1987ን እንደ መስታወት AKEMEL NEGASH


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


1987ን እንደ መስታወት  AKEMEL NEGASH
ትኩስ የወጣትነት ዕድሜውን ማጣጣም ከጀመረ ገና ሦስት እና ዐራት ዓመታት ብቻ ናቸው የተቆጠሩት። ምጥጥ ባለው ገጽታው ዳርቻዎች ላይ ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩት የፀጉር ልቃቂቶች ‹‹ደረስክ ደረስክ›› የሚሉት ይመስላሉ። ዕድሜው የሃያዎቹን መጀመሪያ መርገጡ ቢሆንም ገጽታው እና አኳኋኑ ግን የእድሜውን ያህል ትንሽ አይደሉም። ወጣት ቢላል ዛሬ ደግሞ ሁለመናው ርብሽብሽ ብሏል። አጠር ባለው ቁመናው ላይ እንደ ነገሩ የሆነው አለባበሱ ተዳምሮ ሲታይ ጋብቻ ለመፈጸም አንድ ወር የቀረው ሙሽራ አይመስልም። በአእምሮውም ከአንድ ወር በኋላ ስለሚፈጽመው ጋብቻ ሳይሆን ከአንድ ቀን በፊት ስለተፈጠረው አሳዛኝ ክስተት ነው ደጋግሞ እያሰበ ያለው።
ቢላል የትናንቱ ዓይነት ክስተት እውን እንዳይሆን ከርዕይ አጋሮቹ ጋር በመሆን ብዙ ቢጥርም ሊሳካለት አልቻለም። እንዲህም ሆኖ ግን ላለፉት ዐራት ዓመታት ሌት ከመዓልት ሲተጋለት የነበረው ማኅበራቸው ‹‹በዚህ ዱብ ዕዳ ክስተት ምክንያት ይገታል›› የሚል ግምት አልነበረውም። ለዚህም ነበር ገና ከማለዳው ጉዳዮቹን ከውኖ የማኅበሩ ጽ/ቤት ወደሚገኝበት ጉለሌ ሠፈር ሲከንፍ የነበረው። ቢላል ግምቱ ስህተት እንደነበር የተረዳው የማኅበሩ ጽ/ቤት ሲደርስ ነበር። የጽ/ቤቱ ግቢ እና አካባቢው በሥርዓቱ ታጣቂዎች ተከብቧል። ቢላል ያለምንም ፍርሃት ወደ ማኅበሩ ጽ/ቤት ቅጽር ሲገባ ቢሮው ሳይሆን የፖሊስ ‹‹ፓትሮል›› ነበር የተቀበለው። በዕለቱ ቢላልን ጨምሮ ከሰባት በላይ የማኅበሩ አባላት እና ሠራተኞች በሥርዓቱ ኃይሎች ተይዘው ወደ ማዕከላዊ ወህኒ ቤት ተወሰዱ።
ከቢላል እና ባልደረቦቹ መያዝ አንድ ቀን በፊት የካቲት 14/1987 የተከሰተውና ለ 10 ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው የአንዋር መስጊድ ግርግር ያመጣው ዳፋና ድኅረ ክስተቱ ለቢላል እና ለባልደረቦቹ ወህኒ መውረድ ብቻ የተረፈ አልነበረም። ዛሬ የኢትዮጵያ ሙስሊም ለሚገኝበት የታሪክ እውነታ ማሳያ መስታወት ነው። ክስተቱን በቅርበት የሚያውቁት አንድ ምሁር ‹‹የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የታሪክ መጠምዘዣ›› ሲሉ ከ 1997 የኢትዮጵያ ፖለቲካና ምርጫ ጋር ይመስሉታል – በብዙ መልኩ ወደ ኋላ የጎተተን መሆኑን በማስታወስ።
ክስተቱ በደፈናው ‹‹በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ጉባዔ ውስጥ የተፈጠረ የሥልጣን ሽኩቻ›› ተብሎ በወቅቱ በነበሩ የመንግሥት ብዙኀን መገናኛዎች ቢገለጽም ብዙዎች ግን ክስተቱን ከሕዝብ የ‹‹ሥልጣን ይገባኛል›› ጥያቄ ጋር አያይዘው ሊያነሱት ይሞክራሉ።
የደርግ ጉባዔ
በኢትዮጵያ ለዘመናት ነግሦ የቆየው ሰለሞናዊው ሥርዓተ መንግሥት ፍጻሜ በሆነው የኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መብት እና ኅልውና ሥልታዊ በሆነ መንገድ ይገፋ ነበር። የመብት ረገጣዎቹ መገለጫ ዓይነት ብዙ የነበረ ቢሆንም ሙስሊሙን ኅብረተሰብ መሪ ድርጅት አልባ ማድረግ ግን ዐቢይ የሥርዓቱ መገለጫ ነበር ማለት ይቻላል። እስከ 1960ዎቹ አጋማሽ መቆየት የቻለው የኃይለሥላሴ መንግሥት በወቅቱ በአገሪቱ በተከሰተው ድርቅ እና ችጋር፣ በከተማና በገጠር በተነሳው የተማሪዎችና መምህራን አመፅ፣ እንዲሁም የኤርትራ የነጻነት ጥያቄ ባስነሳው ውዝግብ የሥርዓቱ ውስጣዊና ውጫዊ ጥንካሬዎች መፈረካከስ ጀምረው እንደነበር ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌ. ዴሌቦ ‹‹የኢትዮጵያ የገባር ሥርዓትና ጅምር ካፒታሊዝም›› በሚለው መጽሐፋቸው አስነብበዋል። የሥርዓቱ ሁለንተናዊ በደል ገፈት ቀማሾች የነበሩት ኢትጵያውያን ሙስሊሞች ለመውደቅ መንፈቅ የቀረውን የኃይለሥላሴ መንግሥት ለመቃወም በሚያዝያ 12/1966 300‚000 (ሦስት መቶ ሺህ) ሙስሊሞች የተገኙበት ትዕይንተ ሕዝብ አካሄዱ። በትዕይንተ ሕዝቡ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ የሚገቡትን የዜግነት መብቶች ቢጠይቅም የኃይለሥላሴ መንግሥት ለጥያቄዎቹ በጎ ምላሽ ሳይሰጥ ቆይቶ በመስከረም 2/1967 ፍጻሜውን አገኘ።
በሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም የተቃኘው የደርግ መንግሥት ሥልጣን ላይ ሲወጣ የሕዝቡን የመደራጀት ጥያቄ ገሸሽ ማድረግ አልተቻለውም። ለዚህም ነበር እንደ ሌሎች ሲቪል ማኅበራት ሁሉ ‹‹የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ጉባዔ›› በሚል ሥያሜ ሙስሊሞች መሪ ድርጅት ማቋቋም የቻሉት። በወቅቱ ከፍተኛ ጉባዔው ከመላው አገሪቱ በተመረጡ የሕዝብ እንደራሴዎች መመራት ባይችልም በመሐል አገር ሕዝብ የሚያውቃቸው 50 ዑለሞችና ኢማሞች ከየብሔረሰቡ ተውጣጥተው በመሪነት ቦታው ላይ መቀመጥ ችለው ነበር።
ከፍተኛ ጉባዔው የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በውስጡ ለማሳተፍ 4 ዓይነት የአባልነት ኮታዎችን አስቀምጦ የነበረ ሲሆን የከፍተኛ ጉባዔውን 50 በመቶ የአባልነት ወንበር የሚይዙት ዑለማዎች እንዲሆኑ፣ 30 በመቶ ምሁራን፣ 10 በመቶ አዛውንቶች፣ እንዲሁም 10 በመቶ ወጣቶች በተቋሙ ውስጥ ውክልና እንዲኖራቸው ተደርጓል።
ይህ ከፍተኛ ጉባዔ በታላቁ ዓሊም ሐጂ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብ ሊቀመንበርነትና በሐጂ ኢብራሒም ዐብዱሰላም ምክትልነት ይመራ የነበረ ሲሆን በወቅቱ በነበረው ፖለቲካዊ ጫና ምክንያት ከፍተኛ ጉባዔው ይህ ነው የሚባል ጠንካራ ተግባር ማከናወን ሳይችል ቀርቶ እንደነበር የድርጅቱን ታሪክ በስፋት የሚያውቁት ሸኽ ሙሐመድ ዘይን ዘህረዲን ያስረዳሉ።
እንደ ሸኽ ሙሐመድ ዘይን ገለጻ ከፍተኛ ጉባዔው እስከ 1970ዎቹ መጨረሻ ድረስ ያለ አመርቂ ሥራ ቆይቶ በ 1970ዎቹ መባቻ ወጣቶች ተሳትፎ የሚያደርጉበት ‹‹የዳዕዋና ኢርሻድ ኮሚቴ›› ተቋቁሞ እንቅስቃሴውን ማሳደግ ችሎ ነበር። ይህም እንቅስቃሴ ቢሆን በአንዋር መስጊድ ኢማምና በከፍተኛ ጉባዔው ሊቀመንበር ሐጂ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብ ሕልፈት ተገታ። የሊቀመንበሩን ሕልፈት ተከትሎም ተተኪያቸውን የማስቀመጡ ሂደት በጉባዔው አባላት መካከል ትልቅ አለመግባባትን ፈጠረ። ይህ ክስተት የተሠጋውን ያህል ግጭት ባይፈጥርም የአዲሱ ሊቀመንበር ሐጂ ዑመር ሑሴን መመረጥ ከውዝግብ የፀዳ አልነበረም።
