መሪ አልባ ህዝብ የመፍጠር ግብ:- ኢንጂነር ይልቃልን እንደ ማሳያ (ሸንቁጥ አየለ)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ወያኔ ገና ከጽንሰቷ ጀምሮ ከምትከተላቸዉ መሰረታዊ መርሆዎች ዉስጥ
አንዱና ዋናዉ የኢትዮጵያን ህዝብ መሪ አልባ ማድረግ ነዉ::
እተማሪዎች እንቅስቃሴ ዉስጥ የነበሩ: ኢህአፓ ዉስጥ የነበሩ ምርጥ
የአመራር ብቃት ያላቸዉን እያደነች ስታጠፋና ስታስጠፋ ነበር::
በተለይም ደግሞ ወደ ስልጣን ከመጣች ብኋላ ይሄንኑ የማይነቃነቅ
የዘላለም መርኋን ተግባራዊ ማድራጓን አስፋፍታ ቀጥላበታለች::
በጀግንነት እና በወኔ ፊት ለፊት ወጥረዉ የያዟት የፕሮፌሰር አስራት
እርምጃ ለወያኔ ያሳያት ነገር ቢኖር ገና ብዙ መሪ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎች
ህዝቡ እናዳለዉ ነበርና ፕሮፌሰር አስራት : የመጀመሪያዉ ሰለባ
ተደረጉ::
ከዚያ ብኋላ ማህበረሰቡ በምንም ዘርፍ የሚያምናቸዉና መሪ የሚሆኑ
ሰዎች እንዳይወጡ ግለሰቦችን እራስ እራሳቸዉን መቀጥቀጥ:
ማደናበር: መወንጀል: መክሰስ: ማሰር: መግደል እና ብሎም መጨረሻ
ፓርቲያቸዉን ማስፍረስ ዋና ስራዋ አድርጋ ቀጥላበታለች:: ጋዜጠኛ
የለም: ምሁር የለም: የፓርቲ መሪዎች የሉም: የሰበአዊ መብት ተሟጋች
የለም: የሀገር ሽማግሌ የለም: ባለሀብት የለም ወያኔ ሁሉንም የመሪነት
አቅም ያላቸዉን ወይም ሊኖራቸዉ ይችላል የተባሉትን መጀመሪያ
በፕሮፖጋንዳ እና በማጥላላት ቀጥላ ደግሞ በማያወላዉል እርምጃ
ከምድረ ገጽ ታጠፋቸዋለች::
ኢንጂነር ይልቃል የተዋጣለት የፖለቲካ ሰዉ መሆኑን ቁጭ ብዬ
ካወራሁት ብኋላ ተረድቸዋለሁ:: ሰማያዊን : አንድነትን እና መኢአድን
በአንድ አምጥቶ ምርጫ 2007 ዓም የዲሞክራሲ ፋና ማብሪያ
ለማድረግ እጅግ ጉጉት የነበረዉ ፖለቲከኛ ነበር:: ይሄን ሁሉ
ያስተዋልኩት እነዚህን ሶስት ፓርቲዎች በአንድ ላይ በማምጣት የ2007
ዓም ምርጫን ታምራዊ ለማድረግ የሶስቱንም ፓርቲ መሪዎች (ኢንጅነር
ይልቃልን: ኢንጅነር ግዛቸዉን እና አቶ ማሙሸትን) በተናጠል እና በጋራ
በማነጋገር እርስ በርሳቸዉም በጥልቀት እንዲነጋገሩ ማድረግ ከቻልኩ
ብኋላ ነበር:: እነዚህ ሶስት ፖለቲከኞች ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ምን
ያህን ቀናኢ እንደሆኑ ዉስጣቸዉን እያነበብኩ በተቃራኒዉ ደግሞ እነሱ
የሚታገሉለት ህዝብ ምን ያህል እንደተረዳቸዉም በአርምሞ
የማንሰላስልበት ጊዜን በደንብ አግኝቼ ነበር:: የይልቃልን የማቻቻል :
ሌሎችን የማድመጥ እና ተቃዋሚዎችን አንድ ላይ አሰባስቦ ለመታገል
ያለዉ ቅንነት እና የመሪነት ብቃት ያለዉ ፖለቲከኛ መሆኑን ያስተዋልኩ
እለት ወያኔ አንድ ቀን በዚህ ጀግና ላይ ጣቷን እንደምታነሳ ገምቼ ነበር::
ግምቴ ብዙም ዉሎም አላደረም ኢንጅነር ይልቃል ላይ ከፍተኛ
የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ወያኔ ከፈተች:: እናም አንዳንድ ሰዎችም ስለዚህ
ጀግና ሳያዉቁ የወያኔ የድብቅ ሰራዊት በማህበራዊ ሚዲያዉ እና በልዩ
ልዩ ሚዲያዎች የሚያናስፈዉን ወሬ እንደ ቁም ነገር ተከትለዉ አብረዉ
