- ዋሊያዎቹ ከብዙ መንገላታት በኋላ አልጀርስ ገቡ!
ዘገባ – ናታ
በጋቦን አስተናጋጅነት ለሚካሔደው የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ “J” ከአልጄሪያ፣ ሌሴቶ እና ሲሺየልስ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ አልጀርስ አቅንቷል። ሁለቱ ቡድኖች ቀዳሚውን ጫወታቸውን ዐርብ ቀን አልጀርስ ላይ ሲያደርጉ የመልሱን ደግሞ ከአራት ቀናት በኋላ አዲስ አበባ ላይ እንደሚያደርጉ የውድድሩ መርሃግብር የጊዜ ሰሌዳ አመላክቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋሊያዎቹ ከቀያይ ቀበሮዎቹን ለመግጠም የተደረገው የተጫዋቾች ምርጫ ላይ አያሌ ሕጸጾች ተፈጽመዋል። ለተከላካዩ ዋሊድ አታ የተደረገው ጥሪ የተሳሳሳተ በመሆኑ ቡድኑን ዋጋ አስከፍሏል። አሁንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሰራር ያለሙያተኛ መቀጠሉን ተያይዞታል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በውጭ ሀገር ለሚገኙ ተጫዋቾች ጥሪ ሲያደርግ በስዊድን ለሚገኘው ተከላካዩ ዋሊድ አታ ያደረገው ጥሪ የተሳሳተ ነበር። ይኸውም ፌዴሬሽኑ የጥሪ ደብዳቤውን በኢሜይል የላከው ለዋሊድ የቀድሞ ክለብ ለቱርኩ ጌንሥቤርሊ ነበር። አሁን በስዊድኑ አስተርስትንድ ክለብ የሚገኘው ዋሊድ ለብሔራዊ ቡድን ለመጫወት ፍላጎት ስላለው ከኢትዮጵያ ጥሪ ይደረግልኛል ብሎ ቢጠብቅም የደረሰው መልዕክት አልነበረም። በዚህም የተነሳ ብሔራዊ ቡድኑ ለአልጄሪያው ጨዋታ በሚያደርገው ዝግጅት ላይ ሳይገኝ ቀርቷል።
ወሊድን ጨምሮ ልምድ ያላቸው ሳላዲን ባርጌቾና ሳለዲን ሰኢድ በጉዳት ከቡድኑ ጋር አለመካተታቸው በውጤቱ ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚያስከትል ከወዲሁ አስቀድሞ ተገምቷል። አሰልጣኝ ዩሃንስ ሳህሌ ቡድኑ ትጥቅ በአግባቡ እንዳልተሟላለት የገለፁ ሲሆን የቡድን መሪውም ከአሰልጣኞች ጋር በጋራ መስራት ላይ ድክመት እንዳለበት ተነግሯል። እነዚህን ሁሉ አያሌ ችግሮች ታቅፈው በዳሸን ቢራው አማካኝ አስራት መገርሳ እየተመሩ አልጀሪያን ይገጥማሉ።
ብሔራዊ ቡድኑ ግብጽ ላይ ለስምንት ሰዓታት ትራኒዚት ያደረገ ሲሆን ምንም ዓይነት ማረፊያ ሳይዘጋጅለት በአግዳሚ ወንበሮችና ሻንጣቸውን ተንተርሰው ተጋድመዋል። በአልጀሪያም አስቀድመው ሆቴልና ማረፊያ ስላልተዘጋጀላቸው መንገላታታቸው ተዘግቧል። አንድ ብሐራዊ ቡድን የአገር ክብር ነው የደርሶ መልስ ቻርተር አውሮፕላን ለቡድኑ ተጫዋቾችና አባላት ሊዘጋጅላቸው ይገባ ነበር።
ፌደሬሽኑ እስፖንሰሮችን በማፈላለግ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር የጉዞ ቅድመ ዝግጅቶችን ማድረግ ይገባው ነበር። ይህ ባለመሆኑና በተለመደው የእግር ኳስ ማኅበሩ ዝርክርክ አሰራር ምክንያት ብሄራዊ ቡድኑ ለከፍተኛ እንግልትና ድካም ተጋልጠዋል።
መልካም ውጤት ለብሔርዊ እግርኳስ ቡድናችን ይሁን!