ወልቃይት ፀገዴና ፀለምት፥ በዐይኔ ካየሁትና ከታዘብኩት [በያሬድ ጥበቡ]
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ወልቃይት ፀገዴና ፀለምት፥ በዐይኔ ካየሁትና ከታዘብኩት [በያሬድ ጥበቡ]Yared Tibebu
መግቢያ
የዛሬ 39 አመት ግድም ለሶስት አመታት ያህል ከሰኔ 1969 እስከ ሰኔ 1972 አም ድረስ በፀለምት፥ ዋልድባ፥ ቆላወገራና ወልቃይት ውስጥ የኢህአፓ ሰራዊት አባል በመሆን በእግሬ ተጉዣለሁ ። በአማካይ በቀን 5 ሰአት እንጉዋዝ ስለነበር፥ በአመት 9000 ኪሎሜትር፥ በሶስቱ አመት ቆይታዬ 27000 ኪሎሜትር ያህል መንገድ ተጉዣለሁ ማለት ነው። በነዚህ አካባቢዎች ምናልባት ያልገባሁበት መንደር ላይኖር ይችላል ። ዛሬ እነዚህ አካባቢዎች በነዋሪው ህዝብና በአገዛዙ መሃል የማንነት ጥያቄ የውጥረት ማእከል ሆነዋል ። ከ39 አመታት በፊት ወልቃይትንና ፀለምትን ሳውቃቸው ምን ይመስሉ እንደነበር የማስታውሰውን ያህል ባካፍልስ ብዬ ብእሬን አነሳሁ ።
የምሰጠው ምስክርነትና የማነሳው ክርክር በማውቀው የመልክእምድር አቀማመጥና የህዝቡ ባህል ላይ የተመሰረተ ነው ። የክርክሬ ማጠንጠኛ፥ እንደ ተከዜ አይነት ታላላቅ የተፈጥሮ ወሰኖች በትናንሽ አይዲዮሎጂዎች ቢገሰሱ ከፍተኛ ውዝግብና አለመረጋጋትን ስለሚያስከትሉ ጥንቃቄን ይሻሉ የሚል ነው ። በተጨማሪም የተከዜን አይነት የተፈጥሮ ወሰኖች ተሻግረው ከአጎራባች ህዝብ እቅፍ ውስጥ የተስተናገዱ ማህበረሰቦች፥ ያስጠጋቸውን ህዝብ ማንነት የመፈታተን መብት ሊኖራቸው አይገባም ብዬም ለመከራከርም ነው ።
ተከዜ ፥ ታላቁ የተፈጥሮ ወሰን
ወሎና ጎንደርን አያዋሰነ ተከዜን ከሚቀላቀለው የፅላሬ ( ጥራሪ) ወንዝ ጀምሮ፣ ትግራይንና ወሎን፣ ትግራይንና ጎንደርን፣ ከዚያም ጎንደርንና ኤርትራን የሚያዋስነውን ታላቁን የተከዜ ወንዝ፣ ከምንጩ ከኩል መስክ ተነስቶ ሱዳን ከሰላ አካባቢ እስኪገባና አትባራ ተብሎ እስኪሰየም፣ በነዚህ በተጠቀሱት የክፍላተሃገራት ወሰኖች ሁሉ በእግሬ ያቆራረጥኩና በሁለቱ አይኖቼ ያየሁ ሰው በመሆኔ፣ ስለ ድንበር አካለዩ ተከዜ መናገር ከሚችሉ ጥቂት ኢትዮጵያውያን መሃል ነኝ ። በመጀመሪያ ተከዜን ያየሁት በሰኔ 1969 ሀይል 17 የምትባል የኢህአፓ ሰራዊት አባል ሆኜ፣ ከአሲምባ ትግራይ ተነስተን ወደ ፀለምት ጎንደር ባደረግነው ጉዞ ወቅት ነው ። የግባን ወንዝ ስንሻገር የኮንጎ ላስቲክ ጫማዬን የሰኔ ውሃ ሙላት ይዞት ሄዶ ስለነበር፣ በጨርቅ በተጠቀለለ እግር እየተጓዝኩ ነው ተከዜን የተሻገርኩት ።
