- በሕመምተኛ ልጁ ሕክምና ስም በርካታ አጥቢያዎች በ፻ሺሕዎች እያወጡ በሰጡበት ኹኔታ፥ “እኔ ሳላውቅ ስሜን ለማስጠፋት የተሠራ ነው” በሚል ምዝበራውን ለማስተባበል እየጣረ ነው
- ግማሽ ሚሊዮን ብር እንዲሰጠው የተወሰነበት የእንጦጦ ኪዳነ ምሕረት አስተዳደር ኮሚቴ ውሳኔ ቃለ ጉባኤ፣ በአስተዳደራዊ ውሳኔ ተሽሮ ውሳኔውን በሚያስተባብል ሌላ ቃለ ጉባኤው እንዲቀየር ሓላፊዎቹን አስገድዶ ነበር
- “ድጋፉን የሰጠነው ተዋቅሮ በተላከ ኮሚቴ በተጠየቅነው መሠረት ነው፤” ያሉት ዐሥር የገዳሙ አስተዳደር ኮሚቴ አባላት ትእዛዙን ባለመቀበላቸው በየማነ ከሥራና ከደመወዝ ታግደው ነበር
- የእገዳ ርምጃውንና አጠቃላይ ኹኔታውን ከገዳሙ ሓላፊዎች ያዳመጡት ፓትርያርኩ፥ “እርሱ ቀንደኛ ሌባ ነው፤ እናንተም ሌቦች ናችኹ” ሲሉ ገሥጸው ጉዳዩ በአስቸኳይ እንዲጣራ አዘዋል
- በሥራ አስኪያጅነት ሥልጣኑ አጥቢያዎችን በማስፈራራት ከብር 3 ሚሊዮን በላይ የሰበሰቡለት አማሳኝ አጋሮቹ፥ “እርሱ አያውቅም፤ ከግል ገንዘባችን ነው የረዳነው” በሚል ራሳቸውን ከተጠያቂነት ለማዳንና ምዝበራውን ለማስተባበል ልዩ ጽ/ቤታቸውን ደጅ እየጠኑለት ነው
- “እገሌንና የእገሌን ልጅ አሳክመናል፤ ከኪሳችን እንጂ ከሙዳየ ምጽዋት አልነካንም፤” የሚሉት አማሳኞቹ፥ “የቅዱስነታቸውን አእምሮ እንቀይራለን” በሚል ጉዳዩን ለማዳፈን ይንቀሳቀሳሉ
* * *
(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፮ ቁጥር ፰፻፵፭፤ ቅዳሜ መጋቢት ፲፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም.)(ቃለ ጉባኤውን ከዜናው በታች ይመልከቱ)
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ ለልጃቸው ሕክምና የገንዘብ ርዳታ የወሰኑላቸውን የእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ዐሥር የአስተዳደር ኮሚቴ አባላትን ከሥራና ከደሞዝ ያገዱ ቢኾንም ፓትርያርኩ እግዱን ሽረውታል፡፡
ሥራ አስኪያጁ፣ “ለታማሚ ልጃቸው ማሳከሚያ” በሚል ገንዘብ በማሰባሰብ ላይ እንደነበሩ መዘገቡ የሚታወስ ሲኾን፤ ከእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ብቻ ግማሽ ሚሊዮን ብር በገዳሙ አስተዳደር ኮሚቴ እንዲሰጣቸው ቢወሰንም፤ የገዳሙ ሒሳብ ሹም ክፍያውን አልፈጽምም በማለታቸው ውዝግብ ተፈጥሮ እንደነበር ይታወቃል፡፡
በሥራ አስኪያጁ እግድ ተላልፎባቸው የነበሩት የአስተዳደር ኮሚቴ አባላት፣ ሥራ አስኪያጁ ከትላንት በስቲያ፣ መጋቢት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በጽ/ቤታቸው ጠርተዋቸው፣ “ስሜን ለማስጠፋት እኔ ሳላዛችኹ ኾን ብላችሁ የሠራችኹት ነው፤” በሚል ግማሽ ሚሊዮን ብር ለመስጠት የወሰኑበትን ቃለ ጉባኤ ውሳኔውን በሚያስተባብል አስተዳደራዊ ውሳኔ ሽረው ቃለ ጉባኤን እንዲቀየሩ እንዳዘዟቸው ይናገራሉ፡፡
