/ ሰንደቅ ሪፖርታዥ/
በነሐሴ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. 26 ያህል የሚሆኑ በቦሌ ክፍለከተማ ወረዳ 2 የሚገኙ ነጋዴዎች በውጭ ዜጎች በተለይ በቻይና ዜጎች የህገወጥ ንግድ ምክንያት ስራቸውን ማከናወን ባለመቻላቸው ለቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት ያቀረቡት ማመልከቻ እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱን ለሰንደቅ ጋዜጣ ገልጸዋል።
ቅሬታ ካቀረቡት መካከል በቦሌ ሩዋንዳ በሚኒ ማርኬት ተሰማርተው የሚገኙት ወ/ሮ ትክክል ተበጀ ስለችግሩ ሲያስረዱ፣ “ በአካባቢው የውጭ ዜጎች ስለሚበዙ የገበያ ጥናት በማድረግ ባለፉት ሶስት ዓመታት ለምግብ ፍጆታዎች የሚውሉ ምርቶች እያቀረብን እንገኛለኝ። አሁን ላይ ግን በሕገወጥ የቻይኖች ዜጎች አካባቢያችን ተወሮ ሱቃችንን ለመዝጋት እየተገደድን ነው። ሰው ባሕር አቋርጦ በሰው ሀገር መንደር ውስጥ ገብቶ ጎመን፣ አሳ፣ አሳማ እና ዶሮ ዘርግቶ ይቸረችራል እንዴ? መንደራችን ዘልቀው የሚቸረችሩ ከሆነ እኛ ዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍሎች የት ሄደን ልንሰራ ነው? ከመንግስት አፍ የሰማነው አንድ የውጭ ሀገር ዜጋ ከ200ሺ ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት ውስጥ ብቻ ተሳታፊ እንደሚሆን እንጂ ችርቻሮ ውስጥ መግባት አይችልም። ጎመን ቸርቻሪ ቻይና አጠገባችን ሱቅ ከፍቶ የገበያ ስርዓቱን ሲያፋልሰው መመልከት በእውነት አስተዳደር አለ ብለን ለመጠየቅ ተገደናል። በዚህም ሳናበቃ ያላንኳኳነው የመንግስት አካል የለም። አሁን ላይ ግራ የገባን ወዴት ሄድን አቤት እንደምንል ነው?” ሲሉ ጠይቀዋል።
አያይዘውም፣ “ቻይኖቹ እንዴት እንደሚሰሩ እያወቅን ለመንግስት ኃላፊዎች ስንናገር በከፍተኛ ምርመራ እንጂ በቀላሉ አሰራራቸውን ማረጋገጥ አንችልም ይሉናል። የንግድ ፈቃድ ተከራይተው እየሰሩ በተደጋጋሚ አሳይተናል። አልፎ ተርፎም አምስት ሱቆች በተጨባጭ ማስረጃ ተረጋግጦባቸው እንዲዘጉ ውሳኔ ተላልፎ ነበር። በሳምንቱ ግን የሆነው ሌላ ነው። የተዘጉት ሱቆች ተከፍተው ወደተለመደ ሕገወጥ ስራቸው ገብተዋል። ሱቆቹ እንዲከፈቱ መመሪያ የሰጠውን አካል እንኳን ማን እንደሆነ ለማረጋገጥ አልቻልንም። መንግስት ማረጋገጫ በእጁ ይዞ የዘጋቸውን ሱቆች ከወዴት የመጣ ሌላ አካል ሊከፍታቸው ይችላል? ፍትህ እስከምናገኝ ድረስ የመንግስት ያለህ እያልን እየጮህን አለን” ሲሉ በተሰበረ አንደበታቸው ተናግረዋል።
