አድዋ መታወቂያችን፤ ምኒልክ ታዳጊያችን – ዶ/ር ኃይሌ ላሬቦ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ዶ/ር ኃይሌ ላሬቦ
የአድዋ ጦርነት በኢትዮጵያውያን እይታ
በዚህ ወር መግቢያ ላይ ኢትዮጵያዉያን የአድዋን መቶ ኻያኛውን ያመት በዓል በያሉበት በአድናቆት አክብረውታል። በየሬድዮ ጣቢያዎቹ፣ በየፓልቶኮቹ፣ በየማኅበራዊ ድርጅቶችና ኢትዮጵያውያን በየተሰበሰቡበት ሁሉ ስለአድዋ ያልተናገረ፣ ያላሰበ፣ ወኔው ያልተቀሰቀሰ የለም ማለት ይቻላል።
እንደታላቅነቱና ታሪክነቱ ከሆነ፣ የአድዋ ድል ያንድ ቀን ብቻ በዓል መሆን የለበትም። የትም አገር ሂደን ታሪክ ብንመረምር፣ መዛግብታቸውን ብንገለባብጥ፣ የአድዋን ዐይነት ታሪክ የሠራ ሕዝብም አገርም የለምና። የአድዋ ድል አሜሪቃ ነፃነቷን ካገኘችበት ድል፣ ከፈረንሳይና ከሩሲያ አብዮት፣ የደቡብ አፍሪቃ ጥቊሮች በጨቋኞቻቸው ነጮች ላይ ካገኙት የእሪና ድል እጅግ ይበልጣል። ጦርነቱ ከውጩ ሲታይ በሁለት ራሳቸውን በቻሉ ነፃና ልዑላን በሆኑ አገሮች መካክል ቢሆንም፣ ጥያቄው ቀጥለን እንደምናየው ስለሰው ዘር መብትና እኩልነት ነው።
ለኢትዮጵያውያን የአድዋ ድል የማንነታቸው መግለጫ፣የልዕልናቸውና የነጻነታቸው ማረጋገጫ ነው ሊባል ይገበዋል። ግን እንደአብዛኛው ድል፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ብቻ አይመለከትም። ለሌላውም ዓለም ሁሉ ይትረፈረፋል። በዚያን ዘመን ጨቋኝ ለነበረው ለነጩ ዘርም ሆነ ለተጨቋኙ ያለም ሕዝብ የነፃነት ፋና ነበር። ድሉን ተከትሎ ጥቁር ሕዝብ በያለበት ሁሉ “ኢትዮጵያዊነት” ለተባለ ለብርቱ የሃይማኖትና የፖሊትካ እንቅስቃሴ መሠረት ሁኖ አገልግሏል። ለነጩ ከኢስብአዊነቱ ጭካኔ፣ ነጭ ላልሆነው ዘር ደግሞ ከሚማቅቅበት ከነጭ የባርነት ቀንበር፣ ሁለቱም ነፃ የሚወጡበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ ያበሠረ ድል ነው። የድሉ ወሬ እንደደረስው በእንግሊዝ መናገሻ በሆነችው በለንደን ከተማ የሚታተመው ዘታይምስ ጋዜጣ ይኸንን በማያወዛግብ ሁኔታ ጥርት አድርጎ እንዲህ ሲል አስቀምጦታል።
“ኢጣልያኖች በጀብድነትም ሆነ በጦር ስልት ከሌሎቹ አውሮጳውያን አያንሱም። .. ድሉ የመላ [ጥቊር] አፍሪቃ ድል መሆኑ አይካድም። ይኸም አስተያየት ወደፊት እያየለ ሄዶ በግልጽ የሚታይ ነው። ወሬው በነፋስ ክንፍ በረኻውን አቋርጦ እየበረረ በመጓዝ በነዚህ አገሮች ከጫፍ እስከጫፍ ተዛምቶ ሲያበቃ፣ አፍሪቃውያን አውሮጳውያንን ማሸነፋቸው አይቀርም የሚለውን ስሜት አነቃቅቷል። ነገሩ አስጊ በመሆኑ በኢጣልያኖች መሸነፍ መደሰት [ለነጮች] ተገቢ አይደለም። ሽንፈቱ የሁላችንና የሌሎችም ጭምር ሽንፈት ነው። ዛሬ ቅኝ ገዢ የሆነችውና ከዚያም ባሻገር የነገይቱ አውሮጳ ሽንፈት ነው።”
ዘታይምስ ግልጽ ያላደረገው ነገር ቢኖር፣ በአድዋ የተዋጋው የኢጣልያን ጦር በቊጥር ብዛትም ሆነ፣ በዘመናዊ የጦር መሣርያውና የወታደሩ ጥራት፣ ባፍሪቃ ምድር ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ፣ ማንም የአፍሪቃ አገር ያልተጋፈጠው የጦር ዐይነት መሆኑን ነው። ሌላው መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር ደግሞ፣ የአውሮጳውያንን ጦር ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ብቻ አልነበረችም። በ፲፰፻፳፫ ዓ.ም. አሁን የጋና መንግሥት አካል የሆነው አሻንቴ በመባል ይታወቅ የነበረው አገር፡ ዓለምን ከጫፍ እስከጫፍ ድረስ ከመቈጣጠርዋ የተነሣ፣ “ፀሐይ የማይጠልቅበት መንግሥት” እየተባለ የሚነገርላትን የእንግሊዝን ጦር ደምሰሶ የጦር መሪዎቹን ቸብቸቦ ለሰለባ ዳርጓል። እንዲሁም በጥር ፲፰፻፸፰ ዓ.ም. የዙሉ ንጉሥ ሴትዋዮ የእንግሊዝን ወራሪ ጦር በእስንድህልዋና ጦርነት ድል አድርጎ ለወሬ እንኳን የሚሆን ሳያስቀር ድምጥማጡን አጥፍቶታል። ሁኖም ብዙም ጊዜ ሳይቈይ ባላንጣቸው በተከታታዩ ጦርነት ነፍስ ዘርቶ ተደራጅቶ ሲመለስ፣ አሸናፊዎቹ የተቀዳጁት አኩሪው ድል ከንቱ ሁኖ ቀረ። በአንጻሩ የአድዋ ድል ከመጀመርያውኑ የለየለት ነበር። ይኸ ድል “አውሮጳውያን በዕውቀት አቻ የሌላቸው፣ በትምህርት የተራቀቁ፣ በሀብት የበለጸጉ በመሆናቸው በጥቁርና በብጫ ሕዝብ በፍጹም ሊሸነፉ አይችሉም” የሚለውን ዘመናት ያስቈጠረውን እምነትና አስተሳሰብ ውድቅ ስላደረገው፣ በመላው ነጭ ዘር ላይ ከፍተኛ ራስ ምታት እንዳሳደረ ጥርጥር አልነበረም። ስለዚም ነው ከላይ የተጠቀሰው ዘታይምስም ሆነ፣ በዘመኑ በጋዜጣነቱ የታወቀውን ሞርቶን እስታንለይን የመሳሰሉ ጸሓፊዎች፣ ኢጣሊያ በጥቁር ሕዝብ ተሸንፋ ራሷ ኀፍረትን ተከናንባ፣ ነጭንም ዘር አስዋርዳ መቅረት የለባትምና፣ በርካታ ጦር ልካ፣ ብልሃቷን አሻሽላ፣ እንደገና ተመልሳ እንዲትዋጋ እያበረታቱ የጻፉትና፣ ጩኸታቸውንም ያስተጋቡ የነበሩት። ግን ሁሉም ከንቱ ሆነባቸው። ሽንፈት ዕጣዋ የሆነባት ኢጣልያን እንኳን ነፍስ ዘርታ ተነሥታ ተመልሳ ባዲስ ኀይልና ብልሃት ሊትዋጋ ይቅርና፣ ያገሯ መንግሥት ራሱ ከሥልጣኑ ወድቆ ከሥራው መባረር ጽዋው ሆኖ ቀረ።
የአድዋ ድል የኢትዮጵያን ህልውናዋንና ነፃነቷን ባለም መድረክ ላይ በግሁድ ለማረጋገጥ በቃ። ከአድዋ በፊት የተለያዩ ቄሳራውያን አገሯን ሊቦጫጭቋትና ሊቈራርሷት ሲሉ ለኻያ አምስት ዓመታት ያህል ሳያቋርጡ ወሯታል። ግብጾች በማያዳግም ሁናቴ በጉንዴት፣ በጒራዕ ባፄ ዮሐንስ እንደተመቱ፣ ኢጣልያኖች ብቅ አሉ። እነሱም በጉልበታቸው፣ በብልሃታቸውና በመሣርያቸው ተማምነው፣ በዲፕሎማሲ ሊበገሩ፣ በልመና ሊታገቱ አልፈለጉም። ለነገሩማ የእነሱንም ጦር ቢሆን በዶጋሌ ለወሬ እንኳን የሚሆን እስከማይቀር ድረስ ታላቁ ጀግና ራስ አሉላ ደምስሰዋቸው ነበር። የኋላ ኋላ ግን፣ ቈይተን እንደምናየው፣ አፄ ዮሐንስ አርቀው ካለማሰብም ይሁን፣ ሳይገነዘቡም ቀርተው፣ ወይንም በመዘንጋት፣ ደጋግመው በሠሩት ስሕተት፣ እሳቸው በድንገት እንዳረፉ፣ ከዚያ ተወስነው ከሚኖሩበት ከባሕር ጠረፍ አገግመው ተነሥተው፣ ልጃቸውን ባንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ሦስቴ አከታትለው ሲያሸንፉ፣ ተቈርጦ የነበር ወሽመጣቸው ታድሶ የልብ ልብ ተሰማቸው። ከዚያ ወዲያ፣ ማን ያቁማቸው። እነሱ የፈለጉትን ካላገኙ፣ ማለትም ኢትዮጵያን ጥገኛቸው ካላደረጉ፣ ይኸም ካልሆነ ደግሞ፣ ቢያንስ ከመሬቷ ሰፊ ይዞታ ተቈርሶ ካልተሰጣቸው፣ ለጦርነት እንጂ ለድርድር እንዳልተዘጋጁ ደጋግመው አስታወቁ። ለማሸነፉ ምንም ጥርጥር አልነበራቸውም። ጦርነቱን በብልሃትና በጀግንነት እንዲመራ የተላከው አዲሱ የጦር መኰንንና የኤርትራ ገዢ የነበረው ጀኔራሉ ባራቲየሪ ወደኢጣልያን አገር ተመልሶ በሄደ ጊዜ ይኸንን ቊልጭ አድርጎ ገአስቀምጦታል። ‘የኢትዮጵያን ጦር ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን፣ ምኒልክን ራሱን በቀፎ ውስጥ ይዤው አመጣዋለሁ” እያለ በየቦታው እየዞረ ሲፎክርና ሲደነፋ፣ ሕዝቡም አምኖት በየደረሰበት በእልልታ፣ በሆታ፣ በዘፈንና በጭብጨባ እየተቀባበለ ሲያጅበውና ሲሸነው ሰነበተ። ሐቁ ግን እሱ እንደሰበከው ስብከት፣ እንደነዛው ጒራ አልሆነም። ይልቅስ የጓዶቹ እንደነአልበርቶነና ዳቦርሚዳ የመሳሰሉት ጄኔራሎች ሕይወታቸው በጦር ሜዳ የሰማይ አሞራና የዱር አውሬ ሲሳይ ሁኖ ሲቀር፣ እሱ ግን ያንን ሁሉ ጒራና ድንፋታ ረስቶ፣ እሾህና ጒድጓድ ሳይለይ፣ እግሬ አውጭኝ እያለ ወታደሩን ጥሎ በመሸሽ አመለጠ። ለኢጣልያን ሕዝብ “ምኒልክን በቀፎ ውስጥ ይዤላችሁ እመጣለሁ” ብሎ ቃል የገባው ታላቁ የጦር መኰንን፣ ብዙም ሳይቈይ ከሥልጣኑ ተሽሮ፣ ወዳገሩ ተጠርቶ እግሩ እንደገባ፣ የጠበቀው ክስና ፍርድ ቤት ነበር።
የአድዋን ድል ወደጦርነት ከመሩት ቅድመ ሁናቴዎች ትይዩ ብናይ፣ የድሉን ምንነትና ታላቅነት፣ ባገርም ሆነ ባለም አቀፍ ደረጃ፣ በደምብ እንድንገነዘብ ይረዱናል። አንድ ኤድዋርድ ግበን የተባለ ገናና እንግሊዛዊ ታሪክ ጸሓፊ ስለኢትዮጵያ ሲናገር ካለው ልጀምር። ግበን፣”ኢትዮጵያውያንን ዓለም ረስቷአቸው፣ እነሱም ዓለምን ረስተውት ላንድ ሺ ዓመት እያንቀላፉ ቈዩ” ይላል። ግበን እንደዚህ ሲል ኢትዮጵያ የሚትባል አገር በካርታ ላይ አልነበረችም ወይንም አንዳንድ ኢትዮጵያውያን አልፈው አልፈው፣ ባለም መድረክ ላይ ብቅ ጥልቅ ማለት እንኳን አቆሙ ማለቱ አይደለም። ሊል የፈለገው፣ በአክሱማውያን ዘመን ባለም መድረክ ላይ በከፍተኛ ደረጃ የተጫወቱትን ሚና ረስተው፣ የዓለምን ታሪክ ሂደት በመልካቸው ከመቅረፅም ሆነ፣ በእምነታቸው ከመምራት ራሳቸውን አገልለው፣ በትንሽቷ በገዛ ራሳቸው ዓለም ውዝግብ ውስጥ ተወጥረው፣ የውስጥ ቤታቸውን ሥራ ከመሥራት አላለፉም ማለቱ ነው። ከአክሱም ውድቀት በኋላ ኢትዮጵያውያን በየጊዜው የውጩን ዓለም ከመጐብኘትም ሆነ ከመጐበኘት አቋርጠው አያውቁም ቢባል ሐሰት አይደለም። ጒብኝቶቹም በአገሩ ውስጥ አንዳንድ አዳዲስ አሳቦች እንዲገቡበት ቢረዱም፣ በዚያው ልክ ደግሞ ጉዳትንም አላመጡም ማለት አይቻልም። ብዙም ሳንራቀቅና ረጅም ዘመን ሳንሄድ በዐሥራ-ሰባተኛው ዘመን ጶርቱጌዞች ያመጡትን መዘዝ ማየት ይበቃል። እንደመሰለኝ፣ ይኸን ብቻ አይደለም ግበን ሊል የፈለገው። ጥንት ባለም መድረክ ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳልተጫወተች ሁሉ፣ አገሯ ምንነቷ እንኳን እስከመጥፋት፣ የቈዳዋ ስፋት እስከመመንመን፣ ገጽታዋ እስከመደብዘዝ ደርሶ ነበር ማለቱም ሳይሆን አይቀርም። አገር ማለት ሰንደቅ ዓላማ ማንጠልጠል፣ ብሔራዊ ባንክ ባለቤት መሆን ብቻ አይደለም። ባለም ደረጃም በተለያየ መልክ ተከብሮና ተፈርቶ መኖርንም፣ በተለያየ መስክ ሚና መጫወትንም ይጠይቃል። ከአክሱማያን ወዲያ ኢትዮጵያውያን ለዚህ አልታደሉም ነበር። የአድዋ ድል ለዚህ በሩን በርገግ አድርጎ ከፈተ። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የተውትን የክብር ቦታ ባለም መድረክ ያዙ።ብዙ ሕዝብ፣ የመንግሥት ባለሥልጣኖችን ጭምር፣ ከተለያየ ዓለም ወደአገሪቷ ጐረፈ።
እንግዴህ የአድዋ ድል መታየት ያለበት ግበን በሚሰጠው አሳብ አንፃር ከሆነ፣ ድሉ ለብዙ ዘመናት ትተኛ የነበረችውን አገር ከእንቅልፏ አነቃት። ሲትነቃም ያስተጋባችው ድምፅ ከፍተኛና ወደር የሌለው ከመሆኑ የተነሣ፣ በየተደመጠበት መላው የዓለም ሕዝብ ባግራሞትና ባድናቂት ተውጦ አብዛኛው በእልልታ፣ ጥቂቱ ደግሞ በወዮታ ተቀበለው። አገሪቷ ከአድዋ ተራራ ሁና እንዳንበሳ ግሣት ያስተጋባችው ጩኸት፣ የማትደፈር ልዑልና፣ ራሷን የቻለች ነፃ አገር መሆኗን በይፋ ከማስታወቅ አልፎ፣ ያኔ ባለም ላይ ሰፍኖ የነበረውን የነጮችን ሥርዐት አርበደበደው። አድዋ ለኢትዮጵያም ሆነ ለዓለም በሙሉ አዲስ ምዕራፍ ከፈተች፤ የራሷን የአገሯን ብቻ ሳይሆን የመላውንም ዓለም ታሪክ ባዲስ መልክና ቅርፅ ሂደቱን እንዲትተልም አዲስ የታሪክ ንድፍ ተነደፈ። አድዋ ለጨቋኞቹ ነጮች ያምባገንነታቸው ዘመን እንዳከተመ፣ ከሥራቸው ሁኖ እየተገፋ ለሚኖረው ላለም ሕዝብ ደግሞ የነፃነታቸው ዕድሜ እንደተቃረበ አበሠረ። እስከዚያም ድረስ ኢትዮጵያ በአድዋ በሠራችው ሥራ ለተጨቋኞቹ የነፃነት ጩራ፣ የቅኝ ግዛት ተስፋ ላስቈረጣቸው፣ እንዲሁም የነጮች አምባገንነት ለመረራቸውና ላስፈራራቸው የድላቸውና የአርነታቸው ዕርቡንና አለኝታ ሁና ቈየች። የአውሮጳውያን ዕብሪት ያንገፈገፋቸው ጃፓኖች ለምሳሌ የአድዋን ድል ባለም ታሪክ በነጮች ዘር ላይ ደርሶ የማያውቅ ውርደት አድርገው አዩት። በሺ ዘጠኝ መቶ ዐራት ዓመተ እግዚእ (ዓ. እ.) ላይ እነሱ ራሳቸው የአድዋን አብነት በመከተል በታሪክ ሁለተኛውን ቦታ ለመያዝ በቁ። ቈይተው የኢትዮጵያ ሊቃውንትም በበኩላቸው የጃፓንን ሥልጣኔ ለመቅዳት ትኩረታቸውን ከአውሮጳ ይልቅ ወደጃፓን ማዞር ጀመሩ። የነዚህ ሁለት ኀይለኞች የሆኑ የጥቊር ዘርና የብጫ ዘር መቀራረብና መፈቃቀር፣ ወደሺ ዘጠኝ መቶ ሠላሳዎቹ ላይ እየተጠናከረ መሄዱ፣ በአውሮጳውያን ጓሮ በጣም አስጊ ሁኖ በመታየቱ፣ በጣምም አከራከራቸው። ኢጣሊያንም ለሁለተኛ ጊዜ ኢትዮጵያን እንዲትወርር ካነሣሧት ውዝግቦችና ሰበቦች አንዱ ይኸው ወዳጅነትና መቀራርብ ሳይሆን አልቀረም ተብሎ በጽኑ ይታመናል።
