ፍለጋ እጅግአየሁ ወዴት ነሽ; Reyot TV – ቴዎድሮስ ጸጋዬ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ፍለጋ
እጅግአየሁ ወዴት ነሽ;
እንዲህ እንደዛሬ የባለእዳነት ስሜት ሲጠጋኝ፣ እንዲህ እንደዛሬ ላገኘኋቸው ደስታዎች በመልሱ ያልከፈልኩት ብድር እንዳለ ሳስብ እልፍ ጥያቄዎች ይጎበኙኛል፡፡ ነፍስ ድረስ የሚደርስ፣ የጠለቀ እና በየጊዜው የሚታደስ እንዲሁምየሚጎመራ ደስታ ከማገኝባቸው የኪነጥበብ ስራዎች መሀል ደግሞ የእጅግአየሁ ሽባባው ዘፈኖች በቀዳሚው ተርታ ይሰለፋሉ፡፡ እናም በግጥሞቿ፣ በዜማዎቿ እና በአዘፋፈኗ ደስ በተሰኘሁ ጊዜ ሁሉ የሚገባትን የምስጋና አምሀ እንዳልሰጠኋት ወይም እንዳልሰጠናት የሚያስታውስ የባለእዳነት ደወል በእዝነህሊናዬ ይደመጠኛል፡፡
በመሆኑም፣ እነኚህን ጥያቄዎች ከእናንተ ከተወደዳችሁ ከሁላችሁም ጋር ላነሳቸው ፈለግሁ፡፡


እጅግአየሁ ወዴት ነሽ;
የሀገሬ ህዝቦች ያላቸውን ተካፍለው በፍቅር እንዲኖሩ፣ ያመረቱትን እንዲገበያዩ፣ በ1 ልብ እንዲቆሙ በዜማሽ ያስታወስሽን እጅግአየሁ ወዴት ነሽ;
ደጉ ንጉስ መጣ፣ ክፉ ንጉስ መጣ ሁሉም ይሄዳሉ እንዳመጣጣቸው፣
ሳቅ እና ለቅሶሽን አይገዙትምእና፣
አይዞሽ እናታለም ኑሪልኝ በጤና
በማለት የሀገርን ዘልአለማዊነት፣ የህዝብን ከመንግስታት አላማ ጉልበት እና ቁመት መብለጥ የሰበክሽን እጅግአየሁ ወዴት ነሽ;
ባደመጥኩሽ ቁጥር ባለእዳነት ያሰቃየኛል እና በጥያቄ እብሰለሰላለሁ፡፡ የትነትሽን እና እንዴትነትሽን ማወቅ እሻለሁ፡፡ አመሰግናለሁ እድሜ እና ጤና ይስጥልኝ ልልሽ እፈልጋለሁ፡፡
አቤት ደም ግባት ቁንጅና አፈጣጠር ውብ እናት፣
ሀገሬ እምዬ ኢትዮጲያ ቀጭን ፈታይ እመቤት
ስትዪ ሀገርን ለሀሳባችን ቅርብ ያደረግሽ፣ በኢትዮጲያዊ ማንነት ስለመኩራት የተናገርሽ፣ ከጎርፉ ጋር ያልነጎድሽ፣ ከነፋሱ ጋር ያልበነንሽ፣ እንደአስተሳሰብሽ እና እንደእምነትሽ እንጂ እንደአንዳንዶቹ የምስኪኖቹን እንባ እና ሳቅ መልሰሽ በመቸርቸር ያልቆመርሽ ያልዘፈንሽ እጅግአየሁ ወዴት ነሽ;
አሞራ ወድጄ አሞራ ሆኛለሁ፣
ነብርም ወድጄ ነብር ሆኜ አውቃለሁ፣
ድብ አንበሳም ነበርኩ ከጥንት ተዋድጄ፣
ዛሬ ግን አልቻልኩም ብርቄን ሰው ወድጄ
ብለሽ ሰው የመሆንን ልእልና፣ ሰው የመሆንን ጥልቅ ትርጓሜ የገለጽሽ፣
እያለ ሲዘፍን ትዝታው ገደለኝ፣
ዛሬ በሰው አገር የሰው ከብት እያየሁ እያንገበገበኝ፡፣፣
በማለት ሰውነታቸውን ጥለው ወደከብትነት ስለወረዱት ነውራቸው ክብራቸው ስለሆነላቸው ሰዎች የተቀኘሽ፣ ስለፍቅር ረሀብ ስለፍቅር ጠኔ የጮኽሽ ውዷ ድምጻዊት የት ነሽ;
ፖለቲከኞቹ ስለአባይ ለመናገር በማይፈልጉበት ወቅት እንደእውነተኛ ከያኒነትሽ ነገሩን በልቡናሽ በማጤን ከ10 አመት በላይ እነርሱን ቀድመሽ እራሱን አባይን የሚያህል ድንቅ ዘፈን ያበረከትሽልን፣
ከጥንት ከጽንሰአዳም ገና ከፍጥረት፣
የፈሰሰ ውሀ ፈልቆ ከገነት፣፣፣
ብለሽ የወንዙን እድሜ ከሰው ልጅም ሁሉ መብለጡን የሚነግር ግሩም ስራ የሰጠሽን እንቁ ድምጻዊት ወዴት ነሽ;
ባደመጥኩሽ ቁጥር ባለእዳነት ያሰቃየኛል እና በጥያቄ እብሰለሰላለሁ፡፡ የትነትሽን እና እንዴትነትሽን ማወቅ እሻለሁ፡፡ አመሰግናለሁ እድሜ እና ጤና ይስጥልኝ ልልሽ እፈልጋለሁ፡፡