ወ/ሮ ትክክል ሌላ አስገራሚ ቅሬታቸውን አስቀምጠዋል። ሕብረተሰቡ በራሱ ተነሳሽነት ለሕግ አካሎች ጥቆማ ለማቅረብ ተስማምቶ ወደ ስራ የገባበትን አጋጣሚ ሲያስታውሱ እንዲህ ነበር ያሉን፣ “ ሁለት ኮንቴነር ሩዝ በአካባቢው ሊራገፍ መጣ። በዚህ ጊዜ ጉዳዩን ለፖሊሶች በስልክ አሳወቅን። ፖሊሶቹም በቦታው ተገኙ። ጉዳዩም ለወረዳ 2 ቀበሌ ሪፖርት ተደረገ። ቀበሌውም ሩዙን ለማራገፍ የመጡትን ሰዎች ሩዙ ወደ ሀገር ውስጥ የገባበትን ዶሴ አሳዩን ሲል ይጠይቃቸዋል። በወቅቱ በወቅቱ ምንም አይነት መረጃ ማቅረብ አልቻሉም። የሩዙ ባለቤቱ ይጠራ ሲባል አቶ ፍትህ የተባለ ግለሰብ ቀረበ። ያለውን መረጃ እንዲያሳይም ተጠየቀ። ከስምንት ሰዓት በኋላ አቶ ፍስሃ ውክልና የለኝም የሚል ምላሽ አቀረበ። ውክልና ያላት ሊንዳ የምትባል ቻይናዊ መሆኗን ተናገረ። ሊንዳም ተጠርታ ቀርባ ውክልናዋን ለፖሊሶቹ አቀረበች። ውክልና ሰጪው አቶ ማሕመድ የተባለ ሰው ነው። አቶ ፍትህ ግን በማጭበርበሩ እስር ቤት እንዲቆይ ተደረገ። ከትንሽ ቆይታ በኋላ ግን አቶ ፍትህ ከማረፊያ ቤት እንዲወጠ ተደረገ። ግራ ተጋባን።” ሲሉ ሁኔታውን ያስረዳሉ።
ወ/ሮዋም ቀጠሉ፣ “በሁለት ኮንቴነር ውስጥ የነበረው ሩዝ በማግስቱ ተራገፈ። የተወሰነውን ከመኪናው ላይ ቻይናዋ ሊንዳ አከፋፈለችው። ጥቆማችንም አፈር በላው። እኛ ቤት ተከራይተን እየሸጥን እነሊንዳ በመኪና እየዞሩ በሕገወጥ መንገድ ለቻይኖቹ ሩዝ ዘይት እና ሌሎች የስጋ ምርቶችን ያከፋፍላሉ። ይሄም አልበቃ ብሏት ሊንዳ፣ አጠገባችን በተከራየችው የንግድ ፈቃድ ትቸረችራለች። መንግስት ባለበት ሀገር ይህ ይፈጸማል ብሎ ማን ይገምታል? ከዚህ በላይ ሕገወጥ በደል ከየት ይመጣል? በአንድ አጋጣሚ አንድ የቻይና ደንበኛችን ለምን ከአካባቢው ሱቆች ግዢ እንዳቆመ ስንጠይቀው፣ በየቤታችን የምንፈልገው እቃዎችን ይመጡልናል ነበር ያለን። እኛ ግን ሱቅ ውስጥ ቆመን ቀርተናል” ብለዋል።
ሌላው ከቅሬታ አቅራቢዎች መካከል የሆነውና እና በችርቻሮ ንግድ የተሰማራው አቶ ንጉሴ አበራ የወ/ሮ ትክክልን ቅሬታዎች ሙሉ ለመሉ እንደሚቀበላቸው ገልጾልናል። በራሱ በኩል ያለውንም ሲያስረዳ፣ “ቻይናዎቹ ባልተፈቀደላቸው የችርቻሮ ንግድ ላይ በመሰማራት የንግድ ስርዓቱ በማፋለስ ላይ ናቸው። ሥራችን ሰርተን ለመንግስት የሚገባውን መክፈል እስኪያቅተን ድረስ ጉዳት አድርሰውብናል። የግብይት ስርዓቱን አበላሽተውታል። አቅማቸው ደከም ያሉ ኢትዮጵያዊያን