ኢትዮጵያ በአክሱማውያን ዘመን ካለም መሪነት ሲትወጣ በጽሙናና በጽማዌ ሲሆን፣ ተመልሳ የገባችው ግን በአድዋ በተጐናፀፈችው ድል ምክንያት በታላቅ ጫጫታና ሁካታ፣ ግርማ ሞገስና ዝና ተጐናጽፋ ነው ቢባል እውነትነት አለው። በድሉ ማለዳ ከዚህ በፊት በንቀትና በትዕቢት እንዳንድ ነፃ አገር ሊያዩዋትና ሊደራደሩ ዝግጁ ያልነበሩ የአውርጳ ታላላቅ መንግሥታት ነን ባዮች፣ አላንዳች እፍረት ወደመናገሻ ከተማዋ እየተሽቀዳደሙ መጒረፍ ጀመሩ። ካድዋ በፊት አገሪቷ የልማት ሥራ እንዳትጀምር የተለያየ ምክንያት በመፍጠር ዕንቅፋት ሁነው የነበሩትም፣ የግንባታ ተግባር ላንዱ አውሮጳዊ አገር ተሰጥቶ ሌሉቹ ብዶ እጃቸውን እንዳይቀሩና፣ ሌላው ቢቀር ትራፊ እንኳን እንዳያመልጥባቸው ለመሰብሰብ ሲሉ፣ በለማኞች ወኪሎቻቸው የአፄ ምኒልክን ግቢ አጥለቀለቁት።
የአድዋ ድል ታላቅነቱ ይበልጥ የሚገለጠው ከጊዜው ጭብጥ ያለም ታሪክ ሁናቴ ሲታይ ነው። አሜሪቃ ታስሳ ተገኘች ከተባለበት ከዐሥራ ስድስተኛው ዘመን ጀምሮ፣ አውሮጳውያን ራሳቸውን ከሌላው የሰው ዘር የተሻሉና የበለጡ ብቻ ሳይሆን፣ የበላይም እንደሆኑ በጡንቻቸው ለማረጋገጥ በቅተዋል። ደካማነትንና በዘመናዊ ሥልጣኔ ወደኋላ ቀርነትን ከአውሬነት እስከማመሳስል ደርሰው ነበር። ከዚህም የተነሣ የክፍለ-አህጉሮቹን ነዋሪዎች፣ታሪክ ለዕልቂት ዳርጓቸዋል በማለት የአሜሪቃን፣ የአውስትራሊያንና የሌላውንም አገር ተወላጅ በጦር ሜዳና በፍልሚያ ካሸነፉት በኋላ፣ በተለያየ መንገድና ዘዴ ገድለው እስከመጨረስ ሲደርሱ፤ ትኩረታቸውን ወደእስያ ከዚያም ወዳፍሪቃ አዞሩ። አፍሪቃን በተመለከተ አንድ ከፍተኛ ስጋት ያሳደረባቸው ነገር ቢኖር፣ ክፍለ-አገሩን ሲቀራመቱት፣ የርስ በርስ ጥል የሚጭር አለመግባባት ተፈጥሮ፣ ራሳቸው እንዳይተላለቁ ነበር። ዋናው ይኸ ይሁን እንጂ፣ ሌላም ተጨማሪ ፍራቻ ነበራቸው። ይኸውም፣ ከዚህ በፊት በአሜሪቃና፣ በአውስትራሊያ እንደሆነ ሁሉ፣ የአፍሪቃም ክፍለ አገር በተወሰኑ በሁለትና በሦስት የአውሮጳውያን መንግሥታት እጅ ብቻ ወድቆ እንዳይቀር የሚል ነበር። እንግዴህ ለእነዚህ አስጊ ውዝግቦች እልባት ሊሰጥ ሲል ነው፣ ያነ የጀርመኑ መንግሥት መሪ የነበረው፣ ኦቶ ቮን ቢስማርክ በአውሮጳ አቈጣጠር በ፲፰፻፹፬ ዓ.ም. ታላላቆች ናቸው የተባሉትን የአውሮጳውያንን መንግሥታት ስብሰባ በበርሊን ከተማ የጠራው። ኢጣልያም ኢትዮጵያን እንዲትከጅልና በማጭበርበርም ሆነ በጉልበት በመሬቷ እግሯን እንዲታስገባ፣ ከዚያም ወደአድዋ እንዲታመራ ያበቃትም ይኸው የበርሊኑ ጉባኤ ነው። ጉባኤው አፍሪቃን በሚመለከት አያሌ ውሳኔዎች ያስተላለፈ ቢሆንም፣ አንኳር ሁኖ የሚታየው ግን አውሮጳውያን በአፍሪቃ ውስጥ ያካሄዱ የነበሩትን የመሬትን ቅርጫ ካጸደቀውና ከባረከው በኋላ፣ በተሻሚዎቹ መንግሥታት መካከል አለመግባባትን በማይፈጥርበት መልኩ እንዲካሄድ ሲል ሦስት ቀንድ የሆኑ ውሳኔዎችን አስተላለፈ። ከነዚህም አንደኛው ያፍሪቃን መሬት ለመቈጣጠር የሚፈልግ አውሮጳዊ መንግሥት፣ በመጀመርያ ደረጃ ከአፍሪቃዊው ገዢ፣ ካልሆነም (ይኸም ማለት አገሩ መንግሥት-አልባ ከሆነ ደግሞ) ከሕዝቡ ጋር የንግድ ውል መዋዋል ይኖርበታል ይላል። ከዚህም ቀጥሎ፣ በሁለተኛ ደረጃ፣ ተዋዋዩ አውሮጳዊ መንግሥት ድርድሩ እንዲጸናለትና እንዲታወቅለት ከፈለገ፣ በበርሊን ጉባኤ ለተፈራረሙት ታላላቅ መንግሥታት ስምምነቱን እንዲያስታውቅ ያስገድዳል። ይሁንና ይኸው ተፈራራሚው አውሮጳዊ መንግሥት፣ ከተቻለ በሰላማዊ መንገድ፣ ካስፈለገም ደግሞ በጉልበቱ አገሩን እቊጥጥሩ ሥር እስካላደረገ ድረስ፣ የውሉ መሬት ለማንም ሊይዘው ለፈለገ የአውሮጳ ኀይል፣ ክፍት እንደሆነ ይገልጣል።
የበርሊን ጉባኤ የነጭ ዘር አፍሪቃን እንዴት መቀራመት እንደሚገባ ውሳኔውን በወረቀት እንዳሰፈረ፣ አውሮጳውያን በተወላጆቻቸውና በምንዶቻቸው ያፍሪቃን ገዢዎችንና ሕዝብን በማታለል፣ የንግድና ጥበቃ የመስጠት ውል ማስፈራረም ተያያዙበት። አስፈራራሚዎቹ ጀሌዎች፣ ብዙውን ጊዜ የሃይማኖት ሰባኪዎችንና ዘመዶቻቸውን፣ የንግድ ድርጅቶችንና ነጋዴዎችን፣ የመልክዐ-ምድር አሳሾችንና አስመሳይ የዕውቀት ተመርማሪዎች ነን ባዮችን ያጠቃልላል ማለት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል፣ መንግሥተ-አልባ በሆኑት የሱማሌ ባላባቶች ግዛቶች፣ የምሥራቅ አፍሪቃዊው የእንግሊዝ የንግድ ኩባንያ፣ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ካሥራ ስድስት በላይ ከሆኑ የተለያዩ የጐሦች መሪዎች፣ በቀኝ ጣታቸው እያስፈረመ ውል ተዋዋለ[1]። ከነዚህም ያገኛቸውን መሬቶች አጠራቅሞ ሲያበቃ፣ የሱማሌ ምድር [ሱማሌላንድ] የሚባል ስም ሰጥቷቸው አንድ በታሪክ ያልነበረ አገር ፈጠረ። ፈረንሳዮችም በዚሁ መልክ በኦቦክ፣ በታጁራና በጂቡቲ የነበሩትን የጐሦች መሪዎች፣ በገንዘብም በእህልም እያታለሉ በማስፈራረም፣ የዛሬዋ ጂቡቲ እንዲትወለድ አበቁ። ኢትዮጵያም የጨለማና የድብልቅልቅ የነበረውን ዘመነ መሳፍንትን ከታሪኳ ነጥላ ጥላ ያንድነቷን የሕዳሴ መሠረት ሊትጥል ታጣጥር በነበረችበት ወቅት፣ አንድ አባ ዮሴፍ ሳፔቶ የተባለ የካቶሊክ ቄስ በሺ ስምንት መቶ ስልሳ ዘጠኝ ዓ.እ አንዲት ብጣሽ መሬት ካንድ የእስላም ባላባት ገዝቶ ለኢጣልያን የንግድ ኩባንያ ሰጠ። በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ሌላ ጨምሮ ገዛና፣ ቀናትም ሳይቈይ እሱ ራሱ የኢጣሊያንን ሰንደቅ ዓላማ ስቅሎ፣ በተገዙት መሬቶቹ ላይ አውለበለበበት። እንግዴህ በአብዛኞቹ የአፍሪቃ ክፍለ አገሮች እንደተደረገ ሁሉ፣ በኢትዮጵያም የባሕሯን ጠረፍ ለመያዝ ፊታውራሪዎቻቸው ሁነው የአውሮጳን ቅኝ ገዢዎች እየመሩ የመጡት፣ የየአገራቸው ቀሳውስትና ነጋዴዎች ነበሩ። የተገዙት መሬቶች ምንም ቅንጣቢ ቢሆኑም፣ ያገራችን ምሳሌዊ አነጋገር “ፈረንጆች እንደመርፌ ይገቡ፣ እንደዋርካ ይሰፉ” እንደሚለው፣ ቀስ በቀስ አካባቢውን ገፍተው እየያዙ በመንሰራራት በአድዋ ጦርነት የራሷን የኢትዮጵያን የልዕልናዋንና የነፃነቷን ህልውና እስከመፈታተን በቁ።
ኢጣልያኖችንም ከአፄ ምኒልክ ጋር በውጫሌ እንዲደራደሩ ያነሣሣቸው የበርሊኑ ጉባኤ ውሳኔ እንደነበር ከቶውኑ አያጠራጥርም። ውሉንም ያካሄደው አንቶኔሊ፣ንጉሡ እንደቅርብ ወዳጃቸውና አማካሪያቸው ያዩት የነበረው የካቶሊኩ የአቡነ ማስያስ የቅርብ ዘመዳቸው ነበር። አፄ ምኒልክ ከዚህ ዕውቅናና ቅርበት የተነሣ ያታልለኛል ብለው እንዳላሰቡ የሚያጠራጥር አይመስለኝም። በአንቶነሊ እምነት መሠረት፣ የውጫሌ ውል ለኢጣልያን የበርሊኑን ጉባኤ የመጀመርያውን ውሳኔ አሟልቶላታል። የሁለተኛውን ውሳኔ ግብ ለመምታት ግን የውሉን አንቀጽ ዐሥራ ሰባት ትርጒም ማወዛገብ ግድ ሆነበት፤ አለበለዚያማ ኢጣሊያን ምኑን ይዛ ናት፣ ኢትዮጵያ የኢጣሊያን መንግሥት ጥገኛ ግዛት ናት ብላ የበርሊኑ ውሳኔ በሚጠይቀው መሠረት ለታላላቆቹ የአውሮጳ መንግሥታት የሚታስታውቀው። ኢጣልያኖች ልበቅኑ ቢሆኑማ ኖሮ፣ የዉሉ አንቀጽ ዐሥራ ዘጠኝ፣ “የተደረገው ውል በአምሐርኛና በኢጣልያንኝ ቋንቋ ትክክል ሁኖ’ መገልበጥ አለበት ይል የለም እንዴ። ትክክል ካልሆነ ማስተካከል እንጂ ምን ያነታርካል፤ ለምንስ ወደጦርነት ይኬዳል። በዚህ ረገድ አፄ ምኒልክም ቢሆኑ ሊፈራረሙ የወሰኑት በንጹሕ ልባቸው ነው ብሎ ማሰቡ የሚያዋጣ አይመስልም። ንጉሡ ገር ቢመስሉም፣ አርቆ የማስብና ነገርን በሰፊው አጥልቆ የማመዛዘን፣ የሚያዋጣቸውንና የማያዋጣቸውንም አቅርቦ የማየት ከፍተኛ ስጦታ ያላቸው መሆኑን በጊዜአቸው የነበሩት የውጭ አገርም ሆኑ ያገር ውስጥ ጸሐፊዎች ይመሰክራሉ። በዚህ አንጻር ሰንመለከት፣ ውሉ፣ ኢትዮጵያን ለማጥቃት ከፍተኛ የተቀነባበረ ሤራ በየአቅጣጫው በኢጣሊያንና በሌሎች አውሮጳውያን እየተሰነዘረ መሆኑን ተገርመው አይተው በመገንዘብ፣ አደጋውን ለመጋፈጥ እስኪዘጋጁ ድረስ ጊዜ ለማግኘት ያህል ብቻ ብለው ያደረጉት ሊሆንም ይችላል ማለቱ ከሐቅ የራቀ አይመስልም። የአድዋ የክተት አዋጃቸውም ሆነ፣ ከዚያም በፊት ለአውሮጳ መንግሥታት የአገራቸውን የድንበር ወሰን እየዘረዘሩት የላኩት ደብዳቤ፣ ግባቸው ይኸ መሆኑን ያሳያል። ከላይ የተጠቀሰው ዘታይምስ ጋዜጣም “ኢጣሊያኖች ያሳመኑት መስሏቸው ሲታለሉ፣ ምኒልክ ግን ተገቢውን ዝግጅት ያደርግ ነበር” ሲል ይኸንኑ አሳብ ያጠናክራል። የማታ ማታ ግን፣ ከሳቸው በፊት አፄ ዮሐንስ የሂወት ውል በመባል የሚታወቀውን ስምምነት በመፈረም፣ የእንግሊዞች የተንኰል ሰለባ እንደሆኑ ሁሉ፣ አፄ ምኒልክም በውጫሌ ውል ኢጣሊያኖች ያታልሉኛል ብለው የተጠባበቁ አይመስልም። ልክ እንዳፄ ዮሐንስ፣ ጉዱን ያወቁት ቈይተው ነው ማለት ይቻላል።
በአፄ ምኒልክ አሻፈረኝነት ኢጣሊያኖች በሰላም ሊፈጽሙት የፈለጉት ኢትዮጵያን ግዛታቸው የማድረግ ተግባር ለመጨናገፍ ስለደረሰ፣ ሦስተኛውን የቤርሊንን ጉባኤ ውሳኔ በግብር ለማዋል፣ ኀይል መጠቀምና ወደጦርነት መሄድ የግድ ሆነባቸው። አንቶነሊ፣ ኢቴጌ ጣይቱን አማርኛውን ትተው፣ በፈረንሳይኛ የተጻፈውን ውል ይመልከቱ ቢላቸው፣ ኀይለኛዋ ንግሥቲቷም፣ “እኛ እምናውቀው በአማርኛ የተጻፈውን ነው እንጂ የፈረንጅ ቋንቋ አናውቅም። አንተ ግን ቋንቋችንን ስለምታውቅ እየው” ቢለው ቢመልሱለት፣ የዉሉን ወረቀት ቀዶ ሲያበቃ፣ “የኢጣሊያ መንግሥት ውሉን በጦር ኀይል ታስከብራለች” አላቸው። በኢጣሊያኖች እይታ ኢትዮጵያ እንደተረዳችው፣ ዉጫሌ የወዳጅነትና የንግድ ስምምነት ሳይሆን የአገርን ልዕልናና ነፃነት በሰላም አሳልፎ የመስጠት ነበር ማለት ይቻላል። በኢጣሊያኖች አስተያየት፣ ይኸ ካልሆነ ደግሞ ለኢትዮጵያ መዘዙ ጦርነትና ተሸንፎ መዋረድ ነበር። ነገሩ እንዴት ጥቊር ዘር ለነጭ ዘር አልገዛም ይላል ነው። በዘመኑ የነበሩትን የነጮችን አስተሳሰብ እጭንቅላታቸው ውስጥ ገብተን እንደነሱ ማሰብ ከቻልን፣ በኢትዮጵያ እምቢተኝነት ኢጣሊያኖች በጣም ሳይገረሙ አልቀሩም። ስለዚህም ነው ሌሎቹ አውሮጳውያኖች በኻያ አምስት ዓመት ውስጥ መላዪቷን አፍሪቃን ለመያዝ እንደበቁ ሁሉ፣ እነሱም ኢትዮጵያን በጥቂት ሰዓታት፣ ገፋ ቢልም ደግሞ በቀናት ውስጥ፣ ከሥራችን እናደርጋታለን ብለው በማሰብ የተነሡት። ግን አልሆነላቸውም። ኢትዮጵያውያን ለመጀመርያ ጊዜ እስከአፍንጫቸው ድረስ ታጥቀው የመጡባቸውን ነጮች፣ ራሳቸው በሠሩት ጠመንጃና ጦር አወደሟቸውና አሳፈፍረው ሸኟቸው።
ፈረንጆች በአድዋ በጥቊር ሕዝብ መሸነፍ ዱብ ዕዳ ሁኖባቸው ያልታሰበ ከፍተኛ ራስ ምታት ፈጠረባቸው። የተለያየ ማደንዘዣም ሆነ ማስታገሻ ፈልገው ሊታከሙና፣ ከበሽታው ሊገላገሉ ይኸም ካልሆነ ደግሞ በሽንገላም ቢሆን ሊፈወሱ ሞክረዋል። ከዚህም የተነሣ ለአድዋ ድል የተለያየ ትርጒም እየሰጡ በጥቁር ኀይል እንዳልተሸነፉ ለማስረዳት ታጥቀው ተነሡ። አንዳንዱ የአድዋ ድል የሚያሳየን የኢጣልያኖችን አለመታደል እንጂ እንደሽንፈት መቈጠር የለበትም አለ። አንዳንዱ ደግሞ ጥፋቱን በመሪው በጦር መኰንኑ ጀኔራል ባራቴሪ ችሎታ ማጣትና፣ በኤርትራ ባንዳዎች በተለይም የኢጣልያን ሰላይ በነበረው በአቶ አውዓሎም ክሕደት ጫንቃ ላይ ጫነ። ሌሉቹ ደግሞ ኢጣልያኖች አካባቢውን በደምብ ካለማወቃቸው የተነሣ ግር ስላላቸውና የጦር ሜዳው ጐጣጐጥነትና ኰረኰንችነት ለኢትዮጵያውያን አመቺ ስለነበር ነው አሉ። ገለልተኛ ሁኖ ለሚሰማ፣ እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች በግልጥ የሚያሳዩት ኢትዮጵያውያን ጣልያንን ያሸነፉት በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን በጥበብም በብልሃትም ጭምር መሆኑን ነው። ፈረንጆች ግን የነጭ ዘር በእውነት አልተሸነፈም ለማለት ይኸን ሁሉ ምክንያት ሲፈጥሩና ሲክቡ፣ ንግግራቸው የግርምቢጦሽ መሆኑ የታየላቸው አይመስልም። የኢትዮጵያውያን የጦር መሪዎችና ወታደሮቻቸው፣ መማር ቀርቶ የጦር ትምህርት ገበታ ምን እንደሆነ እንኳን ሰምተውም አይተውም አያውቁም፤ ያሸነፉት ጦር ግን ባለም ከፍተኛ ናቸው በሚባሉት የጦር ትምህርት ቤቶቻቸው ገብተው ተምረው በተመረቁት፣ እንደነጄኔራል ባራቴሪና ኤሌና በመሳሰሉት፣ ከፍተኞች የኢጣሊያን ጦር መኰንኖቻቸው የሚመራውን ጦር እንደሆነ ተረሳ። ምንም የስለላ ምርምርና ጥናት ያልቀሰሙት ኢትዮጵያውያን፣ በስለላ ተግባር ከፍ ያለ ዕውቀትና ትምህርት ያመረቱትና እሳት የላሱት ኢጣልያኖች ለራሳቸው እንዲሰልሉላቸው ብለው የቀጠሯቸውን ሰላዮችንና አስተርጓሚዎቻቸውን ራሳቸውን መልሰው በቀጣሪዎቻቸው ላይ ተጠቀሙባቸው። እንግዴህ እነዚህ በነጮች ልዕልና አንጐላቸው የተበረዙት አውሮጳውያን ለኢጣልያን ሽንፈት ምክንያት ነው ብለው የሚቀባጥሩት ምክንያቶች የሚያስረዱን ምን ያህል ኢጣልያንን የሚያዋርዱ፤ የኢትዮጵያውያንን ችሎታና ዕውቀት የሚያሞግሱ መሆኑን የተገነዘቡት አይመስልም። የአካባቢውን ዕውቀት በተመለከተ፣ የኢትዮጵያስ ጦር ቢሆን፣ ጭብጥ እንኳን የማይሞላ ካካባቢው ከተመለመለው ጦር ካልሆነ በስተቀር፣ አብዛኛው በጣም ሩቅ ከሆነ ከዳር አገር፣ ማለትም ከደቡብ፣ ከምሥራቅና ምዕራብ፣ ከመስዕና አዜብ፣ ከሊባና ባሕር በክተት የተሰበሰበና፣ ምንም ዐይነት በትምህርት የገበየ የሥነምድር ዕውቀት የሌለው አይደለምን። አመካኞቹ ሽፋፍነውና አድበስብሰው ሊያልፉ የሚፈልጉት እኮ፣ ይኸ መሃይምን ጦር ልክ ከኢጣልያኑ እኩል፣ ላካባቢው እንግዳ ለመሬቱ ባዳ ሁኖ ሳለ፣ በመሬት ካርታ ሥራና በምድር አቀማመጥ ጥናትና ምርምር የተራቀቀውን፣ የኢጣሊያንን ጦር በዕውቀትም በብልሃትም በልጦት ተገኘ ነው። ታዲያ በተቻላቸው መጠን ሊሸፋፍኑት የሚሞክሩትም፣ በግልጥ እንዲህ መናገሩ ከልክ በላይ የሚያሳፍር እንደሚሆንባቸው ስላወቁ ነው ማለቱ ይቀላል። ሐቁ ግን ፍርደ-ገምደልነታቸውን ነው ፍርጥ አድርጎ የሚያሳየው።
