የተወጋ ልብ!


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


Heartbroken

አሜሪካ የመጣው የዛሬ 15 አመት ሲሆን እጅግ ሲበዛ ቀና ሰውና በተለይ እንግዳ የሆኑና ችግር የገጠማቸውን ሀበሾች ስራ በማስገባትና አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ እንደሚተባበር የሚያውቁት በአክብሮት ጭምር ይመሰክሩለታል። በእምነት ይባላል፤ ነጭና ጥቁር አሜሪካውያን የሚያዘወትሩበት የራሱ ሬስቶራንት አለው። ዝቅ ብሎ – ከሰራተኞቹ ጋ እንደጓደኛ ሆኖ አብሯቸው ይሰራል። በእምነት እጅግ ከሚወዳት የልጅነት ፍቅረኛው ልጅ አፍርተው በሚያስቀና የፍቅር ህይወት ይኖሩ እንደነበረና ከአገር ቤት ሳያመጣት በፊትም ሆነ በኋላ ለእሷ ፍፁም ታማኝ መሆኑን በቅርብ ከሚያውቁት በተጨማሪ የፍቅረኛው ስጋ ዘመድ ትመሰክራለች። የንግድ ስራው የተሳካ ስለነበረ የራሳቸውን ቤት በካሽ መግዛት ችለዋል። በዚህ የተሳካ ህይወት ውስጥ እያሉ ድንገት ተነስታ መለያየት እንደምትፈልግ ትነግረዋለች። ምክንያቷን እሱም ሆነ ጓደኞቹና ዘመድ ቢጠይቋትም ምንም ጥፋት እንደሌለው ነገር ግን ሀብትና ንብረት ተካፍላ መለያየት እንደምትፈልግ አሳወቀች። በእምነት ፍርድ ቤት መሄድ ሳያስፈልጋት በመቶ ሺህ የሚቆጠር ዶላር ድርሻሽ ብሎ ሰጣት። ከተለያዩ 2 አመት ቢሆንም እሱ የብቸኝነት ህይወት ይመራል። የተዋወቅኩት ከስራ መልስ ምሽት ጎራ የሚልበትና በብቸኝነት የሚያሳልፈበት የሀበሻ ሬስቶራንትና ባር በረንዳ ለስላሳ ሙዚቃ እያዳመጠ ሲቆዝም ነበር። ካስተዋወቀኝ ጓደኛው ጋር ጥልቅ ወዳጅነት ቢኖራቸውም… ከጊዜ በኋላ በደረሰበት የፍቅር ጉዳት ከሰላምታ በቀር ሁሌም ብቸኝነትን ይመርጣል። ትልቅ ንግድ ያለው ሰው መምሰል አይፈልግም። “ለገንዘብ አይሰስትም፣ ሀበሻ በረንዳ ላይ ካጋጠመው ቀስ ብሎ ጠርቶ ይከፍላል” ትላለች አስተናጋጅዋ። ዳግም ሳገኘው የደረሰበትንና የሰማሁትን እንዲያጫውተኝ ጠየቅኩት። <<እኔም ስላልገባኝ ምን ልንገርህ!? በዝች አለም በንፅህና ያፈቀርኳትና የፍቅሯ ባርያ ሆኜ ታምኜ የኖርኩላት እሷ ብቻ መሆኗን ነው የማውቀው! እሷም ለእኔ እንዲሁ። የተወጋ ልብ ታውቃለህ!? ህመሙ ሲያሰቃየኝ ቢኖርም ፈጣሪን ሳላማርር እኖርበታለሁ! ራስ ወዳድ ሆኜ ለእሷ ክፉ አልመኝም!” አለና ወደዝምታ ተመለሰ። ስንቶች ይሆኑ የበእምነት እጣ ገጥሟቸው ጉዳታቸውን በውስጣቸው ያመቁ!?