ሚኒስትሩ የሚመሩትን መ/ቤት የመንግስት ሕንጻ ከነበረበት አስለቅቀው የራሳቸው የግል ሕንጻ እንዲከራይ አደረጉት::
[ሙስና እና ሽሙጥ = ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
– እየተከታተልክ ነው ለመሆኑ?
– ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
– ቴሌቪዥን ነዋ፡፡
– በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ምን አሰብክ ታዲያ?
– በጣም አስፈሪ ነገር ነው፡፡
– ምኑ ነው የሚያስፈራው?
– ትራምፕ ነዋ፡፡
– ትራኩ ነው ያልከኝ?
– የአሜሪካኑ ትራምፕ ነው ያስጨነቀኝ ስልዎት፡፡
– እኔ ደግሞ የዩሮ ትራኩ ጉዳይ ነው የሚያስጨንቀኝ፡፡
– እኔ እኮ ወሬ ብቻ ይመስለኝ ነበር፡፡
– ምኑ?
– ክቡር ሚኒስትሩ ዩሮ ትራከር አላቸው ሲባል፡፡
– ቢኖረኝ ምን ችግር አለው?
– ያው ከየት ያመጡታል ብዬ ነው?
– ከብዙ ቦታ ላመጣው እችላለሁ፡፡
– ለነገሩ እርስዎ ብዙ ቦታ እንዳለዎት አውቃለሁ፡፡
– ምን አልክ አንተ?
– ማለቴ ሊያመጡበት የሚችሉበት ብዙ አቅም አለዎት ብዬ ነው፡፡
– ዛሬ የፈለኩህ እንዴት አየኸው ልልህ ነው?
– ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
– የሰሞኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር፡፡
– በቴሌቪዥን ነዋ፡፡
– ቀልዱን ተውና ቁምነገሩን አስቀድም፡፡
– ሰው በጣም ተገርሟል ክቡር ሚኒስትር፡፡
– በምኑ ነው የተገረመው?
– ኢሕአዴግ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋቱን በማመኑ ነዋ፡፡
– ይኼ ምኑ ነው የሚያስገርመው?
– ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋቱን ማመኑ ነዋ፡፡
– እስከዛሬ አምኖ አያውቅም?
– አዎና ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ለምን አምኖ እንደማያውቅ ታውቃለህ?
– አላውቅም፡፡
– አጥፍቶ ስለማያውቅ ነዋ፡፡
– ምን አሉኝ?
– አጥፍቶ አያውቅም፡፡
– ለነገሩ አጥፍቶ የሚያውቀው ሌላ ነገር ነው፡፡
– ምን?
– መብራት፡፡
– እ…
– ውኃ፡፡
– እ…
– ኔትወርክ፡፡
– ሌላስ?
– አንዳንዴም የሰው ሕይወት፡፡
– በል በል ሌላ ፖለቲካ ውስጥ አትግባ፡፡
– ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ለማንኛውም አሠራራችንን መለወጥ አለብን፡፡
– እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
– ሁሉን ነገር በአዲስ መልኩ መጀመር አለብን፡፡
– በአዲስ ሲሉ?
– ሕዝቡ በጣም ተማሮብናል፡፡
– እርሱማ ግልጽ ነው፡፡
– ስለዚህ ሕዝቡን ማስደሰት አለብን፡፡
– እኮ በምን እናስደስተው?
– አዲስ ሕንፃ ውስጥ መግባት አለብን፡፡
– ለምን ሲባል?
– ሕዝቡ በደል በደል በሚሸት ሕንፃ ውስጥ ከዚህ በኋላ መገልገል የለበትም፡፡
– እና ምን ይደረግ?
– አዲስ ሕንፃ ውስጥ መግባት አለብን ስልህ፡፡
– የትኛው ሕንፃ ውስጥ ነው የምንገባው?
– የምንገባበትን ሕንፃ እኔ እጨርሰዋለሁ፡፡
– የመንግሥት ሕንፃ ነው?
– የግል ነው እንጂ፡፡
– በኪራይ ክቡር ሚኒስትር?
– አዎና የግል ሴክተሩን እኮ ማበረታታት አለብን፡፡
– እና ከመንግሥት ሕንፃ ወጥተን ወደ ኪራይ እንግባ እያሉ ነው?
– ለሕዝቡ ሲባል የማይደረግ ምንም ነገር የለም፡፡
– ለማን አሉኝ?
– ለሕዝቡ፡፡
– ለእርስዎ ማለትዎ ነው?
[ክቡር ሚኒስትሩ ለምሳ ቤታቸው ሲሄዱ ሚስታቸውን አገኟቸው]
– ምነው ደስ ያለህ ትመስላለህ?