ፈረንጆች የሰጡት የኢጣልያን መሸነፍ ምክንያት ከላይ በተጠቀሱት ብቻ አላቆመም። ጥቊርነታችንን ክደው ፈረንጆች እስከማድረስም ደርሰዋል። በዘር ሐረግ ወንድሞቻቸው እንደሆንን በተራቀቀ ጥናትና ምርምር ለማረጋገጥ በቅተዋል። የኒው-ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በድሉ ማግሥት “እጅግ የታደሉ አፍሪቃውያን” በሚለው አርእስት ያወጣው የነጭነታችን መሠረትና ከአውሮጳውያንም ጋር ያለንን የዘርማንዘር ዝምድነታችንን እንዴት እንደሆነ እንደሚቀጥለው አድርጎ ይገልጣል።
“ኢጣልያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከአበሾች ጋር ያጋጠማቸው ሁናቴ የሚያመለክተው እነዚህ በአፍሪቃዋ እስዊዘርላንድ በሆነችው ተራራማ አገር የሚኖሩት አፍሪቃውያን፣ አውሮጳውያን ቅኝ ግዛት ሲይዙና ሲቀረማመቱ ካጋጠሟቸው ጨለማ በለበሰው በአፍሪቃ ክፍለ አገር ከሚኖረው ከሌላው ጥቊር ሕዝብ የበለጠ ዘር መሆኑ በፍጹም አያጠራጥርም። መብለጣቸውም ከጥንተ ትውልዳቸውና ከዘር ሐረጋቸው ጋር የተያያዘ ነው። ያሁኑ ዘመን ኢትዮጵያውያን ከጥንት ወግና ታሪክ ሲወርዱ ሲዋረዱ የመጡ መሆናቸው ቢታመንም፣ ሐቁ ግን ከቶውኑ ኢትዮጵያውያኖች
ማለትም ጥቊሮች አይደሉም። ታዲያ በጥራታቸው ልክ ከአንግሎሳክሶኖችና ከኬልቶች በምንም ዐይነት የማይተናነሱ ጥርት ያሉ የነጭ ዘር ናቸው። ቋንቋቸውም ሆነ የአካላታቸው ቅርጽ፣ የሴማውያን ዘር አካል ያደርጋቸዋል፤ ማለትም ታሪክ ከሠሩት ከጥንቱ ባቢሎናውያንና አሶርያውያን፣ ሶርያውያንና አይሁዶች ጋር ይዘማመዳሉ። በጥቊርነታቸው ላይ ብቻ ተመሥርቶ ኢትዮጵያውያን ብሎ መጥራቱ ትልቅ ስሕተት ነው። ስሕተቱ የመነጨው ምናልባት ጥንት በሮማይስጥና በጽርዕ ሥነ-ጽሑፎች ከግብፅ ውጭ የታወቁት የአፍሪቃ ሕዝብ እነሱ ብቻ በመሆናቸው ሲሆን፣ ከዚያ ተነሥቶ “ኢትዮጵያ” የሚለው ቃል ቀስ በቀስ አፍሪቃውያንን በሙሉ ለማመልከት በጥቅም ላይ መዋል ጀመረ። አሁን ግን በመላው የአፍሪቃ ክፍለ-አገር ውስጥ የጥቊር ዘር አካል ያልሆነ ይኸ ሕዝብ ብቻ ቢሆንም፣ [ኢትዮጵያ] የአገራቸው መጠርያ ስም ሆኖ ቀርቷል። እንደሐቁ ከሆነ ግን፣ አበሾች ከጥንት ጀምሮ በፍጹም የአፍሪቃ ዘርነት የላቸውም። የጥንት ትውፊታቸውም ቢሆን ከደቡብ ዐረብ እንደመጡ ያመለክታል፤ መልካም አጋጣሚ ሆኖ፣ እስካሁን ድረስ [በነጮች] ወዳልታሰሰ ወዳንድ የደቡብ ዐረብ አውራጃ ለምርምር ጥናት አራቴ ሄዶ የነበረው የጀርመን መንገደኛ ኤድዋርድ ግላሰር ከክርስቶስ በፊት አበሾች በነዚህ አውራጃዎች ይኖሩ እንደነበረ የሚያመለክት ምንም የማያከራክር ማስረጃ እዚያው አግኝቷል።”
ነገሩ ቀልድ ነው እንዳንል አውሮጳውያን በጒሮሯችን ሊወረውሩ የሚፈልጉትን በሙሉ በምርምር አሳብበው እየፈለፈሉ እየሰጡን ሊያሳምኑን ደርሰዋል። ጋዜጣው ይኸንን በሚጽፍበት ዘመን ለምሳሌ የሰውን ጠባይ አጥኚ ነን ባዮቹ የዕውቀት ተመራማሪዎቻቸው (አንትሮፖሎጂስቶች) የጥቊር ሕዝብ ጭንቅላት ከውሻ ጭንቅላት እንደማይበልጥ የጠለቀና የተራቀቀ ምርምር አድርገን በማያወላውል ተጨባጭ ማስረጃ ደርሰንበታል ይሉ አልነበረም ወይ። የቅኝ ግዛትም አሳብ የተጠነሰሰውና እንደ መርህ አድርጎ የተከተለው በዚሁ ዐይነት ማስረጃ በመተማመን ነበር ማለት ይቻላል። ለትዝብት ያህል ብቻ ላንሣውና የዘር አመጣጣችንን በተመለከተ ሌላ ይበልጥ አስተማማኝ የሚባል አስተያየት እንዳለም አለመርሳት ይገባል። በህንድ አገር በጀብዱነታቸውና በአስተዳደር ጥበባቸው የታወቁት ሐቢሽስ የተባሉ ሰዎች፣ በባርነትና በሌላም ረገድ ከአፍሪቃ የሄዱት ሲሆኑ፣ በዘራቸው ኢትዮጵያውያን ናቸው ይባላሉ። የግላሰርን አሳብ ከተከተልን፣ የኢትዮጵያዉያን ዘራቸው ለምን ከነዚሁ ሐቢሽሶች መጣ አንባልም። እንዲያውም ግላሰርን በሁለት ሺ ዓመታት ቀድሞት የኖረው አፖሎንዮስ ዘትያኖና፣ እንዲሁም ታላቁ የቤተክርስቲያን ባለታሪኩ ኤውሳብዮስም ጭምር፣ “ኢትዮጵያውያን ጥንተ ዘራቸው ከህንድ ፈልሰው ወይንም ተልከው መጥተው በዐባይ ሸለቆ ስፋሪዎች ሲሆኑ፣ በጥበባቸውም የሚከተሉት አባቶቻቸውን [ህንዳውያንን] ነው” በማለት ስለሚደግፉን ከግላሰር ፈጠራ ይልቅ ማስረጃው በትውፊት የተመሠረተ ቢሆንም የነሱ አፈ-ታሪክ የሚሻል ይመስለኛል።[2]።
ወደዋናው ነገር እንመለስና ነጮች ራሳቸውን ሊያባብሉ ሲሉ በጥቊር ዘር አለመሸነፋቸውን ለማሳየት ያመጡት የ”አበሻ”ና የ”ኢትዮጵያ” ትርጒምና የዘር አመጣጥ፣ መዘዙ ከነሱ አልፎ ለኛም ተርፏል። አሁን በሥልጣን ያለው መንግሥትም ሆነ፣ በአውሮጳያን የትምህርት ገበታ ተምረው ሲያበቁ፣ የጐጥና የጐሣ መሪዎች የሆኑ አጃቢዎቹ ፖለቲከኞችም፣ ይኽንን የተረት ታሪክ በሰፊው እየተጠቀሙበት ናቸው ማለት ይቻላል። ከነሱም አልፈው አንዳንድ ሁሉን ዐወቅን ባዮች የዩኒቬርሲቲ ምሩቃኖችና ምሁራኖችንም ጭምር፣ እንዲሁም የበላይነት ስሜት አራጋቢዎችና ምናብን ከሐቅ የመለየት ችግር ያላቸው ወሽካቶች ሳይቀሩ ይኸንን ዐይነት አሳብ ያነበንቡታል። ፈረንጆች ጥቊሮችን በመናቅ ያመጡት ወጥመድ ላገራችን ተርፎ ምስቅልቅላችንን እያወጣ መሆኑ ለብዙዎቻችን ግልጥ እየሆነ እንዳለ አልጠራጥርም። በጦር ሜዳ ማሸነፍ ያቃታቸው፣ ባመጡት ያሳብ መርዛቸው ግን ድል ለማድረግ ምንም አልቀራቸውም። ተዘርረን እጃችንን ባንሰጥም፣ ታላቅ ጉዳት አድርሰውብናል፤ እያደረሱብንም ናቸው ማለት ይቻላል። ከፈረንጅ ባገኘው ትምህርትና ምርምር መላቅጡ የጠፋበት፣ አእምሮው የዞረበት ተማርሁ ነኝ ባዩ ትውልድ፣ በሃይማኖትና በትውልድ፣ በባህልና በቋንቋ፣ በንግድና በሰፈራ ለዘመነ አዝማናት ተዋሕዶና ተሳስሮ የኖረውን ሕዝብ ሴማውያንና ኩሳውያን፣ መጤና አገር-በቀል፣ አቈርዝቋዥና ተቈርቋዥ እያሉ በመፈረጅ ባገሪቷና በሕዝቧ ከፍተኛ ጥቃት አድርሰዋል፤ እያደረሱም ናቸው። አጉል ትምህርትም ማለት ይኸ ነው ቢባል ሐሰት አይሆንም።
አድዋን ድል በተመለከተ ፈረንጆች ሊቀበሉት ያልፈለጉት ነገር ቢኖር ኢትዮጵያውያን ያሸነፉት፣ በጦርነታቸው ስልትና ቅንጅት፣ ባሳዩት ትብብርና ጀብዱ፣ ካላቸው ያገር ፍቅር፣ ስሜትና ወኔ የተነሣ፣ የሚወዷትን አገራቸውን ከጠላት እጅ ለመከላከል ደማቸውን እስከማፍሰስ አጥንታቸውን እስከመከስከስ ድረስ፣ ቈራጥ ሕዝብ መሆናቸውን ነው። እነሱም ሆኑ፣ፈረንጅ በተጀነነበት ዘመን የነበረው ያስተሳሰብ ፈሊጥ፣ ጥቊሮችና ሌላውም እነሱን በመሰለ የሥልጣኔ ደረጃ ያለው ሁሉ፣ ሰብአ ትካት እንደመሆናቸው ከበረኻ አውሬ ስለማይለዩ፣ በጐሣና በጐጥ ደረጃ እንጂ፣ እንደሠለጠነው ሕዝብ የተራቀቀና የመጠቀ የአገር ፍቅር ይቅርና ፅንሰ አሳቡም፣ ስሜቱም የላቸውም የሚል ነበር። ልክ የዱር ወይንም ያልተገራ አውሬ ቢነካ ማለትም ቢጠቃ ላይሞት ወይንም መኖርያውን ላይለቅ ሲል፣ ዐጸፋውን የሚመልሰው የደመ-ነፍስ ጉዳይ ሁኖበት እንጂ፣ ስለራሱም ሆነ ስለመኖርያው አስቦና አሰላስሎ፣ ጥቅሙንና ጉዳቱን ተረድቶ አይደለም። እንደምዕራባውያን አስተሳሰብ፣ ነጮች ያልሆኑትም አገራቸው በነጭ ዘር ሲያዝባቸው የደመ-ነፍስ ጉዳይ ሁኖባቸው ሊከላከሉ ይንፈራገጣሉ፣ ይንፈራፈራሉ እንጂ ላገርና ለነፃነት ብለው አይዋጉም የሚል አሳብ ነው ተጠናውቶባቸው የነበረው። ኢትዮጵያውያንም ተፈርጀው የነበሩት በዚሁ መልክ ነበር። በነሱ አስተሳሰብ፣ ኢትዮጵያዉያን ከሥልጣን ሽኩቻና ከግል ጥቅም ውጭ ትብብርና አንድነት ምን መሆኑን በማያውቁ ባላባቶች የሚመሩ የጐሦች ጥርቅማጥርቅም ናቸው። ባላባቶቹ ከንጉሥ ሥር ቢሆኑም፣ በኀይል ብቻ የሚገዙ ስብስብ እንደመሆናቸው፣ ዕድልና ጉልበት ካገኙ ወዲያውኑ መሸፈትና የራሳቸውን ሥልጣን ማደላደል እንጂ ለከፍተኛ ባለሥልጣን መታዘዝ፣ ለሕግ መገዛት፣ ላገር መቆም ወደሚል ፅንሰ-አሳብ ገና አልደረሱበትም የሚለው ፈሊጥ በጣም ተጠናውቶባቸው ነበር። ስለዚህም አፄ ምኒልክን ለመጣልና አገሩን ለመከፋፈል ካቀዱት በርከት ካሉ ዘዴዎች ዋና የነበረው፣ ክርስቲያኑ እስላሙን እንዴት እንደጨቈነ፣ ‘ጋላ’ው በአማራው እንዴት እንደተበዘበዘ፣ ትግሬው በሸዋው ሥልጣኑን እንዴት እንደተቀማ ማጉላት ነበር። በአምባላጌ ጦርነት ከተሸነፈ በኋላ እጁን ለጥቊር እንዳይሰጥ ነፍሴ አውጪኝ ብሎ ሲሸሽ በኋላ ኢትዮጵያውያን እያሳደዱት የገደሉት ቶሰሊ የተባለው የጦሩ መሪ መኰንን ወደዚህ ተራራ ሊሄድ የወሰነው፣ ሰሜንንና ደቡብን የሚያገናኝ መንገድ የሚያልፈበት ያገሩ እንብርት መሆኑ ስለታወቀበት ነበር። የቶሰሊ ዕቅዱና ምኞቱ እጣሊያን ተራራውን ቢቈጣጠር፣ የትግሬና የበጌምድር ሕዝብ ዐምቆት የያዘው የአፄ ምኒልክ ጥላቻ ፈንድቶ ይነሣና፣ ያካባቢው ባላባቶች ነፃነታቸውን ያውጃሉ። ምኒልክም ሊወጋቸው ቢቃጣ የሱ ጦር መክቶ ድራሹን ያጠፋውና ኢጣልያም አገሩን በቀላሉ በእጇ ታስገባለች ብሎ ነበር። እንደተጠባበቀው የአፄ ምኒልክ መንግሥትም አልወደቀም፣ ኢትዮጵያም ነፃነቷን አልተገፈፈችም። እሱ ራሱ የአካባቢው ሕዝብ በጠላትነት ያየው እጣሊያንን እንጂ አፄ ምኒልክን እንዳልሆነ ብዙም ሳይቈይ ቶሎ ብሎ ተረዳ።
የአድዋ ጦር ባፄ ምኒልክ ባይመራ ኖሮ፣ የአገሪቷ ዕጣ ከሌሉቹ የአፍሪቃ አገሮች ባልተለየም ነበር የሚል ጽኑ እምነት አለኝ። ካፄ ምኒልክ በፊት አፄ ዮሐንስ፣ ከሳቸውም ቀጥሎ ልጃቸው ራስ መንገሻ በየጊዜአቸው ጣሊያንን ተጋፍጠዉታል። አፄ ዮሐንስ ኢጣልያንን ሲዋጉ ቀርቶ ስማቸው ብቻ ሲጠራ እንኳን የሚያበረግጓቸውና የሚያንቀጠቅጧቸው ራስ አሉላን የመሰሉ ታማኝ የጦር መኰንን ቢኖሯቸውም፣ ልክ አስቀድመዋአቸው እንደነገሡት እንደዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በብልሃትና ዐሪቆና አራቅቆ በማየት እንደአፄ ምኒልክ አልታደሉም። የሦስቱም ጀግንነታቸውም ሆነ አገር-ወዳድነታቸው እንዲሁም ሃይማኖተኝነታቸው በፍጹም የሚያጠያይቅ አይደለም። ሁለቱ የፈረንጆችን ተንኰል ዘገይተውም ቢሆን የተረዱት ቢመስሉም፣ እንደአፄ ምኒልክ ግን በዘዴና በብልሃት ጊዜውን ጠብቆ ጠላትን መምታትን ሆነ፣ የኢትዮጵያንም ሕዝብ በፍቅርና በብልሃት ሊያስተዳድሩና ሊመሩ፣ ተቀናቃኞቻቸውንም ባላባቶች በወዳጅነትና በጥበብ ሊይዟቸው አልቻሉም። በአድዋ ጦርነት ጊዜ ኢትዮጵያ እንደአፄ ምኒልክ መሪ በማግኘቷ በጣም ዕድለኛ ናት ያሰኛል[3]። በዚህ አንፃር ሲናይ፣
“ምኒልክ ተወልዶ ባያነሣ ጋሻ፣
ግብሩ ዕንቊላል ነበር ይኸን ጊዜ አበሻ።”
የሚለው አነጋገር እውነትነት አለው ማለት ይቻላል።
አፄ ምኒልክ የኢትዮጵያን ዘመናዊ አንድነቷን ባደላደሉ በሰባት ዓመት ውስጥ ነው እንግዴህ ሕዝቡን በአስገራሚና ሊታመን በማይቻል መንገድ ተባብሮ እንዲዋጋና ድል እንዲቀዳጅ ያደረጉት። ሠራዊቱ የተዋጋው ላገሩ ነፃነት ብቻ ሳይሆን በአፄ ምኒልክም ፍቅር ተነሽጦ ነበር ማለት ይቻላል። ንጉሠ-ነገሥቱ ባስተላለፉት የክተት ዐዋጅ
“ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም። አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ርዳኝ፤ ጉልበት የሌለህ ደግሞ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሐዘን ርዳኝ።”
ሲሉ ሕዝባቸው ያስተዳደራቸውን ቅንነትና ጥሩነት አይቶ ለሳቸውም ሆነ፣ ከልብ ለሚንሰፈሰፍላቸው ነገሮች፣ ማለትም ላገር፣ ለሃይማኖት፣ ለልጅና ለሚስት ፍቅር፣ እስከጦር ሜዳ እንዲከተላቸው ሕይወቱን እስከመስጠት እንዲዋጋላቸው ነው የሚጣሩትና የሚለምኑት ያሉት።
እስኪ ያለፈውን በጭካኔው የታወቀውን የደርግን መንግሥት በጐን እንተወውና፣ “ሕዝብን እወክላለሁ፣ በሕዝብ ተመርጫለሁ” እያለ በየጊዜው የሚለፈልፈው ያሁኑ መንግሥት፣ ደፍሮ “ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም። አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም።” ሊል ይችላል ወይ ብለን እንጠይቅ። በብዙዎቻችን ግምትና እምነት በፍጹም የሚታሰብ አይመስለንም። ቢልም ካይነ-አውጣነትና ከትዝብት በስተቀር ሌላ ትርፍ ሊኖረው አይችልም። በርግጥ በጭቈና ሥር ያለ ሕዝብ አሳቡን በነፃ ለመግለጥ ባለመታደሉ ምርጫ አጥቶ ዝም ቢልም፣ በሚሰማው በሌላው ዓለም ዘንድ ግን ከትዝብት ውጭ የሚያተርፍ ነገር አይኖርም።