በሥራ አስኪያጁ ዕውቅና ተዋቅረው ከተላኩት የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴዎቹ ሦስቱ መጥተው በጠየቁት መሠረት መኾኑን በመጥቀስ በተለይ የገዳሙ አለቃ በስተርጅና እንደማይዋሹና ኹለት ቃል እንደማይናገሩ በማስረዳት፣ የሥራ አስኪያጁን፥ “ውሳኔያችኹን በውሳኔ አስተባብሉ’’ ትእዛዝ ባለመቀበላቸው፤ “በስሜ አጨብርብራችኋዋል፤ እኔ ይሰጠኝ ብዬ አላዘዝኩም፤ ሒሳብ ሹሟ ክፍያውን አልፈጽምም ማለታቸው ትክክል ናቸው፤ ልታግዷቸው አይገባም ነበር፤” በማለት ኹሉንንም ከሥራና ከደመወዝ ማገዳቸውን እንዳሳወቋቸው ገልጸዋል፡፡
“ሥራ አስኪያጁ እገዳውን ካስተላለፉብን በኋላ የታገድንበትን ደብዳቤና የገንዘብ ድጋፉን የወሰንበትን ቃለ ጉባኤ ይዘን ቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር በመግባት አስረዳናቸው፤” ያሉት የአስተዳደር ኮሚቴው አባላት፣ የገንዘብ ድጋፉን ስለሰጡበት ኹኔታና ስለ እግዱ የሚከተለውን ብለዋል፡-
“የሲ.ኤም.ሲ ቅዱስ ሚካኤል አለቃ፣ የሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም እና የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ጸሐፊዎች መጥተው አዋጡ አሉን፤ ባናዋጣ እንደምንባረር ዛቱብን፤ ትባረራላችሁ፣ ርምጃ እንወስድባችኋለን ሲሉን እኛ ምን እናድርግ? ወደን አይደለም፤ ከሥራችን እንባረራለን፤ ከደረጃችን እንወርዳለን፤ ማን የሚሰማን አለ? ሰበብ ፈጥሮ ነው የሚያግደን፤ ፍትሕ የሚሰጠን አጥተን ነው ይህን ያደረግነው፤ ሒሳብ ሹሟን፥ እነርሱን አግጄ ወደ ሥራ እመልስሻለሁ ብሎ በማለሳሰለስ እኛን ኹላችንን አገደን፡፡”
ፓትርያርኩ፣ “ገንዘቡ በትክክል ወጥቷል ወይ?” ብለው የጠየቋቸው ሲኾን እነርሱም፥ “አዎ፣ አሰባሳቢ ኮሚቴዎች መጡ፤ አግዙን ብለው ጠየቁን፤ እንዲሰጥ ተፈራርመን ወሰንን፤ እኛ ማወራረድ ስላለብን ቸግሮን በቃለ ጉባኤ ተፈራርመን ሰጠነው እንጂ ሌሎቹ አጥቢያዎች በእጁ አይደለም ወይ ያለሰነድ የሰጡት፤” በማለት ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡
አቤቱታውን ያዳመጡት ፓትርያርኩ፤ የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅና የገንዘብ ርዳታ የወሰኑትን አቤቱታ አቅራቢዎች፣ “እርሱ ቀንደኛ ሌባ ነው፤ እናንተም ሌቦች ናችሁ፤ እኔ ታምሜአለሁ ብላችሁ 500 ሺሕ አውጥታችሁ ልትሰጡኝ ነው ወይ? ገመናችሁ ባይወጣ ስትሞካከሹ ትኖሩ ነበር፤” በማለት መገሠጻቸው ተነግሯል፡፡
እገዳውን በተመለከተም፣ “ማን ላይ ነው ጨዋታ የሚጫወተው፤ እርሱ ንጹሕ መስሎ እናንተን ሕግ ተላላፊ ለማድረግ አይችልም፤” በማለት በአስቸኳይ እገዳው ተነሥቶላቸው ወደ ሥራቸው እንዲመለሱና ጉዳዩም እንዲጣራ በልዩ ጽ/ቤታቸው በኩል ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ ትእዛዝ መስጠታቸው ታውቋል፡፡
ጉዳዩ የብዙዎች መነጋገርያ ከመኾን አልፎ በፓትርያርኩ ተግሣጽና ውሳኔ ክፉኛ መረበሹ የተነገረለት የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ ባለፈው ቅዳሜ ረፋድ አማሳኝ አጋሮቹን በሀገረ ስብከቱ አዳራሽ በመጥራት፣ እርሱ ሳያውቅ ከየግላቸው እንደተሰበሰበና የአጥቢያዎቹ ገንዘብ እንዳልተነካ በማስመሰል የሚያስረዱ አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ ወደ ፓትርያርኩ መላኩ ተገልጿል፡፡
