በደቡብ ኦሞ የኦህዲኅ መሪ አቶ ዓለማዬሁ መኮንንና አንድ ጠንካራ አባል ታሰሩ – ግርማ በቀለ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት ም/ሊቀመንበርና የዞኑ ጽ/ቤት ቤት ኃላፊ አቶ ዓለማዬሁ መኮንንና በንቁ የፖለቲካ ተሳትፎው የሚታወቀው አባል አቶ አብረሃም ብዙነህ በጂንካ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙ ተረጋግጧል፡፡ እስራቱ የተፈጸመው መጋቢት 17 ቀን 2008 ዓ.ም ቤታቸው ከማለዳው 12 ሰዓት እስከረፋዱ 4፡20 ከተፈተሸ በኋላ እንደሆነ ከስፍራው በቀጥታ መረጃውን ያደረሱን ምንጮች እንደገለጹት ከአቶ ዓለማዬሁ ቤት ከዞኑ የተለያዩ መረጃዎችን የሚመጡ መረጃዎችን የሚመዘግቡበት ማስታወሻ፣የራሳቸውና የባለቤታቸው የእጅ/ሞባይል ስልኮች የተወሰዱባቸው ሲሆን ከአቶ አብረሃምም የእጅ ስልካቸው ተወስዷል፡፡
የድርጅታችን አመራሮች አቶ ኢንዲሪስ መናንና አቶ ዳዊት ካብትይመር በቦታው ፣እንዲሁም የአቶ ዓለማዬሁ ወንድም አቶ በዛብህ መኮንን በፍተሸው ቦታ ተገኝተው የተመለከቱትን ሲያስረዱ በአቶ ዓለማዬሁ ቤት ብቻ ሰባት የታጠቁ የከተማው ፖሊሶች ለፍተሻ በሚል መገኘታቸው የተያዦችን ቤተሰብና የአካባቢውን ነዋሪ እንዳሸበረ መመልከታቸውን አስረድተው በሰላም አገር ይህን ማድረግ ህዝብን ከማሸማቀቅና ማሸበር ሌላ ትርጉም ሊኖረው አይችልም፣ ይህም የገዢውን ፓርቲ የቆቅ /ሚዳቋ ህይወት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
እነዚሁ የመረጃ ምንጮች እንደገለጹት የከተማውን ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ታሳሪዎቹ በዕለት ሁኔታ መዝገብ ሳይመዘገቡና ወደ እስር ክፍል ሳይወሰዱ በግቢው ውስጥ መቀመጥ ማለት ምን የህግ ትርጉም አለው… ብለው ለጠየቁት መልስ መስጠት የተቸገሩት አዛዡ –እስካሁን እኛ እስረኛ አንላቸውም፣ ተጠርጣሪ ለማለትም ስላልተመዘገቡ እንቸገራለን፣ ንጹህ ናቸው ማለትም አይደለም፤ ለጥያቄ ጉዳይ የፈለጋቸው አካል ሲመጣ ይለያል በማለት የመለሱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እኚህ ፖሊስ አዛዥ ከዚህ በፊት አቶ አብርሃም በተመሳሳይ በታሰሩበት ጊዜ እህድ ቀን እንዲፈቱ ያደረጉ መሆናቸውን አስታውሰው በተቃራኒው ደግሞ አቶ ዓለማዬሁ መኮንን ‹‹ነጻነት በሌለበት ፍትህ የለም ፣ፍትህ በሌለበት ነጻነት የለም›› ብለሃል በሚል በታሰሩበት ጊዜ የዞኑ ፖሊስ አዛዥ እንዲፈቱ ቢነግሯቸውም ለመፍታት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ራሳቸው መጥተው እንዳስፈቷቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡
እነ አቶ ዓለማዬሁ በዕለት ሁኔታ ሳንመዘገብና የተያዝንበትን ጉዳይ ሳናውቅ በፖሊስ ጣቢያው ግቢ መቆየት አንችልም፣ አንፈቅድም፣ህጋዊ ባለመሆኑ ህገወጥነትን አንተባበርም በማለታቸው ወደ ወንጀል ምርመራ ክፍል እንዳስገቧቸው ይህ እየተዘጋጀ ባለበት ተጨማሪ መረጃ ደርሶናል፡፡
እነዚህ አባላት ከዚህ በፊት አቶ ዓለማየሁ የካቲት 15/08 እንዲሁም አቶ አብረሃም መጋቢት 03/08 ታስረው እንደነበርና ያለምንም መረጃና ማስረጃ መታሰራቸው ሳያንስ እያንዳናዳቸው የ 800 ብር ዋስ ጠርተው መለቀቃቸው ይታወሳል ፡፡
አቶ ዓለማዬሁ መኮንን የዞኑን ተጨባጭ ሁኔታ እና በአገሪቱ አጠቃላይ ፖለቲካ ግልጽ መረጃና ትንታኔ በተደጋጋሚ በኢሳት የሚያቀርቡ ቆራጥ ታጋይ መሆናቸው ፣‹‹ደቡብ ኦሞ ዞን›› ደግሞ በስኳር ልማት ስም ዜጎች ያለጥናትና ፈቃዳቸው የሚፈናቀሉበት ፣ በኢንቨስትመንት ስም የህወኃት ሰዎችን የመሬት ቅርምት የምታስተናግድ በነዋሪዎቿ ‹‹የመከራ ምድር›› በሚል የምትጠራ ደረጃ የደረሰች፣ ድሃ ግን በተፈጥሮ የታደለች የጀግኖች ምድር መሆኗ ይታወቃል፡፡
በተመሳሳይ አቶ ስለሺ ጌታቸው የሚባሉ የከተማዋ ነዋሪ በዛሬው ቀን ቤታቸው ተፈትሾ እንደታሰሩ ምንጮች የገለጹ ሲሆን፣ ሌሎች ዛሬ ረፋድ ላይ አቶ ስለሺን ከፖሊሶች ጋር ‹‹ሊሊ ግሮሰሪ›› አይተናቸዋል ብለዋል፡፡
ግን እስከ መቼ መርዶ ነጋሪ የጅብ ባል ሆነን እንዘልቃለን፣ ከዚህ ሁሉ ነጻ ለመውጣት እያንዳንዳችንና ሁላችን ለነጻነታችንና መብታችን በቆራጥነትና በጽናት በኅብረት እንቁም መልዕክታችን ነው፡፡ በቸር ያገናኘን፡፡