ወደፀለምት መሻገሪያው በጣም ረበዳ ሸለቆ ስለነበር፣ የተከዜን ገመገም ጠዋት መውረድ የጀመርን፣ ወንዙን ተሻግረን አቀበቱን እስክንወጣ ቢያንስ የስድስት ሰአት መንገድ እንደወሰደብን ትዝ ይለኛል ። እጅግ አድካሚ ጉዞ ነበር ። ከሰአት በኋላ ፀለምት ውስጥ ከሚገኝ መንደር ደረስን ። ከፀሀይ መግቢያ አቅጣጫ ታላቁ የአቤር ተራራ ቁልቁል በንቀት ይመለከተንም፣ ያስፈራም እንደነበር ትዝ ይለኛል ። ቁልቁል ወደመጣንበት የተከዜ ሸለቆ የሚገፈትረን ነበር የሚመስለው ። ልክ እንደኛ ሁሉ አስቸጋሪውን የተከዜ ሸለቆ አቋርጠው የመጡ የትግራይ ሰዎች ከነባሩ የስሜን ሰው ጋር የፀለምትን ማህበረሰብ መስርተው፣ ትግርኛም አማርኛም እየተናገሩ ይኖራሉ ። ከአዴት፣ ከአቢይ አዲ፣ ከአክሱም አካባቢ ከጉማ አምልጠው ወይም የሰው ህይወት አጥፍተው፣ ወይም ችግር አብሮአቸው ፀለምት ላይ ከወባና ወበቅ ጋር እየታገሉ፣ የተከዜን ገመገም ይዘው የሰፈሩ የትግራይ ሰዎች ብዙ ናቸው ። ጎንደር መሬት ላይ የሰፈሩ ትግራዋዮች።
አሲምባ የነበረው የኢህአፓ ሰራዊት በየካቲት 1970 አም “ትግራይ ለትግሬዎች” በሚል በህወሐት ድንገት ያልታሰበ ጥቃት ተሰንዝሮበት በብዙ መቶ ለሚቆጠሩ ጓዶች ሞትና መቁሰል ምክንያት ሆነ። ትግራይ ውስጥ መቆየት ስላልተቻለም ወደ ኤርትራ ማፈግፈግ የግድ ሆነ። ሰራዊቱ በጀብሀ አስጠላይነት ስር ስድስት ወራት ተኮምቢያ አካባቢ፣ ጋሽ ወንዝ ዳር ከከረመ በኋላ መሰከረም 1971 ላይ ወደ ፀለምት ሲመጣ፣ የተከዜን ወንዝ ለመሻገር ስንት መከራና ችግር ማለፍ ነበረበት ። ተከዜ እስኪጎድል ኤርትራ ውስጥ በነበረው ቆይታ ወቅት በረሃብ የተነሳ የሰንሰል ቅጠል እንደ ጎመን እየቀቀለ ተመግቧል፣ ጋሽ ወንዝ እያላጋ ያመጣውን የግመል ሬሳ ስጋ በልቶ በተቅማጥ ተሰቃይቷል ። ፀሊም ቤቶች የሚኖሩበትን የወልቃይት ቆላ መዘጋ አቆራርጦ ዛሬማ ወንዝን ተሻግሮ፣ በዋልድባ ገዳም አልፎ ፀለምት መምጣት ነበረበት። ከዋልድባ ወደፀለምት ለመሻገር ግን ወደ ተከዜ የሚገብረው የእንስያ ወንዝ የማይበገር ስለነበር፣ ሰውና አጋሰስ የሚያሻግር ከብረትና ሲሚንቶ የተሰራ አነስተኛ ድልድይ ፀለምት ያለው የሪጅን አመራር አዘጋጅቶ መጠበቅ ነበረበት ። ይህ ሁሉ አበሳ ታይቶ ነበር ሰራዊቱ ከመንፈቅ እንግልት በኋላ ፀለምት የደረሰው ። ፀለምት እንደደረሰም ደርጉ ወረራ አዘጋጅቶ ጠበቀው ። ያንን መመከት የግድ ነበር ። ከደርጉ ጋር የሚደረጉት የመከላከል ውጊያዎች እንደተጠናቀቁም፣ የአሲምባውና የጎንደሩ ጦር እንዲዋሃድ ተደረገ በዚያን ዘመን ቋንቋ ተቅሊጥ ይባል ነበር፣ አረብኛ ሳይሆን አይቀርም፣ ከኤርትራ ግንባሮች ከወረስናቸው የሽምቅ ቃላቶች መሀል መሆኑ ነው።
ወልቃይትን እንዳየሁት
የሰራዊቱ ውህደት እንደተፈፀመ፣ እኔ አዲስ በሚከፈተው ሪጅን አራት ውስጥ ተመደብኩና፣ በመጀመሪያ ቆላወገራን ከፀለምት የሚያገናኘውን መስመር ለማለሳለስ እስከ ጃኖራና አጅሬ ድረስ ተጓዝን ። ከዚያም መልስ ወልቃይትን ከኢዴህና ደርጉ ቁጥጥር ነፃ ለማድረግ፣ ከተማይቱን አዲ ረመፅን ለመቆጣጠር ኦፐሬሽን ተዘጋጀ ። ተልእኮውም በቀላሉ ተፈፀመ ። ወልቃይትን ማስተዳደርም ጀመርን ።