ሐጂ ዑመር የጠቅላይ ጉባዔውና የሸሪዓ ፍ/ቤት ሊቀመንበር ሆነው መሠየማቸው በጠቅላይ ጉባዔው አባላት መካከል ከፊል ቅያሜን አሳድሮ ቢቆይም የአዲሱ ከፍተኛ ጉባዔ ሕልውና በሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን መቆጣጠር ተፈተነ።
በወታደራዊው መንግሥት መውደቅ ማግሥትም ጉባዔው ‹‹ከደርግ መንግሥት ጋር መቀበር አለበት›› የሚለው የብዙዎች እምነት ሆነ። በተለይም ከደርግ መንግሥት የደኅንነት መሥሪያ ቤት ጋር የቀጥታ ግንኙነት የነበረው የሐጅና ዑምራ ኮሚቴ ይፈጽማቸው ከነበሩ አሥተዳደራዊ በደሎች እና ሃይማኖታዊ ጣልቃ ገብነቶች ጋር ተዳምሮ ሕልውናው እንዲያከትም መደረጉን ሸኽ ሙሐመድ ዘይን ያስረዳሉ።
ሁለቱ አንጃዎች
ከፍተኛ ጉባዔውን አፍርሶና አመራሩን አውርዶ አዲስ የሥራ አመራር መዋቅር ለመፍጠር ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ ኮሚቴ ተዋቅሮ በወቅቱ ሥራውን ጀምሮ ነበር። ይህ ኮሚቴ ራሱን ‹‹ጊዜያዊ የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ጉባዔ›› በሚል ሠይሞ በፊት አውራሪ ሐጂ ሙሐመድ ራሕመቶ ሊቀመንበርነት እንቅስቃሴውን ማድረግ ጀመረ። በሌላ አቅጣጫም ወንበሩን ላለማስነጠቅ የሚሻው የከፍተኛ ጉባዔው አመራር ‹‹ከጊዜያዊ እስልምና ጉዳዮች ጉባዔ›› ኮሚቴ ጋር ፍትጊያ እና ትንቅንቅ ውስጥ ገባ።
ጊዜያዊ ኮሚቴውን የሚመሩት የወቅቱ የአዲስ አበባ መስጊዶች ሊቀመንበር እና ሰብሳቢ ፊት አውራሪ ሐጂ ሙሐመድ ራሕመቶም ኮሚቴውን በማስተባበር የጉባዔውን አመራሮች ከሥልጣን ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረታቸውን ቀጠሉ።
ይህን በሁለቱ አጀንዳዎች መካከል የተከሰተውን የ‹‹ሥልጣን ይገባኛል›› ውዝግብ ለመፍታት የወቅቱ የክልል 14 መሥተዳድር የአሥተዳደርና የፖሊስ ኃላፊዎች አቶ ኻሊድ ዐብዱራሕማንና አቶ ሐሰን ሺፋ ጣልቃ በመግባት ከሁለቱም አንጃዎች አምስት አምስት ሰዎች ተውጣጥተው ጊዜያዊ አስመራጭ ኮሚቴ እንዲያዋቅሩ ትዕዛዝ ይጣሉ።
የዚህ አስመራጭ ጊዜያዊ ኮሚቴ ሊቀመንበር ከከፍተኛ ጉባዔው አንጃ እንዲሆን ሲወሰን ምክትል ሊቀመንበሩ ደግሞ ከተቃዋሚው (ከጊዜያዊ የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ጉባዔ) ወገን እንዲሆን ይደረጋል።
በሌላ አቅጣጫም በ 1936 በንጉሡ የወጣውን የናኢባና የሸሪዓ ፍርድ ቤት አዋጅ ለመመርመርና ለማጠናከር በሚያዚያ 1984 በተቋቋመ ኮሚቴ ውስጥ የሕዝብ ግንኙት ኃላፊ ሆነው ተመርጠው የነበሩትና ኋላም ሰብሳቢ የሆኑት የትግራይ ተወላጅ ግራዝማች ሐዲስ ኑርሑሴን ‹‹የታሪክ ማስታወሻ፤ የብሔርና የሃይማኖት ጭቆና በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ባዘጋጁት ረቂቅ ድርሳን የወቅቱ የቅዱስ ቁርኣን ማኅበር ሊቀመንበር ሐጂ ሙሐመድ አወል ረጃ አስመራጭ ኮሚቴው ውስጥ ለመግባት ጥረት አድርገው በአቶ ሐሰን ሺፋ ከልካይነት መሳተፍ ሳይችሉ ቀርተው እንደነበር ጽፈዋል።
ግራዝማች በተጨማሪም የማስመረጥ ሂደቱ ከተጀመረ በኋላ ከሁለቱም ወገኖች ከተመረጡት አሥር ግለሰቦች መካከል የአብሬት ሸኽ ልጅ ከሆኑት ሰይድ መዚድ በስተቀር ሁሉም በአጭር ጊዜ ውስጥ የሐጂ ሙሐመድ አወል ረጃ አቀንቃኝ ሊሆኑ እንደቻሉ ጽፈዋል። የአስመራጭ ኮሚቴው ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት ሸኽ ሙሐመድ ዘይን በበኩላቸው አሥሩ አስመራጭ አባላት ዐራት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከወረዳ አንስቶ የተመረጡ 500 የሚደርሱ አባላት ያሉት ጠቅላይ ጉባዔ በማዋቀር ፍትሐዊ ምርጫ ማካሄዳቸውን ይገልጻሉ – አድሎአዊነት ያልነበረ መሆኑን በማስገንዘብ።
ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡ አምስት መቶ አባላት ያሉትን ጠቅላላ ጉባዔ ያዋቀረው አስመራጭ ኮሚቴ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ሊቀመናብርቶችና ሥራ አስፈጻሚ አባላትን አስመረጠ። አስመራጭ ኮሚቴው እንደ ዋና መሥፈርት አስቀምጦት የነበረውና ከፊል ውዝግብ አስነስቶ የቆየው ቅድመ ሁኔታ ‹‹ሊቀመንበሩና ምክትል ሊቀመንበሩ ዓሊም መሆን አለባቸው›› የሚለው ነበር።
ይህ ቅድመ ሁኔታ ከመመሪያው እንዲወጣ የሚፈልጉ ግለሰቦች ብቅ ብለው የነበረ ሲሆን ዋነኛ ምክንያታቸውም ‹‹ዑለሞች መች መምራት ይችሉና?›› የሚል ነበር። ሆኖም በጠቅላላ ጉባዔው ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው ዑለሞች ‹‹መቼ የመሪነቱን ዕድል ሰጣችሁን?!›› የሚል ሙግት በማንሳት ቅድመ ሁኔታው እንዲጸና አደረጉ።
በወቅቱ የአስመራጭ ኮሚቴው አባል የነበሩ አንድ ሥማቸው እንዲጠቀስ የማይሹ ግለሰብ መሥፈርቱን ከመመሪያው እንዲያወጡ ማስፈራሪያና ዛቻ ደርሶባቸው እንደነበር በመግለጽ የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ገብተውበት የነበረውን ፍርሃትና ሥጋት ያስታውሳሉ። ይህንኑ መሥፈርት አስመልክቶ በጥቅምት 1985 የወጣው ‹‹ቢላል›› መጽሔት ‹‹ምርጫው እንዲሳካ›› በሚል ርዕስ ‹‹ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ወክሎ የሚቀመጥ ሰው ከማንምና ከምንም የጠራና ስለሃይማኖቱ ብቁ እውቀት ያለው፣ ጥቅም የማያሸንፈው፣ በዘር በጎሣ የማያምን፣ ዲኑን ለማገልገል ፍላጎት ያለው›› መሆን እንዳለበት በማስገንዘብ ለተቀመጠው መሥፈርት ያለውን ድጋፍ ለማሳየት ሞክሯል።
(የጠቅላላ ጉባዔው ተሳታፊዎች ከፊል ገጽታ — ‹‹ቢላል›› መጽሔት፤ ኅዳር 1985)
በአዲሱ አስመራጭ ኮሚቴ ከከፍተኛ ጉባዔነት ወደ ጠቅላይ ጉባዔነት ሥያሜ ለተለወጠው የሕዝበ ሙስሊሙ ተቋም መሪነት ቦታ ከጥቅምት አምስት እስከ ጥቅምት ስምንት 1985 ለዐራት ቀናት በተደረገው ጉባዔ እና ምርጫ ሸኽ ሙሐመድ አሕመድ ሰዒድ ሊቀ መንበር፣ ሐጂ ሙሐመድ ሐሰን ደግሞ ተቀዳሚ ሊቀመንበር ተደርገው ተመርጠዋል። ሐጂ ሙሐመድ አወል ረጃ በበኩላቸው ሁለተኛ ምክትል ሊቀመንበርና የተቋሙ የኢኮኖሚ (ፋይናንስ) ዘርፍ ኃላፊ ሆነው ተመርጠዋል።