በማግባባት እና በስማቸው ንግድ ፍቃድ በማውጣት በሕገወጥ መንገድ ከገበያ ውጪ ሊያደርጉን ከጫፍ ደርሰዋል። አነስተኛ ጉርሻ እየሰጡ እኛንም መንግስታችንንም ለከፋ ችግር እያጋለጡ ነው የሚገኙት። ወደ ኢትዮጵያ መንግስት ካዝና የማይገባ የንግድ አሰራር ነው የሚከተሉት። ግብይት የሚፈጽሙት እርስ በእርሳቸው ነው። በስማቸው ንግድ ፍቃድ የወጣባቸው ኢትዮጵያዊያን ከግብይይቱ የሚገኘውን ገንዘብ አያውቁትም። ወደ ስራቦታውም አያደርሷቸውም። በፈለጉ ሰዓት ቻይናዎቹ ሀገር ጥለው ይወጣሉ። ዓመታዊ ሒሳባቸውን ሳያሳውቁ በገቢዎች ምርመራ ሳይደረግባቸው ሀገር ጥለው ይወጣሉ። ወይም በሌላ ኢትዮጵያዊ ስም አዲስ ፈቃድ ያወጣሉ። ገቢዎች ንግድ ፈቃዱን ተከትሎ ምርመራ ሲያደርግ ግን እዳው ለእኛው ልጆች ይሆናል። ምንም ባልተሳተፉበት ግብይት ውስጥ ለአደጋ የሚጋለጡ የእኛው ሰዎች ናቸው። ለእስርም የተዳረጉ አሉ። ይህ የሚሆነው መንግስት ባለበት ሀገር ውስጥ መሆኑ ያሳዝነኛል። በተወሰነ ደረጀ የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ንግድ ጽ/ቤት ሊያግዙን ሞክረው ነበር። ግን ሊገፉበት አልቻሉም። በተጨባጭ ማስረጃ የተዘጉ ሱቆች እንዲከፈቱ ተደርጓል። ለእኛ እንቆቅልሽ ነው የሆነብን። ግብይቱን ተወዳዳሪ እና ፍትሃዊ እንዳይሆን አድርገውታል። ስራችን መቀጠል በማንችልበት ሁኔታ ውስጥ ነው የምንገኘው። የመንግስት ያለህ እያለን ፍትህ እስከምናገኝ ድረስ መጮሃችን እንቀጥላለን” ብለዋል።
በአሳማ፣ በዶሮ እና በአሳ ስጋ ምርቶች ላይ የተሰማራው አቶ ታጠቅ ወርቁ በበኩላቸው ቻይናዎቹ ንግድ ፈቃድ ሳያወጡ አየር በአየር የስጋ ምርቶች ላይ ተሰማርተዋል። እኛ ከቄራ ሥጋ ማረጃዎች እያመጣን ነው የምናከፋፍለው። ቻይኖቹ በተለይ አሳማ ከየት እያመጡ እንደሚያከፋፉሉ እንኳን አናውቅም። በትንንሽ ሚኒባሶች ስጋ ጭነው ይመጣሉ። በአካባቢያችን ለሚገኙ ለቻይና ሕገወጥ ሱቆች በፍጥነት አከፋፍለው አራግፈው ይሰወራሉ። በተደጋጋሚ ለሚመለከተው የመንግስት አካል አቤት ብለናል የተሰጠን አጥጋቢ ምላሽ ግን የለም። የሚገርመው በራሳችን ተነሳሽነት ለጤና ቢሮ ለገቢዎች ጥቆማ ስናቀርብ ቻይናዎቹ ከመቼው የእኛን መጠቆም ሰምተው እንደሚሰወሩ ሁሌም ይገርመናል። እኛ ሕግ እያከበርን እነሱ ሕግ የሚጥሱ ከሆነ እንዴት ነው ወደፊት ሰርተን ራሳችን መቀየር ምንችለው?” ሲሉ ጠይቀዋል።
