ያልተነገረው የራስ አሉላ ታሪክ – Achamyeleh Tamiru


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


Achamyeleh Tamiru   ያልተነገረው የራስ አሉላ ታሪክ

ዳግማዊ አጼ ምኒልክን በአገር ሻጭነት የሚወነጅሉ ድርሳናትን በማሳተም ረገድ የትግራይ ብሔርተኞችን የሚስተካከላቸው የለም። መረን የለቀቀው ይህ ጸረ-ምኒልክ ዘመቻቸው ዳግማዊ ምኒልክ በአለም መድረክ የተደነቁበትን የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ድል የሆነውን የአድዋ ድልም እስከማጥቆር ይዘልቃል።

የጸረ ምኒልክ ፕሮግራማቸው ዋነኛ አላማ በምኒልክ ታሪክ ግብዓተ መሬት ላይ እነሱ «የትግራይ ናቸው» የሚሏቸውን ሰዎች ታሪክ መጻፍ ነው። ይህ ፕሮግራማቸው ጊዜ በሰጣቸው ሀይል እየተስፈነጠረ «ታሪክን እንደገና መጸፍ አለብን» በሚለው የጋራ ፕሮጀክታቸው ታግዞ ከቃል በማለፍ «የአድዋ ድል በትግራይ ህዝብ ተጋድሎ የተገኘ ነው» በሚል «አዲስ ትርክት» ወደ ተግባር ተሸጋግሮ ተመልክተናል።

«አፍሪካዊ ጀኔራል» በሚል ስም ሁላችንም የምንጠራቸው ራስ አሉላ አባ ነጋ በትግራይ ብሔርተኞች ዘንድ የምኒልክን ክብር እንዲወርሱ ከታጩት የጦር መሪዎች መካከል ቀዳሚው ናቸው።

ራስ አሉላ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ አካካቢ የነበረው የፖለቲካ መንፈስ ውጤት ናቸው። በዘመናቸው ለኢትዮጵያ አገራቸውና ለትግራይ ህዝብ ክብር ሲሉ በጀግንነት ተጋድለዋል። እስከ ዛሬ ድረስ ስለራስ አሉላ ስንሰማ የኖርነው የበቃ የፖለቲካ ሰውነታቸውን ብቻ ነበር።

ሆኖም ግን ራስ አሉላ ከዘመኑ መንፈስ የመነጨ ጎደሎ ጎንም ነበራቸው። ምናልባት ይህንን ጎደሎ ጎናቸውን እስከዛሬ አልሰማነው ይሆናል። እኔ ዛሬ ይህንን ሰምተነው የማናውቀውን የራስ አሉላን ጎደሎ የማቀርበው የአሉላን ክብር ለማጉደል አይደለም። በፍጹም! አሉላ ኢትዮጵያዊ ጀግና ናቸው።

ሆኖም ግን ዛሬ አጼ ምኒልክን «በአገር ሻጭነትና በከሀዲነት» ተግባሮች ለሚከሷቸው የትግራይ ብሔርተኞች፤ «የአድዋን ድል መርተዋል» ብለው አዲስ ታሪክ የሚጽፉላቸው ራስ አሉላም በዘመናቸው ከአጼ ምኒልክ በላይ «በአገር ሻጭነትና በከሀዲነት» ጭቃ ውስጥ ሰጥመው እንደነበረ ማሳወቅ ያስፈልጋል።

Achamyeleh Tamiru's photo.

ይህንን ታሪክ የሚነግሩን እሥራኤላዊው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ሀጋይ ኤርሊክ ናቸው። የአሉላ አድናቂ እንደሆኑ የሚነገርላቸውና የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሀጋይ ኤርሊክ «Ras Alula and the Scramble for Africa: A Political Biography : Ethiopia & Eritrea 1875-1897» በሚል ርዕስ የራስ አሉላን ደብዳቤዎች ከጥሊያን ቤተ መዘክር ሰብስበው በጻፉት የታሪክ መጽሀፋቸው ውስጥ ራስ አሉላ ከጥሊያኖች ጋር «ምኒልክ እ.ኤ.አ. በ ግንቦት 2፥1889 አ.ም. ውጫሌ ላይ ከናንተ ጋር ተፈራርሞ ሊሰጣችሁ ከተስማማው መሬት በላይ የሚልቅ አገር እኔ ልስጣችሁ» ብለው ተስማምተው እንደነበር ዶሴዎችን በአስረጂነት በማቀረብ የራስ ኣሉላ ሌላ ገጽታ ያስነብቡናል።