ጉባዔው ከሾማቸው ሰባት የሥራ አስፈጻሚ አባላት በተጨማሪም ሃያ ስምንት የሥራ አመራርና ሰባት የአሥተዳደር ዘርፍ ሠራተኞችን መርጧል። ምርጫው የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ያልነበረበት ቢሆንም ሂደቱ በውንብድና የተሞላ እንደነበር የሚናገሩ አልጠፉም። የጉባዔውንና የምርጫውን ሙሉ ሂደት የታዘበ የቀድሞ የ‹‹ቢላል›› መጽሔት አዘጋጅ ‹‹በምርጫው የመጨረሻ ሰዓታት በተሠራ አስገራሚ ድራማ ሐጂ ሙሐመድ አወል ረጃና ደጋፊዎቻቸው ተመርጠው የምርጫው ሒደት ተጠናቀቀ›› በማለት ለየሙስሊሞች ጉዳይ ትዝብቱን አጋርቷል።
የአስመራጭ ኮሚቴው ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት ሸኽ ሙሐመድ ዘይን ኮሚቴው አስቀምጧቸው ከነበሩት ሁለት ዐቢይ ዓላማዎች አንዱን፣ ማለትም ጠቅላይ ጉባዔውን አገር አቀፍ በሆነ መልኩ በማዋቀር ረገድ የተሳካለት መሆኑን ሲገልጹ ለጠቅላይ ጉባዔው ጥራት ያላቸው መሪዎች በማስመረጥ በኩል ግን ብዙም ሊሳካላቸው እንዳልቻለ ያስረዳሉ። ለዚህም ለተቋሙ በሊቀመንበርነት የተመረጡትን የሐጂ ሙሐመድ አሕመድ ሰዒድን አሥተዳደራዊ ብቃት አናሳነት በዋቢነት ይጠቅሳሉ። ይህም በተግባር መታየቱን የሚገልጹ በርካቶች ናቸው።
አዲሱ ጠቅላይ ጉባዔ (መጅሊስ) ከመንግሥትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ባገኘው ድጋፍ በኅዳር 1985 ወደ ሥራ በገባበት ወቅት ነበር ለየካቲት አሥራ ዐራቱ የአንዋር መስጊድ ግርግር መነሻ ክብሪት የተጫረው።
የጠቅላይ ጉባዔው የሥራ አመራር ቦርድ ሥራውን በጀመረበት ወቅት ባደረገው የመጀመሪያ ስብሰባ አጀንዳ አድርጎ አስቀምጦ የነበረው የአቻ ማኅበራትን ጉዳይ ነበር። ጉባዔው በደርግ ውድቀት ማግሥት የተቋቋሙ የተለያዩ ኢስላማዊ ማኅበራት የሚሠሩት ‹‹የእኔን ሥራ በመሆኑ የሥራ ምስስሎሽ ያላቸው ማኅበራት አያስፈልጉም›› በሚል ምክንያት ማኅበራቱ እንዲፈርሱ ውሳኔ አሳለፈ። እንዲፈርሱ ከተወሰነባቸውና በወቅቱ ከፍተኛ እውቅና አግኝተው ከነበሩ ማኅበራት መካከል ‹‹ሙነዘመተ ሸባብ›› በጉልህ ይጠቀሳል።
ወጣቶቹ
ኢሕአዴግ በግንቦት 1983 ደርግ ወድቆ የምኒልክ ቤተ-መንግሥት ከገባ በኋላ በተዋቀረው የሽግግር መንግሥቱ ቻርተር የመደራጀት ነጻነት በመከበሩ በርካታ ማኅበራትና ሲቪል ተቋማት ፈቃድ አውጥተው መንቀሳቀስ ጀምረው ነበር። የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ድርጅት (ኢ.ሙ.ወ.ድ) (በተለምዶ አጠራሩ ሙነዘማ) ከእነዚህ የመጀመሪያዎቹ ማኅበራት አንዱ ነበር።
ማኅበሩ ምንም እንኳ የኢሕአዴግን ወደ አዲስ አበባ መግባት ተከትሎ ፈቃድ በማውጣት በሕጋዊነት መንቀሳቀስ ቢጀምርም ምሥረታው በደርግ የመጨረሻዎቹ የአገዛዝ ዓመታት እንደ ነበር የማኅበሩ የዳዕዋ ሥርጭት ክፍል ውስጥ ያገለግል የነበረው ወጣት ቢላል ተማም ይገልጻል።
እንደ ቢላል አባባል በወቅቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይማሩ የነበሩ ሙስሊም ወጣቶች የማኅበሩን የምሥረታ እና የዓላማ ጥንስስ በውይይት ያዳብሩት ነበር። ኢ.ሙ.ወ.ድ (ሙነዘማ) ፈቃድ አውጥቶ ሕጋዊ እውቅና ካገኘ በኋላ ሙስሊም ወጣቶችን በእምነት የማጽናት ዓላማ በመያዝ የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወን ጀምሮ ነበር። ከእነዚህም ሥራዎቹ ውስጥ ለወጣቶች በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ አጫጭር እና ረጃጅም ሥልጠናዎችን ማዕከሉ በሚገኝበት ጉለሌ ይሰጥ ነበር። እነዚህን ሥልጠናዎች ለመካፈል እና የማኅበሩም አባል ለመሆን በርካታ ወጣቶች ከመላዋ አገሪቱ ወደ ማኅበሩ ጽ/ቤት ይጎርፉ ነበር።
በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ወጣት ድርጅት ውስጥ ለአንድ ወር ከሃያ ቀን ያህል የተርቢያ ሥልጠና እንደወሰደ የሚናገረው የ 33 ዓመቱ ጎልማሳ ረጀብ ኸድር ሥልጠናውን ከማግኘቱ በፊት የነበረውን አናሳ እውቀትና ለሃይማኖቱ የነበረውን ግዴለሽነት በማስታወስ በሥልጠናው በመሳተፉ ያገኘውን ሃይማኖታዊ እውቀትና ቅንዓት ይጠቁማል። ‹‹ሙነዘማ እስከ ዛሬ ቢኖር ኖሮ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሃይማኖተኛ እና ዓሊም ወጣቶችን ማፍራት ይቻል ነበር›› በማለትም ሐሳቡን ይሰነዝራል። የወጣቶቹ ድርጅት ከሚሰጣቸው የተመላላሽ እና የአዳር ሥልጠናዎች በተጨማሪም ‹‹የጁሙዓ መልዕክት›› በሚል ርዕስ በየሳምንቱ ዐርብ በምትሠራጭ በራሪ ወረቀት እና ‹‹አድ ዳዕዋ›› የሚል ሥያሜ በነበራት የድርጅቱ ወርሐዊ መጽሔት ሰበካ ያካሂድ የነበረ ሲሆን ጠጠር ያሉ ኢስላማዊ ጉዳዮች የሚነሱባቸው ሕዝባዊ የውይይት መድረኮችንም በቋሚነት ያሰናዳ ነበር።
እነዚህ የድርጅቱ እንቅስቃሴዎች በወጣቶች በኩል ሰፊ ተቀባይነትን ከማግኘታቸውም በላይ የወጣቶችን የዲን ትጋት በማሳደግ ረገድም ከፍተኛውን ሚና ተጫውተው እንደነበር ድርጅቱን በቅርበት ያውቁ የነበሩ አንድ ምሁር ያስረዳሉ። ምሁሩ የማኅበሩን ሥልጠና ያገኙ ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ ማኅበሩን ያገለግሉ የነበሩ ወጣቶች ሙሉ ጊዜያቸውን ለማኅበሩ አገልግሎት ሰጥተው እንደነበር ያወሳሉ። ወጣት ቢላል በበኩሉ የድርጅቱ አገልጋዮች የመኝታ ሰዓት እንኳ እንዳልነበራቸው ከመግለጽ አይቦዝንም። ‹‹ትዳር ያለው ትዳሩን፣ ሥራ ያለው ሥራውን ትቶ ለማኅበሩ እንቅስቃሴ ደፋ ቀና ይል ነበር›› በማለት የወቅቱን ሁኔታ ለማስቃኘት ይሞክራል።
የወጣት ድርጅቱ ከሌሎች አቻ ማኅበራት በተለየ መልኩ ያደርገው የነበረው እንቅስቃሴ በመንግሥትና በሌሎች ወገኖች ትኩረት ውስጥ ከትቶት እንደነበር የሚናገሩት ምሁሩ በተለይም ማኅበሩ በአደባባይ ውይይት ያደርግባቸው የነበሩ ሸሪዓ ነክ ጉዳዮች በጠላቶች ዒላማ ውስጥ ከትተውት እንደነበር ሳይገልጹ አያልፉም። እንደ ምሁሩ ገለጻ ሁኔታውን ለማርገብ ጥቂት ግለሰቦች ወደ ማኅበሩ ሊቀመንበር ሸኽ ሰይድ አሕመድ ሙስጠፋ በመሄድ የማኅበሩን አካሄድ ለማለሳለስ ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ሁኔታዎች ግን ከመርገብ ይልቅ ተካርረው መሄዳቸውን ቀጠሉ።