“እኛ የኃይሌን[ኃይሌ ኣብርሃ] ልጅ ሌላም አሳክመናል፤ ግን ከራሳችን ከግል ገንዘብ ነው፤ ለእርሱም ያደረግነው ይኼን ነው፤ እርሱ ግን አያውቅም፤” በማለት፣ ሕጋዊነት ሳይኖራቸው ቁጥጥር የማይደረግበትን ገንዘብ በሕክምና ድጋፍ ስም በማሰባሰባቸው ከሚከተላቸው ተጠያቂነት ራሳቸውን ለማዳንና ሥራ አስኪያጁም በሚሊዮኖች የመዘበረበትን አካሔድ ለማስተባበል የፓትርያርኩን ልዩ ጽ/ቤት ደጅ በመጥናት ላይ መኾናቸው ተመልክቷል፡፡ “ከኪሳችን የመርዳት ልምድ ስላለን ቅዱስነታቸውን አግኝተን አእምሯቸውንና አመለካከታቸውን ማስተካከል አለብን፤” በሚል ተግሣጻቸውን ለመመለስና ለመቀየር ማቀዳቸው ታውቋል፡፡
ከአሰባሳቢ ኮሚቴው አባላት፡- የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የሲ.ኤም.ሲ ቅዱስ ሚካኤል፣ የመካኒሳ ቅዱስ ሚካኤል፣ የሳሪስ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ የጀሞ ቅድስት ሥላሴ፣ የገርጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የጻድቁ አቡነ አረጋዊና ገብረ ክርስቶስ፣ የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ አለቆች፤ የሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም አለቃና ጸሐፊ፤ የብሔረ ጽጌ ቅድስት ማርያም አለቃና ሒሳብ ሹም፤ የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል አለቃና ተቆጣጣሪ፤ የብሥራተ ገብርኤል ጸሐፊና ሒሳብ ሹም፤ የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም፣ የጽርሐ አርያም ቅዱስ ሩፋኤልና የደብረ አሚን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጸሐፊዎች ይገኙበታል፡፡
* * *

የሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ገዳም አስተዳደር ኮሚቴ የስብሰባ ቃለ ጉባኤ
የስብሰባ ቀን፡- 25/06/2008 ዓ.ም.
የስብሰባ ቦታ፡- በገዳሙ አስተዳደር ቢሮ
የስብሰባ ሰዓት፡- ከቀኑ 3፡00 ጀምሮ
ተሰብሳቢ አባላት፤
- ክቡር ሊቀ ሊቃውንት ቆሞስ አባ ገብረ ማርያም ገብረ መስቀል – የገዳሙ አስተዳዳሪና የጉባኤው ዋና ሰብሳቢ
- ክቡር በኵረ ትጉሃን ቆሞስ አባ ገብረ ማርያም ገብረ እግዚአብሔር – የገዳሙ ምክትል አስተዳዳሪና የጉባኤው ምክትል ሰብሳቢ
- መልአከ ፀሐይ አባ ቀለመ ወርቅ አዳሙ – የገዳሙ አስተዳደር ኮሚቴ አባል – የጉባኤው አባል
- መ/ር አባ ማቴዎስ ከፍያለው – የገዳሙ አስተዳዳር ኮሚቴ አባል – የጉባኤው አባል
- አባ ገብረ ትንሣኤ ብሬ – የገዳሙ አስተዳደር ኮሚቴ አባል – የጉባኤው አባል
- ሊቀ ጠበብት ተከሥተ ብርሃኑ – የገዳሙ አስተዳደር ጉባኤ አባል – የጉባኤው አባል
- መሪጌታ ፍሬ ስብሐት አለነ – የገዳሙ አስተዳደር ጉባኤ አባል – የጉባኤው አባል
- መሪጌታ አክሎግ ደሴ – የገዳሙ አስተዳደር ጉባኤ አባል – የጉባኤው አባል
- መዘምር አብርሃም አንዳርጌ – የገዳሙ አስተዳደር ኮሚቴ አባል – የጉባኤው አባል