አፄ ምኒልክ ግን በጥበብና በፍቅር እንደሚያስተዳድሩ፣ ሕዝቡም እንደሚወዳቸው ሌላው ቀርቶ ጠላቶቻቸው በመሆናቸው ስለሳቸው ጥሩነት አይናገሩም የሚንላቸው አውሮጳውያን እንኳን ሳይቀሩ፣ ባድናቆትና በሙገሳ ደጋግመው ይናገራሉ። ንጉሠ-ነገሥቱ ደግ ብቻ አይደሉም፣ ብልጥም ነበሩ። እሳቸውም መኳንቶቻቸውም የአድዋን ድል ሊቀዳጁ የቻሉት ፈረንጆች በተንኰልና በሽንገላ ቢመጡባቸው፣ ተንኰልን በተንኰል፣ ጦርነትን በጦርነት ዐጸፋውን በመመለስ ነው። ከዚህ በላይ እንደተጠቀሰው፣ የለንዶኑ ዘታይምስ “ኢጣሊያኖች ንጉሡን ያሳመኑ መስሏቸው ሲታለሉ፣ እርሱ ግን በመሣርያ እየተዘጋጀ ቈይቶ፣ ዐጸፋውን ሰጣቸው” ሲል የንጉሠ-ነገሥቱ ሥራቸው በዘዴና በዐሪቆ አሳቢነት የተመራ ነበር የሚለውን አስተያየት ያጠናክራል። ጣሊያኖችም ሲጽፉ “ምኒልክ ከቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ ነገሥታት የሚለየው ነገር ቢኖር፣ ሁካታ ባለበት በድል ሰዓት፣ በተሸናፊዎቹ ላይ አይጨክንም ብቻ ሳይሆን የምሕረት እጁንም ለጠላቱ መዘርጋቱ ነው” ብለው ጽፈዋል። እንግዴህ ንጉሡ እንደልበ-ስፊ መሪ ተብለው የሚደነቁት በወዳጆቻቸው ዘንድ ብቻ አይደሉም፤ በጠላቶቻቸውም ጭምር እንጂ።
አፄ ምኒልክ ታላቅ መሪ መሆናቸው ቊልጭ ብሎ የሚታየው ከቀደሟቸው መሪያቸው ከአፄ ዮሐንስ ተግባር አንፃር ሲናያቸውም ጭምር ነው። ኋላ እንደምናየው ከኢጣልያን ጋር ጦርነት ለመጀመርያ የተፋለሙት አፄ ዮሐንስ እንጂ አፄ ምኒልክ አልነበሩም። ንጉሠ-ነገሥቱ ራስ አሉላ ኢጣሊያንን በዶጋሌ ወግተዋቸው፣ ለወሬም ሳያስቀሩ በመደምሰሳቸው እንደመሸለም ፈንታ ገሠጿቸው ብቻ ሳይሆን፣ ቈይተው ከሹመታቸውም እንዳነሧቸው ይታወቃል። ጣሊያኖች ያንን
“እንደቀትር እሳት ቱርክን ገላመጠው፣
ጣሊያንም ወደቀ እያንቀጠቀጠው፣
አጭዶና ከምሮ እንደጭድ አሳጣው።”
ተብሎ በተቀኘለት ጀግና ላይ አፄው ይኸን በማድረጋቸው ደስታውን አልቻሉትም። ተሽቀዳድመው ኻያ ሺ ጦር በመላክ ሰሓቲን ቢይዙና የማይደፈር ምሽግ ሠርተው ቁጭ ቢሉ፣ አፄ ዮሐንስ የአፄ ምኒልክን በሁለት ዕጥፍ ያህል የሚበልጥ ወደሁለት መቶ ሺ ሠራዊት ይዘው ሊዋጉ ብቅ አሉ። በለሳቸው ቀንቶ ደግሞ፣ ክደዋቸው ለኢጣልያን አድረው የነበሩ፣ የኢጣሊያንም ታማኝ ባለሟል በመሆናቸው ምሥጢራቸውን ብቻ ሳይሆን ዐቅማቸውንና ዕቅዳቸውን ሁሉ የሚያዉቁ፣ ደጃዝማች ደብብ የተባሉ ዘመዳቸውም በደምብ ከታጠቀ ሠራዊታቸው ጋር ሁነው ሊረዷቸው ገቡላቸው[4]። አፄ ዮሐንስ ይኸንን ሁሉ ዕድል አግኝተው ኢጣሊያንን ወደምፅዋ ተመልሳችሁ ሂዱ እያሉ ሁለት ደብዳቤዎች ከመጻፍና ለሁለት ወር ያህል ከማፋጠጥ ውጭ ሌላ ምንም የረባ ነገር ሳይሠሩ ተመለሱ። ያውም የሆነው እንደአፄ ምኒልክ በረጅም መንገድና ጒዞ ሳይወጠሩ፣ የስንቅና የቀለብ ችግር እምብዛም በማያሳስባቸው፣ በገዛ ግዛታቸውና ቤታቸው ውስጥ ነበር ማለት ይቻላል።
አፄ ምኒልክ በብልህ መሪነታቸው በአድዋ ለኢትዮጵያ ድል ቢያጐናፅፏትም፣ የተዋጋውና ለድሉ ያበቃው ግን በአዲስ መልክ ያቋቋሙት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ድሉም የሕዝቡ የአንድነቱ መግለጫ፣ የማንነቱ ማረጋገጫ ሆነ። ሠራዊቱ በጣም ሩቅ ከሆነው አገር ጀምሮ፣ ከተለያየ ኅብረተ-ሰብ ከያንዳንዱ መንደር የተወጣጣ ጦር ነበር። በዚህ የመጀመርያው የአንድነቱና የአገሩ ነፃነትና ልዕልና ፈታኝ ጦርነት ያልተሳተፈ አልነበረም ማለት ይቻላል። ጐጥና ጐሣ፣ ቋንቋና ሃይማኖት፣ ጨዋና ባለጌ፣ ዕድሜና ፆታ ሳይለይ፣ ወንድና ሴት፣ ልጅና ሽማግሌ፣ ተራና መኰንን፣ ባለዳባና ባለካባ፣ እስላምና ክርስቲያን ሳይባል፣ ከስሜኑና ደቡቡ፣ ከምሥራቁና ምዕራቡ፣ ከመስዑና አዜቡ፣ ከባሕሩና ሊባው፣ ሁሉም ከየመጣበት ቀዬው በኢትዮጵያዊነቱ፣ በአገር ልጅነቱ ብቻ ቁሞ፣ ደረቱን ለጦር፣ እግሩን ለጠጠር በመስጠት፣ በዠግንነት ተዋግቶ አጥንቱን በመከስከስ፣ ደሙን በማፍሰስ፣ ኅብረቱንና አንድነቱን፣ ወንድማማችነቱና ቤተሰብነቱን ያጸደቀበት ድል ነው[5]። ሕዝቡ ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ በተወለደችበት ማግስት አንድነቱን በደሙ ጥምቀት አጥብቆታል ማለት ይቻላል። ለሚወዱት አገርና ሕዝብ የራስን ሕይወት አሳልፎ ከመስጠት የበለጠ ነገር የለም ብቻ ሳይሆን መተግበርም አይቻልም።
መርሳት የማይገባን ነገር ቢኖር፣ አድዋ መደምደሚያው ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን ኢጣልያንን ድል ያደረጉት አንዴና ሁለቴ ብቻ ሳይሆን አከታትለው በሦስት በተለያዩ ጦርነቶች ነው። መጀመርያ በአምባ አላጌ ሁኖ፣ የሰሜኑን ሕዝብና ባላባቶቻቸውን ካፄ ምኒልክ ጭቈና አገላግላለሁ ብሎ ሊያሳምፅ ተራራውን ይዞ የነበረውን የሕልመኛውን የቶሴሊን ጦር ደምስሰው ብትንትኑን አወጡ። ጨቋኙ ጣሊያን እንጂ ምኒልክ እንዳልሆነ ሊያስተምሩት ደግሞ፣ እርሱን ራሱን ነፍሴ አውጭኝ ብሎ ሲሸሽ አሳድደውት ይዘዉት ገደሉት። ይኸ ድል የኢትዮጵያዉያኖችን መንፈስ አጠናከረ፤ ወኔአቸውን ይበልጥ ቀሰቀሰ፤ ያ፣ ራስ መንገሻን አከታትሎ ሦስቴ በኰዓቲት፣ በሰንዓፈና በደብረ-ሐይላ በማሸነፉ ምክንያት፣ ኢትዮጵያን በሙሉ ባንዴ እመዳፌ ውስጥ አስገባታለሁ ያለው እብሪተኛ መኰንንንና ጦሩን ኢምንት በማድረጋቸው ታላቅ ኩራትና በራስ መተማመን ተሰማቸው።
ኢጣሊያኖች ግን ከዚህ ድል ጠቃሚ ትምህርት እንደመማር፣ የአዙሮ ማየት እንገት አጥተው ልባቸውን አደንድነው ለሁለተኛው ዙር ጦርነት ተዘጋጁ። የአምባላጌ ዐይነት ውድቀት እንዳይገጥመን ብለው፣ በጥቂት ጊዜ ውስጥ የማይደፈር፣ ጠንካራ እርድ በመቀሌ ሠርተው ጠበቁ። በምንም መልክ የማይሸነፉ መሰላቸውና ከፍተኛ እብሪት ተሰማቸው። በምሽጉ መግቢያ ዙርያውን የጠርሙስ ስብርባሪ ተነሰንሶበታል፤ ከዚያም በማከታተል ወፍ እንኳን የማያሳልፉ ሹል ዕንጨቶችና ድቡልቡል የእሾኽ ሽቦ አጥር ተተክለውበታል፤ ቀጥሎ ደግሞ የሦስት ሜትር ስፋት ያለው ካብ ተገንብቶበታል። የኢትዮጵያ ጦር የሚዋጋ አለጫማ በሌጣ እግሩ ቢሆንም፣ጋሻውን እያነጠፈ የጠርሙሱን ስብርባሪ ዐለፈ፤ ግን ወደዕንጨቶቹና ወደእሾኻማ የሽቦ አጥሩ ሲደርስ አብዛኛው በነዚሁ እየተዘነጠለ፣ ከነሱም ያመለጠው የኢጣሊያን መትረየስ እየተርከፈከፈበት እንደወፍ ሬሳ በሹል ዕንጨትና፣ (ያን አልፎት የሄደ ደግሞ) በድቡልቡሉ የእሾህ ሽቦ እየተንጠለጠለ ቀረ። የመቀሌ ምሽግ በሰው ብዛት፣ በወንዶች ጀግንነት፣ ባገር ወኔ፣ በመሣርያ ጥቃት የማይፈታ ሁኖ ተገኘ። የኢትዮጵያን ጦር እየለቃቀመ በጭካኔ በላው፤ ወሽመጥ ቈራጭ፣ ወኔ አቅላጭ ሆነ። ባለቀው ጀግና ብዛት በሐዘን ተውጠው የነበሩት የኢትዮጵያ ፀሐይ በመባል የሚታወቁት እቴጌ ጣይቱ የወንዶቹን ጀግንነት በሴቶች ብልሃት ባይተኩ ኖሮ ወደአድዋ መጓዙ ሕልም ሆኖ ሊቀርም በቻለ። ይሁንና እሳቸው ለሞተ ተዝካሩን ለማዉጣት፣ ልጁን ለማሳደግ፣ ለቀረ ደግሞ ለመሸለም ቃል ገብተው ኢጣልያኖች ለውሃቸው የሚጠቀሙትን ምንጭ ካስያዙ በኋላ ነው ኢትዮጵያኖች ከከፋ ዕልቂትና ከመንፈስ ውድቀት ድነው ወደአድዋ የተጓዙት።
እቴጌም ለውሃ ጠባቂዎቹ፣
ጠጅ በብዙ ቀንድ እየተሞላ፣ በማለፊያ ወጥ እንጀራ እየተፈተፈተ በመሶብ ሁኖ፣ ፍሪዳው ታርዶ ሥጋው በእንቅብ እየሆነ ከሌሊቱ በዘጠኝ ሰዓት ይሰዱላቸው ነበር። ትጥቃቸውን ሳይፈቱ፣ እንቅልፍ ሳይትኙ፣ ለአንድ ቀን የሚያስመርረውን ጦርነት ዐሥራ-ዐምስት ቀን ሙሉ ሌትና ቀን እየተዋጉ፣ ውሃውን ከልክለው፣ በጭንቅ ኢጣሊያኑን ከዕርዱ እንዲወጣ አደረጉት።”
ኢጣሊያኖቹ ከውሃ ጋር ሲጨነቁ፣ ራስ መኰንን ዕድሉን ተጠቅመው ሽቦውን ቈረጡ። ከራስ አሉላም ጋር ከካቡ ሁነው ሠራዊታቸውን ቈሉት። ያ የተማመኑበት ምሽግ ዋጋ-ቢስ ሆነና እጅ ከመስጠት ሌላ ምርጫ እንደሌላቸው ሲረዱ ሁሉም ተማረኩ። እንዴህ ሁኖ በሴቶቹ ጥበብ የተጠናቀቀው የመቀሌ ድል ወደአድዋው መራ።
መምህር አፈ ወርቅ ገብረ ኢየሱስ የአድዋ ድል ምን ያህል የአዲሲቷ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያንድነትና የትብብር ውጤት መሆኑን በሰላ ብዕራቸው ሲገልጡ፣
“የሸዋ[6] ፈረስኛ፣ የጐጃም እግረኛ፣
የትግሬ ነፍጠኛ፣ የአማራው ስልተኛ፣ …
ከእንዝርት የቀለለ የጁዬ፣
ተነብር የፈጠነ በጌምድሬ፣
ተቋንጣ የደረቀ ትግሬ፣
ከአሞራ የረበበ ደቡቤ፣
ከንብ የባሰ ጐጃሜ፣
እያባረረ በየጐዳናው ዘለሰው።
” በማለት የያንዳንዱን አካባቢ ሕዝብ ጀብዱነቱንና ጀግንነቱን ንጥር ምጥን አድርገው በጊዜው ቋንቋ ለታሪክ አስፍረውታል።
የበርሊን ጉባኤ
በቅርቡ ጊዜ የአድዋን ጦርነትንም ሆነ አፄ ምኒልክን አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በሰጣቸው በጐሣ ክፍፍል፣ በፖሊትካው ቅርጽና ዐይን የሚያዩና የሚተረጒሙ እንዳሸን እየተፈለፈሉ መጥተዋል። አብዛኞቹ ግን የገዢው መንግሥት ባለሥልጣኖች ከተወለዱበት አካባቢ የሚመጡና ከነሱም ጋር በሥጋ ወይንም በትግል የተሳሰሩ የትግርኛ ቋንቋ ከሚናገሩ ሰዎች መካከል የወጡ ናቸው ቢባል እውነተኝነት አለው ማለት ይቻላል። እያንዳንዳቸው የሚሉትን ለመናገርና ለመተቸት ፍሬም ጥቅምም የለውም። እንዲሁም
የሁላቸውን ስምና ሥራ መጥቀሱ ዋጋ-ብስ ብቻ ሳይሆን ፍላጎቱም የለኝም፣ ቦታም አይበቃም። ለግንዛቤ ያህል ሁለት ብቻ ላነሣ እወዳለሁ። በመጀመርያ ደረጃ እምቢታ አንፃር ወረርቲ፤ ታሪኽ ሃፀይ ዮሃንስ 4ይ ንጉሠ ነገሥቲ ዘኢትዮጵያ ባለሰፋፊ ገጾች መጽሐፍ ነው። ጸሐፊው የአያሌ የትግርኛ መጻሕፍት ደራሲ ነው በመባል የሚታወቀው መምህር ገብረ-ኪዳን ደስታ ነው። መምህር ገብረ-ኪዳን በግእዝና በቤተ-ክርስቲያን ትምህርት ተኰትኲቶ በማደጉ የመጻፍ ችሎታውን እንዲያዳብር የረዳው ይመስላል። ካልተሳሳትክሁ፣ የመምህርነት ቅጽልም ያገኘው ከዚያው ከቤተክርስቲያን ትምህርት ሙያ ጋር በተያያዘ ዕውቀቱ ነው ብዬ እገምታለሁ። ደራሲው ወያኔ ገና እጫካ እያለ አድሮለት በመጠኑ ካገለገለ በኋላ፣ ከድቶ ወደደርግ መንግሥት ገባ። እሱም በሽፍቶቹ አውራጃ እያዞረው ለስብከቱ ሊጠቀመው ቢሞክር፣ ምንም ፋይዳ እንደማያመጣና ጉዱን የሚያውቀው ያገሩ ሕዝብ ደግሞ የውስጥ ስለላ ሊያካሂድ እንጂ በዉኑ አምኖ አልገባም የሚል ወሬ ቢያናፍስ አገለለው ተብሎ ይወራል። መጽሐፉ ለደራሲው ያልተጠበቀ ዝና፣ በተለይም የመንደሩ ተወላጆች ከሆኑት ባለሥልጣኖች ዘንድ ዕውቅናና ክብር-ቢጤ ስለሰጠው በየመገናኛውና ባንዳንድ የኢትዮጵያውያን ስብሰባዎች ተጋብዞ ሲደሰኩር ታይቷል። ሰፋ ያለ አንባቢና ገቢ እንዲያገኝለት መጽሐፉን ወደብሔራዊ ቋንቋ እያስተረጐመም ነው ይባላል።
ሌላው መጽሐፍ ፍኖተ ገድል ከ1967-1977[7] በሚል ርእስ በአቶ ብሥራት አማረ የተደረሰ ነው። አቶ ብሥራት እንደብዙዎቹ የወያኔ ተከታዮችና ታጋዮች የዐሥራ-ሁለተኛ ክፍል ፈተናውን እንደወደቀ ወደጫካ እንዳመራ ይነገራል። ከዚያም በስለላና አፈና ክፍል ሲሠራ ቈይቶ፣ ድርጅቱ በአፄ ምኒልክ ቤተ-መንግሥት ሲገባ፣ እሱም በአዲስ አበባ ከተማ ተቀጥሮ በነበረበት መስክ እንደቀጠለ ይነገራል። ከዚያም በሙስና ተከሶ ወደአሜሪቃ አመለጠ። እዚያ በፖሊትካ ጥገኝነት ሲኖር ቈይቶ፣ ባንድ ስሙ ካልታወቀ የአሜሪቃ ዩኒቬርሲቲ እያስተማረ እያለ ከላይ የተጠቀሰውን መጽሐፍ ጽፎ፣ ሊያስታውቀው ሲል ተመልሶ አዲስ አበባ ሲገባ ባለሥልጣኖቹ (ገመናውን ሁሉ ረስተው) የተቀበሉት በታላቅ ክብርና ሆሆታ ነበር ይባላል[8]።
በግልጥ እንደሚታየው እነዚህና እነሱን የመሳሰሉ ጸሓፊዎች በሕይወታቸው እንደየጊዜውና ሁናቴው ጐራቸውን እየለወጡ በመንሳፈፍ ከመሄድ ውጭ አቋምም ሆነ፣ ታሪክ-ነክ መጽሐፍም ለመጻፍ ተገቢው ትምህርትና ሥልጠና ዕውቀቱም ጭምር የሌላቸው መሆናቸው ግልጽ ነው። በመጻሕፍታቸው መግቢያ ላይ ግባቸው “የተጣመመውን የጥንት ታሪክ ማቃናት፣ የተዛባውን ማስተካከል፣ እውነታውን መመዝገብ ነው፤ ማጣመምም ሆነ ማዛባት መወገዝ የሚገባቸው ተግባራት ናቸው” ብለው በመናዘዝ ያስተጋባሉ። ግን ሥራቸውን ላነበበ እነሱ ራሳቸው የተካኑት እውነትን በማዛነፍና በማቆላመም ስለሆነ የቤተ ክርስቲያን ደወል ይመስል ድምፃቸውን ከማክለልና ከማናር የማያልፉ ፍሬ-ቢሶችና ግብዞች ሰባኪዎች ናቸው ማለቱ አይከፋም። ባነሡት በያንዳንዱ ነጥብ ላይ ኂስ እያወጡ መሄድ ተገቢ መስሎ ሊታይ ይችላል። ለእንደኔው ግን ጊዜ ማጥፋት እንጂ ሌላ ጥቅም የለውም። ሁኖም አንድ እየተመላለሱ የሚነበንቡት ነገር ቢኖር አማርኛ ተናጋሪውን ሕዝብ (ማለትም ኢትዮጵያውያንን) ማጥላላት፣ አፄ ምኒልክን ማንቋሸሽ፣ በተቃራኒው በዚያው ልክ ደግሞ ከአማራው ጋር በደም፣ በጋብቻ፣ በባህልና ታሪክ በጥብቅ እንዳልተሳሰሩ ይመስል የሰሜኑን በተለይም ደግሞ የትግራይ ትግርኛ ተናጋሪውን ታሪክና ትግል ማጋነን፣ አፄ ዮሐንስንም ማሞገስ እንደሆነ ማሳሰቡ ተገቢ ይመስላል።