በኅዳር 26/1985 በሕንድ የዐራት መቶ ዓመታት ዕድሜ ያለው የአዮዲያ መስጊድ በሒንዱ ጽንፈኞች መፍረሱን ተከትሎ ኢ.ሙ.ወ.ድ (ሙነዘማ) ድርጊቱን የሚቃወም ትዕይንት ሕዝብ ለማካሄድ በታኅሣሥ 4/ 1985 በአዲስ አበባ ከተማ ሰልፍ ጠራ። ይህ ድርጊት ሙስሊም ባልሆኑ ወገኖች ብቻ ሳይሆን በሙስሊሙ በኩልም ተቃውሞ ገጠመው። የማኅበሩ መሥራች አባል እንደሆኑ የሚናገሩትና የማኅበሩ መማክርት ጉባዔ ምክትል ጸሐፊ የነበሩት ሐጂ ሙሐመድ አወል ረጃ የሰልፉን ሐሳብ ውድቅ በማድረግ የማኅበሩ አመራሮች የሰልፉን ሐሳብ እንዲሰርዙ ቢወተውቱም ሊሳካላቸው አልቻለም ነበር። ሐጂ ሙሐመድ አወል በአመለካከት ረገድም የወጣት ድርጅቱ የ‹‹ሠለፊያ››ን አስተሳሰብ ለማስፋፋት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ብልሃት ያልታከለበት መሆኑንና የሌሎችንም ቡድኖች አስተሳሰብ መጫን እንደሌለበት የሚያስታውሱ ተደጋጋሚ ምክሮችን ለድርጅቱ አመራሮች መለገሳቸውን ይናገራሉ። ሐጂ ሙሐመድ አወል በወቅቱ ሰላማዊ ሰልፉ እንዲሰረዝ አቅርበዋቸው ከነበሩ መከራከሪያዎች መካከል ‹‹የኢትዮጵያን ሙስሊም ጥያቄ ሳንመልስ የሌሎች አገራትን ሙስሊሞች ጥያቄ ማንሳት ከመርሕ አንፃር ተገቢ አይደለም›› የሚለው ይገኝበት የነበረ ሲሆን ዋነኛ መሟገቻ ነጥባቸው የነበረው ግን ‹‹ሰልፉ ትኩረት ውስጥ ይከትተናል፣ ያስመታናል›› የሚል እንደነበር ሐጂ ሙሐመድ አወል ዛሬ ላይ ሆነው ያስታውሳሉ። ውዝግብ ያስነሳው ሰልፍ በመጀመሪያ ፈቃድ ተከልክሎ እንደነበር የሚገልጸው ቢላል በበኩሉ ድርጅቱ ግን ፈቃዱን ቢነፈግ እንኳ ሰልፉን ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይል በማሳወቁ ሰልፉ ፈቃድ አግኝቶ በታኅሣሥ 4/1985 ሊካሄድ መቻሉን ያስረዳል።
ከ 30 ሺህ በላይ ሰዎች በተሳተፉበት በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ለወቅቱ የሕንድ እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሮች የተጻፉ ደብዳቤዎች ተነበዋል። ‹‹ሰልፉ የሚጠበቅበትን ውጤት ባያመጣም ድምጻችንን አሰምተን ተመልሰናል›› ይላል ቢላል – ዓላማውን ከውጤቱ ጋር እያነፃፀረ። ሌሎች ወገኖች ደግሞ ሰልፉ በስሜት ብቻ የተደረገ እንደነበር በመጥቀስ ወቀሳቸውን በሙነዘማ ላይ ይሰነዝራሉ። ምሁሩ በበኩላቸው ‹‹የቦስኒያን ጭፍጨፋ በመሰሉ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ድርጅቱ መንጠልጠል ያበዛ ነበር›› በማለት አካሄዱን ይወቅሳሉ። የዚህ ሰላማዊ ሰልፍ መከናወን አዲሱን ጠቅላይ ጉባዔ በምክትል ሊቀመንበርነት በሚመሩት በሐጂ ሙሐመድ አወል ረጃና ሙነዘማን በመሰሉ አቻ ማኅበራት መካከል የተፈጠረውን ክፍተት የበለጠ አሰፋው።
(በየኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ድርጅት የተዘጋጀውና በሕንድ አገር የተፈጸመውን የመስጊድ ማፍረስ ወንጀል የሚቃወም ትዕይንተ ሕዝብ — ‹‹ቢላል›› መጽሔት ታኅሣሥ/1985)
3+8>0
በ 77 ዓመቱ ጎልማሳ ሐጂ ሙሐመድ አሕመድ ሰዒድ የሚመራው አዲሱ ጠቅላይ ጉባዔ ላይ ገና ከጅምሩ የአመራር ምርጫውን አስመልክቶ ቅራኔ የነበራቸው ማኅበራት ተቋሙ በምሥረታው የመጀመሪያ ስብሰባ የማኅበራቱን አላስፈላጊነት በመግለጽ እንዲፈርሱ መወሰኑ የማኅበራቱን ጥርስ አስነከሰበት። መጅሊሱ ይህን ውሳኔ ሲያሳልፍ ምንም ዓይነት የሕግ ማእቀፍ አልተከተለም ነበር።
የኢትዮጵያ ዑለማዎች ማኅበር እንዲፈርሱ ከተወሰነባቸው ማኅበራት አንዱ ሲሆን ከወሎ አውራጃ በመወከል ከ 1966 ጀምሮ በከፍተኛ ጉባዔው የሐጅና ዑምራ ዘርፍ ውስጥ ያገለገሉት ሐጂ ምቾት አሕመድ ጠቅላይ ጉባዔው ‹‹የዑለማ ም/ቤቱ ፈርሶ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ውስጥ ይጠቃለል›› በሚል ያሳለፈው ውሳኔ ዑለማዎችን በሙሉ አስቆጥቶ እንደነበር ያስታውሳሉ። ‹‹ውሳኔው የዑለማዎችን ክብር የነካ ነበር።››
ሌሎች ወገኖች በበኩላቸው ጠቅላይ ጉባዔው ኢስላማዊ ማኅበራት በሙሉ እንዲፈርሱ ሲወስን በሐጂ ሙሐመድ አወል ረጃ የሚመራው ማኅበር እንዲፈርስ አለመወሰኑ የማኅበሩ አመራሮች በሐጂ ሙሐመድ አወል ላይ እንዲያተኩሩ ምክንያት ሆኗቸዋል። በሂደት የጠቅላይ ጉባዔውን ውሳኔ የተቃወሙና ሌሎች የጠቅላይ ጉባዔው ሕጋዊነት ላይ ጥያቄ ያነሱ አምስት ማኅበራት የጠቅላይ ጉባዔውን ሕልውና ለመታደግ ግንባር ፈጠሩ። እነዚህ ማኅበራት የኢትዮጵያ ዑለማዎች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ አንሷረ ሱንና ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ድርጅት (ሙነዘማ)፣ የኢትዮጵያ ዳዕዋና እውቀት ማኅበርና በግራዝማች ሐዲስ ኑርሑሴን የሚመራው የሸሪዓ ፍርድ ቤትን አቅም ለመመርመርና ለማጠናከር የተቋቋመ ኮሚቴ ናቸው። እነዚህ ግንባር የፈጠሩ ማኅበራት ተጠሪዎችና ሌሎችም የሙስሊም ኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት የጋራ መድረክ ተዘጋጅቶ ተከታታይ ውይይቶች መካሄድ ጀመሩ። በማኅበራቱ አደረጃጀት የሚካሄዱት እነዚህ የውይይት መድረኮች በሙስሊሙ ኅብረተሰብ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ‹‹ሙስሊሙ ኅብረተሰብ መብቱን ለማስከበር ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄድ አለበት›› በሚል ደመደሙ።
ማኅበራቱ በጥምረት ሰኞ ኅዳር 19/1987 ሰልፍ ለማድረግ ከክልል 14 መሥተዳድር ‹‹ከአሥር ሺህ ያላነሰ ሰው የሚሳተፍበት›› የሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድ አወጡ። አዘጋጆቹ በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ለሚገኙ መስጊዶች እና የሙስሊም እድሮች የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ በማቅረብም ሕዝቡን አዘጋጁት። በሰላማዊ ሰልፉ ዕለት በመርካቶ እና ዙሪያዋ የሚገኙ ሱቆች ለወትሮው ከሚከፈቱበት ሰዓት ዘግይተው እንደነበር የሚገልጸው ሁኔታውን በወቅቱ የተመለከተው የ‹‹ቢላል›› መጽሔት አዘጋጅ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ሰልፉ ወደሚጀመርበት የማዘጋጃ ቤት ሜዳ ይተም እንደነበር ያስታውሳል።
