የአዲስ አበባ የታክሲ ማኅበራት በድርድር ወደ ሥራ ተመልሰዋል
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ሰሞኑን ተግባራዊ የሆነውን የትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ቁጥር 208/2003ን በመቃወም አድማ አድርገው የነበሩት የታክሲዎች ማኅበራት፣ ባሏቸው ጥያቄዎች ላይ ድርድር አድርገዋል፡፡ የታክሲ አሽከርካሪዎች በተለያዩ እርከኖች የተቀመጡትን ጥፋቶች ለሁለተኛ ጊዜና ከዚያ በላይ ጥፋት ሲፈጸም 14 ነጥቦች ያህል ከሞላ፣ ለስድስት ወር የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ዕገዳና የተሐድሶ ሥልጠና እንደሚወሰድ የሚደነግገውን ይህን ደንብ ተቃውመዋል፡፡
በደንቡ ላይ የአዲስ አበባ ታክሲ አሽከርካሪዎች፣ 13 የታክሲ ማኅበራትና ሦስት የሀይገር ሚዲ ባስ ማኅበራት ተቃውሟቸውን በደብዳቤ እንዳስገቡ፣ የብሌን ታክሲ ባለንብረቶች ማኅበር ሰብሳቢ አቶ ኑረዲን ቢታሞ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ይኼንን የተቃውሞ ደብዳቤ ለፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ ለአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ፣ ለትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ለተወካዮች ምክር ቤት የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዳስገቡም አመልክተዋል፡፡
የሪከርዱ ምዝገባ የታክሲዎችን አሠራር ከግምት ውስጥ እንዳላስገባ የሚገልጹት አቶ ኑረዲን፣ የታክሲ አሽከርካሪዎች ጥያቄ መጀመሪያ እንዲመልስም ጠይቀዋል፡፡ አሁን የወጣው ደንብ ነጥቦችን በመመዝገብ የአሽከርካሪነት ብቃት መረጋገጫ ፈቃድ ዕገዳን መወሰኑ ትክክል እንዳልሆኑ የገለጹት አቶ ኑረዲን፣ በገንዘብ ብቻ መታለፍ አለባቸው የሚሏቸውን ጥፋቶችም ጨምረው አስቀምጠዋል፡፡ የታክሲ ታሪፍ ይሻሻል በማለት ለዓመታት የጠየቁ መሆናቸውን የሚገልጹት አቶ ኑረዲን፣ አቅርቦትና ትርፍ በማይጣጣምበት ሁኔታ ሪከርዱ ተግባራዊ መደረግ የለበትም ይላሉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ አራት ነጥብ የሚመዘገብበት መኪና ደርቦ መጫን ከከተማዋ የመንገዶች ሁኔታ ጋር የማይጣጣም መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በደንቡ ውስጥ ግልጽ ያልሆኑ ጥፋቶችም እንዲሻሻሉ አስተያየታቸውን ለሚመለከታቸው አካላት እንዳቀረቡ አቶ ኑረዲን ይናገራሉ፡፡ የጥፋት እርከኖቹ በእኩል መንገድ መታየት የለባቸውም የሚሉት አቶ ኑረዲን የትራፊክ ቀይ መብራትን መጣስ፣ ጫት፣ አልኮልና አደንዛዥ ዕፆችን ተጠቅሞ መንዳት በአጠቃላይ የሰውን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥሉት በሪከርዱ እንዲያዙ ከታክሲ ባለቤቶችና አሽከርካሪዎች የተውጣጡ አባላት አስተያየት መስጠታቸውን አክለዋል፡፡
የካቲት 19 ቀን 2008 ዓ.ም. በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን አዳራሽ ውይይት ከተደረገ በኋላ ሪከርዱ ለሦስት ወራት ያህል ተግባራዊ እንዳይሆን መደረጉ ተገልጿል፡፡ የአዲስ አበባ አሽከርካሪዎች የካቲት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ሥራ የማቆም አድማ የመቱ ሲሆን፣ ይኼም መረጃውን ካለመስማት ጋር የተያያዘ እንደሆነም አቶ ኑረዲን አክለዋል፡፡
ከተለያዩ የመንግሥት አካላት በተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ መሠረትም በስልክ ለተለያዩ አሽከርካሪዎች እንደደወሉ የሚናገሩት አቶ ኑረዲን፣ ከየካቲት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የታክሲ አሽከርካሪዎቹ ወደ ሥራ እንደተመለሱ ገልጸዋል፡፡
Reporter Amharic