ደራሲዎቹ አዲስ መረጃ አገኘን ብለው የሚያመጡት ርግጠኛ ነኝ ብዙዎቻችን ደጋግመን ያነበብነው ስለሆነን አዲስነቱ ከምኑ ላይ እንደሆነ ማወቁ ግር ሳይለን እንደማይቀር እገምታለሁ። በጠቅላላ ጥናታቸውና ምርምራቸው ጥርት አድርጎ የሚያሳየው አዲስ ነው የሚሉትን መረጃዎች፣ የታሪክ ትምህርትና አላፊነት እንደሚጠይቀው ሁሉ፣ አበጣጥሮ የማየት፣ ከጊዜውና ከአካባቢው አስተሳሰብና አሠራር አገናዝቦና አመዛዝኖ የማተትና የመተንተን ችሎታቸው የመከነ እንጂ የሰከነ አለመሆኑን ነው። መጻሕፍቱ ለፖሊቲካ ወረት ሲባል የተጻፈ የተረትነት እንጂ የታሪክነት ባሕርይና ይዘት ስለሌላቸው፣ ዕውቀትን በማገበየት ደረጃ ዋጋ-ቢስ ናቸው ማለት ተገቢ ፍርድ ይመስለኛል። እንደዚህ ዐይነቱን አርቲ-ቡርቲ ርግጠኛ ነኝ ጸሓፊዎቹ የቀሰሙት በትምህርት ገበታ ላይ ሳይሆን፣ በመሸታ ቤትና በጫካ የትግል ሜዳ ውስጥም ነው ብሎ ማመኑ ይሻላል። ጽሑፋቸውን ሳነብ አንድ ትዝ ያሰኘኝ ነገር ቢኖር ግን ገና ተማሪ ሳለሁ ያነ በሳቅና በፌዝ ያነበብሁትን፣ ትግሊ ኤርቲራ፣ ካበይ ናበይ በሚል አርእስት፣ ታጋዮቹ አፏቸውን በማሞጥሞጥ ቊንጮ መምህራችን ናቸው በሚሏቸው በአቶ መለስ ዜናዊ የተደረሰውን መጽሐፍ ነበር። ልክ እንደዚሁ መጽሐፍ፣ ደራሲዎቹ ከዚህም ከዚያም በቀነጫጨቡትና በዘነጣጠሉት የመረጃ ስብስብ በመደገፍ፣ ፍሬከርሥኪን እየወሸከቱ እንደእውነት ለማቅረብ ይሞክራሉ። ተረታቸው ራሳቸውን የሳቱትንና የአድርባዮችን የማወቅ ፍላጉት ሊያረካ ይችላል። ከዚያም አልፎ ደግሞ፣ በየቻሉበት ቦታ በድኻው ሕዝብ ገንዘብ ድግሪያቸውን በችርቻሮ ያገኙትን የቀጣሪዎቻቸውን ስሜት ሊያፈነድቅ፣ የጀሌዎቻቸውን ቀልብ ሊስብ፣ ለደራሲዎቻቸው ደግሞ ከልብ የሚጐመጁትን ዕውቅናና መጠነኛ የኪስ ገቢ ለጊዜውም ቢሆን ሊያስገኝላቸው ይችል ይሆናል። በታሪክና ባገር አንፃር ሲታይ ግን ከትዝብትና ውርደት በስተቀር ሌላ ርባን ያላቸው አይመስለኝም። ጸሓፊዎቹ ቢዋሹም ታሪክ ግን አይዋሽም።እንደመሰለኝ አብዛኛው ሕዝብ መሃይምን በሆነበት አገር በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ያስተሳስብ ትልም ለመከተል ተረትንና ታሪክን ማደበላለቅ እንደዘመናዊነት እየታየ ነው። ታዲያ ‘ሰው ቢታጣ ተመለመለ ጐባጣ” ነውና ነገሩ የዕውቀት ብቃታቸውን በግዢ እንጂ ከትምህርት ገበታ ተሰማርተው ባልገበዩት፣ ባስተያየታቸው ድንብርብር በመንፈሳቸው ሳባራ በሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣኖች ዘንድ፣ እንደነዚህ አሳባቸውን በጽሑፍ አስፍረው መቀባጠር የሚችሉት የለየላቸው ጭንጩ ምሁራን ሁነው መታየታቸው አይቀርም። አለበለዚያማ መጻሕፍታቸውን በሆታና በእልልታ መቀበሉ ለምን አስፈለገ።
ይኸንን እንደመቅድም ካሳረግሁ ወዲያ እንግዴህ ደራሲዎቹ ያወላገዱትን ለማቃናት፤ ያዛነፉትን ለማስተካከል ስለአድዋም ሆነ ስለአፄ ምኒልክ የሚሉትን እንስማቸው።
በነዚህ አፈ-ቀላጤዎቹ ደራሲዎች አነጋገር፣ የአድዋ ጦርነት የተካሄደው በኢትዮጵያና በኢጣሊያን መንግሥት መካከል መሆኑ ቀርቶ፣ በነፃው በትግራይ መንግሥትና በኤርትራው የኢጣሊያን መንግሥት መካከል ነው፤ የጠቡም መነሾው የኤርትራው የኢጣሊያን መንግሥት ትግርኛ ተናጋሪውን ሕዝብ በሙሉ አንድ አድርጎ ሊገዛ በመመኘት፣ ትግራይን ሊይዝ ስለፈለገ እንጂ፣ ከልዑላዊው የትግራይ መንግሥት አልፎ የመሄድ አሳብም ፍላጎትም አልነበረውም። ጦርነቱ በስሕተት ከኢትዮጵያ ጋር ሊያያዝ የበቃው ደግሞ፣ የትግራይ ገዢ በኢጣሊያን እንደተሸነፈ፣ ከጐረቤት መንግሥት ርዳታ ቢጠይቅ፣ ምኒልክና የሸዋ ጦር በመምጣቱ ነው። ረዳቱ የምኒልክና የሸዋ ሠራዊት ከእሪ ባዩ የትግራይ መንግሥት ጋር ጐን ለጉን በመዋጋት ድል ነሥቶ ኢጣሊያንን ካሸነፈ በኋላ፣ ወደመጣበት ወደሸዋ ሰተት ብሎ ተመለሰ እንጂ አልቈየም፤ ስለዚህም ድሉ መከበር ያለበት በትግራይና በአድዋ እንጂ በኢትዮጵያ አይደለም ባዮች ናቸው።
እኔ እንደማውቀው፣ ትግራይ ከኢትዮጵያ እናቷ ተለይታ ራሷን የቻለች ነፃና ልዑላዊት መንግሥት ሁና ራሷን ያስተዳደረችበት ወቅት በታሪክ የለም፣ ታይቶም አይታወቅም[9]። እስከአፄ ዮሐንስ ዐራተኛው ዘመን ድረስ፣ መናገሻ ከተማቸው በደቡብ አካባቢ በነበረበት ጊዜ እንኳ፣ ነገሥታቱ አገር አቋርጠው የንግሥናቸውን ሥርዐት ሊያካሂዱ ወደአክሱም ይጓዙ የነበረው ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ቢትሆንና፣ ጥንታዊነቷም ቢታወቅ፣ ከሌላውም የአገሪቷ ክፍሎች ይበልጥ ቢትከበር እንጂ፣ ነፃና ልዑል አገር በመሆኗ አይደለም። ምናልባት የጸሓፊዎቹ ስሕተት የኢትዮጵያን ያስተዳደር ታሪክና ሥርዐት ካለማወቅ የመነጨ ይሆናል ብለን መገመቱ የሚበጅ ይመስላል። ስሕተቱ ይኸ ከሆነ ደግሞ፣ ለማረም ያህል መታወቅ ያለበት ነገር አለ። ይኸውም፣ በጊዜው ያገሩ የአስተዳደር ሥርዐት መሠረት አካባቢውን ከውስጥም ሆነ ከውጭ ጠላት መከላከልም መጠበቅም ሆነ፣ ሕዝቡን በፍትሕና በርትዕ ማስተዳደርን ጭምር፣ ያካባቢው ገዢ፣ ማለትም የባላባቱ አላፊነትና ግዴታ ነበር። ንጉሠ ነገሥቱ ጣልቃ የሚገባውና፣ ካስፈለገም ባላባቱን ከሥልጣኑ የሚሸረው፣ እነዚህን ግዴታዎች ሳያሟላ ሲቀር ብቻ ነው ማለት ይቻላል። ጠላት ወርሮ ካሸነፈ፣ ወይንም ሕዝቡ በባላባቱ ተበደልሁ፣ ተገፋሁ ካለ፣ አገሩንና ሕዝቡን ማረጋጋቱ የንጉሠ-ነገሥቱ ፈንታ ነበር። ያነ የትግራይ ባላባት፣ ማለትም ገዢ በነበሩት፣ በራስ መንገሻ ላይም የደረሰውና፣ የአድዋም ጦርነትና፣ የጦርነቱ ማግስት ሁናቴ የሚያስረዳው ይኸንኑ ነው። ኢጣልያን እየተንሰራራ እስከግዛታቸው በመምጣት፣ ራስ መንገሻን ባንድ ዓመት ውስጥ ሦስቴ ቢያሽንፋቸው፣ ኢጣልያን ማርኳቸው ወስዶ፣ ንጉሠ-ነገሥቱንም ሆነ አገሩን እታላቅ ውርደትና ትዝብት ላይ እንዳይጥል በሚል ሥጋት አፄ ምኒልክ ተወጥረው እንደነበር ይታወቃል። ከዚህም የተነሣ፣ እኔ እስከሚደርስ ድረስ እንዳትዋጋ ብለው በጽኑ ቢያዟቸው፣ ራሱ እንደተነገራቸው አደረጉ። ንጉሠ-ነገሥቱ እንደደረሱም፣ ራሱ ከሠራዊታቸው ጋር አብረው ጐን ለጐን ተሰልፈው በዠግንነት በመዋጋት ኢትዮጵያን ለድል አበቁ። ግን ብዙም ሳይቈዩ በንጉሠ-ነገሥቱ ላይ ቢሸፍቱና፣ በአማላጅም በቀጥታም ተለምነው እምቢ አልታዘዝላቸው ቢሉ፣ ጦር ተልኮባቸው ተሸንፈው ከሥልጣናቸው ተሸረው በግዞት ሞቱ። ደጋግመን በኢትዮጲያ ታሪክ የምናየው፣ ባላባቶቹ በተቻላቸው መጠን እርስበርስ በንጉሠ-ነገሥቱ ላይ በሻጠርም ሆነ፣ ካስፈለገ ከውጭ ጠላትም ጋር እንኳን በማበር ለሥልጣን መሻኰት የተለመደ ነው። አፄ ዮሐንስ በአፄ ቴዎድሮስ ላይ ሸፍተው ለውድቀታቸው ከእንግሊዞች ጋር እንደተባበሩ ሁሉ፣ አፄ ምኒልክም፣ አልሆነላቸውም እንጂ፣ ልክ እንደዚያው ከኢጣሊያኖች ጋር በመመሳጠር አፄ ዮሐንስን ሊጐዱም ሊጥሉም ሞካክረዋል። ይኸ በንጉሠ ነገሥቱና በመኳንንቶቹ መካከል የነበረው የሥልጣን ሽኩቻ፣ የሚገዙትን አገር ነፃና ልዑላዊ አያደርገውም። ጉልበት እስካለው ድረስ፣ ንጉሠ-ነገሥቱ ገዢዎቹን መቼም ቢሆን ሊሽራቸውና ግዛታቸውን ለሌላ ሊሰጥ ይችላል።
ጸሓፊዎቹ በአፄ ምኒልክም ላይ የተለያዩ ከባድ ወቀሳዎችን ይሰነዝራሉ። ባነጋገራቸው ኢትዮጵያን በቄሳራውያን ዘመን ያጋጠሟትን ችግሮች አብዛኛውን፣ በቀጥታም በአዙሪትም፣ በንጉሠ-ነገሥቱ ደጃፍ ላይ የሚጥሉ ይመስላል። ክሶቹ ብዙዎች ቢሆኑም እንዲያው ለናሙና ያህል ከአድዋ ድል ጋር የተያያዘውን ጥቂቱን ላብራራ። በደራሲዎቹ አስተያየት፣ አፄ ምኒልክ የማይረካ የሥልጣን ጥም ያላቸው ሰው ነበሩ፤ ሥልጣንም ለመያዝ ሲሉ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ሲያሻጥሩ ቈይተው፣ በመጨረሻ የዉጫሌ ውል ከኢጣልያን ጋር ተዋዋሉ፤ የዚህ ስምምነት ውጤት ደግሞ ኢትዮጵያን ወደብ-አልባ አድርጎ አስቀራት ብቻ ሳይሆን፤ ኤርትራን ማለትም የባሕረ-ነጋሽ ግዛት በመባል የሚታወቀውን ምድሪ ባሕሪን ለጠላት መሸጥ ሆነ። ከዚህም የተነሣ፣ እስከአፄ ዮሐንስ ሞት ድረስ አንድ የነበረውን የትግራይን ትግርኛ ተናጋሪ ኅብረተ-ሰብንም በሁለት ከፋፈሉት የሚል ነው።
ታሪክና ልምድ የብዙዎቻችንም ትዝብት እንደሚነግረን፣ ሥልጣን መቋመጥን በተመለክተ ዝንባሌው በሁሉም ሰው ዘንድ ያለ ስለሆነ ክሱ አገባቢነት የለውም ማለት ይቻላል። እስከ አፄ ምኒልክ ጊዜ ድረስ የነበረ አስተሳሰብም ሆነ ሥርዐት፣ ንጉሥ የሚመረጠው በእግዚአብሔር እንጂ በሰው አይደለም ይል ስለነበር፣ ያኔ በኢትዮጵያ ምድር ከመኳንንቱና ከመሳፍንቱ የሚወለድ ይቅርና፣ ያንዲት ዕለት ቀለብ እንኳን የሌለው ቡትቶ ለባሽ ድሃም ቢሆን፣ ሕልሙ አንድ ቀን የእግዜር ፈቃዱ ሁኖ፣ እሱም የንጉሥነት በትር እጨብጥ እሆናሉ ብሎ አያስብም አይባልም። በተባበሩት የአሜሪቃ መንግሥታት አገር ያለነውም የምናየው፣ ዕድሉ ሁኖለት ያገሩ ፕሬዚደንት ለመሆን የማይቋምጥ አሜሪቃዊ የለም ማለት የሚቻል አይመስለኝም። አፄዎቹ ቴዎድሮስም ሆኑ ዮሐንስ የንጉሥነትን በትር የጨበጡት ካባቶቻችው ወርሰው ወይንም በሕዝቡ ተመርጠው ሳይሆን በጉልበታቸው እንደነበር ክርክር የማያስፈልግ ሐቅ ነው። አፄ ምኒልክም ከንጉሣዊ ቤተሰብ በመወለዳቸው፣ ከቀደሟቸው ሁለቱ ነገሥታት፣ ማለትም ካፄዎቹ ቴዎድሮስና ዮሐንስ፣ ይበልጥ የንጉሥነት አልጋ ይገባኛልነት አላቸው ቢባልም፣ የጨበጡት ግን እንደነሱ በሞት ሽረት ፍልሚያ ነው፤ ጉልበትም ብልሃትም ተጠቅመዉበታል። ለነገሥታቱ ከዙፋኑ ላይ እንዴት ወጡ የሚለው ጥያቄ ጉዳያቸው አይመስልም። አgባብ ያለው ጥያቄና ዋና ጭንቀታቸው ማነጣጠር ያለበት፣ ከነገሡ በኋላ ምን ሠሩ ላይ በሚለው ነው። ለነሱ ንጉሥነት መሣርያ እንጂ፣ የዓላማቸው ፍጻሜ አልነበረም። ለመረጣቸው ፈጣሪያቸው ተልዕኮውን ማለትም ግዳጃቸውን ለመፈጸም የሚጠቀሙበት መሣርያ። በዚህ ዐይነት አስተሳሰብ ተመሥርተው ነው እንግዴህ፣ አፄ ቴዎድሮስ ንጉሥነታቸውን የጨለማና የድብልቅልቅ ጊዜ በመባል የታወቀውን ዘመነ-መሳፍንትን አክትመው፣ የአዲስቷን ኢትዮጵያ መሠረት ሊጥሉ ሲጠቀሙበት፣ አፄ ዮሐንስ ደግሞ ለግንባታው ሊያዉሉ ሞከሩት። ሁኖም ሁለቱም እንደፈለጉት አልሆነላቸውም። አፄ ቴዎድሮስ ያስተዳደር ብልሃትና አደብ አንሷቸው፣ በመጨረሻ (ማጋነን አይሆንብኝና)፣ አንዲት እፍኝ እንኳን የማትሞላ አካባቢ ብቻ ንጉሠ-ነገሥት ሁነው፣ በተግባራቸው ከውጭ እያስጐተቱ ባስመጡት በእንግሊዝ ጠላታቸው ወረራ ሰበብ በተስፋ-ቅብጸት ራሳቸውን ሲገድሉ፣ አፄ ዮሐንስ ደግሞ ለንግሥ ላበቃቸውው ለቄሳራዊው ለእንግሊዝ መንግሥት ውለታ ሊመልሱ ሲሉ ባፈሩት ደርቡሾች ጠላቶቻቸው እጅ ሕይወታቸው ዐለፈች።
የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ መከፋፈልን በተመለከተ ግን ተጠያቂው አፄ ዮሐንስና የሰሜኑ አገሮች ተከታዮቻቸውና መኳንቶቻቸው ድርጊቶች እንጂ አፄ ቴዎድሮስም አፄ ምኒልክም አልነበሩም። እውነት ነው፣በአገር-ወዳድነትና በጀግንነት፣ ካስፈለገም በሃይማኖተኝነት አፄ ዮሐንስ በምንም መልክ አይታሙም። የሞቱት ላገራቸውና ለሃይማኖታቸው ሲሉ ሰማዕት ሁነው ቢባል ሐቅነቱ አይካድም። ላገር መሪነት ግን ብቁ አልነበሩም ብቻ ሳይሆን ጊዜውና አካባቢው ከሚጠብቀው ግዳጅ ጋር የሚመጣጠን ዕውቀቱም፣ ችሎታውም፤ ብስለቱም አልነበራቸውም ማለት ይቻላል። እኚህ ንጉሠ-ነገሥት የሚታወቁት በአክራሪነታቸው ቢሆንም፣ ሥራቸውንም ሆነ አስተያየታቸውን ጠባብነትና ገራገርነት ያጠቋቸው ነበሩ ማለቱ የሚቀል ይመሰለኛል። ይኸም ሐቅ እንጂ የራሴ ፈጠራ እንዳልሆነ አንዳንድ ጸሓፊዎችም ሆኑ፣ በተከታታይ የሠሩት ሥራቸው ይመሰክራሉ። አፄ ዮሐንስን በቅርቡ ያውቃቸው የነበረው እንግሊዛዊው አውጉስቱስ ብላንዲ ዋይልድ ለምሳሌ አፄ ምኒልክ በጣም የሚደነቅ ራዕይ ብቻ ሳይሆን፣ ዐርቆና ሰፋ-አድርጎ የማሰብ ችሎታ አላቸው ብሎ ሲያሟግሳቸው፣ አፄ ዮሐንስን ግን ከሳቸው ቢነፃፀሩ “እንደልጅ ናቸው” ብሎ ያጣጥላቸዋል። አፄ ዮሐንስ እነዚህን ጠባዮች ማንጸባረቅ የጀመሩት ገና ዙፋኑን ከባላንጣቸው ከአፄ ተክለ ጊዮርጊስ በጦር ኀይል እንደተረከቡት ነበር ማለት ይቻላል።