በወቅቱ በማዘጋጃ ቤት ሕንፃ ላይ ይገኝ የነበረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከሕንፃው አናት ላይ ሆኖ ያነሳው ተንቀሳቃሽ ምስል ከፒያሳ አራዳ ገበያ እስከ ለገሐር የተዘረጋው ጎዳና በሰልፈኞች ተሞልቶ እንደነበር አሳይቷል። ‹‹የሕዝቡ ቁጥር ከፍተኛ መሆን የጥያቄውን ሕጋዊነት ያሳያል›› የሚሉት ሐጂ ምቾት የሕዝቡ ቁጥር ከፍተኛነት መንግሥትን ብቻ ሳይሆን የሰልፉን አዘጋጆች ጭምር ያስደነገጠ እንደነበር ሳይጠቅሱ አያልፉም።
የሰልፈኛው ሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ መሆን የሰልፈኞች ተወካዮች ከጠቅላይ ሚኒስተር ታምራት ላይኔ ይልቅ ፕሬዚደንቱ አቶ መለስ ዜናዊ ተቀብለው እንዲያናግሯቸው ምክንያት መሆን እንደቻለ ብዙዎች ያምናሉ። ሰልፈኞቹ በተወካዮቻቸው አማካኝነት 11 ጥያቄዎቻቸውን ለፕሬዚደንት መለስ ዜናዊ አቅርበው የነበረ ሲሆን ዋነኛ አንኳር ጥያቄ አድርገው ያነሱትም የጠቅላይ ጉባዔውን በአንድ ግለሰብ መዳፍ ውስጥ መውደቅ ነበር። ፕሬዚደንቱ በምላሻቸው የጠቅላይ ጉባዔውን አመራሮች ‹‹እናንተው እንደሾማችሁ እናንተው ልታወርዷቸው ትችላላችሁ›› በማለት አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተው እንደሸኟቸው ኅዳር 20/1987 ታትሞ የወጣው ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ አስነብቦ ነበር። በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ እና ግርግር ተደጋግሞ ይነሳ የነበረው የሐጂ ሙሐመድ አወል ረጃ ስም ነበር። የማኅበራቱ ተወካዮችም ‹‹ጠቅላይ ጉባዔውን በመዳፋቸው ሥር አስቀምጠውት አምባገነናዊነትን አስፍነዋል›› እያሉ ሲከሷቸው ተሰምቷል።
ከ 1950ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በሸቀጣ ሸቀጦች ንግድ የተሠማሩትና በ 1961 ለንጉሡ ፓርላማ የትግራይን አውራጃ ወክለው የተወዳደሩት፣ የኋላ ኋላም በአስመጪና ላኪነት ንግድ ተሠማርተው የነበሩት ሐጂ ሙሐመድ አወል ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ጉባዔ እና ከ 1987 የአንዋር መስጊድ ግርግር ጋር ተያይዞ ሥማቸው ተደጋግሞ ይነሳል። የዛሬው የ 62 ዓመት ጎልማሳ ኢስላማዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳትፎ ማድረግ የጀመሩት ከትውልድ ቀዬአቸው ትግራይ ክልል ነበር። በትግራይ ክልል በተለያዩ የግብረ ሰናይ ሥራዎች ተሳትፎ ሲያደርጉ ቆይተው በ 1970ዎቹ መጨረሻ ከሰባት ከማይበልጡ ሰዎች ጋር የኢትዮጰያ ቅዱስ ቁርኣን ማኅበርን መመሥረታቸውን ኅዳር 1985 ለታተመው ‹‹ቢላል›› መጽሔት ገልጸዋል።
ከ 1980 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ጉባዔ በተራ አባልነት ማገልገላቸውንም ጨምረው ያስረዳሉ። ሐጂ ሙሐመድ አወል ድርጅታቸው ቅዱስ ቁርኣን ማኅበር ከ 1982 አንስቶ ሲያደርጋቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎች ዘርፈ ብዙ እና አመርቂ እንደነበሩ ያስታውሳሉ። በወቅቱ በመላዋ አገሪቱ 157 መድረሳዎችና 40‚000 (ዐርባ ሺህ) የቁርኣን ተማሪዎችን ያስተምሩ እንደነበር የሚገልጹት ሐጂ ሙሐመድ አወል ይህ እንቅስቃሴያቸው መንግሥትንና ቤተ-ክህነትን ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ከትቷቸው እንደነበር ያሰምሩበታል። ‹‹ይህን ሥጋታቸውን ለመቅረፍ እኔን ከኃላፊነት ቦታዬ የማውረድ ዕቅድ ነበራቸው›› ይላሉ ሐጂ ሙሐመድ በማኅበራቱ የተደረገውን ተቃውሞ ሰልፍ አስመልክቶ ምላሽ ሲሰጡ።
ሌሎች ወገኖች የኅዳር አሥራ ዘጠኙ ተቃውሞ ሰልፍ የጥቂት ማኅበራት ሳይሆን የሕዝብ የመብት ጥያቄን የታከከ ስለመሆኑ ቢከራከሩም ሐጂ ሙሐመድ ግን ከእንቅስቃሴው ጀርባ የቅዱስ ቁርኣን ማኅበርን ሰፋፊ ሥራዎች ለማስቆም የታለመ ሤራ እንደነበር ያስረዳሉ። ‹‹በኅዳር አሥራ ዘጠኝ የተቃውሞ ሰልፍ የማኅበሩ አመራሮች እኔን ማስወገድ ይችሉ የነበረ ቢሆንም በሰሩት ስህተት ምክንያት ያሰቡት ሳይሳካላቸው ቀርቷል›› የሚሉት ሐጂ ሙሐመድ ተወካዮቹ ካቀረቧቸው አሥራ አንድ ጥያቄዎች ውስጥ ሦስቱ ብቻ እርሳቸውን የሚመለከቱና ቀሪዎቹ ግን ስሜት የተንጸባረቀባቸው፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ሊተገበሩ የማይችሉ የነበሩ መሆናቸውን ያነሳሉ። ‹‹እስቲ አሁን ‹ሙስሊም ሚኒስትሮች ይሾሙልን› ብሎ መጠየቅ ምን ይባላል?›› ይላሉ።
ከተቃውሞ ሰልፉ በኋላ የማኅበራቱ ጥምረት ከመንግሥት ባገኘው አዎንታዊ ምላሽ በመነሳት ሐጂ ሙሐመድ አወል ረጃን ከሥልጣን የማውረድ እንቅስቃሴ ጀመረ። ጠቅላይ ጉባዔው የሙስሊሙ ሕዝብ የጋራ ተቋም እንደመሆኑና ጉዳዩም የወቅፍ ጉዳዮችን በሚያየው የሸሪዓ ፍ/ቤት ሥልጣን (jurisdiction) ሥር በመሆኑ የኢስላማዊ ድርጅቶቹ ጥምር ኮሚቴ ጉዳዩን ለሸሪዓ ፍ/ቤት አቀረበው። ግራዝማች ሐዲስ ኑርሑሴን ባዘጋጁት ረቂቅ መጽሐፍ አባሪ ተደርጎ የቀረበው የሸሪዓ ፍ/ቤት ውሳኔ ሐጂ ሙሐመድ አወል በማኅበራቱ አማካኝነት በሸሪዓ ፍ/ቤት ለቀረበባቸው ክስ ችሎት ቀርበው ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ እንደቀሩ ተገልጿል።
የሸሪዓ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ተከሳሹ በሌሉበት ተመልክቶ በሰኔ 2/1986 ሐጂ ሙሐመድ አወል ከሥልጣናቸው እንዲነሱ እና ከሳሾቹ ድርጅቶችም አዲስ ጠቅላይ ጉባዔ እንዲያደራጁ ውሳኔ አስተላለፈ። ይህ ውሳኔ ከዐራተኛ ፖሊስ ጣቢያ ፖሊሶች በተገኙበት የጠቅላይ ጉባዔው በር ተሰብሮ በአዲስ ቁልፎች ተቀይሮ ተፈጻሚ ሆነ። ሐጂ ሙሐመድ አወል ግን የቢሮ ሰበራው የፍ/ቤት ትዕዛዝ አካል እንዳልነበር ይገልጻሉ። ያም ሆኖ ግን ሁኔታው ሐጂ ሙሐመድ አወልን ወደ መደበኛ ፍ/ቤት ከመሄድና ይግባኝ ከመጠየቅ አልገታቸውም። የሐጂ ሙሐመድ አወል ይግባኝ በመደበኛ ፍ/ቤት መታየት መጀመሩ እና ‹‹የሸሪዓ ፍ/ቤትን ሥልጣንና ተግባር የሚያቃልል ነው›› መባሉ ደግም በተራው ትልቅ የውዝግብ ምንጭ ሆነ። በተለይም የሸሪዓ ፍ/ቤት ውሳኔ አስገዳጅ ሆኖ አለመገኘት ትልቅ ነውጥ ፈጥሮ እንደ ነበር ሸኽ ሙሐመድ ዘይን ያስረዳሉ።
በዕለቱም እንዲህ ሆነ!