- ቀሲስ ዘነበ ብርሃኑ – የገዳሙ ዋና ጸሐፊ – የገዳሙ ጸሐፊ ኾነው በተገኙበት ስብሰባ ተደርጓል፡፡
የዕለቱ ጉባኤ በጸሎት ተከፈተ፡፡ የዕለቱን ስብሰባ አጀንዳ ክቡር ሊቀ ሊቃውንት ቆሞስ አባ ገብረ ማርያም ገብረ መስቀል የገዳሙ አስተዳዳሪና የጉባኤውም ሰብሳቢ ለጉባኤው አባላት ሲያስረዱ፤ ክቡር ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ልጃቸውን ለማሳከም ይችሉ ዘንድ ቀደም ሲል ለዚኽ ዓላማ የተዋቀሩ ኮሚቴዎች መጥተው ድጋፍ እንድናደርግ ጠይቀውን ሳለ እስከ አኹን በኛ በኩል የአዎንታም ኾነ የአሉታ መልስ ያልሰጠን ሲኾን ሌሎች ገዳማትና አድባራት ግን ቀድመውን ለዚኽ ዓላማ የተቻላቸውን የሰጡ ስለኾነ እኛም ይህንኑ መሠረት አድርገን ከሌሎች ገዳማትና አድባራት መለየት የሌለብን በመኾኑ በዚኽ ዙሪያ በጋራ ተመካክረን የተቻለንን ድጋፍ ለክቡር ሥራ አስኪያጅ ለልጃቸው ማሳከሚያ የሚውል ድጋፍ ማድረግ በምንችልበት ዙሪያ በጋራ መክረን አንድ ውሳኔ ላይ መድረስ እንድንችል የተደረገ ስብሰባ ነው፤ ሲሉ ሰብሳቢው ለጉባኤው አባላት በማስረዳት ጉባኤያቸውን አጠቃለዋል፡፡
የጉባኤው አባላትም ከክቡር ሰብሳቢው የተሰጠውን አጀንዳ ገለጻ በጽሞና ከማድመጥ በመነሣት በመሠረተ ሐሳቡ ዙሪያ ጉባኤው ሲመክር፣ አኹን ላይ የቀረበው አጀንዳ ተገቢነት ያለው መኾኑ ቢታመንም ከተጠየቀበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አኹን መዘግየቱ ተገቢ አለመኾኑን ጉባኤው የተቸ ሲኾን ያም ኾነ ይህ አነሰ በዛ የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ በወቅቱ ይደረግ እንኳ ቢባል በሰዎች እጅ መላኩ ጥርጣሬ ውስጥ በመገባቱ የተነሣ ነገ ዛሬ ሲባል ሊዘገይ እንደቻለ የጋራ ግንዛቤ ተወስዶ ያም ኾነ ይህ አኹንም ቢኾን ድጋፍ ካደረጉ ከሌሎች ገዳማትና አድባራት እኛ መዘግየታችን ቢታመንም ድጋፍ ማድረጉ የረፈደ ስለማያሰኝ የገዳማችን ታላቅነት ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ታይቶ ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅ በጉባኤው አጠያያቂ ኾኖ አልተገኘም፡፡
ስለኾነም ለዚኽ ለተቀደሰ በጎ ዓላማ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ የተገባ መኾኑ ታምኖ ለክቡር ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ለታማሚ ልጃቸው ማሳከሚያ ይረዳቸው ዘንድ ዓላማውም የሰውን ፍጡር የማዳን በጎ ምግባር ስለኾነ ከገዳሙ ገቢ ላይ ብር 500‚000(አምስት መቶ ሺሕ) ወጪ እንዲመደብ ኾኖ ከዚኹ ውስጥ ብር 300‚000(ሦስት መቶ ሺሕ) በገዳሙ ስም፤ ቀሪው ብር 200‚000(ኹለት መቶ ሺሕ ብር) ደግሞ በገዳሙ ሠራተኞች ስም ተሰይሞ ለክቡር ሥራ አስኪያጅ በክቡር ሊቀ ሊቃውንት ቆሞስ አባ ገብረ ማርያም ገብረ መስቀል የገዳሙ ዋና አስተዳዳሪና የጉባኤው ሰብሳቢ እጅ እንዲያደርሱ ሲል ጉባኤው ሙሉ ሓላፊነት በመስጠት ልዩነት በሌለው ድምፅ ወስኖ የዕለቱን ስብሰባ 4፡30 ሰዓት በጸሎት ዘግቶ ፈጽሞ ተነሣ፡፡
የዋና እና የምክትል ሰብሳቢውን ጨምሮ የዐሥር የአስተዳደር ኮሚቴው አባላት የማይነበብ ፊርማ አለው