አድዋ ላይ ለሀገራቸው ሲሉ ህይወታቸውን፣ ደማቸውን፣ አካላቸውን እና ማንኛውንም የአለም ትሩፋት ንቀው እና ሰውተው ልክ በሌለው ቸርነት ነጻነት የሰጡንን ኢትዮጲያውያን እና ኢትዮጲያዊያት ለመመልከት የህሊናሽ አይኖች የበሩልሽ፣ አንደበትሽም እነርሱን ለማክበር የተጋልሽ፣ የጣልናቸውን እሴቶች፣ የተውናቸውን የእራሳችንን አሻራዎች አጥርተሽ ማየት የቻልሽ፣ ከስነቃላዊ ግጥሞቻችን እና ከትውፊቶቻችን ጋር ያስተዋወቅሽን፣ ታሪክ በማሻገር ታሪክ የሰራሽ እጅግአየሁ ሆይ ወዴት ነሽ;
ባደመጥኩሽ ቁጥር ባለእዳነት ያሰቃየኛል እና በጥያቄ እብሰለሰላለሁ፡፡ የትነትሽን እና እንዴትነትሽን ማወቅ እሻለሁ፡፡ አመሰግናለሁ እድሜ እና ጤና ይስጥልኝ ልልሽ እፈልጋለሁ፡፡


ስለሸማው፣ ስለጥለቱ፣ ስለሀገር በቀል ጥበባቱ ያቀነቀንሽ፣ የባለሀገሩን ደስታ እውቀት እና እውነት በዜማ ስለሽ ያሳየሽን፣ ባለዋሽንቱን ከጆሮአችን ጋር ያጎዳኘሽ፣ ወደኋላ ሄደን ስር መሰረታችንን እንድናጤን እንድናከብር ያስተማርሽ፣ እውነትን እጅግ አድርገሽ ያየሽ እጅግአየሁ የት ነሽ;
ከሙዚቃው አምባ ብናጣሽ፣ ከታላቁ መድረክ ላይ ባናይሽ፣ ከጆሮአችን ብትርቂ ለእኛ ከባድ ክስረት ነውና እባክሽ የት እና እንዴት እንዳለሽ ንገሪን፡፡ የሀገር ልሳን ነሽ እና ስላንቺ ይገድደናል፡፡ የታሪካችን ድምጽ፣ የማንነታችን ጠበቃ ነሽና ባንቺ ላይ የሚሆን ሁሉ በእኛ ላይ እንደሆነ ነው፡፡ ወደስንኙ፣ ወደቅኝቱ፣ ወደቅኔው ተመለሺልን፡፡ ይበልጥ እውነት፣ ይበልጥ ጥበብ፣ ይበልጥ ፍቅር ተናገሪልን፡፡
አሜን፡፡
ቴዎድሮስ ጸጋዬ / March 2015

Source – https://www.facebook.com/permalink.php?story_fbid=430234097134803&id=100004446491615