በመደበኛ ፍ/ቤት መታየት የጀመረው የሐጂ ሙሐመድ አወል ይግባኝ የሸሪዓ ፍ/ቤቱን ውሳኔ ውድቅ ባደረገ መልኩ የራሱን ውሳኔ ማሳለፉ ብዙዎችን ያስደነገጠ ነበር። በፍ/ቤቱ ውሳኔ ዐራተኛ ገጽ ላይ ‹‹የናኢባና የቃዲ ጉባዔ ቤቶች የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን የጋብቻ፣ የቀለብ መቁረጥ፣ የሕፃናት አሥተዳደርን፣ ስለ ወቅፍ ስጦታ፣ ስለ አወራረስ ጉዳይ እንዲያዩ በአዋጅ ሥልጣን ተሰጣቸው እንጂ የገንዘብ መቀጫና የእሥራት ቅጣት እንዲወስኑ በአዋጅ በግልጽ ሥልጣን አልተሰጣቸውም። እንደ መደበኛ ፍ/ቤቶች የገንዘብ መቀጫና ነጻነትን የሚያሳጣ የእሥራት ቅጣት አይወስኑም›› የሚል ዐረፍተ ነገር ሠፍሮ ነበር። በመሆኑም የዚህ ውሳኔ ጭብጥ በተሰማባቸው የፒያሳው ኑር መስጊድና በታላቁ አንዋር መስጊድ ውስጥ መጠነኛ ግርግር እና ጉርምርምታዎች ተፈጠሩ።
የእስልምና ጉዳዮችን እንደ አዲስ ለማዋቀር እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረው የአምስቱ ማኅበራት ጥምረት በበኩሉ አዳዲስ ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማዋቀር የጀመረውን ሂደት ሲያጧጡፍ ሐጂ ሙሐመድ አወልም የራሳቸውን ጥረት በሌላ አቅጣጫ ያደርጉ ነበር። ሐጂ ሙሐመድ አወልን ከእነዚሁ ማኅበራት ተወካዮች ጋር የአዲስ አበባ የሥራ ኃላፊዎች ማደራደራቸውን ቢቀጥሉም ሁኔዎች ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሱና በሁለቱ ቡድኖች መካከል የሚደረገው የቃላት ጦርነትና ፍትጊያ እየተካረረ ቀጠለ። የመሥተዳድሩ ባለሥልጣናትም ለሁለቱም ቡድኖች ድጋፍ በመስጠት ሁኔታውን የከፋ እያደረጉት ስለመሆኑ በብዙዎች ታመነበት። ግራዝማች ሐዲስ በረቂቅ መጽሐፋቸው የመሥተዳድሩ ባለሥልጣናት አቶ ሐሰን ሺፋ እና አቶ ዐሊ ዐብዶ ለሐጂ ሙሐመድ አወል ረጃ ቡድን ይወግኑ እንደነበር ጽፈዋል።
የወቅቱን ሁኔታ በአንክሮ ይከተታሉ እንደነበር የሚገልጹትና ከአል-አዝሐር ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ለ 30 ዓመታት ያህል በአወሊያ ት/ቤት ያስተማሩት ሐጂ ዐብደላህ ኢድሪስ ‹‹መንግሥት የሁለቱን አንጃዎች ግጭት ይፈልገው ስለነበር ሁለቱንም አንጃዎች ያግዝ ነበር›› ይላሉ። የቀድሞ የ‹‹ቢላል›› መጽሔት አዘጋጅ በበኩሉ ‹‹የመንግሥት አስፈጻሚ አካል ሥልታዊ ዝምታን መርጦ ከቆየ በኋላ የሥልታዊ ዝምታው ምንነት እና ዓላማ በየካቲት 14/1987 ተገለጠ›› ይላል።
የካቲት 14 የዝሑር ሶላትን ለመስገድ አንዋር መስጊድ የገቡት የሐጂ ሙሐመድ አወል ቡድን አባል እና ወዳጅ ሐጂ ሰዓዱ ጀማል ከጥቂት ምእመናን ጋር በፈጠሩት እሰጥ አገባ እና ‹‹ራሳቸውን ለመከላከል›› ወደ ሰማይ በተኮሱት ጥይት ምክንያት በአካባቢው ከፍተኛ ግርግር ተፈጠረ። ሁኔታውን ለማረጋጋት በአካባቢው የደረሱትን ፌዴራል ፖሊሶች (ፈጥኖ ደራሾች) ተኩስ በመቃወም ምእመኑ ወደ ፖሊሶች ድንጋይ መወርወር ጀመረ። ግጭቱም በፖሊሶችና በመስጊዱ እና አካባቢው በሚገኙ ሙስሊሞች መካከል ሆነ።
ታዛዦቹ የፈጥኖ ደራሽ ፖሊሶች በዘመነ ደርግ እንኳ ተፈጽሞ የማያውቅ አስደንጋጭ ነገር ፈጸሙ። ድንጋይ በሚወረውሩባቸው ምእመናን ላይ እየተኮሱ ከነጫማቸው ታላቁ አንዋር መስጊድ ውስጥ ገቡ። የወቅቱ ኢማም ሐጂ ዙልመካን በማይክራፎን ‹‹ፖሊሶች! አላህን ፍሩ! አትተኩሱብን!›› ሲሉ ይሰሙ ነበር። የተከበረው አንዋር መስጊድ የጦርነት አውድማ መሰለ። ሁከት እና ብጥብጡ ከግቢው ውጪም እየሰፋ ሄደ፡፡ በፖሊሶች ድርጊት የተቆጣው የአካባቢው ሕዝብ እና የጎዳና ተዳዳሪዎችም ጭምር ፖሊሶቹን እና መኪናዎቻቸውንም ጭምር ዒላማ አድርገው ጥቃት ሰነዘሩ። የፖሊስ መኪናዎችና ሞተር ሳይክሎች ተቃጠሉ።
በመጨረሻም ከሁሉም የከፋውን የአሥር ሰዎች ሕልፈት አስከተለ – አሥሩ ምእመናን ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ነበር ሕይወታቸውን ያጡት። ግርግሩ ከቀኑ 7 ሰዓት አንስቶ እስከ 10 ሰዓት ድረስ ቀጥሎ ነበር።
በዚያው ዕለት ምሽት የኢትዮጵያ ሬዲዮ በ 2፡00 ሰዓቱ የዜና እወጃ ‹‹በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ጉባዔ ውስጥ በተፈጠረ የሥልጣን ሽኩቻ ሳቢያ በተቀሰቀሰ ሁከት ለጊዜው ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ሲሞቱ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን ኢ.ዜ.አ ዘገበ›› የሚል አስገራሚ ዜና አስደመጠ። በዚያው ዕለት ምሽት ከዜና እውጃ በኋላ የወቅቱ የአዲስ አበባ መሥተዳድር ፕሬዚደንት የነበሩት አቶ ተፈራ ዋልዋ መግለጫ ሰጡ። መስጊዶችም ለሦስት ቀናት እንደሚዘጉ ተነገረ። ከግርግሩ ጀርባ ‹‹አሉ›› የተባሉ የጊዜያዊ አደራጅ ኮሚቴ አባላትና አመራሮች፣ እንዲሁም ሐጂ ሙሐመድ አወልና አጋሮቻቸው በሙሉ በዚያው ምሽት በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደረገ። ግራዝማች ሐዲስ በመጽሐፋቸው ሐጂ ሲራጅ ሙሣ የተባሉ የጊዜያዊ አደራጅ ኮሚቴ አባል መገደላቸውን ጽፈዋል። ግለሰቡ ‹‹ሊያመልጡ ሲሞክሩ ፖሊስ ገደላቸው›› ቢባልም ማምለጥ የማይችሉና ያለመነጽር ማየት እንኳ የማይችሉ አረጋዊ እንደነበሩ ይታመናል።
የግርግሩ ንዝረት
