ድምፃዊ ኤፍሬም ታምሩ በውርስ የተላለፈን የፈጠራ ሥራ ያለምንም ፈቃድ ለግል ጥቅሙ አውሏል ተብሎ ክስ ተመሠረተበት፡፡


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


‹‹አዕምራዊ ንብረቱ በውርስ መተላለፉን የሚያሳይ ማስረጃ የለም››  ኤፍሬም ታምሩ

ድምፃዊ ኤፍሬም ታምሩ የአዕምራዊ ንብረት ጥበቃ አዋጅን በመተላለፍ፣ በውርስ የተላለፈን የፈጠራ ሥራ ያለምንም ፈቃድ ለግል ጥቅሙ አውሏል ተብሎ ክስ ተመሠረተበት፡፡


ኤፍሬም ሕግ በመተላለፍ የገንዘብና የሞራል ጉዳት አድርሷል ተብሎ  በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስድስተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ክስ የተመሠረተበት፣ በ1977 ዓ.ም. ‹‹ቀይ ዳማ›› ወይም ‹‹የድንገት እንግዳ›› በሚል ርዕስ ያወጣው ዘፈን አቶ ማስረሻ ሽፈራው የተባሉ የኪነ ጥበብ ባለሙያ ግጥምና ዜማ ድርሰት መሆኑን እያወቀ ክፍያ አለመፈጸሙ ተጠቅሶ ነው፡፡
ድርሰቱ የአባታቸው መሆኑን በመግለጽ ክስ የመሠረቱት ወ/ሮ ቤተልሔም ማስረሻ የተባሉ ግለሰብ ሲሆኑ፣ አባታቸው በሕይወት ባይኖሩም በውርስ የተላለፈላቸውን መብት ኤፍሬም የቅጅና ተዛማጅ መብቶችን ሳያስከብር ከፈቃዳቸውና ከዕውቅናቸው ውጪ፣ የሕግ ጥበቃ የተደረገለትን የሙዚቃ ሥራ በመዝፈንና በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን እንዲለቀቅ ማድረጉን በክሳቸው አካተዋል፡፡
ኤፍሬም ቀደም ብሎ የሠራቸውን የሙዚቃ ሥራዎች በድጋሚ እንደሚሠራ በማስተዋወቅና ዘፈኑን ለማስታወቂያ ሥራነት በማዋል ከፍተኛ ጥቅም ማግኘቱን የሚጠቅሱት ከሳሽ፣ ከግጥምና ከዜማ ደራሲው ፈቃድ አግኝቶ ቢሆን ኖሮ ሊከፍል የሚገባውን 30 ሺሕ ብርና ፈቃድ ሳያገኝ በሕግ ጥበቃ የተደረገለትን መብታቸውን በመጣሱ ላደረሰባቸው የሞራል ጉዳት 140 ሺሕ ብር፣ በድምሩ 170 ሺሕ ብር ሊከፍላቸው እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡
ተከሳሽ ከሟች አባታቸው የአዕምሯዊ ንብረቱን በውርስ ስለማግኝታቸው የሚያሳይ ማስረጃ አለማቅረባቸውን በመግለጽ የቅድመ ክስ መቃወሚያ ያቀረበው ኤፍሬም፣ ይጠይቁ ቢባል እንኳን መብታቸውን መጠየቅ የነበረባቸው ደራሲው ከሞቱ በሦስት ዓመታት ውስጥ እንደነበር ጠቁሞ፣ አሁን ክስ የቀረበበት ከ13 ዓመታት በኋላ በመሆኑ ይርጋ እንደሚያግደው አስረድቶ ክሱን ተቃውሟል፡፡ ከሳሽ የተረጋገጠ መብትና ጥቅም እንደሌላቸውም በመቃወሚያው ገልጿል፡፡
ፍርድ ቤቱ በመጀመርያ መቃወሚያው ላይ ብይን ለመስጠት ለመጋቢት 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