አሠቃቂ የመኪና አደጋዎች መንስኤዎች አከራካሪ ሆነዋል


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


Addis admass : የሾፌሮች ጥፋት ወይስ የመኪኖች ብልሽት? የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ መዝረክረኩስ?
በአዲስ አበባ ከሰሞኑ 24 ሰዎችን ለሞትና ለአካል ጉዳት የዳረጉ ሦስት አሰቃቂ የመኪና አደጋዎች ሳቢያ በሾፌሮች ብቃትና ስነ ምግባር እንዲሁም በመኪኖች የቴክኒክ ምርመራና በመንጃ ፍቃድ አሰጣጥ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች በርክተዋል፡፡

ባለፈው ሃሙስ ሰሚት አካባቢ የመንገድ አካፋይ ግንብ ደርምሶ በተገለበጠ ኢሮትራከር የጭነት መኪና፣ የ4 ወጣቶች ህይወት ተቀጥፏል፡፡ የተደረመሰው ግንብ፣ ባጃጅ መኪና ላይ በማረፉ ነው፣ ሹፌሩን ጨምሮ አራቱ ወጣቶች የሞቱት፡፡ ከሟቾች መካከል አንዷ፤ ህፃን ልጇን ከት/ቤት ለማምጣት እየተጓዘች የነበረች እናት ናት፡፡

ከፒያሣ ቁልቁል ወደ ቴዎድሮስ አደባባይ ይጓዝ በነበረ ሃይገር ባስ የደረሰው ጉዳትም ብዙ ነው፡፡ አካባቢውን የጦርነት ሜዳ አስመስሎታል፡፡ መንገድ የሚሻገር እግረኛን በመግጨት ነው የጀመረው። በፍጥነት ቁልቁል እየተንደረደረ ሌላ እግረኛ ከገጨ በኋላ፤ ወዲህና ወዲያ በየአቅጣጫው 6 መኪኖችን አተራምሷል። ከመብራት ምሰሶ ጋር ሲላተምም አልቆመም፡፡ የመኪናው ፍሬን፣ ሳይሆን፤ በመጨረሻ ቴዎድሮስ አደባባይ አጥር ጋር ተጋጭቶ ነው የቆመው፡፡ በአደጋው አንድ ሰው መሞቱንና 18 ሰዎች ያህሉ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው የትራፊክ ጽ/ቤት አረጋግጧል፡፡

ማክሰኞ ከሌሊቱ 8 ሰዓት ተኩል የደረሰው አደጋም ዘግናኝ እንደሆነ የገለፁት ም/ኢ/ር አሰፋ መዝገቡ፤ አደጋው የአልኮል መጠጥ መዘዝ መሆኑን ጠቂመዋል። አሽከርካሪው የጭነት አሸዋ መኪናውን አቁሞ ከሄደ በኋላ ነው፣ ረዳቱ በውድቅት ሌሊት መኪናውን አስነስቶ ወደ መጠጥ ቤቶች የዘመተው፡፡ በየመጠጥ ቤቱ አልኮል እየጠጣ ሲዞር ቆየ፡፡ መጨረሻው አላማረም፡፡ መሣለሚያ አካባቢ፣ ተኝቶ የነበረ የጐዳና ተዳዳሪ ላይ ወጣበት። የጭነት መኪናው ጎማ፣ የጎዳና ተዳዳሪው ጭንቅላት ላይ በመውጣት፣ መሬት ለመሬት ሲጎትተው ህይወቱ አልፏል፡፡
በየጊዜው ብዙ አሳዛኝ አደጋዎች እንደሚደርሱ ጠቅሰው፤ በዚህ ሁለት ሣምንት ውስጥ በህይወት ላይ የደረሱት አደጋዎች ግን በጣም ዘግናኝ ናቸው ብለዋል፤ ረ/ኢ አሰፋ፡፡  የዘግናኝ አደጋዎቹ መንስኤ፣ የአሽከርካሪዎች የብቃት ጉድለትና የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ብልሹነት ነው? ወይስ ቸልተኝነትና የስነ ምግባር እጦት? ወይስ የፍሬን ብልሽት የመሳሰሉ የመኪና የቴክኒክ ችግሮች?
“ለአደጋዎቹ አሽከርካሪዎቹ ተጠያቂ ናቸው” የሚሉት ረ/ኢ አሰፋ፤የተሽከርካሪን ቴክኒካዊ ብቃት ሳያረጋግጥ ጉዞ የሚጀምር አሽከርካሪ፣ የብቃትና የስነ ምግባር ጉድለት አለበት ብለዋል፡፡  አብዛኛው አደጋ በአሽከርካሪዎች ብቃት ማነስ ሳቢያ የሚከሰት እንደሆነ አምናለሁ የሚሉት አቶ ክፍሌ ሙላቱ፣ ከሃያ ዓመት በላይ በሾፌርነት እንደሰሩና “ሲኖ ትራክ” እንደሚያሽከረክሩ ተናግረዋል፡፡ ድሮ የከባድ መኪና መንጃ ፍቃድ ያገኘነው፤ በየደረጃው ከ2ኛ ደረጃ መንጃ ፈቃድ ጀምረን በቂ ልምድ በማካበት ነው ያሉት አቶ ክፍሌ፤ “አሁን ግን፣ እድሜው ሳይደርስ 18 አመቴ ነው እያለ አጭበርብሮ በአንዴ 4ኛ መንጃ ፍቃድ ሲያወጣ እናያለን ብለዋል፡፡
ሲኖትራክን እያሽከረከሩ ለ2 አመት መስራታቸውን አቶ ክፍሌ ገልፀው፣ “መኪናው በፍሬን በኩልም ሆነ ሌላ የቴክኒክ ጉድለት የለበትም ዋናው ችግር ያለው ከአሽከርካሪዎቹ ብቃት ላይ ነው ይላሉ፡፡
የከባድ መኪኖች መካኒክና አሽከርካሪ ደምስ ይልማ በዚህ ይስማማል፡፡ ሲኖትራክ ከሌሎች ተሽከርካሪዎች የተለየ የቴክኒክ ችግር የለበትም ይላል፡፡ ፍሬኑም ችግር የለበትም የሚለው ባለሙያው፤ ዛሬ አብዛኞቹ አሽከርካሪዎች ወጣት ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ ምክንት በቸልተኝነትና በአደንዛዥ ዕፅ ግፊት፣ ጥንቃቄ በጎደለው ፍጥነት የሚያሽከረክሩ መበራከታቸው ለአደጋ መንስኤ ሆኗል፡፡በመዲናዋ ለሚደርሱ አደጋዎች የመንጃ ፍቃድ አወጣጡ አስተዋጽኦ አበርክቷል የሚለው መላምት በጥናት ተፈትሾ መረጋገጥ እንዳለበት የሚገልፁት ም/ኢ አሰፋ መዝገቡ በበኩላቸው፤ ያለ ስልጠና በህገወጥ መንገድ፣ መንጃ ፍቃድ የሚያገኙ ሰዎች መኖራቸው አሣሣቢ ነው ብለዋል፡፡
የተሽከርካሪዎች ብቃት ምርመራና ማረጋገጫን በተመለከተ የተለያዩ የአሠራር ግድፈቶች እንዳሉ ይነገራል ያሉት ም/ኢ/ር አሰፋ፤ ይሄን ለመከላከል ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