አለቃ ዐጽሜ እንደሚነግሩን፣ ገና ዘውዳቸውን እንደደፉ፣ ከንጉሥ ሥልጣን ሰገድ ማለትም ከአፄ ሱስንዮስ ዘመን ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን “ሠላሳ አምስቱን ሹመት የሰጡት፣” የቀድሞ ነገሥታትም ሆኑ፣ ተተኪያቸውና ወራሻቸው አፄ ምኒልክ እንዳደረጉት ሁሉ፣ ከሌላው አካባቢም ለመጣው ጭምር ሳይሆን፣ “ለትግራይ ተወላጆች ብቻ ነበር።” ሥልጣንንና ሹመትን ላገር አስተዳደር ሳይሆን ከጐጥና ከወገን ሽልማት ውጭ እንዳይተላለፍ በማድረጋቸው፣ አፄ ዮሐንስ በአገሪቷ ቋንቋ ቢነጋገሩም፣ የመላዪቷ ኢትዮጲያ ንጉሥ ነገሥት መሆናቸውን የዘነጉ ይመስላል። ለነገሩ አሁንም በሥልጣን ያለው፣ ንጉሠ-ነገሥቱ ከተወለዱበት አካባቢ የመጣውና፣ ልክ እንደሳቸው ሥልጣኑን በጦሩ ኀይል ብቻ የያዘው መንግሥትም ቢሆን ያደረገውና እያደረገም ያለው ይኸንኑ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህም የተነሣ አንዳንድ ልበ-ገርም ሆነ ሁናቴውን ከሩቅ ሁኖ የሚያስተውል፣ ሰሜኖች፣ ባይሆን ገዢዎቻቸው፣ እንደዘመኑ ሰፋ አድርገው በአገርና በሕዝብ ደረጃ ከማሰብ፣ ጐጥነትና ጐሣነት የተጠናወታቸውና የሚቀላቸው ናቸው፤ ስለዚህም የመራቀቅም ሆነ ከጊዜው አብሮ የመራመድ ችግር አለባቸው ሊል ይችላል። ከገዢው መደብ ተባርረው፣ ካልሆነም ተሳስተናል በማለት ተገንጥለው የወጡት፣ የዚያው አካባቢ ተወላጆች፣ ኋላ ያቋቋሟቸው ድርጅቶችም ሆኑ ሥራቸው ሲታይ አስተያየቶቹ እውነተኝነት አላቸው የሚያሰኝ ይመስላል። ከዋናው አሳቤ ወጣ ብዬ፣ ይኸንንም ያነሣሁት ለትዝብት ቢሆንም መታሰብ ያለበት ቁም ነገርነት የለውም ማለት አይቻልም። አስተያየቴን እዚሁ ላቁምና ወደዋናው ነጥቤ ልመልስላችሁ። የአፄ ዮሐንስ ስሕተታቸው በንግሣቸው ዕለት ድርጊት ብቻ አላበቃም ልበላችሁ። ይልቅስ እየተደራረበና እየተከማመረ በመሄድ ለዉጫሌ ውልም ለአድዋ ጦርነትም ከዚያም አልፎ ለማይጨው መሠረት እስከመጣል ድረስ ተጓዘ። እንዴት እንደዚህ ሆነ ተብዬ መጠየቄ ስለማይቀር፣ እስኪ ታገሡኝና ባጭሩ ላብራራ።
የሂወት ወይንም የአድዋ ውል ተብሎ በሚታወቀው በእንግሊዝና በኢትዮጵያ መንግሥታት መካከል በአድዋ ከተማ በሺ ስምንት መቶ ሰባ ሰባት ዓ. ም. በተፈረመው ስምምነት መሠረት፣ በደርቡሾች ተከበው ለዕልቂት የቀረቡትን የግብፃውያንን ጦር አፄ ዮሐንስ ለመታደግ ከቻሉ፣ እንግሊዝ በግብፆች እጅ የተያዘውን ቦጎስን ለናት አገር ለኢትዮጵያ መልሶ ሊሰጥ፣ እንዲሁም በግብፆች ቊጥጥር ሥር የነበረውን ምፅዋንም፣ ለአገሪቷ ንግድ ነፃ ወደብ ሊያደርግላት ለንጉሠ-ነገሥቱ ቃል ገባላቸው። አፄ ዮሐንስ ግዳጃቸውን ከብዙ መሥዋዕት ጋር ቢዋጡም፣ ያተረፉት ግን የደርቡሾች ጥላቻና ጠላትነታቸው ብቻ ሆኖ ቀረ። መዘዙም ቈይቶ አላስፈላጊ ጦርነትና ሞታቸው ይሆናል። እንግሊዞች ግን ተጠቅመዉባቸው ሲያበቃ፣ ቃላቸውን ባለመጠበቃቸው ይቅርታም አልጠየቁ፤ በሠሩትም ሽንገላ አላፈሩበትም። ምክንያቱም ለንጉሠ-ነገሥቱ ቦጎስም አልተሰጣቸውም፣ ምፅዋንም ቢሆን ለሳቸው ሳይሆን ዉሉን ላልተፈረመው ኢጣልያን ነው እንዲይዘው የጋበዙት። እውነቱ ግን ንጉሠ ነገሥቱ ግብፆችን ከደርቡሾች እጅ ያስለቀቁበትን ቦታ ለመያዝ በቂ ጉልበትም መሣርያም ነበራቸው። ግን አልያዙም። ኋላም ግብፆቹ ምፅዋን ለቀው ባዶውን ጥለው ወዳገራቸው ሲገቡ ገሥግሠው ሄደው በእጃቸው ባደረጉ ነበር። ይኸንን እንደማድረግ ግን፣ እንግሊዝን እንዳንድ ገባራቸው (ሎሌአቸው ብንልም ያስኬዳል) መስለው መለመንና መማለድ መረጡ። እሳቸው አቤቱታቸውንና ምልጃቸውን በሚያቀርቡበት ወቅት በቤተ መንግሥታቸው የእንግሊዝ መንግሥት ምስለኔ የነበረው አቶ ፖርታል እንደሚነግረን፣ “ምስኪን ግብፅ፣ ለስሙ ያህል እንኳን ዋጋ ያለው ጦር የላት። የሚታመኑ የጦር መኰንኖች የሏት። ገንዘብም ሆነ፣ የመበደር ዐቅም የላት፤ ሰውም የላት።” ስለዚህም ነው ኢጣልያኖች ምፅዋ ባለቤት የሌላት ባዶ ወደብ መሆኗን ሲያዩ፣ ከአሰብ እየገሠገሡ መጥተው በመያዝ ግብፆችን የተኩት። ያኔም ቢሆን፣ አፄ ዮሐንስ የወሰዱት እርምጃ ቢኖር፣ እንደልማዳቸው ስሞታቸውን ለእንግሊዞች ከማቅረብ አላለፈም። ለትዝብት ያህል መታወስ ያለበት፣ ግብፃውያን ባገራቸው ውስጥ በደረሰባቸው ውዝግብ ምክንያት የለቀቁት ምፅዋን ብቻ አልነበረም፤ ሐረርንም ጭምር እንጂ። የሐረርን መለቀቅ ጭምጭምታ እንደሰሙ፣ የያኔው ንጉሥ ምኒልክ አካባቢውን ይቈጣጠሩ የነበሩት አውሮጳውያን እንዳይቀድሟቸው ተሽቀዳድመው ገሥግሠው ሂደው፣ አውራጃዋን ከዐራት መቶ ዓመታት በኋላ፣ ወደቀድሞ እናቷ መለሱ፤ አውሮጳውያንም እንዳይዳፈሩና ጦርነት እንዳይገጥሙ ሲሉ ለምን እንደወሰዷት ገልጸው ለነዚሁ መንግሥታት በጽሑፍ አስታወቁ፤ እንዳይቃጡም የጦር ኀይልና አዲስ አስተዳደር አቋቊመው ወደመናገሻቸው ተመለሱ። እንዳልኩት፣ አፄ ዮሐንስም እንደዚያው ግብፆቹንም ሆነ ኢጣሊያኖቹን ለመጋፈጥ ከበቂ በላይ ሠራዊትም መሣርያም እንደነበራቸው የሚያከራክር አይደለም።
ኢጣሊያኖቹ ከምፅዋ ወጥተው ገፍተው ወደደጋው ሲንሰራፉ፣ ከላይ እንዳልነው፣ ጀግናው መኰንናቸው ራስ አሊ በዶጋሊ ላይ ድምጥማጣቸውን ቢያጠፋ፣ ራሱ ያተረፋት የንጉሣቸውን ተግሣጽና ቅጣት ነበር። ቈይተውም ኢጣሊያኖቹ ንጉሠ-ነገሥቱን ታዝቧቸው ሲያበቃ ንቋቸው፣ እንደገና ገፍተው ሰዓቲትን ቢይዙባቸው፣ ንጉሠ ነገሥቱ ወደሁለት መቶ ሺ ያህል ሠራዊት ይዘው ዘመቱ። ይሁንና ለማስፈራርያ ያህል እንኳን አንድ ጥይት ሳይተኲሱ ትተው ተመለሱ[10]። ከዚያ ወዲያ ነው እንግዴህ በራስ አሊ ጀብዱ ተቈርጦ የነበረው የኢጣልያኖች ወሽመጥ ታድሶ፣ ነፍስ ዘርቶ የተነሣው። ኋላም ንጉሠ-ነገሥቱ ኢጣልያኖቹን በይዞታቸው ትተው፣ የሂወትን ስምምነት ለማክበር ለእንግሊዝ ሲሉ ያፈሰሱትን ደም ሊበቀሉ አገራቸውን የወረሩትን ደርቡሾች ሊወጉ ሄዱ። አገሩን የተዉት ሌጣውን በኢጣሊያን ጦር እጅ ነበር ማለት ይቻላል። ኢጣሊያኖችም በተቻላቸው መጠን ከመፈንጨት አልተቈጠቡም ቢባል አባባሉ ትክክል ይመስለኛል። ንጉሠ-ነገሥቱ በደርቡሾቹ በጥኑ እንደቈስሉ፣ በቈየው ስምምነት መሠረት አልጋቸውን ለንጉሥ ምኒልክ ሳይሆን ልጄ ብለው በሞት ጣር ላይ በድንገት ለተናዘዙት ለወንድማቸው ልጅ ለራስ መንገሻ ሲተው፣ ሰዎቻችው ዱብዕዳ ሁነባቸውና ከፍተኛ አለመግባባት፣ አምባጓሮና ትርምስምስ በመካከላቸው ተፈጠረ። በመጨረሻም እያሳደዱን ናቸው ብለው ከሚያስቧቸው ደርቡሾች እጅ አምልጠው፣ እየታመሱና እየተተራመሱ ወደመናገሻቸው ሲደርሱ፣ ጦራቸውም ሆነ፣ መንግሥታቸው ምስቅልቅሉ ስለወጣ፣ ኢጣሊያንን ለመውጋት ቀርቶ ራሳቸውን ለመከላከል እንኳን ዐቅሙም መሣርያውም አልነበራቸውም ማለት ይቻላል። ሁናቴው የጠቀመው ኢጣሊያኖችን ብቻ ነበር። በለስ ቀንቷቸው፣ ንጉሠ-ነገሥቱ ገና ሰዓቲትን ትተው ዞር ሲሉ ሊንሰራፉ የጀመሩት እነሱ፣ በጥንት ስሙ ምድሪ ባሕሪ ኋላም ኤርትራ ብለው የጠሩትን አገር ገፍተው ይዘውት ቈዩ። ከራስ መንገሻ ጋር የቀረው፣ በሥልጣን ሽኩቻ ፍጥጫው ሲፋፋም፣ ገሚሱ ሲሸፍት፣ ሌላው ከኢጣልያኖች ሲተባበርና እየመራቸውም የቀረውን የሰሜኑን አገር ሲያስይዝ፣ ጥቂቱ ወደደቡብ ማለትም ወደንጉሥ ምኒልክ አመራ። ይኸ ሁሉ የሆነው ከውጫሌ ውል በፊት እንጂ በኋላ አልነበረም።
እንግዴህ ይኸ ሁሉ የሚያሳየን፣ የትግራይ ትግርኛ ተናጋሪን ኅብረተ-ሰብ በመከፋፈል ረገድ ያፄ ምኒልክ እጅ አለበት ማለት ሐቁን ከማዛባት ሌላ ዓላማ ያለው አይመስለኝም። በጊዜው በኢትዮጵያ ውስጥ የየአካባቢው ገዢዎች የነበሩት ባላባቶች፣ አውሮጳውያን በሚለግሡላቸው ልዩ ልዩ ስጦታና በሚሰጡት ተስፋ እየተታለሉ፣ ከአስተዳደራቸው ሥር የነበሩትን ግዛቶች እየቈራረሱ ይሰጡ እንደነበረ ሁሉ፣ የቀድሞዋ የባሕር ነጋሽ ምድሪ ባሕሪ፣ ማለትም የዛሬይቱ የኤርትራ ገዢዎችም፣ ገና የውጫሌ ውል ከመፈራረሙ በፊት አገራቸውን ለኢጣልያን አስረክበው ነበር ቢባል ሐሰት አይደለም። የውጫሌ ውልም ያጸደቀውና ያንጸባረቀው ይኸንን ተጨባጭ በምድር ላይ የነበረውን ሁናቴና፣ ሰፊዋን ኢትዮጵያን ሊውጧት ተዘጋጅተው እላይዋ ላይ ያንዣብቡ ከነበሩት የአውሮጳውያን ቄሳሮች መንጋጋ ለማዳን፣ መፋለምም ካስፈለገ ደግሞ ጊዜ ለማግኘትና ለመዘጋጀት ታስቦበት ነው ማለት ይቻላል። ማን ታዲያ ይወቀስ ከተባለ ደግሞ፣ ሁኔታዎቹ በአፄ ዮሐንስና በልጃቸው በራስ መንገሻ ጫንቃ ላይ እንጂ በአፄ ምኒልክ ላይ እንደማይጣል ያስረዳሉ። አፄ ዮሐንስ ገና ኢጣልያ እግሯን በቀይ ባሕር ሲታስገባ፣ በደምብ ሳትደራጅ፣ ፊት ለፊት ተጋፍጠው፣ በእንጭጯ ለማስቀረት ሲችሉ እንድትንሰራራ ዕድል ሰጡ። ጦራቸውን አስታጥቀው ግብፅንም ኢጣሊያንንም መምታት ሲገባቸው፣ ለሥልጣን ያበቋቸውን እንግሊዝ ላንድ ነፃ አገር ገዢ በጣም በሚያሳፍር መልኩ መለመንን መረጡ።
“የምፅዋን በር እኔን ደስ ይበለው ብለው እንደከፈቱልኝ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የማያልፈውን
የመንግሥተ ሰማይን በር ከፍቶ ደስ ያሰኝልኝ…እኔንም ከርስዎ ጋር በምክር አንድ ሁኜ፣
ከፈቃድዎ ለመዋል ያብቃኝ፤ ጥንቱንም በእግዚአብሔር ፈቃድ ለመንግሥት የበቃሁ፣
እርስዎ በሰጡኝ መድፍ፣ ነፍጥ፣ ባሩድ ነው፤ አሁን ደግሞ ይልቁን ፈጽመው ደስ ያሰኙኝ።
ከዚህ በፊትም እናት ለልጅዋ እንድትጨነቅ፣ ለኔ መንግሥት ሲጨነቁ ይኖራሉ። የምፅዋን
በር እንድይዝ ያድርጉኝ ብዬ እለምናለሁ።”
ብለው ለእንግልጣሪቱ ንግሥት ቪክቶርያ የጻፉት ደብዳቤ አሁን ለሚያነብ ለማንም ኩሩ ኢትዮጵያዊ የሚያሳፍር ነው ብል የተሳሳተ ስሜት ያለኝ እኔ ብቻ ነኝ ብዬ አልገምትም። አፄ ምኒልክም በበኩላቸው
እንደዚህ ዐይነቱን መልእክት ባይጽፉም፣ በመጠኑም ቢሆን የቊልምጫ ደብዳቤ ለአውሮጳውያን አላኩም አይባልም። በግልጥ ልኳል። ከኢጣልያን ንጉሥ ጋር ሲጻጻፉ፣ እርስዎን የመሰለ አባት የለኝም እስከማለት ደርሰዋል። ያገር ክብርና ልዕልና ተነካ ብለው ካመኑ ግን ንጉሠ-ነገሥቱ ቊርጠኝነትን እንጂ ልመናን አያውቁም ነበር። አባቴ እያሉ ሲያቈላምጡት ቢቈዩም የኢጣሊያን ንጉሥ የውጫሌን ውል እሳቸው በፈለጉት መልክ ሊያሻሽሉ ፈቃደኛ አለመሆኑን እንደተረዱ፣ እንደዚያ ዐይነቱን ውል አለመፈረማቸውን አስታወቁ። “ዛሬም ቢሆን ይህንን የምቀበል ሰው አይደለሁም” ካሉ በኋላ፣ ኢጣሊያኖችን በሙሉ ካገራቸው አስወጥተው፣ ማንም የኢጣሊያን ሰው ደግሞ ወዳገራቸው እንዳይገባ አሳውቀው ለጦርነት ወደአድዋ አመሩ።
ሌላው በአፄ ምኒልክ ከሚሰነዘሩት ክሶች አንዱ፣ ንጉሠ-ነገሥቱ ድል አግኝተው እያሉ ድሉን እስከመጨረሻው ገፍተው ኤርትራን ጭምር ነፃ እንደማዉጣት ዕድሉን ሳይጠቀሙ ወደኋላ ተመለሱ የሚል ነው። ወቀሳው የጊዜውን የፖሊቲካና ንጉሥ-ነገሥቱ የተጋፈጡትን ተጨባጭ የሆኑ ውዝግቦችና ችግሮች በደምቡ የሚያገናዝብ ሁኖ አይታይም። ባገራችን “ማን ይንገር የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ” የሚል አባባል አለ። አባባሉም ትክክል እንደሆነ አያጠራጥርም፤ ምክንያቱም ከዐይን ምስክር የበለጠ ማስረጃ የለም። እንግዴህ በጦርነቱ ወቅት የነበሩት በተመልካችነትም ሆነ በተዋጊነት የተሳተፉትና ጥቂት ቈይተው የጻፉት ንጉሠ-ነገሥቱ ኢጣሊያንን ከያዙት ከሰሜን አገር ግዛታቸው ጠራርጎ የማስወጣት አሳብ እንደነበራቸው ያስረዱናል። ሁኖም በሰፊው ያሰማሯቸው ታማኝ የሆኑ የአገሩ ነዋሪዎች የነበሩ ሰላዮቻቸው የነገሯቸውን አስተማማኝ ነው ብለው ያመኑትን ወሬ አዳምጠው ከሠራዊታቸውና ባካባቢው ክነበረው ተጨባጭ የፓለቲካ ሁናቴ፣ ከኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ጥቅምም ሆነ፣ ባካባቢው በወቅቱ ከነበረው የአውሮጳውያን የፓሊትካ አሰላለፍና፣ ውጊያው ከጫረው ዋና ምክንያት ጋር አጣምረው ቢያሰላስሉት ፍላጎታቸው እንደማይከናወን ተረድተው እንደተው እንገነዘባለን።