– እንዴት አልደሰት?
– እኮ ምን ተገኘ?
– ያው አፉን ከፍቶ የነበረው ሕንፃችን ተከራይ ተገኘለት፡፡
– ማን ሊከራየው ነው?
– እኛ ነና፡፡
– እናንተ ማን ናችሁ?
– የእኛ መሥሪያ ቤት፡፡
– ምን?
– አዎን ሁሉን ነገር ጨርሼዋለሁ፡፡
– ለምንድን ነው ቢሮ የምትቀይሩት?
– በአዲስ መንፈስ ሥራ መጀመር አለብና፡፡
– ያላችሁበት የመንግሥት ሕንፃ አይደል እንዴ?
– ቢሆንስ?
– ታዲያ ከዛ ወጥታችሁ ወደ ግለሰብ ሕንፃ ልትገቡ?
– ምን አለበት?
– ለነገሩ ከመንግሥት ሕንፃ ወደ መንግሥት ባለሥልጣን ሕንፃ ነው የገባችሁት፡፡
– አመጣሽው ጨዋታውን፡፡
– ያን ያህል ልዩነት ያለው አይመስለኝም፡፡
– ያው ነው ስልሽ፡፡
– የእኔ ሥራ ብቻ ተቀዛቅዟል፡፡
– የትኛው ሥራሽ?
– የፈርኒቸሩ ሥራ ነዋ፡፡
– ለእሱም ቢዝነስ ሥራ አግቼልሻለሁ፡፡
– ምን ተገኘ?
– አዲሱ ሕንፃ ውስጥ ስንገባ አዲስ ፈርኒቸር ያስፈልገናል፡፡
– የድሮዎቹ ምን ሆኑ?
– ወንበሮቹ ራሳቸው ግፍ ግፍ ይሸታሉ፡፡
– ታዲያ ወንበሮቹ ሳይሆኑ ወንበሮቹ ላይ የተቀመጡት እኮ ናቸው ግፈኞቹ፡፡
– ቢሆንም ሕዝቡ በእነዚህ ግፈኛ ወንበሮች ከዚህ በኋላ መገልገል የለበትም፡፡
– እኔማ ደስ ነው የሚለኝ፤ ቢዝነስ አገኘሁ፡፡
– ስለዚህ ተዘጋጂ፡፡
– ስለእሱ አታስብ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ሲገቡ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
– አቤት ክቡር ሚኒስትት፡፡
– አንድ ሐሳብ መጥቶልኝ ነው፡፡
– የምን ሐሳብ?
– አዲሱ ቢሮ ስንገባ አዲስ ፈርኒቸር መግዛት አለብን፡፡
– ምን?
– ሁሉን ነገር በአዲስ መንፈስ መጀመር አለብን ስልህ፡፡
– ፈርኒቸሮቹ ከተገዙ እኮ ስድስት ወራቸው ነው፡፡
– ስማ ቢሆኑም ሕዝቡ በእነዚህ ግፈኛ ወንበሮች መገልገል የለበትም፤ መቀየር አለባቸው፡፡
– መቀየርማ ያለባቸው ሰዎቹ ናቸው፡፡
– ሰዎቹን መቀየር ከባድ ስለሆነ ወንበሮቹን ብንቀይራቸው ይሻላል፡፡
– ሕዝቡ እኮ የተማረረው በወንበሮቹ ሳይሆን በሰዎቹ ነው፡፡
– አየህ በወንበሮቹ ጀምረን በሰዎቹ እንቀጥላለን፡፡
– ለማንኛውም የሰዎቹን ቅያሬ ስንጠብቅ ቀኑ እንዳይደርስብን፡፡
– የምኑ ቀን?
– የምፅዓት ቀን!
[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ቢሯቸው ገባች]
– ጠዋት የት ሄደሽ ነው?
– አንድ ጉዳይ ገጥሞኝ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ታዲያ አታስፈቅጂም እንዴ?
– ስልክዎትን ብለው ብለው አልሠራ አለኝ፡፡
– ሞክረሽልኝ ነበር?
– በጣም ብዙ ጊዜ ነው የሞከርኩት ክቡር ሚኒስትር፡፡
– አየሽ ሌላም ሰው ቢፈልገኝ አልገኝም ማለት ነው፡፡
– ለእኔ አልሠራልኝም ነበር፡፡
– ሕዝቡ የሚማረረው እኮ እንደዚህ እየሆነ ነው፡፡
– እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
– ስልኬ በአዲስ መቀየር እንዳለበት ገብቶኛል፡፡
– እ…
– አዲስ አይፎን ያስፈልገኛል፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ የአይቲ ክፍል ኃላፊውን አስጠሩት]
– አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ሕዝቡ ምን ያህል እየተማረረ እንደሆነ ታውቃለህ አይደል?