የአካባቢውን የንግድ ማሕበረሰብ ቅሬታዎች አስተናግደን ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ንግድ ጽ/ቤት ነበር ያመራነው። የጽ/ቤቱ የንግድ ኢንስፔክሽን እና ሬጉላቶሪ ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ መስፍን ያዴሳ የአካባቢውን የንግድ ማሕበረሰብ ቅሬታዎች እንደሚያውቁት ነግረውናል። አቶ መስፍን እንደሚሉት የሕግ ንግድ ክፍተት በመጠቀም ሕገወጥ የንግድ ሥራዎች ላይ የቻይና ዜጎች ተሰማርተው እንደሚገኙ መረጃዎች አሉ። ከዚህም በላይ ርቀት ሄደን የሚጠረጠሩ ነጋዴዎችን በድርጅታቸው ስለሚሰሩ የውጭ ሀገር ዜጎች መረጃ እንዲያቀርቡ ጠይቀናል። እርምጃም የተወሰደባቸው አሉ። ችግሩን ከስሩ ለመፍታት ግን ተጨማሪ ስራዎችን መስራት ይጠበቅብናል። ለችግሩም መፍትሄ እንሰጠዋለን ብለዋል።
የሰንደቅ ዝግጅት ክፍል በቦሌ ሩዋንዳ ወረዳ 2 ይህን ዘገባ ለማሰናዳት በሄድንበት ጊዜ የታዘብነውን ለአቶ መስፍን ያዴሳ ያቀረብነውን እናካፍላችሁ። በወረዳ 2 እግር ጥሎት የሄደ ሰው አብዛኞቹ የአካባቢው ሱቆች በቻይና ጽሁፎች አጊጠው ይመለከታሉ። ወደ መደብሮቹ ሲዘልቁ ደግነቱ አብዛኛው ቻይናዊያን ነው የሚገቡት፣ ቻይናዎች በመደብሩ መሸጫዎች ውስጥ ሆነው ደንበኛ ሲያስተናግዱ ትመለከታላችሁ። በአጋጣሚ የካሽ ሬጅስተር ማሽን ስትመታ ያየናትም እንስት ቻይናዊት ነበረች።
በእነዚህ የቻይና ዜጎች መደብር በሚመስሉ ሱቆች ውስጥ አንድም በቻይና ዜጋ ስም የወጣ የተጻፈ የንግድ ፈቃድ አታገኙም። የንግድ ፈቃዶቹ የወጡት በኢትዮጵያዊያን ስም ነው። በኢትዮጵያ ሕግ ንግድ ፈቃድን አይደለም ለውጭ ሀገር ሰው ለኢትዮጵያዊያን ማከራየትም ሆነ ውክልና መስጠት አይቻልም። በመንግስት አካላት መመለስ ያለባቸውም ጥያቄዎች፣ ቻይናዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡበት ቪዛ አይነት ምን ይመስላል? የስራ ፈቃድ እንዴት ነው የሚያገኙት? የተፈቀደላቸው የቆይታ ጊዜ ማለቅ አለማለቁን የሚከታተለው አካል ስራውን በተገቢ ሁኔታ እየተወጣ ነው? ቻይናዎቹ በምን አይነት ስራዎች ላይ መሰማራት አይችሉም? ተሰማርተው ሲገኙስ እርምጃ የሚወስደው አካል ማነው? ከኢትዮጵያ የንግድ ማሕበረሰብ ጋር ግጭት ውስጥ ቢገቡ በኢትዮ-ቻይና ግንኙነት ላይ ወደፊት ሊያሳድር የሚችለው ተፅዕኖስ ታስቦበታል? እና ሌሎችም ምላሽ የሚሹ ነገሮችን ከስፍራው መታዘብ ችለናል።
በመጨረሻም ይህ ጽሁፍ ከተሰናዳ በኋላ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ሊንዳ በተባለችው ቻይናዊት ላይ ክስ ሊመሰርት መሆኑን ለማወቅ ችለናል።n