የኤርትራ ተወላጆች የነበሩት ሰላዮቻቸው ቊጥሩ ሰፊ የሆነ ያረፈ ጦር ከኢጣሊያን አገር ገና እንደደረሰ፣ በአስመራ፣ በምፅዋና በከረን ደግሞ እጅግ ብዙ የጠላት ሠራዊት በጽኑና በማይደፈሩ ምሽጎች በተጠንቀቅ ይጠባበቅ እንዳለ ነገሯቸው። ይኸ ሁናቴ እውነት እንጂ ሐሰት አለመሆኑን ራሱ የኢጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአድዋ ድል ማግሥት ለአገሩ ሸንጎ ባቀረበው ገለጻ በማያወላግድ መንገድ ጥርት ብሎ ቁጭ ብሏል። በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያ አምባገነኑን የነጭ ዘር አሸንፋ ለመጀመርያ ጊዜ በድፍኑ ዓለም እንዲደፈር አድርጋለች። ይኸም ለነጮች እንደማይወጣላቸውና “ኢትዮጵያም ኤርትራን ቢትነካ፣” ከብቧት ያሉት ኀያላን መንግሥታት በብራስልስ ከተማ በተደራደሩት ውል መሠረት ዝም ብለው እንደማያዩ፣ ታዲያ ከኢጣልያን ጐን እንደሚሰለፉና፣ በተለይ ደግሞ እንግሊዝ ኢጣሊያን ሁለተኛ ግንባር በሐረርጌ በኩል እንዲትከፍት፣ ፈረንሳይም በጂቡቲ በኩል ወደኢትዮጵያ የሚገባውን መሣርያ ላታስተላልፍና እሷም ራሷ ላትሸጥ፥ (ሁለቱም አገሮች) እንደተስማሙና እንዳረጋገጡላት፣ ሚኒስትሩ በዚሁ ለኢጣልያን ሸንጐ ባቀረበው ዘገባ ያመለክታል። ርግጠኛ ነኝ ይኸም ወሬ ቢሆን በሰላዮቻቸውና በግቢያቸው በነበሩ የአውሮጳ ተወላጆች አማካሪዎቻቸው አማካይነት ለአፄ ምኒልክ ደርሷቸዋል። አውሮጳውያን አይተባበሩም ብሎ ማሰቡ ቅሌት ነው። ሊሆን አይችልም አይባልም። ለምሳሌ ያህል፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ ለአዝማናት ደመኞች ጠላቶች ቢሆኑም፣ ፈረንሳዮች ኻያ ዓመት ሙሉ በጀግንነት በተዋጋቸው በቱኮሎሩ መንግሥት መሪ በሳሞሪ ቱሬ ላይ የኋላ ኋላ ለድል የበቁት፣ በእንግሊዞች ትብብር ነው። ምዕራባውያን ጥቅማቸውና የነጭ ዘር ክብር የተደፈረ መስሎ ከታያቸው ኢትዮጵያን ለማጥቃት ከኢጣልያንም ጋር የማይተባበሩበት ምክንያት የለም። የሳሞሪ ቱሬ ዕጣ ላፄ ምኒልክም አይደርስም ማለት አይቻልም[12]። ዐርቆ-አሳቢ እንደመሆናቸው፣ አፄ ምኒልክ በብዙ ኢትዮጵያውያን ደምና ትግል የተገኘውን ድል ኤርትራን ነፃ ላውጣ ብለው መቆመር አልፈለጉም። በተፈጥሯቸው ውጤቱ በማይታወቅና በማያስተማምን ጉዳይ ላይ እጃቸውን ሊያስገቡ የማይፈልጉ ንጉሥ ናቸውና።
የአፄ ምኒልክ ችግራቸው ግን ከዚያም የከፋ ነበር ማለት ይቻላል። ሠራዊታቸው ጦሩን አንግቦ ስንቁን ተሸክሞ ከቤቱ ከወጣ ከሰባት ወር በላይ አስቈጥሯል። ከዚህም ሦስቱን ወር ያሳለፈው በትግራይ ሲዋጋ ነው። ስንቁን ሙጥጥ አድርጎ ጨርሶ እከፍተኛ ራብ ላይ ስለነበር፣ እንኳን ለውጊያ ቀርቶ በሕይወትና በሞት መኻል እየጣረ ነው የነበረው። እንደድሮው ጦር የትግራይን ምድር ባላገሩን ዘርፎ ለምን አይበላም እንዳይባል፣ አፄ ምኒልክ የትግራይን ሕዝብ ቀርቶ፣በጠላት አገርም እንኳን ይኸን ዐይነቱን ተግባር የሚፈቅዱ ሰው አልነበሩም። ወታደሩ ደፍሮ ቢገኝ፣ትርፉ የንጉሠ-ነገሥቱን ጥላቻና ቊጣ ማትረፍና ለከፍተኛ ቅጣት ራስን መዳረግ ነው። ንጉሠ-ነገሥቱ ውጥረታቸውን አይተው ከአማካሪዎቻቸው ቢወያዩ፣ ሁሉም አንድ ልብ አንድ ድምፅ ሁነው፣ “ሠራዊቱ ሦስት ወር ተጐድቶ ስለተቸገረ፣ የከሳውን አውፍረን፣ የሞተውን ተክተን ከርመን እንመለስ[13]” አሉና ወደሸዋ ጉዟቸውን ጀመሩ ሲሉ በጊዜ የነበሩ ጸሓፊዎች በሙሉ ይመሰክራሉ።
አፄ ምኒልክ ወደጒራዕ ሊጓዙ ፈልገው በማይ-ፈረስ እንደሰፈሩ እናውቃለን። ይኸንንም ያደረጉት ጠላትን ከኤርትራ ሊያባርሩ ሲሆን፣ ለምን በዚህ አሳብ እንዳልገፉ ላንድ ለሠራዬ ቄስ ሲገልጡ፣ “ወደ አገርህ መቅረባችን፤ እዚያ መምጣት አስበን ነበር። ልመጣ ያልቻልሁትም በመጀመርያ ደረጃ ቀለብ አጣን፤ ሁለተኛም አዲስ ጠላት ደርሷአል አሉን። አንተ እንደምታውቀው እኔ ደም ማፍሰስ አልወድም፤” ያሉት ጸሓፊዎቹ የሰጡትን ምስክርነት ያጠናክራል። ውጊያው እንዳለቀ የአድዋን የጦር ሜዳ ዙሮ ያየው እንግሊዛዊው ዋይልድ፣ ተዋጊዎቹን የኢትዮጵያን ባለሥልጣኖችንና ምርኮኛውን የኢጣልያንን የጦር መኰንን ጀነራል አልበርቶኔን ካነጋገረ በኋላ በጻፈው ጽሑፍ አፄው ኤርትራን ለመውረር ያላስቻላቸው ዋናው ምክንያት የስንቅ ችግር እንደነበር ይገልጣል[14]። እንዲሁም ወደአዲስ አበባ የተወሰዱት የኢጣሊያን ምርኮኞች በመንገዳቸው ላይ የገጠማቸውን እየገለጡ ለቤተሰቦቻቸው በጻፏቸው ደብዳቤዎች፣ ኢትዮጵያውያን ባሳዩት ሰብእናና በሰጧቸው መስተንግዶ እያደነቁ ሲናገሩ ቈይተው፣ ችግራችን በቂ ምግብ ማግኘት ነበር፤ እሱንም ተከልክለን ሳይሆን ኢትዮጵያዉያን ራሳቸው የሚበሉት ስላልነበራቸው ከኛ ይበልጥ ተቸግረው ነበሩ” እያሉ ይገልጣሉ።
አፄ ምኒልክ በዚህ አስቸጋሪ ሁናቴ ተወጥረው ሳሉ ነው እንግዴህ፣ ኢጣልያኖች የምራቸውን ሊደራደሩ መፈለጋቸውን ሲያውቁ፣ “እኔም የምፈልገው ዕርቅ ነውና እኔ በወደድሁት ከታረቃችሁ የሚስማማኝም ቃል ከሆነ እውነተኛ ሰው አዲስ አበባ ድረስ ይምጣና ይጨርስ” ብለው ወደከተማቸው የተመለሱት።
የአፄ ምኒልክ አሽሟጦች መረዳት ያቃታቸው ዋና ነገር ቢኖር፣ የአድዋ ጦርነት መነሾው ኢጣልያኖች በሺ ስምንት መቶ ዘጠና ዓ. እ. ላይ ግዛታችን ናት ብለው ኤርትራ የሚል አዲስ ስም ሰጥተው ላለም ሁሉ ካስታወቁት ምድር አልፈው፣ የኢትዮጵያን መሬት በመውረራቸው መሆኑን ነው። ኢጣሊያኖች የቅኝ ግዛቱን ካፄ ዮሐንስ ሞት በኋላ በሰሜን የተፈጠረውን ትርምስምስና ምስቅልቅል ተገን አድርገው ነው የያዙት። ግን ራስ መንገሻ ከአፄ ምኒልክ አኩርፈው በነበሩበት ወቅት “የመረብ ውል” ብለው በራሳቸው ተነሣሥተው ከኢጣልያን ጋር በገቡት በሺ ስምንት መቶ ዘጠና አንድ ዓ. እ. ስምምነት፣ የኢጣሊያን ይዞታና ግዛት መሆኑን በጣታቸው ፊርማ አረጋግጠውላቸዋል። የአድዋ ጦርነት፣ የአፄ ዮሐንስ ተተኪዎችና አፄ ምኒልክም ራሳቸው እሺ ብለው የፈረሙትንና ኢጣልያንም እንደግዛቱ ከያዘው ሰባት ዓመት ያስቈጠረውን መሬቱን መልሶ ለመውሰድ እንዳይደለ መታወቅ አለበት። እውነት ነው ኢጣሊያን ኢትዮጵያን ሲትወጋ የውጫሌም የመረብም ዉሎች ስለፈረሱ፣ በውሉ ለታወቀላትም የመሬታ ይዞታ መብት የላትም። ይኸ በግብር ሊውል የሚችለው ግን ኢትዮጵያ ልዕልናዋንና ነፃነቷን በማያሰጋ መንገድ ከተቻለ በሰላም ካልተቻለ በግድ ከኢጣሊያን እጅ ለማስለቀቅ ከቻለች ብቻ መሆኑ አያጠራጥርም። በዚህ ጽኑ እምነት ተመሥርተው ንጉሠ-ነገሥቱ ወታደራቸው የስንቅ ችግር እያለው፣ ኤርትራን ተሻግሮ ኢጣሊያንን መውጋት የተቀናጁትን ድል አደጋ ላይ ሊጥልና፣ ኢትዮጵያንም በጠላት እጅ ሊትወድቅ ትችላለች በሚል ስጋት ተዉት። በነጭ አምባገነንነት ዘመን ብዙዎች እንደህንድና ቻይና የመሰሉ አገሮች ሳይቀሩ ሰፊውን አገራቸውን ከነጣቂዎቹ ምዕራባውያን እጅ ለማዳን ሲሉ በርካታ መሬት ከግዛታቸው እየቀነጨቡና እየሸራረፉ ሰጥተዋል። አሁን ግን ጉልበት አግኝተው ነጮቹ ሲለቁ ካልሆነም በኀይል በማስለቀቅ መልሰው ሊወስዷቸው በቅተዋል። ታዲያ ይኸንን የጊዜውን ፈሊጥ ተጠቅመው አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን ከነጭ እጅ ቢታደጓት ክፋቱ ምንድር ነው።
አፄ ምኒልክ በአዲስ አበባ በተዋዋሉት ስምምነት ወደአድዋ ጦርነት የመራው የውጫሌ ውል ፈርሶ፣ ሌላ አዲስ ውል ሲፈርሙ መረብ መላሽን (ማለትም የኢጣልያንን ኤርትራን) በሰላምም፣ በጦርም ከኢጣሊያን ሊያስለቅቁ ባይችሉም፣ አገሩ በሙሉ የኢትዮጵያ መሬት መሆኑን፣ ኢጣሊያም በምንም ምክንያት ቢትለቀው በከፊልም ሆነ በሙሉ ለሌላ ሦስተኛ መንግሥት እንዳታስተላልፍ፣ ታዲያ ለባለቤቷ ለኢትዮጵያ መልሳ እንዲታስረክብ ያስገድዳል። ይኸንን እስምምነቱ ውስጥ የተከተተውን
“… የኢጣሊያ መንግሥት ከዚህ አገር ለማንም ማን መንግሥት መስጠትና መልቀቅ አይቻለውም። ዛሬም የኢጣሊያ መንግሥት በእጁ ከያዘው አገር መልቀቅ ያማረው እንደሆነ ለኢትዮጵያ መንግሥት ይመልሳል።”
የሚለውን አንቀጽ ዐምስትን ኢጣሊኖች ተቀብለውት በፊርማቸው ሲያጸድቁላቸው፣ አፄ ምኒልክ በወቅቱ በጦር ኀይል ለመያዝ ዐቅማቸው ባይፈቅድላቸውም፣ ሕዝቡና መሬቱ ግን የኋላ ኋላ የኢትዮጵያ ሀብት መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ስለዚህም ኢትዮጵያ የመረብ መላሽ ባለቤትነቷ በገሃድ ከታወቀ፣ ጊዜውን ጠብቃ አንድ ቀን በግድም ሆነ በሰላም፣ አለበለዚያም በውል ከኢጣሊያን እጅ መልሳ እንደሚትረከብ ንጉሠ-ነገሥቱ ርግጠኛ ነበሩ ማለት ባይቻልም ለመጪው ትውልድ ጠንካራ መሠረት ጥለውለታል ቢባል ሐሰት አይደለም። እርሳቸው የጀመረቱን ወደአስደሳች ፍጻሜ ማድረስ የተከታዩ ትውልድ ዕጣ ፋንታው ነው።
ኢጣልያን የአድዋን ጦርነት የመረጠችው፣ በዘመኑ አከራካሪ ባልነበረው ነጭ ዘር ከሰው ሁሉ ዘሮች ምርጥ ፍጥረት ስለሆነ የትም ቢሄድ የበላይነት አለው የሚል መርህ ዋነኛ እምነቷ ስለነበር ነው። ስለዚህም እንደሌላው ነጭ በየትም ሕዝቧን ሊታሰፍር፣ የማንኛውንም የሌላውን ዘር ሀብት አለጭቅጭቅ ሊትወርስ፣ ሕይወትና ነጻነት ሊትቈጣጠርና ሊትነፍግ፣ ለሞትም ሊትበይን፣ ማለትም ሊትገድልና በራሷ ዘር ሊትተካ ግዴታና አላፊነት አለኝ ባይ ነበረች። ስለዚህ ኢትዮጵያ በማንም ነጭ ሳትያዝ የቀረች ብቸኛ የጥቊር አገር ስለሆነች፣ ለኔ ትገባኛለች ባይ ነበረች። የኢትዮጵያ እምቢተኝነት ወደአድዋ ጦርነት አመራ። የአድዋ ድል እንግዴህ ስለሰው ዘር እኩልነት፣ ስለሕግ የበላይነት፣ ሰው በሰብኣዊነቱ ለሕይወት፣ ለሀብት፣ ለነጻነት ስላለው መብቶች አለመደፈርም ነው። ድሉ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውንን ላለም አስታወቀ። አፄ ምኒልክም ዕድሉን ላገር ግንባታ ተጠቀሙት። ጤናማ በነበሩት በዐሥራ ሦስት ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያን ወደከፍተኛ ሥልጣኔ ለማራመድ በነበራቸው ምኞት፣ በጊዜው የነበሩትን የተለያየ የሥልጣኔ ዘርፍ ከመላ ጐደል አንድ ባንድ ወዳገር ውስጥ አስገቡ። ከባቡር ሐዲድ እስከሴቶች መብት መጠበቅ ድረስ ያልነኩት ነገር የለም። ባርያ እንዳይፈነቀል፥ የእጅ ሥራ እንዲከበር፣ ጐጥና ጐሣ እንዲጠፋ፣ ወታደርና ነፍጠኛ ድኻውን እንዳይበዘብዝ፣ ማንም እንደፈለገ እንዲያመልክ እንጂ በሃይማኖቱ ምክንያት እንዳይሰደድ፣ ገበሬው ከመሬቱ እንዳይነቀል በየጊዜው አዋጅ አስተላልፈዋል። ለሹሞቻቸው፣ ሥልጣን ለሰው አገልግሎት እንጂ ለራስ ጥቅም መዋል እንደሌለበት አስተምረዋል። በሥልጣን በመባለግ ሕዝብን ለበደለና ለጨቈነ፣ “አገር የሚገዛው በብልሃትና በጥበብ እንጂ በጭካኔ” አይደለም በማለት ገሥጸዋል። ካልሰማም ከሹመቱ ሊያወርዱ ተገደዋል። ሁሉንም በፍቅርና በብልሃት ከመምራታቸው የተነሣ፣ ሕዝባቸው እንደንጉሠ-ነገሥት ሳይሆን እንደእናት በማየት “እምዬ ምኒልክ” የሚል ቅጽል እስከመስጠት ደርሷል።
የአፄ ምኒልክ ኂሰኞች ሊረዱት ያልቻሉት እሳቸው በጣሉት መሠረት ላይ አገሪቷን የመገንባት ትውልዳዊ አላፊነትና ግዴታ እንዳላቸው ነው። እንደረሱትም መረዳት ከፈለግን ወደሩቅ ሳንሄድ እስኪ በአድዋ የተፈጸመውን ድል በቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ በነሱ ሥርና መሪነት ከተጐናፀፈው ሌላ ድል ጋር እናነጻጽር። በሁለቱ ጦርነት መካከል ያለው ልዩነት በጣም ብዙ ቢሆንም አንዳንድ ጠቃሚ አሳብ ሊሰጠን፣ የገዢዎቹንም ባሕርይ ለመገንዘብ ጭላንጭል ሊሆንልን ይችላል።
የወያኔ መንግሥት እንደድሮው ነገሥታት በጠመንጃ ኀይል የአፄ ምኒልክን ግቢ ከተቈጣጠረ በኋላ፣ እንደዋና መርሀ-ግብሩ አድርጎ የፈጸመው ምድሪ ባሕሪን ማለትም የኢጣሊያንን ኤርትራ ራሷን የቻለች ነፃና ልዕልት አገር እንዲትሆን ነው። ከመካከላቸው ጭንጩ ምሁር የተባለው መሪያቸው መለስ ዜናዊ ድርጅቱ ገና በጫካ ሳለ ትግሊ ኤርትራ፣ ናበይ ካበይ በሚል አርእስት በትግርኛ ቋንቋ በጻፈው መጣጥፍ ቢጤ አገሪቷን እንደኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት አድርጎ ፈርጇታል። ከሰውና ከሥልጣኔ ተለይቶ እዱር ውስጥ ከ’ታጋዮቹ’ ጋር ሁኖ በደምብ ሳይገነዘብ የሸረበው የካርል ማርክስና የኅብረ-ስብኣዊነት ርእዮተ ዓለም አእምሮውን አደነባብሮት ካልሆነ በስተቀር በመጽሐፉ የተወሸከተው ትችት እላይ ካየነው የታሪክ ዘገባ በጣም ይጋጫል። እንግዴህ አስተሳሰቡ በዚህ መልክ የተኰለኰለ ቡድን ነው ወደአፄ ምኒልክ ቤተመንግሥት እየገሠገሠ ገብቶ በዙፋናቸው ቊጭ እንዳለ ኤርትራ ከቀኝ ገዢዋ ኢትዮጵያ ተገላግላለች ሲል ባዋጅ ሁለቱን አገሮች መልሶ የከፋፈለ። የኤርትራም መሪዎችም ቢሆኑ፣ የቀኝ ገዢዎቻቸውን የኢጣሊያንን ቅርስና ውርስ የሚያደንቁና የሚያመልኩ ነበሩ። የኢጣሊያኖች የአስተዳደር ዘመን አገሪቷ መሰል በማይገኝለት የኢሰብኣዊ ሥቃይና የአረመኔኣዊ ግፍ ማጥ ውስጥ ተዘፍቃ በኀይል ታጣጥር የነበረችበት የቀውጢ ወቅት እንደነበር ረስተውታል። ኢትዮጵያም ያን ለሕዝቡም ለነሱም እናት አገራቸውና የነፃነት አምባቸው፣ ተስፋቸውና ሙጥኛቸው እንደነበረች ዘንግተውታል። ይኸ እንዳልሆነ ሁሉ፣ ነፃነታቸው እንደታወጀ፣ መሪዎቹ ለኢትዮጵያ የነበራቸው መርህ ያው፣ “ልጅ አባቱን፣ አይብ አጓቱን” እንደሚባል፣ ከኢጣሊያን ቀኝ ገዢአቸው በወረሱት ፈሊጥና እምነት መሠረት ወይ መበታተን ካልሆነም በሞግዚትነት ማስተዳደር በሚል አቋም የተወቀረ ነበር። እንግዴህ ኤርትራ በምንም መልክ ኢጣልያን ባትመስልም፣ መሪዎቻችዋ ግን ሕልማቸው ትልቅ ነበር ማለት ይቻላልና በድንበር አመኻኝተው ባድሜ የተባለውን አካባቢ ሊወስዱ በ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. የሰሜን ኢትዮጵያን ወረሩ።
