የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ኢሳትን እያዳመጠች ልጃቸው ኒዮሊበራሎችን እየተከተለች የቤታቸው ንትርክ ጦፏል::


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


[ክቡር ሚኒስትሩ እሑድ ቀን ከቤታቸው ሊወጡ ሲሉ ልጃቸው አገኘቻቸው]

Source – Reporter Amharic
–    ወዴት እየሄድክ ነው ዳዲ?
–    ዘመድ ልጠይቅ፡፡
–    ምን ዓይነት ልብስ ነው የለበስከው?
–    ያው ዊኬንድ ስለሆነ ቱታ ነዋ ያደረኩት፡፡
–    እኔ የጠየቅኩህ ቀለሙን ነው?
–    ቀለሙማ እንደምታይው አረንጓዴ ነው፡፡
–    እሱ ነዋ ችግሩ፡፡
–    ይኼ ቀለምማ ችግር የለውም፡፡
–    በጣም አለው እንጂ፡፡
–    አረንጓዴ ለምን እንደምለብስ ታውቂያለሽ?
–    ለምንድን ነው የምትለብሰው?
–    አገሪቷ እየለመለመችና እያደገች ስለሆነ እሱን ላመላክት ነዋ፡፡
–    እየለመለመች?
–    አዎና፡፡
–    ድርቅ ገብቷል እየተባለ ሲወራ አልነበር እንዴ?
–    እ…
–    ለማንኛውም ዛሬ የሚለበሰው አረንጓዴ ሳይሆን ቀይ ነው፡፡
–    ለምን ተብሎ?
–    ቫላንታይንስ ዴይ ነዋ፡፡
–    ምንድን ነው ደግሞ እሱ?
–    የፍቅረኛሞች ቀን፡፡
–    መንግሥት የሚያከብረው ቀን ነው?
–    ኧረ በመላ ዓለም የሚከበር ነው፡፡
–    የኒዮሊብራሎች በዓል ነው አትይኝም ታዲያ?
–    እኔ እሱን አላውቅም፡፡
–    ለመሆኑ ቀኑ ምንድን ነው?
–    ፍቅረኛሞች ፍቅራቸውን የሚገልጹበት ቀን ነው፡፡
–    ምን ማለት ነው?
–    በቃ አንዳቸው ለአንዳቸው ፍቅራቸውን በዚህ ቀን ይገልጻሉዋ፡፡
–    በሌሎቹ ቀኖች ጥላቻቸውን ነው የሚገልጹት ማለት ነው?
–    እንደ እሱ ማለቴ አይደለም ዳዲ፡፡
–    ለነገሩ ተይው በዚህ በተወደደ ፍቅር በዓመት አንዴ እንኳን ሰው መዋደዱ ቀላል አይደለም፡፡
–    ለማንኛውም ዳዲ ዛሬ አንተም ማሚን እራት መጋበዝ አለብህ፡፡
–    ቤት ምግብ የለም እንዴ?
–    ነገርኩህ እኮ ዛሬ የፍቅረኛሞች ቀን ነው አልኩህ፡፡
–    ለእኔና ለእናትሽ ሁሉም ቀን የፍቅረኛሞች ቀን ነው፡፡
–    ለማንኛውም እኔ የቤቱን ዕቃ ቀለም ልቀይረው ነው፡፡
–    የቱን ዕቃ?
–    መጋረጃውን፣ ሶፋውን፣ ብቻ ሁሉንም ነገር፡፡
–    ምን ዓይነት ቀለም ልታደርጊው?
–    ቀይ ነዋ፡፡
–    እንግዲህ እንደፈለግሽ፡፡
–    እኮ ዳዲ አንተም ቱታህን ቀይረዋ፡፡
–    ምን ላድርግ?
–    ቀይ ቱታ፡፡
–    ለነገሩ ከቀይ ቀለም ጋር ችግር የለብኝም፡፡
–    ስለዚህ ትቀይረዋለህ?
–    አንቺን ካስደሰተሽ እቀይረዋለሁ፡፡
–    ታንኪው ዳዲ፡፡
–    የማልቀይረው ሌላ ዓይነት ቀለም ቢሆን ነበር፡፡
–    ምን ዓይነት ቀለም?
–    ሰማያዊ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር ሆነው ቴሌቪዥን እየተመለከቱ ነው]
–    ለምንድን ነው አንተ ዜና ላይ የማትቀርበው?
–    ምን ሠራሁ ብዬ?
–    ምንም እየሠራህ አይደለም እንዴ?
–    የዕለት ተዕለት ሥራዬን ነዋ እየሠራሁ ያለሁት፡፡
–    እኮ እሱም ቢሆን ለምን በዜና አይቀርብም?
–    ዜና እኮ አዲስ ነገር መሆን አለበት፡፡
–    ከመቼ ጀምሮ?
–    ሁሌም ቢሆን እንደዚህ ነው፡፡
–    ዛሬ ስከታተል አልነበር እንዴ ዜና?
–    እና ምን አየሽ?
–    ይኸው የአንተ ጓደኛ የቴሌቪዥን ጣቢያውን ጐበኙ ተብሎ አይደል እንዴ ዜና የተሠራላቸው?
–    እ…
–    ለዛውም መክፈቻ ዜና ነው፡፡
–    ምን ችግር አለው ታዲያ?
–    ጣቢያው እኮ የሕዝብ ነው፡፡
–    ማን አይደለም አለ?
–    አትመጻደቁ እባካችሁ?
–    እንዴት ማለት?
–    ጣቢያው ከዚህ በፊት የደርግ ፕሮፓጋንዳ መንፊያ ነበር ትላላችሁ፡፡
–    እና አልነበረም?
–    አሁንስ ምንድን ነው?
–    የሕዝብ ድምፅ የሚሰማበት ጣቢያ ነዋ፡፡
–    ኧረ ሰው እንዳይሰማህ?
–    ቢሰማስ ምን ያመጣል?
–    ይኼ ነገራችሁ እኮ ነው ችግር እየፈጠረ ያለው፡፡
–    እንዴት?
–    ሰው እንደማትሰሙ አውቆ በግድ እንድትሰሙ ያደርጋችኋላ፡፡
–    ምን ለማለት ፈልገሽ ነው?
