አቶ ዮናታን ተስፋዬ ተጨማሪ 28 ቀን የምርመራ ጊዜ ተሰጠበት
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
አቶ ዮናታን ተስፋዬ ተጨማሪ 28 ቀን የምርመራ ጊዜ ተሰጠበት
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
በሽብር ተጠርጥሮ ላለፉት ሁለት ወራት በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ በእስር ላይ የሚገኘው የሰማያዊ ፓርቲ የቀድሞው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ተጨማሪ የ28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተሰጥቶበታል፡፡
ዛሬ የካቲት 15/2008 ዓ.ም አራዳ ፍርድ ቤት ለ3ኛ ጊዜ የቀረበው ዮናታን ተስፋየ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡ በዚህም በቀጣይ መጋቢት 13/2008 ዓ.ም ለ4ኛ ጊዜ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡
እስካሁን የተከሳሽነት ቃሉን እንዳልሰጠ ለችሎት የገለጸው ዮናታን በእስር በሚገኝበት ማዕከላዊ ከጠበቃው ጋር እንዲነጋገር እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ከታሰረ ጊዜ ጀምሮ አንድም ቀን ጠበቃውን አግኝቶ ለማነጋገር እንዳልቻለ የተገለጸ ሲሆን፣ አሁንም ከጠበቃው ጋር ሳይመካከር ቃሉን ለመስጠት እንደማይፈልግ ለችሎት አስረድቷል፡፡
የአቶ ዮናታንን ችሎት ለመከታተል በስፍራው የተገኙ ቤተሰቦቹ፣ ወዳጆቹ፣ ጋዜጠኞችና የዲፕሎማቲክ ኮሚኒቲ ተወካዮች ችሎቱ በዝግ በመታየቱ ችሎቱን መከታተል አለመቻላቸው ታውቋል፡፡