ከየካቲት 14 የአንዋር መስጊድ ግርግር ሰዓታት በኋላ በተለይም ምሽቱን ታክኮ የተያዙት ሰዎች ቁጥር በጣም ከፍተኛ ነበር። እነዚህ ከ 45 በላይ ግለሰቦች በጠቅላይ ጉባዔው፣ በጊዜያዊ አደራጅ ኮሚቴው፣ በኢ.ሙ.ወ.ድ እና በሌሎች ሙስሊም ማኅበራት ውስጥ የታቀፉና ብዙዎቹም በመሪነት ቦታ ላይ የተቀመጡ ነበሩ። ‹‹የእነዚህ ግለሰቦች መታሰር በሙስሊሙ ኅብረተሰብ ሁለንተናዊ መስተጋብር ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተጽእኖ ሳይታለም የተፈታ ነበር›› ይላሉ የሙስሊሞች ጉዳይ ያነጋገረቻቸው ምሁር።
የቀድሞው የ‹‹ቢላል›› አዘጋጅ በበኩሉ ከየካቲት 14 ግርግር በኋላ መንግሥት ሲወስዳቸው የቆዩ ወሰን አልባ እርምጃዎች በግርግሩ ዕለት ምሽት የኢትዮጵያ ሬድዮ ባወራው ዜና የተቃኙ ነበሩ። እንደ ጋዜጠኛው በኅዳር 19 የተቃውሞ ሰልፍ ወደ 300 ሺህ የሚጠጋን የአዲስ አበባ ሙስሊም ሕዝብ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ድረስ አግተልትለው የወሰዱትን የሰልፉን አደራጆች መያዝ የመንግሥት መነሻ ተግባር ነበር።
የመንግሥት እርምጃ ስፋትና ትልቀት ግን ከዚህም በላይ ሆኖ ታይቷል። የአንዋር መስጊድ ግርግር በየካቲት 14 ተከስቶ በየካቲት 15 የእነቢላል ማኅበር የሙነዘማ ጽ/ቤት ታሸገ። የድርጅቱ አባላትም በወቅቱ ክስ የተመሠረተባቸው ‹‹በአገሪቱ እስልምናን በኃይል ለማስፋፋት በመጣርና ወጣቶችን የሽብር ተግባር እንዲፈጽሙ በማሠልጠን›› ተብሎ ቢሆንም ታሳሪዎቹ የሙነዘማ አባላት ከሦስት ዓመት እስር በኋላ በጥቅምት 1990 በነጻ ተሰናብተዋል። በዚህ ቀን ታስረው ክስ ከተመሠረተባቸው ሠላሳ አምስት ግለሰቦች መካከል ሃያ ሰባቱ በነጻ ተለቅቀዋል።
የሙነዘማ አባላት ከእስር በነጻ ቢለቀቁም ድርጅታቸው ግን ሥራውን እንዳይቀጥል ተደረገ። ሙነዘማ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ በታወጀው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተስፋ ጥለው በከፍተኛ ሞራል እና ትኩስ የሥራ ስሜት ኢስላማዊ እንቅስቃሴዎችን የተቀላቀሉ ተቋማት እና ማኅበራት ‹‹ይብቃችሁ›› ተባሉ። ቢላል ‹‹ከዚያች ቀን በኋላ ሥማቸውን ያልሰማኋቸው በርካታ ድርጅቶች አሉ›› ይላል ሐዘን ባጠላበት መልኩ። ከእስር የተረፉት ግለሰቦች ጥቂቶች እግራቸው ወደመራቸው መሰደድን መረጡ። ለሥራ ጉዳይ ከአገር ውጪ እንደነበሩት የሙነዘማ ሊቀመንበር ሸኽ ሰይድ አሕመድ ሙስጠፋ ያሉት ደግሞ እስራቱን በመሥጋት አለመመለስን መረጡ። አገር ቤት ያሉ ዑለማዎችና ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች ተሸማቀቁ። የዲን እንቅስቃሴዎችም ገጽታቸው እየደበዘዘ መታየት ጀመረ። እነ ሐጂ ሙሐመድ ወሌ የጀመሯቸው የቂራኣት ሐለቃዎች ተበተኑ። እነ ሙሐመድ አወል ረጃ የከፈቷቸው መድረሳዎችም ተዘጉ።
ቢላል ሐጂ ሙሐመድ አወል ረጃ ይሠሯቸው የነበሩ በርካታ ሥራዎችን በማስታወስ ‹‹ሙሐመድ አወል ረጃ ከታሰረ በኋላ አንድም ቁርኣን ቤት አልተከፈተም›› በማለት በድፍረት ይናገራል። ሐጂ ሙሐመድ አወል ረጃም ወቅቱ የፈጠራቸውን ችግሮች በመዘርዘር በብዙ መልኩ ወደኋላ እንደመለሳቸው ይገልጹና ከ 1987 በፊት 157 የቁርኣን መድረሳዎችና 40‚000 (ዐርባ ሺህ) የቁርኣን ተማሪዎች እንደነበሯቸው በማስታወስ አሁን ግን በቁጥር 13 የሚሆኑ መድረሳዎች ብቻ እንዳሏቸው ሐዘን በተቀላቀለበት ስሜት ሐሳባቸውን ይሰነዝራሉ። ሁሉም በየፊናው ይሠራቸው የነበሩ ተግባሮች ተቆርጦ የወደቀ ዛፍ ሆኑ።
ከግርግሩ በኋላ የመንግሥት ዐይኖች አሁንም ድረስ በሙስሊም ድርጅቶች እና ግለሰቦች ላይ ተተክለው መቅረታቸውን የሚጠቁሙ በርካታ ድምጾች ይሰማሉ። የግርግሩ ውሽንፍር የነካቸው ሙስሊም ተቋማት እስከ መጨረሻው እንቅስቃሴያቸው ተገትቷል። የሙስሊሞች ጉዳይ ያነጋገረቻቸውን ምሁር ‹‹የየካቲት አሥራ ዐራቱ የ 1987 ግርግር እና መንግሥት እሱን ተከትሎ የወሰዳቸው እርምጃዎች 7 ዓመት ነዝሮናል›› እንዲሉ ያስቻላቸውም ይህን ከግምት ማስገባታቸው ይመስላል።
ቢላል የቀድሞ ድርጅቱን ኢ.ሙ.ወ.ድ.ን (ሙነዘማን) አስመልክቶ እንደሚያስረዳው በየካቲት አሥራ ዐራቱ ግርግር ድርጅታቸው ምንም ዓይነት ሚና ያልነበረውና ጊዜያዊ አደራጅ ኮሚቴው ጠቅላይ ጉባዔው እንዲፈርስ በወሰነበት የውሳኔ ወረቀት ላይ የኢ.ሙ.ወ.ድ የመስማሚያ ማኅተም እንዳላረፈ ያስታውስና ድርጅቱ እና አባላቱ ግን በተቃራኒው በሽብር ተግባር ተከስሰው ሥራቸውን እንዲያቆሙ መደረጉን ይጠቁማል። የሙነዘማ አባላት ግን ከምንም በላይ በስንት ልፋት ያቋቋሙት ድርጅታቸው ያለጥፋቱ መዘጋቱና ያለወንጀል ለዓመታት መታሰራቸው ዛሬም ከአሥራ አምስት ዓመታት በኋላ እንደከነከናቸው ነው። በሐሳባቸው የዳዕዋ መድረካቸውን ያስነጠቃቸውን የየካቲት 14/1987 ግርግር መጥፎ አጋጣሚ ይረግማሉ።
ታዛቢዎች ይህን ከግምት በመክተት መንግሥት ከግርግሩ ዕለት ጀምሮ የወሰዳቸው እርምጃዎች አስቀድሞ የታሰበባቸው እንደሆኑ ይናገራሉ። ‹‹የሁለቱ አንጃዎች ጥፋት ለመንግሥት በር ከፍቷል›› የሚለው ደግሞ የቀድሞው የሙነዘማ አባል ወጣት ነው። እንደዚህ አስተያየት ሰጪ አባባል በሁለቱም አንጃዎች በኩል የተሰለፉ ግለሰቦች በወቅቱ ግባቸውን ማሳካት ባይችሉም የመንግሥትን የልብ መሻት ግን መሙላት ችለዋል።
መስታወቱ ላይ የቆመ ኡምማ!