በመጽሀፉ ላይ የሚገኘው ማስረጃ «ነጻ ትግራይን ለመመስረት» ጣሊያኖች የሚረዷቸው ከሆነ ራስ አሉላ ቀደም ብለው ያስተዳድሩት የነበረውን የመረብ ምላሽ ምድር [ የዛሬውን ኤርትራ] ሙሉ በሙሉ ለጥሊያን ለመስጠት ተስማምተው እንደነበር ይነግረናል ። ይህ ማለት ራስ አሉላ አባ ነጋ ምኒልክ በውጫሌ ውል ለጥሊያን አሳልፈው ለመስጠት ከተስማሙት መሬት የሚበልጥ አገር ለጥሊያን አሰልፈው ለመስጠት ዝግጁ ነበሩ ማለት ነው።

የአሉላ አድናቂው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ሀጋይ ኤርሊክ ይህንን ታሪክ ከታች በታተመው የመጽሀፋቸው ገጽ 164 ላይ ሲገልጹ፤

«The rebellious Alula urgently needed a practical alternative to Mengesha’s policy, and he thought in terms of Italian support for an autonomous Tigre. Ras Alula was prepared to give the Italians more than Menilek had given them in Wuchale; the whole of Marab Mellash, his previous one and only domain» ይሉናል።

በግርድፉ ይህ ሲተረጎም፤

« እምቢተኛው አሉላ ራስ መንገሻ የምኒልክን ንጉሰ ነገስትነት አምነው ለመቀበል ቁርጥ ማድረጋቸውን በሰሙ ጊዜ ወዲያውኑ ሊተገብሩት የሚችሉት አማራጭ ፖሊሲ ፍለጋ ገቡ፤ ነጻ የትግሬ መንግስትም ለማቆም ሻቱ፤ ለተፈጻሙነቱም የጣሊያንን ድጋፍ ፈለጉ። ለዚህ አግቦ ምላሽም ምኒልክ በውጫሌ ስምምነት ለጥሊያን እንዲሰጡ ከተገደደዱት መሬት የሚልቅ አገር ለጣልያን አሳልፈው ለመስጠት ዝግጁ ነበሩ፤ ይህ ራስ አሉላ ለጥሊያን አሳልፈው ሊሰጡ የተዘጋጁት መሬት አሉላ ራሳቸው በሕይወት ዘመናቸው እንዲያስተዳድሩ የተሾሙበት አንድና ብቸኛው ግዛታቸው የነበረችውን [በኋላ ኤርትራ የተባለችውን] መረብ ምላሽን ነው።»

እንግዲህ አጼ ምኒልክን «በአገር ሻጭነትና በከሀዲነት» ሲወነጅል የኖረ ሁሉ ዛሬም በቃሉ ጸንቶ ከአጼ ምኒልክ በላይ አገር አሳልፈው ሊሸጡ የተስማሙትን ራስ አሉላንም አንደበቱ ሳይታጠፍ ድምጹን ከፍ አድርጎ «ውግዝ ከመ አርዮስ አሉላ እንግዳ እቁቢ» ማለት አለበት።

የኔ እምነት ግን ወዲህ ነው። ራስ አሉላ ምንም እንኳ የውጫሌ ስምምነት ለጥሊያን እንዲሰጥ ከሚፈቅደው መሬት በላይ አሳልፈው መረብ ምላሽን በሙሉ ለጥሊያን ለመስጠት ከሁሉ አስቀድመው ተስማምተው የነበሩ ቢሆኑም፤ በዘመናቸው በቻሉት መጠን ላገራቸው ባደረጉት በጎ ተግባር ግን ለዘላለም በትውልድ ሁሉ ሲከበሩ ሊኖሩ ይገባል እላለሁ። የአጼ ምኒልክም ታሪክ መያዝ ያለበት በዚህ መንፈስ ነው። ከዚህ ውጭ አንዱን አጥቅቶ ለሌለኛው የመከላከል አካሄድ ዘረኝነት ብቻ ነው የሚሆነው።