የወያኔም መንግሥት “የኤርትራ ጦር ባድሜ የተባለችውን ግዛታችንን በጒልበት ሊወስድብን ነውና፣ የጐበዝ ያለህ ተደፍሮ የማይታወቅ ታሪክህ ስለተደፈረ፣ መጥተህ ምታዉና ትምህርት አስተምረው” ሲል የክተት ዐዋጅ ዐወጀ። የኢትዮጵያም ሕዝብ እንደልማዱ እናት አገሩን ከጥቃት ሊከላከል፣ የጥንት ጀግንነቱን ሊያስመሰክር፣ በገፍ ወጣ። በተለይም፣ ወደዚያ ጦር ሜዳ የሄደውን ያንዳንድ የሱማሌ ኅብረተ-ሰብ አባላት ወኔና ጀብዱ ለዜና አቅርበው ሲታዩና የሚናገሩት ሲሰማ አድዋን ትዝ ያሰኛል። የማንም ዐይን እንባ ይተናነቀዋል፣ መንፈሱ ይነካል፣ ወኔው ይንቀሰቀሳል። በዚህ ውጊያ የጠፋው የአካባቢው ንብረትና የሰው ሕይወት ብዛት ሳይቈጠር፣ ወታደሩ ብቻ ከሰባ ሺ በላይ ሕይወቱን ሠውቷል ይባላል። ይኸም ማለት የአድዋ ከዐሥር ጊዜ በላይ ዕጥፍ መሆኑ ነው። ያ ሁሉ መሥዋዕት ተከፍሎ የሚገርመው ግን ከድሉ በኋላ የታየው ውጤት ነው።
በሥልጣን ላለው መንግሥት ኤርትራ የገዛ እጁ ፍጡር ነበረች። እንደፈጠራት የሠራችውን ጥፋት ተመርኲዞ ከድሉ በኋላ ወደኢምንት በቀየራት ነበር፤ ካልሆነም የኢትዮጵያን የዘለቄታ ጥቅም የሚጠብቅ፣ ወይንም ዳግመኛ በኢትዮጵያ ጉዳይ ውስጥ ፈጽሞ እንዳትገባ የሚያደርግ ውል በተፈራረመ ነበር። ግን አንዱም አልሆነም። የሆነው ማንም ጭንቅላት ያለው ማመን የሚያዳግተው፣ በታሪክም ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ የጉድ ጉድ ነው ቢባል ሐሰት አይደለም። ከአድዋ ድል በኋላ በኢትዮጵያና በኢጣሊያ መካከል የተደረገውን ትርጒም የሌለውን፣ የቅኝ ግዛት ውል ለዘመናት ሙቶ ከተቀበረበት በግር ተፈረስ አስፈልጎ አንሥቶት ሕያው አደረገውና ድርድራችን በዚህ ይሁን አለ። የኤርትራም መሪዎች ደስታውን ስላልቻሉ፤ ቦረቁ፤ ፈነጩ ማለት ይቻላል። ነገሩ ያ ሁሉ የኢትዮጵያ ሠራዊት የተሠዋለትን ድል መልሶ ለኤርትራ ሸጠው ሆነ። በዚህ ብቻ አላቆመም። ድርድሩ በተካሄደበት ወቅት፣ በሄግ የተቋቋመው የገላጋዮቹ ቡድን “የኢትዮጵያ መሬት ናቸው” ብሎ አንዳንድ አካባቢ ወሰኖ ሰጠ። የወያኔም መንግሥት “መሬቶቹ የኢትዮጵያ አይደሉም፤ አንቀበልም፤” ሲል ደረቱን ነፍቶ አንገቱን ገትሮ ለኤርትራ እንዲሆኑ ተሟገተ። በርግጥ የቡድኑ አባላት፣ ማመኑ አቅቷቸው በመደነቅ ወይ የጉድ ጉድ ሳይሉ አልቀሩም። ቡድኑ ምርጫ ሲያጣ መሬቶቹን አለፍላጎቱ ለኤርትራ አሳልፎ ሊሰጥ ተገደደ። ይሁንና በዚህ ብቻ አላበቃም።
የድርድሩ ውሳኔ ይፋ በሆነ ጊዜ፣ ያኔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የነበረው አቶ ሥዩም መስፍን፣ “በጦር ሜዳ ያገኘነውን ድል፤ በሕግ አስመሰከርነው፤ ባድሜ ለኛ ተፈረደች” ብሎ ደነፋ። የፖሊትካ ጨዋታ እንጂ ሐቅ አልነበረም። እውነቱ ያ ከሰባ ሺ በላይ ሠራዊት ሕይወቱን ሠዋለት የተባለው ባድሜ፣ መንግሥት ራሱ መዳኛ ብሎ ባቀረበው የቅኝ ግዛት ውል መሠረት የኤርትራ ናት ተብሎ ተበየነ። ሠራዊቱ አጥንቱን የከሰከሰለት፣ ደሙን ያፈሰሰለት ባድሜ የከንቱ ከንቱ ሁኖ ተገኘ። ብልህና አስተዋይ የሆነው የተዋጋነው ለካስ የኢትዮጵያን ሳይሆን የወያኔንና የቡችሎቹን ሥልጣንና ክብር ለመጠበቅ ኑሯል ሳይል አልቀረም። በሠለጠነ ዓለም ቢሆን፣ እንደዚህ በሕዝብ ሕይወት ላይ የሚቀልድ መንግሥት ላንዳፍታ እንኳን ሳይቈይ፣ በፈቃዱ ሥልጣኑን ለቆ በሄደ፤ ካልሆነም ቢያንስ ቢያንስ ለአገሩ ሕዝብ ከፍተኛ ይቅርታ በጠየቀ፣ እንደዚህ ዐይነቱን ስሕተት ላይደግም ቃል በገባ። የኢሕአደግ መንግሥት ግን አንዱንም አላደረገም፤ ይልቅስ ምንም እንዳልሆነ አስመስሎ ሥራውን እንደወትሮው ቀጠለ። በዚህም ሥራው ለሕዝብና ለአገር ጥቅም ያልቆመ መንግሥት መሆኑን በግልጥ አስረዳ ማለት ነገሩን ማቃለል ይሆናል። ጥቂት ክብደት የሚኖረው ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ከልክ በላይ ናቀ ቢባል ትርጒም ይኖረዋል።
ስለናቀም ነው እንግዴህ የአገሯን ድንበር እየሸረሸረ፣ መሬቷን እየሸነሸነ ለባዕድና ለጐረቤት አገር የሚሰጥ፣ ከሌላው እየነጠቀ ለወገኑና ለደጋፊው ብቻ የሚያድል፣ አገር ገንቢዎችንና ያንድነት አራማጆችን የሚያስር፣ የቀለም ምሁራንንና የነፃ ጋዜጦች ጸሓፊዎችን በእስር ቤት የሚያጉር፣ የሃይማኖት መልእከተኞችንና ሰባኪዎችን የሚያሳድድ፣ ላገር ጥቅም እንደመቆም ለባዕድ ቱኪ ሁኖ የሚያገለግል። ይኸንን ሁሉ አፄ ምኒልክና የአድዋ ትውልድ ቢሰማ ምን ይል ይሆን።
ይኸ መንግሥት ነው እንግዴህ በቅርቡ የአፄ ምኒልክን ስም ለማጉደፍ ሲል ከፍ ያለ ዘመቻ የሚያካሄድ ያለው። ዘመቻውም ግቡን እንዲመታ ሲል፣ ያልሞከረው ስልት፣ ያላደረገው ሥራ፣ ያላጠፋው ገንዘብ የለም። ያም ሁሉ ሁኖ ግን አፄ ምኒልክን በቅኝ ገዢነት ከሚፈርጁ ከጥቂቶች የብሔረ-ሰቦቻችን ነፃ አውጪ ነን ብለው ራሳቸውን በራሳቸው ከሾሙት የዘመኑ ‘ባላባቶች’ና ድርጅቶቻቸው ዘንድ ካልሆነ በስተቀር፣ በጠቅላላ ዘመቻው የሠመረለት አይመስልም። በአዞዎቹ ቄሳራውያንና በነጣቂ ባላባት የተጥለቀለቀውን የዘመኑን ዉሃ በብልሃትና በጥበብ እየዋኙት እርሳቸውም ሳይነኩ፣ አገራቸውም ሳትጐዳ ማትረፍ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንና ልጆቿን ለዝናና ለታሪክ ያበቁት አባት በቀላሉ ይሸነፋሉ ብሎ ማመኑ አስቸጋሪ ነው። ሁኖም የአድዋ ጀግኖች ተተኪው ትውልድ እነዚህን ከንጉሠ-ነገሥቱ ቤተ-መንግሥት ውስጥ ተወሽቀው ስማቸውንና የገነቡትን አገር ለማጥፋት ያወጁትን የአስሶ ደምስስ ክተት አዋጃቸውን የመቅጨትና የመቀልበስ ግዴታ እንዳለባቸው መርሳት አይገባቸውም። የአፄ ምኒልክ የአድዋ ክተት አዋጅ ድምፅ፣ ማለትም “አገር የሚያጠፋ፣ ሃይማኖት የሚለውጥ፣ ጠላት መጥቷል…. እንግዴህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም፣ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ርዳኝ፤ ጉልበት የሌለህ ደግሞ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል” በምትችለው መንገድ ርዳኝ የነሱም “የአገር አድን” ጥሪ ድምፅ መሆን ይገበዋል። በየአደባባዩ፣ በየአድባራቱ፣ በየመስጊዱ፣ በየቀዬው፣ በየመገናኛ መሣርያ፣ እንዲሁም አገር-ወዳድ ኢትዮጵያዉያን በየተሰቡበትና በሚገኙበት ሁሉ በጨራራ ድምጽ ከመቼም ጊዜ ይልቅ ማስተጋባት ያስፈልጋል። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ፣ በቋንቋና ሃይማኖት፣ በፆታና ዕድሜ፣ በሙያና ማዕርግ፣ በቀዬና ወገን ሳይለይ ለአገሩ፣ ለልጁ፣ ለሚስቱ ሲል በኢትዮጵያዊነቱ ካልተሰበሰበ ፋይዳው ሸንፈትና ጥፋት መሆኑ አምኖ መቀበል ይኖርበታል። የነአሻንቴ፣ የነዙሉ፣ የነቱኮሎር ጦር የኋላ ኋላ ድል እንዲሆን ካበቁት ምክያቶች ዋናው ልክ ኢጣልያን የአካባቢውን የሰሜኑን ጦር በተከታታይ ድል እንደነሣች ሁሉ፣ እነሱም ጠላታቸውን በተናጠል በመፋለማቸው ነበር። የአድዋ ጦር መለዮው ኢትዮጵያዊነት፣ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ ብዙ ብሔረ-ሰብን ያካተተ አንድነት ነበር። አንድነት ኀይል ነው እንደተባለ፣ አንድነታቸውን መከታ አድርገው፣ በቊጥሩ ብዛት ከዚያ በፊት በአፍሪቃ ምድር ያልታየውን የነጮችን ጦር ብትንትኑን አወጡ። የአድዋ ድል የኢትዮጵያውያን መታወቂያ፣ የነጻነታቸው ዋስትና ብቻ ሁኖ አልቀረም። ለድፍኑ ዓለም ጭቁን ሁሉ የሐርነት ጨረርና መመኪያቸው ሆነ። እንግዴህ በዓሉ በኢትዮጵያ ሳይወሰን፣ ቢቻል በመላው ዓለም፣ ካልሆነም በአፍሪቃ ክፍለ-አገር ደረጃ እንዲከበር ቢጣር ተገቢ ነው። ይኸንን ግብ ለመምታት ኢትዮጵያውያን መጀመርያ ቤታቸውን ማጥራት፣ የአድዋ ድል ያመጣላቸውን ክብርና የአንድነታቸውን መታወቂያ ማሳደስ ይኖርባቸዋል። ቸር ወሬ ይግጠመን።
ማስታወሻዎች
[1]እያንዳንዱ ውል፣ “እኔ እገሌ የ [ጐሣው ስም] መሪ ራሴን፣ መሬቴንና በሥሬ ያሉትን ሰዎች በሙሉ ይዤ የብሪታንያው የምሥራቅ አፍሪቃ [የንግድ] ኩባንያ ጥገኛ ለመሆን ወስኛለሁ። በሱም [በኩባንያው] ግዛትና መንግሥት ሥር እንደመሆኔ፣ ኩባንያው በመሬቴ፣ ባገሬና በሕዝቤ ላይ የበላይ ገዢና አስተዳዳሪ መሆኑን ተቀብያለሁ” ይላል።
[2]እንዲያው ለፈገግታ ያህል ላውጋችሁ« በነጮች ትምህርት ቤት አስተምር በነበርሁበት ወቅት አንዳንድ በፈተናው ባገኘው ነጥብ የተቈጣው ተማሪ በጽሑፍ ግምገማው ወቅት ቁጭቱን ሲወጣ “ይኸ ህንዳዊ የሚጠይቃቸው ጥያቄዎች አንጉል የሚያኦሩ ናቸው። … ይኸንን ዐይነቱን ደደብ ህንድ ለምን ትቀጥራላችሁ፤ በአሜሪቃ ምድረ-ሰማይ ከሱ የተሻለ አስተማሪ ታጣ እንዴ” ሲል ተማሪው በአነጋገሩ የሚገልጥልኝ የሰብእናዬ ቅርጽ ዝምድናዬን ከዐረብ ይበልጥ ለህንድ እንደሚያቀርበኝ ይታየው እንደነበር ነው።
[3]ማስረጃ ካስፈለገ ሩቅ መሄድ አያስፈልገንም። እንዲያው ለምሳሌ ያህል ብቻ ልጥቀስ። ያፄ ቴዎድሮስ ጨካኝነታቸው ያደባባይ ወሬ ስለሆነ መዘርዘር አያስፈልገውም። በአፄ ምኒልክ ዘንድ ግን የተዋጓቸውን ባላንጦቻቸውን ስመውና አቅፈው ሲያበቃ ወደጥንቱ ሹመታቸው ማዕርግና ቦታ መመለስ የተለመደ ሲሆን፣ አፄ ዮሐንስ እንደዚህ ዐይነት ተግባር በመሥራት እምብዛም አይታወቁም። ሌላው ቢቀር ርኅሩኅና የእኅታቸው ባል የነበሩትን ባላንጣቸውን አፄ ተክለ-ጊዮርጊስን ከማረኳቸው በኋላ እንኳን፣ እንደመማር ዐይናቸውን በጭካኔ አሳውረው በተራራ አስረውዋቸው ነው የሞቱት።
[4]ደጃች ደበብ ለአፄ ዮሐንስ የገቡላቸው፣ ኢጣልያን እንደሚሸነፍ ርግጠኛ ስለነበሩ ነበር ይባላል።
[5]አንድ መድፈኛ የኢጣሊያን ጋዜጠኛ በማጋነን መልክም ቢሆን የሕዝቡን ኅብረትና ትብብር ሲገልጥ፣ “ሕዝቡ ከሁሉም ብሔረሰብ የተወጣጣ ነው። ይዋጋ የነበረው ፈረሱም፣ በቅሎውም፣ አህያውም ባንድነት ከሰው ጋር ሁኖ ነው። በጦርነት የገጠመን መደበኛ ወታደር አልነበረም። ሴቶች፣ ሽማግሌዎች፣ ቄሶችና ቈማጣዎችም ሳይቀሩ ይዋጉን ነበር።” ይላል።
[6]ሸዋ ያኔ የሚያመልክተው፣ የአሁኑን በስሙ የሚጠራውን ጠቅላይ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን ከደቡቡ፣ ከምሥራቁና ከምዕራቡ ያለውን አፄ ምኒልክ ንጉሥ በነበሩበት ጊዜ ያስተዳድሩ የነበረውን የመኻሉን አገር በሙሉ ነው። በጦርነቱ ጊዜ ኢጣልያን ያዋክቡ የነበሩትና ውሃ የሚመጣባቸውን ምንጮቻቸውን በሙሉ ይዘው የነበሩት የ ኦሮሞ ፈረሰኞች ነበሩ።
[7]በዚህ መጽሐፍ ላይ አቶ መኰንን ዘለለው (ዮሴፍ) “ጥላቻና የመከፋፈል አባዜ ይቁም” በሚል አርእስት በተጻፈ ጽሑፍ ሰፊ ኂስ ጽፎበታልና ስሕተቶቹን ለመገንዘቡ ማንበቡ ጠቃሚ መስሎ ይታየኛል።
[8]ሌላው በነዚህ ሁለቱ ጐን መከተት ይገባል ብዬ ያሰብሁት አቶ ሙሐመድ ጃዋር የሚባለውን ነበር። ግን ጽሑፎቹንና ንግግሮቹን ካዳመጥሁ በኋላ ሰውዬው የአንጐል ቀውስ የሚያጠቃው ስለመሰለኝ የሚያስፈልገው ከሒስ ይልቅ የአእምሮ በሽታ ሐኪሞች ርዳታ ስለመሰለኝ ዕዳ ላልሆንበት ብዬ ትቼዋለሁ።
[9]በዘመነ መሳፍንት የተከሠተው ሥርዐት አልባ ያስተዳደር ሁናቴ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ የንጉሠ-ነገሥቱ ሥልጣን የላላበት የውድቀት ጊዜ እንጂ በመደበኛነት አይታይም። የቈየውም ብዙ አይደለም።
[10]የሚያሳዝነው ይኸ ለኢጣልያን የተባለው ጦር ቁጭቱን በመጀመርያ ላይ የተወጣው በንጹሕ የጐጃም ሕዝብ ላይ ነበር።
[11] ለናሙና ስል ለኢጣልያን ንጉሥ የላኩትን ነው እዚህ ያስቀመጥኹት።
[12]እንግሊዞች ከድሉ በኋላ ለጽርኡ ንጉሥ እስክንድርና እሱን ለመሰሉት በዓለም ታሪክ ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱት መሪዎች የሚሰጡትን “ታላቅ” የሚትለውን ቅጽል በመጀመርያ ላይ ለአፄ ምኒልክም ሰጥተው “ታላቁ አፄ ምኒልክ” በማለት ታላቅነታቸውን አውቀው ነበር። ኋላ ቅጽሉን ያነሡት ኢጣልያኖች እንዲህ ማለቱ ኢጣሊያንን ብቻ ሳይሆን የነጭን ዘር በሙሉ ያዋርዳል ብለው ስለወቀሷቸው ነው ተብሎ ይታመናል።
[13]“ያነ የኢጣሊያን ጦር እስከምፅዋ ሊያባርሩ ምክረው ነበር። ግን ሠራዊቱ ሦስት ወር በረኀብ ተጐድቶ ነበርና ተቸገሩ። የከሳውን አውፍረን ከርሞ እንመለስ አሉና ተመለሱ። (አለቃ ተክለ ኢየሱስ፣ የኢትይጵያ ታሪክ)። ጸሓፌ ትእዛዝ ገብረሥላሴ በታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ፣ መምህር አፈወርቅ ዮሐንስ በዳግማዊ አጤ ምኒልክ የሚነግሩን ይኸንኑ ችግር ነው።
[14]“የአፄ ምኒልክ ድል ሙሉ ለሙሉ እንዳይሆን ያቆመው ጦሩን ያጋጠመው የስንቅ እጥረት ብቻ ነበር።”