በሥነምግባራችን ከኢዴህ ቀማኛ ሰራዊትም ሆነ ከደርጉ ማዳፋት ተግባር እጅግ የተሻልን ብቻም ሳይሆን፣ የወልቃይት ህዝብ በመቶ አመታት ታሪኩ ሰምቶትና ገምቶት የማያውቅ ህዝብን አገልጋይ ሰራዊት ሰለነበረን፣ ሊወደንና ሊያፈቅረን ጊዜ አልወሰደበትም ። ቤቱን፣ ማእዱን፣ ጎተራውን ከፍቶ በፍቅር ተቀበለን ። ፍርሃቱ ጥለነው እንዳንሄድ ብቻ ነበር ። የህዝብ አስተዳደር ኮሚቴዎች እያቋቋምን፣ ወንጀለኛ እየቀጣን፣ ቀማኛ እያደንን በሄድን ቁጥር፣ “ፈጣሪ ይህን መልካም አሳይቶ መልሶ አይነሳንም” የሚል የመተማመን ሃሳቡን ህዝቡ ያካፍለን ጀመር ።
በመጀመሪያ የኢህአፓ ተዋጊ ክንፍ የአንዲት አሃዱ ወይም ጋንታ የፖለቲካ ኮሚሳር በመሆን ከፅልእሎ እስከ ቀፍቲያ ፣ ከአዲ ረመፅ እስከ አዲ ጎሹ የህዝብ አደራጅ በመሆን ከወልቃይት ህዝብ ጋር ኖሬአለሁ። ከመሶባቸው ተመግቤአለሁ፣ መደባቸው ላይ ተኝቻለሁ፣ በልጆቻቸው ሠርግ ታድሜአለሁ፣ በለቅሶና አጎበራቸው ላይ ተቀምጫለሁ። አስተምሬአለሁ፣ ቀስቅሻለሁ ። ከኢዴህ ጋር ሆነው፣ ወያኔን ሲታገሉ ስለከፈሉት መስዋእትነት ሲተርኩ አድምጫለሁ። “ገዳይ ደደቢት ፣ መጠጊያ ድንጋይ በሌለበት”ብለው ሲፈክሩ ተመልክቻለሁ ። ብቻዬንም አልነበርኩም፥ በመቶ የሚቆጠሩ አብረውኝ የነበሩ ታጋዮች ዛሬም በአሜሪካ ይገኛሉ። የትግራይ ልጆች የነበሩም ብዙ ናቸው ። እንዲያውም ህዝብ በማደራጀቱ ስራ የበለጠ እነርሱ ተመድበው ስለሰሩ፥ የተሻለ መመስከር ይችላሉ።
ወደ አሲምባ ካቀናሁበት ከጥር 1969 ጀምሮ፣ በትግራይም ሆነ ጎንደር ካየሁዋቸው በሺህ ከሚቆጠሩ መንደሮች፣ የወልቃይት መንደሮች በሶስት ነገሮች ጉልህ ልዩነት ነበራቸው ። አንደኛው፣ ከፍተኛ የሆነ የቆርቆሮ ቤቶች ከምችት ያሉባቸው መንደሮች ብዙ ነበሩ ። በተለይ ከአዲ ረመፅ ወደ ቀፍቲያ መሻገሪያ አቅጣጫ ያሉት መንደሮች፣ እነ ብላምባ ሉቃስና ብላምባ ቅርሺ የመሰሉት ማህበረሰቦች የሳንቃ ወለል የሌላቸው ከመሆናቸው በቀር፣ በስርአት የተገጠሙ የተላጉ በሮችና መስኮቶች ያሉዋቸው፣ የመኝታ ክፍሎቻቸው የተለዩ፣ የቦንዳ አልጋዎች ያሉዋቸውና በዘመናዊ የቤት እቃዎች የሚገለገሉ ነበሩ ። ወተቱ፣ ቅቤው፣ እርጎው፣ ጠላው እንደ ልብ ነበር ። ሴት ወይዘሮው ንፁህ የሚለብስ፣ ወንዱ አውቶማቲክ ጠብመንጃ የታጠቀ የጠገበና የኮራ ህዝብ ነበር።
ለሁለተኛ ጊዜ ተከዜን የተሻገርኩት ከአዲ ጎሹ አካባቢ ወደ ኤርትራ መሻገር በተገደድኩበት ወቅት ነው ። ቀኝ እግሬ ላይ መጅ ወይም callous አብቅዬ መራመድ ተቸግሬ ስለነበር፣ የሰራዊታችን ሀኪሞች የነበሩት ስእለና መልአኩ ቀዶጥገና አድርገውልኝ ማገገም ላይ በነበርኩበት ወቅት ነበር ወያኔ ወልቃይትን የወረረው።
