በኦሮሚያ ክልል በየዕለቱ ግድያ እንደሚፈፀምና ሰዎችም በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር እንደሚውሉ «ሒውማን ራይትስ ዎች»ባወጣው ዘገባ ገለጸ።
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
የሒውማን ራይትስ ዎች ዘገባ
የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይላት በኦሮሚያ ክልል ሰላማዊ ተቃውሞ ሰልፎች ባካሄዱ ሰዎች ላይ አስከፊ እና ደም አፋሳሽ ርምጃ እየወሰዱ ነው ሲል መንበሩን ኒው ዮርክ ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት፣ «ሒውማን ራይትስ ዎች» ዛሬ ባወጣው ዘገባ ገለጸ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት በዘገባው እንዳስታወቀው፣ ጎርጎሪዮሳዊው 2016 ዓ,ም ከገባ ወዲህ በዚሁ አካባቢ ከሞላ ጎደል በየዕለቱ ግድያ እንደሚፈፀም እና ሰዎችም በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር እንደሚውሉ መረጃ ደርሰውታል። የፀጥታ ኃይላት ካለፈው ጥር ወር አንስቶ በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ እንዳሻቸው ተኩስ መክፈታቸውን፣ በእስራትም ወቅት ሰዎችን መግደላቸውን፣ በጅምላ ማሰራቸውን እና የቁም ስቅል ማሳየታቸውን የተቃውሞ ሰልፈኞች እና የዓይን እማኞች ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ተናግረዋል።
«ሒውማን ራይትስ ዎች» ወደ ኦሮሚያ አካባቢ መግባት ላይ ገደብ ስላረፈ የራሱን አጥኚዎች ወደ አካባቢው ልኮ ምን ያህል ሰው መገደሉን ወይም መታሰሩን ለማጣራት አለመቻሉን ጠቁሞዋል።
ኢትዮጵያውያን የመብት ተሟጋቾች እአአ ከኅዳር 12፣ 2015 አንስቶ ከ 200 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ማለታቸውን «ሒውማን ራይትስ ዎች» አመልክቶዋል። የጸጥታ ኃይሎችም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ክስ ሳይመሰረትባቸው በቁጥጥር ስር አውለዋል ብሏል።
ተቃውሞው አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች የቀጠለ ቢሆንም፤ ከእነዚህ አካባቢዎች ስለ ተቃውሞዎቹ የሚሰማው መረጃ በጣም ትንሽ መሆኑን የ«ሒውማን ራይትስ ዎች» የአፍሪቃ ቀንድ ባልደረባ ፌሊክስ ሆርን ለፈረንሳይ ዜና ወኪል፣ « አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።
Source: DW Amharic