የሙስሊሞች ጉዳይ ያነጋገረቻቸው ምሁራን በኅዳር 1987 የመንግሥት የልብ መሻት እውን ከሆነባቸው አንኳር ጉዳዮች አንዱ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ጉባዔ ጠለፋ እንደሆነ ያምናሉ። የየካቲት አሥራ ዐራቱን ግርግር ተከትሎ መንግሥት የወሰዳቸው እርምጃዎች አንዱን ወገን ብቻ ሳይሆን በጠቅላይ ጉባዔው (በመጅሊሱ) በኩል የነበሩ አካላትንም ያስደነገጡ እንደነበር ይታመናል።
ይህም መጅሊሱን ሰው አልባ ተቋም አድርጎት ታይቷል። በወቅቱ ተቋሙ መሪ ማጣቱ ‹‹ያሳሰበው›› መንግሥት ግለሰቦችን በመጋበዝ ተቋሙን ዳግም እንዳቋቋመ የሚገልጹት ሸኽ ሙሐመድ ዘይን ዘህረዲን በአዲሱ አደረጃጀት ዑለማዎች እንዳይካተቱ መደረጉ በብዙ መልኩ የዑለማዎችን ሞራል እና ክብር እንደነካ ያስረዳሉ። የሙስሊሞች ጉዳይ መጽሔት በቁጥር አሥር እትሟ ከ 1987 በኋላ የመጅሊሱ ሕልውና ከዑለሞች ብቻ ሳይሆን ከሙስሊሞችም እጅ ተፈልቅቆ ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያነት መዋል እንደጀመረ ገልጻ ነበር። ምሁራኑ ለዚህ ሐሳባቸው ማጠናቀሪያነት ከተጠቀሰው ወቅት ጀምሮ በ 1992 ከተደረገው የይስሙላ ምርጫ ውጪ ምንም ዓይነት ምርጫ አለመደረጉንና ሕዝቡ የሚያምንባቸው መሪዎች አለመቀመጣቸውን በምክንያትነት ይጠቅሳሉ።
ሸኽ ሙሐመድ ዘይን ‹‹ተቋሙ ከ 1987 ወዲህ መንግሥትን መምሰል የጀመረው ከሥያሜው ነው›› በማለት ‹‹‹የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ጉባዔ› የሚለውን ‹የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት› ወደሚል በመለወጥ›› የሥያሜ ሽግግሩ ከሥርዓቱ ሸንጎዎች ጋር ያለውን ምስስሎሽ እንደጀመረ ያሳያሉ። ሕዝበ ሙስሊሙን የማገልገል ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦችም ወደ ተቋሙ እንዳይቀርቡ በጠቅላይ ም/ቤቱ እና በክልል እስልምና ጉዳይ ቢሮዎች ‹‹ወሐቢያ ብለው የሠየሙት ቡድን አባላት እንዳይካተቱ›› መደረጋቸውን ሸኽ ሙሐመድ ዘይን ያስረዳሉ። ሌላው አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው ‹‹እኛ አገር አንገቱን ቀና ያደረገ ሁሉ ‹ወሐቢያ› የሚል ሥያሜ ተሰጥቶት ወደ መጅሊስ ድርሽ እንዳይል ተደርጓል›› ይላሉ። ምሁራን ከዚህ በኋላ በተቋሙ ተሹመው የሚመጡ ግለሰቦች መንፈሳዊም ሆነ አካዳሚያዊ እውቀት የሌላቸው የፖለቲካ ቅጥረኞች መሆን መጀመራቸውን በልበ ሙሉነት ይናገራሉ።
ሸኽ ዐብደላህ ኢድሪስ ከ 1987 በኋላ ነጻ የዑለማዎች ማኅበር ለማቋቋም ከዕድሜ እና እውቀት አጋሮቻቸው ጋር ያደረጉት ጥረት እንኳ እንዳልተሳካ በመጥቀስ በ 2000 ዓ.ል የዑለማዎች የምክክር መድረክ የፈረሰበትን አሳዛኝ አጋጣሚ ያስታውሳሉ። በ 1987 ግጭት የሸሪዓ ፍ/ቤት አቅም እና ሥልጣን ዋነኛ አጀንዳ እንደነበር የሚያስታውሱት ደግሞ ሸኽ ምቾት አሕመድ ናቸው።
ሸኽ ምቾት ‹‹የሸሪዓ ፍ/ቤት ሥልጣንና ኃላፊነት ለመጅሊሱ መሰጠት የለበትም›› የሚለው ሙግት ሙሉ በሙሉ እንዳከተመለት በመግለጽ ዛሬ መጅሊሱ የሸሪዓ ፍ/ቤት ውስጥ ያለውን ሚና፣ በተለይም በአዋጁ የተሰጠውን ዳኞችን የመጠቆም ሥልጣን ያወሳሉ። የቀድሞ የሸሪዓ ፍ/ቤት ቃዲ የነበሩ ሌላ ግለሰብ ግን መጅሊሱ የሸሪዓ ፍ/ቤት ውስጥ ያለው ሥልጣን ዳኞችን በመጠቆም ብቻ ያልተገደበ እንደሆነና የፍ/ቤቱን ውሳኔዎች የማጽደቅም ጭምር የጓሮ ሥልጣን እንደተሰጠው ይናገራሉ። ሌሎችም ወገኖች የዚህን ሐሳብ እውነትነት ያጸድቃሉ። ታዛቢዎች ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ የሚሆንባቸው በየጊዜው በሚታደስ የኤን.ጂ.ኦ ሰርቲፊኬት የሚንቀሳቀሰው መጅሊስ በአዋጅ በተቋቋመው የሸሪዓ ፍ/ቤት ውስጥ የውሳኔ ሰጪነት ሚና ማግኘቱ ነው።
1987 የፈጠረው ቀውስ እና ጠባሳ ገና የሻረ አይመስልም። ቁስሉን የሚያመረቅዙ ክስተቶች ግን በየአቅጣጫው ብቅ ብቅ እያሉ ነው። ለዚህም ነው የሙስሊሞች ጉዳይ ያነጋገረቻቸው ምሁራን ‹‹የ 1987 ዓይነት ግርግር ዛሬም ላለመከሰቱ ዋስትና የለንም›› የሚሉት። ‹‹በሰኔ 2003 የተጀመረው ‹‹አሕባሽ››ን የማስፋፋት ፕሮጀክት ፍጻሜው የ 1987ን ክስተት ዳግም ለመመለስ የታለመ ነው›› የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ምሁሩ ‹‹በደፈናው ያንን ማለት ባይቻልም ምልክቶችን እያየን ነው›› ይላሉ። ሌሎች በበኩላቸው ከ 2003 መባቻ ጀምሮ የነበሩ ወቅቶች ከድኅረ 1987 ጋር በጉልህ መልኩ እንደሚመሳሰሉ ምሳሌ በመጥቀስ ያስረዳሉ። መጅሊስ ለ 1987 ግርግር መነሻ የሆነው ‹‹ከእኔ ውጪ ሌላ ኢስላማዊ ድርጅት መኖር የለበትም›› የሚለው አቋሙ ምንም መሻሻል ሳይታይበት ዛሬ ላይ ተደርሷል። በ 1987 ሙነዘማ በአሸባሪነት ተፈርጆ እንዲዘጋና አባላቱ ወህኒ እንዲወርዱ እንደተደረገው አሁንም በተመሳሳይ መልኩ የመጅሊስን መሪነት የማይቀበሉ ድርጅቶች እና ወገኖች በአሸባሪነትና በጸረ-ሰላም ኃይልነት መፈረጅ ጀምረዋል።
መጅሊሱ እንዲፈርሱ የሚሻቸው ድርጅቶች የሕጋዊ-ሰውነት ደረጃ ከመጅሊሱ ጋር ተቀራራቢ ብቻ ሳይሆን ተመሳሳይ ቢሆንም በመጅሊሱ ‹‹ቀጭን ትዕዛዝ›› ከመፍረስ አልዳኑም። የድኅረ 1987 እርምጃዎች ዐቢይ መገለጫ የነበረው የኢስላማዊ ተቋማት ፈቃድ ሥረዛ መሆኑን እነዚሁ ወገኖች በማስታወስ የድርጅቶች የሥራ ፈቃድ ነጠቃ ጥቂት በማይባሉ ኢስላማዊ ድርጅቶች ላይ መጀመሩን ይገልጻሉ።
ሥራ እንዲጀምር ፈቃድ ተሰጥቶት በወራት ውስጥ ፈቃዱን እንዲመልስ የተደረገው ‹‹የሙስሊሞች ሊግ›› አንድ ምሳሌ ተደርጎ የሚቀርብ ሲሆን በተለያዩ ክልሎችም ተመሳሳይ እርምጃዎች በመወሰድ ላይ ናቸው። ለእነዚሁ ድርጅቶች የሥራ ፈቃድ ነጠቃ እየቀረበ ያለው ምክንያት ከድኅረ 1987 በመሠረቱ የማይለይ ቢሆንም የመጅሊሱ ሚና ግን ከፍተኛ መሆኑን ታዛቢዎች ሳይገልጹ አያልፉም። እርምጃዎቹ ኢስላማዊ የፋይናንስ ተቋማትን፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን፣ እንዲሁም በጥናትና ምርምር ሥራ ላይ የተሠማሩ ማዕከላትን እንኳ የሚምሩ አይመስሉም። እነዚህ ተቋማት ለሚመለከታቸው አካላት ‹‹አቤት›› ቢሉም ሰሚ አላገኙም – ልክ እንደ 1987!
የአንቀሳቃሽ ግለሰቦች እስራት፣ የዳዒዎች ግዞት እና ስደት፣ ይህን ተከትሎም በፍርሃት መሸበብ እና የኢስላማዊ እንቅስቃሴዎች ወደ ኋላ መገታት ቀጣዮቹ ፈተናዎች እንደሆኑ መተንበይ እንደሚቻል ምሁራኑ ያስገነዝባሉ።
ጉዟችን ወደ 2005 ሳይሆን ወደ 1987 መሆኑን የሚጠቁሙ ቅስቶች በየአደባባዩ ተተክለዋል። ግን ሕዝብ ስንት ዓመት ወደ ኋላ ይጓዛል?
ይህ ሐተታ በጥር 2004 በየሙስሊሞች ጉዳይ መጽሔት ቅጽ 2 ቁጥር 16 ላይ ታትሞ ነበር፡፡