ይሄን ጀግና መሪ ማጣጣል ያዙ:: መሪ ማግኘት እንዲህ ቀላል ነገር
እንዳልሆነ ለመረዳት በጣም የተቸገረ ማህበረሰብ የኛ ማህበረሰብ
ነዉ:: አንድ መሪ ከማህበረሰቡ ዉስጥ ሲከስም ሌላ የሱ አይነት መሪ
ለማዉጣት ስንት ጊዜ እንደሚፈጅ የተረዳ ማህበረሰብ ሁሉንም
መሪዎቹን ነቅቶ ይጠብቃቸዋል:: ይከላከልላቸዋል:: የኛ ማህበረሰብ ግን
ስለ እሱ ዲሞክራሲ እና መብት የሚታገሉ መሪዎች ሲታሙ አብሮ ያማል
ወይም ደግሞ አንባገነኖች ሲያጣጥሏቸዉ አብሮ ያጣጥላል::
በመሪዎች ላይ የሚሸረቡ ደባዎችን ከመመርመር ይልቅ “አንተ እንዲህ
ተባለ እኮ እያለ” የሚናፈሱ አሉባልታዎችን አብሮ ያናፍሳቸዋል::
በተለይም በቅርቡ እንጂነር ይልቃል ከዶክተር መራራ ጋር በመተባበር
ሰማያዊን እና ኦብኮን በማጣመር ለኢትዮጵያ ህዝብ የዲሞክራሲ ጥያቄ
እንደሚታገሉ ሲያበስሩ ወያኔዎች እንዲህ የገዘፈ የፖለቲካ እርምጃ
ለማምጣት የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞችን እና መሪዎችን ቶሎ ብለዉ
ከህዝብ አይን እንደሚያስወግዷቸዉ በደንብ ገምቼ ነበር:: ሆኖም
የወያኔ የጥቃት ጦር ኢንጅነር ይልቃል ላይ እንዲህ በፍጥነት
ይስፈነጠራል ብዬ ግን አላሰብኩም ነበር::
ኢትዮጵያኖች በደንብ አስተዉሉ:: የወያኔ ዋና ግቧ እንደ ኢንጂነር
ይልቃል አይነት ደፋር ሰዎች በማህበረሰቡ ዉስጥ እንዳይኖሩ ብሎም
ማህበረሰቡ መሪ አልባ እንዲሆን ነዉ:: አሁን ወያኔ በኢንጂነር ይልቃል
ላይ የወሰደችዉ እርምጃ ሰማያዊ ፓርቲን ያለ መሪ ማስቀረት ብቻ
ሳይሆን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ እመሃከሉ አንድም መሪ እንዳይኖር
ለማድረግ ነዉ:: ህዝብ ያለመሪ መንቀሳቀስ አይችልም:: ህዝብ ዝርዉ
ነዉ:: ደፋር መሪዎች እና መንገድ የሚያሳዩት ያስፈልጉታል::እናም
አንድን ህዝብ ለዘላለም ለመግዛት እና ባሪያ ለማድረግ ከተፈለግ
የመጀመሪያዉ እርምጃ መሆን ያለበት ህዝቡን ያለመሪ ማስቀረት ነዉ::
እህዝቡ መሃል የሚመላለሱ: ህዝቡ በአይኑ የሚያያቸዉ ደፋር መሪዎች
እንዳይኖሩ ማድረግ ነዉ የወያኔ ዋና ግብ::
በዚህ ረገድ እንደ ወያኔ የተሳካለት የለም:: ኢንጂነር ይልቃልን አሁን
ከፓርቲዉ ማባረር ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ህዝብ አይን እንዲሰወር እና
ህዝቡም መሪ እንዳይኖረዉ ለማድረግ ወያኔ በርካታ ጠመዝማዛ
መንገዶችን እየተከተለች ነዉ:: ተንኮልና ሸሯም ይቀጥላል::
መጀመሪያ ፓርቲዉን በአሉባልታ እና በብዙ ችግር እንዲናጥ ሲያደርጉ
ቆይተዉ አሁን ደግሞ ይሄዉ መሪዉን ከፓርቲዉ እንዲባረር
አድርገዉታል::
አንድነትን በቁጥጥራቸዉ ስር አድርገዉታል:: መኢአድን በቁጥጥራቸዉ
ስራ አድርገዉታል:: ሰማያዊንም እንዲሁ በቁጥጥራቸዉ ስር አደረጉ
ማለት ነዉ::
ያለ ማንም ተወዳዳሪ ጠቅላላ ጉባኤ በሙሉ ድምጽ የሚመርጣቸዉን
መሪዎች ወያኔዎች በጓዳ እየገቡ ፓርቲያቸዉንም ይነጥቋቸዋል ብሎም
ከህዝብ አይን መሪ እንዳይኖር በርካታ ደባዎችን ይፈጽማሉ:: የኢትዮጵያ
ሰዉ በጥንቃቄ ማስተዋል ያለበት የዚህ ሁሉ ዋናዉ ግቡ ህዝቡን ያለ
መሪ ለማስቀረት ነዉ::