በየቦታው ተበታትነን የነበርን ጥቂት ታጋዮች፥ ከአዲ ረመፅ ወጣ ባለች መንደር ስለወረራው ሁኔታና ሰራዊታችንም የት እንደሚገኝ ከአርሶአደሮቹ ለማጣራት በምንሞክርበት ጊዜ እዚያ መንደር ውስጥ እንደምንገኝ ወያኔ ስላወቀች አመሻሽ ላይ ታጋዮቿን ልካ በተኩስ አጣደፈችን ። ተኩስ በሌለበት አቅጣጫ እያፈገፈግን ተበታተንን ። ብላምባ ሉቃስ አድሬ የበለጠ መረጃ ሳሰባስብ፣ አዲ ጎሹ አካባቢ የነበሩት ተዋጊ አሃዱዎች ወደ ኤርትራ መሻገራቸውን አስተማማኝ ወሬ ሰማሁ።
ከሌሊቱ በአስር ሰአት ላይ ተነስቼ ገበሬዎቹ ወደቆላ እርሻቸው በሚወርዱበት አሳቻ ቁልቁለት ከደጋው መሬት ወደ አዲ ጎሹ አቅጣጫ ወደሚወስደው በረሃ ወረድኩ ። ድንገት የወያኔ አባላት ቢይዙኝ ወደኤርትራ ጠብመንጃ ለመግዛት እንደሚሄድ የጠገዴ ነዋሪ በመንገድ ላይ ትብብር እንዲደረግልኝ የሚያሳስብ ባለማህተም ደብዳቤ ይዤ የኢህአፓ ሰራዊት አባልነቴን የሚጠቁሙ ቁሶችን በሙሉ አሳዳሪዎቼ ጋ ትቼ ነበር ። ከደጋው ወርዶ ሰው የማይኖርበትን በረሃማ ስፍራ ብቻ ይዞ መጓዙ ከፀሀዩ ቃጠሎና ከውሃ እጦቱ ጋር ተዳብሎ መቋቋም የሚቻል አልነበረም ። ሆኖም ከአስር ሰአት ያህል የእግር ጉዞ በኋላ ከተከዜ ወንዝ ደረስኩ ። ለመጀመሪያ ጊዜም ለላንቃዬ ማርጠቢያ የሚሆን ውሃ አግኝቼ ጠጣሁ ። ከወንዙ ማዶ እረኞች ከብቶቻቸውን ሲጠብቁ ተመለከትኩ ። ተሻግሬም ተገናኘኋቸው ። ኤርትራውያን እረኞች ነበሩ ። በጋይት የሚባሉ ላምና በሬዎቻቸውም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከምናውቃቸው ለየት ያሉና እጅግ የደለቡ ነበሩ ።
አዳር ከኤርትራ እረኞች ጋር
እረኞቹ በረሃብና ጥም መጎዳቴን ሲያዩ በእንጨት ጮጮ ከያዙት ወተት አጠጡኝ ። አብሬያቸው አድሬ በበነጋታው መንገዴን ብቀጥል እንደሚሻልና፣ የኤርትራ መንደሮች እስክደርስ የብዙ ሰአት እግር መንገድ ስለሚቀረኝ ልቸገር እንደምችል ነገሩኝ ። በሃሳባቸውም ተስማማሁ ። ፀሀይ ከማዘቅዘቋ በፊት ከብቶቻቸውን ወደነፋሻማው ዳገት መንዳት ጀመሩ ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ላሞችና በሬዎች በአንድ ላይ ሲታገዱና ሲጠበቁ ሳይ የመጀመሪያዬ ነበር ። ወደ በረታቸው የሚያመሩበት ዳገት ለከባድ መኪና የተሰራ ጥርጊያ ይመስል ነበር ። ዳገቱን ለአንድ ሰአት ያህል ከወጣን በኋላ ከከብቶቹ በረት ደረስን ። እረኞቹ ከብቶቹን በረት ውስጥ ካስገቡ በኋላ፣ ትልቅ የካምፕ እሳት ማዘጋጀት ጀመሩ ። ከተከዜ ወንዝ ዳርቻዎች የሰበሰቧቸውን ጠጠሮች በማሽላ ሊጥ እየጠቀለሉ የሚነደው እሳት ውስጥ ይዶሉ ጀመር ። ብርኩታ ተብሎ የሚጠራው እራታቸው እንደሆነ ነገሩኝ ። ሆዴ እስኪቆዘር ብዙ ብርኩታ በላሁ ።
ወልቃይት ፀገዴና ፀለምት፥ በዐይኔ ካየሁትና ከታዘብኩት
[በያሬድ ጥበቡ]
መጋቢት 1 ቀን 2008 አም