይሆኑም ብዬ አምናለሁ፡፡

Addis admass