– በጣም ተማሯል፡፡
– ሕዝቡን እኔን ሊያገኘኝ አልቻለም፡፡
– ቢሮ መቼ ተቀምጠው ያውቃሉ?
– ቢሮ ባልቀመጥም ቢያንስ በስልክ ሊያገኘኝ ይገባል፡፡
– ስልክዎትን የሚያውቀውማ ይደውልልዎታል፡፡
– የማያውቀውም ቢሆን ቢያንስ በኢሜይል ሊያገኘኝ ይገባል፡፡
– ታዲያ ለምን አያገኝዎትም?
– አየህ ኮምፒዩተሮቻችን አሮጌ ናቸው፡፡
– እ…
– አሁን አዲስ ሕንፃ ውስጥ ስለምንገባ ሁሉንም በአዲስ ኮምፒዩተር መተካት አለብን፡፡
– ክቡር ሚኒስትር አሁን ያሉት ኮምፒውተሮች እኮ ከተገዙ ገና ስድስት ወራቸው ነው፡፡
– ስማ ቴክኖሎጂው እኮ በየጊዜው ነው የሚቀያየረው፡፡
– እ…
– ስልኮቻችንም በአዲስ መቀየር አለባቸው፡፡
– ጨረታ ይውጣ?
– ቢሮክራሲ አያስፈልግም፡፡
– ምን?
– እኔ እጨርሰዋለሁ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ የኮምፒዩተር ቢዝነስ የሚሠራው ወንድማቸው ጋ ደወሉ]
– አቤት ጋሼ፡፡
– የት ነው ያለኸው?
– ካርታ እየተጫወትኩ ነው፡፡
– አንተ ልጅ ይኼ ካርታ ሱስ ሆነብህ አይደል?
– ያው በዘር እኮ ነው ሱስ የሆነብን ጋሼ፡፡
– እኔ የት ነው ካርታ ስጫወት ያየኸው?
– ያው አንተ በመሬት ካርታ ነዋ የምትጫወተው፡፡
– ለማንኛውም አሁን ሥራ አግኝቼልሃለሁ፡፡
– የምን ሥራ ጋሼ?
– ለቢሯችን ሙሉ ኮምፒዩተር እንድታቀርብ፡፡
– እየቀለድክ ነው ጋሼ?
– የምን ቀልድ ነው? እውነቴን ነው፡፡
– ከስድስት ወር በፊት ነው እኮ ለሙሉ ቢሮው ኮምፒዩተር ያቀረብኩት፡፡
– እና ይኼኛውን አትፈልገውም?
– ኧረ እንደሱ ማለቴ አይደለም፤ በጣም ደስ ብሎኝ ነው፡፡
– ምኑ ነው ደስ ያለህ?
– በቃ በዚህ ሥራ ሕንፃዬን እጨርሰዋለሁ ብዬ ነዋ፡፡
– ሕንፃህንም ተጨማሪ ቦታ ስለሚያስፈልገን መከራየታችን አይቀርም፡፡
– አንጀት አርስ ነህ ጋሼ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ስብሰባ ተጠርተው ሄዱ፤ ሳያስቡት መገምገም ጀመሩ]
– ክቡር ሚኒስትር ከብልሹ አሠራርዎት ሊታቀቡ አልቻሉም፡፡
– እናንተ ከእኔ ውጪ ሰው አይታያችሁም እንዴ?
– ይኸው ባለፈው ተገምግመው አሁንም ያው ነዎት፡፡
– ምን አደረግኩ?
– ይኸው አዲስ ሕንፃ ውስጥ ካልገባን እያሉ ነው፡፡
– በአዲስ መልክ ሥራ መጀመር ስላለብን ነዋ፡፡
– ደግሞ ሕንፃው የእርስዎ ነው አሉ?
– በተመጣጣኝ ዋጋ እስካከራየሁት ድረስ ምን ችግር አለው?
– እ…
– ፈርኒቸሮቹንም ቢሆን በአገር ዋጋ ነው የምናቀርበው፡፡
– ሌላስ?
– ኮምፒዩተሮቹም ቢሆኑ ሌተስት የሆኑት እኛ ጋ ስላሉ ነው፡፡
– ወይ ቅሌት፡፡
– ይህንንም ያደረግነው ሥራችንን በአዲስ መንፈስ ለመጀመር ነው፡፡
– እርስዎም በአዲስ መልክ ጀምረውልኛላ፡፡
– ምኑን?
– ሌብነቱን!