–    ያልኩት በደንብ ስለገባህ ማብራራት አያስፈልገኝም፡፡
–    ከፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር ገጥመሻል ማለት ነው?
–    በእናትህ እነዚህን ልማታዊ ቃላት ከመደርደር የሕዝቡን ድምፅ በሚገባ ብታዳምጡ መልካም ይመስለኛል፡፡
–    የሕዝቡን ድምፅ አታዳምጡም እያልሽኝ ነው?
–    ብታዳምጡማ ይኼ ሁሉ ባልተፈጠረ፡፡
–    የተቃዋሚዎቹን ጣቢያ ማዳመጥ ጀመርሽ እንዴ?
–    ሰውዬ እውነቱን ለምን ትሸሻለህ?
–    ለመሆኑ እውነቱ ምንድን ነው?
–    አሁን ጥሩ ጥያቄ አነሳህ፡፡
–    እኮ ንገሪኛ?
–    ሕዝቡን ካዳመጥክ እውነቱን ታገኛለህ፡፡
–    ሕዝቡንማ እያዳመጥነው ነው፡፡
–    እያላመጥነው ነው ያልከኝ?
–    የለም የለም፤ እያዳመጥነው ነው፡፡
–    ብታዳምጡትማ ይኼ ሁሉ ባልመጣ፡፡
–    ይኼ ሁላ ምን?
–    ብጥብጥ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ እንደገቡ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
–    አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    ምን ወሬ አለ?
–    ወሬ መቼ ይጠፋል ክቡር ሚኒስትር?
–    ለነገሩ የሚሠራ ሰው ነው ያጣነው፡፡
–    የሚሠራም አይጠፋም ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    ለማንኛውም ወሬውን ንገረኝ እስቲ?
–    ነጋዴዎች ደስተኞች አይደሉም፡፡
–    ደግሞ ለምን?
–    በዚህ በኤልሲ ጉዳይ ነዋ፡፡
–    ይኸው አንበሸበሽናቸው አይደል እንዴ?
–    አይ ብሔራዊ ባንክ አዲስ መመርያ አውጥቷል እኮ፡፡
–    የምን መመርያ?
–    በአንድ ጊዜ በተለያዩ ባንኮች ኤልሲ መክፈት አይቻልም የሚል መመርያ ወጥቷል፡፡
–    ለምን?
–    ፍትሐዊ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ክፍፍል እንዲኖር ነዋ፡፡
–    ፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል ሳይኖር ይኼ እንዴት ሊሆን ይችላል?
–    ጥሩ ነጥብ ነው ያነሱት፡፡
–    እና አሁን ባንዴ ከአንድ ባንክ የምንጠይቀውን የውጭ ምንዛሪ ይሰጡናል?
–    ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ይጠይቃሉ እንዴ?
–    ማለቴ ነጋዴዎች የሚጠይቁትን ይሰጧቸዋል?
–    እሱን የምናየው ጉዳይ ይሆናል፡፡
–    ለመሆኑ እኛን ለማጥፋት ነው እንዴ ቆርጠው የተነሱት?
–    እኛን ሲሉ አልገባኝም፡፡
–    ማለቴ ነጋዴዎችን ሊያጠፉ ማለቴ ነው፡፡
–    እንደዛ እንኳን አይመስለኝም፡፡
–    አለቀልን በለኛ፡፡
–    እርስዎ ነጋዴ ሆነዋል እንዴ?
–    ማለቴ አለቀላቸው ልልህ ፈልጌ ነው፡፡
–    አይ ራስዎትን እያስገቡ ሲያወሩ ግራ ገብቶኝ ነው፡፡
–    ያው ነጋዴዎች እኮ የእኛው አካል ናቸው ብዬ ነው፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ነጋዴ ጋ ደወሉ]
–    ከየት ተገኙ ክቡር ሚኒስትር?
–    ምንድን ነው የምሰማው እባክህ?
–    ምን ሰምተው ነው?
–    የኤልሲውን ጉዳይ፡፡
–    ቆየ እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    ታዲያ ምንድን ነው የምናደርገው?
–    መላ መቼ ይጠፋል ብለው ነው?
–    ምንድን ነው መላው?
–    በቃ 17 ኩባንያዎች መሥርቶ በየባንኩ ወረፋ ማስያዝ ነዋ፡፡
–    የምን ወረፋ?
–    የዶላር!
[ክቡር ሚኒስትሩ ወዲያው ሚስታቸው ጋ ደወሉ]
–    እስቲ የምታምኛቸው ስንት ዘመዶች አሉሽ?
–    ምን እያልከኝ ነው?
–    የጠየኩሽን ለምን አትመልሺም?
–    ምን ሊያደርጉልህ?
–    በስማቸው ድርጅት ለመክፈት፡፡
–    ሁለት እህቶች አሉኝ፡፡
–    ሌላስ?
–    አገር ቤት ደግሞ ሁለት የአክስቶቼ ልጆች አሉ፡፡
–    በቃ በአስቸኳይ ይምጡ፡፡
–    ለምን?
–    በስማቸው ድርጅት እንከፍታለን፡፡
–    ያለን ድርጅት አይበቃንም?
–    እነዚህኞቹን ድርጅቶች ለሠልፍ ነው የምንፈልጋቸው?
–    ለሠልