በኦሮሚያ በተፈጠረው ሕዝባዊ አመፅ ንብረታቸውን ያጡ ባለሀብቶች መንግሥት ካሳ እንዲከፍላቸው ጠየቁ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በተፈጠረው ሕዝባዊ አመፅ ንብረታቸው የወደመባቸው የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች፣ መንግሥት ካሳ እንዲከፍላቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አመለከቱ፡፡
ታማኝ የዜና ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ንብረታቸው የወደመባቸው 14 የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች የደረሰባቸውን ጉዳት በመዘርዘር መንግሥት ተገቢውን ካሳ እንዲከፍላቸው ጥያቄያቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ የቀረቡትን የካሳ ጥያቄዎች በአንክሮ የተመለከተው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ጉዳዩን ወደ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መምራቱን ምንጮች ተናግረዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባለሀብቶቹ ያቀረቡዋቸውን የካሳ ክፍያ ጥያቄዎች፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንዲገመግም ማዘዙን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከአበዳሪ ባንኮችና ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጋር ተባብሮ የቀረቡትን የካሳ ጥያቄዎች እንዲመረምር መመርያ ተላልፎለታል፡፡
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጋር ተባብሮ በመሥራት ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ መንግሥት የቀረበውን የካሳ ጥያቄ ለማስተናገድ ፈቃደኝነት እንዳለው የገለጹት ምንጮች፣ በባለሀብቶቹ የቀረበው የንብረት ግምት የተጋነነ እንዳይሆን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
በኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሚገኙ አንድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራር የካሳ ጥያቄ ማመልከቻዎችን በጥንቃቄ በመገምገም ላይ ነው፡፡ ‹‹ጉዳዩ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ አገራዊ ጉዳይ በመሆኑ በቦርድ ደረጃ የተያዘ ነው፤›› ብለዋል ኃላፊው፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጋር ተባብሮ በመሥራት ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ኩባንያዎቹ ያቀረቡትን የንብረት ግምት መጠን በማጤን የመድን ሽፋን ያላቸውንና የሌላቸውን እንዲለዩ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ አስተማማኝ ሰላም አለ ከሚል እሳቤ ባለሀብቶቹ በአብዛኛው በጦርነት ወይም በሁከት ለሚከሰት የንብረት ውድመት የመድን ዋስትና አልገቡም፤›› ያሉት ኃላፊው፣ ኮሚሽኑ ጉዳዩን ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጋር በመተባበር በማጣራት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ባለሀብቶቹ በአጠቃላይ ያቀረቡት የካሳ ጥያቄ መጠን ለማወቅ አልተቻለም፡፡
መንግሥት በካሳ ጥያቄው ላይ እየሠራ በመሆኑ የክፍያው መጠን ገና ተለይቶ እንዳልታወቀ የገለጹት ኃላፊው፣ መንግሥት ለወደሙት የባለሀብቶች ንብረቶች ተመጣጣኝ ክፍያ ለመፈጸም ቁርጠኝነት እንዳሳየ አስረድተዋል፡፡
ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ ባለፈው ኅዳር ወር በኦሮማያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው አመፅ መንግሥት ቁጥሩን በይፋ ያልገለጸው የበርካታ ሰዎች ሕይወት የጠፋ ሲሆን፣ ግምቱ በውል ያልታወቀ የግልና የመንግሥት ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል፡፡ ሁከቱ በቱሪስትና የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል እየተገለጸ ነው፡፡

Reporter Amharic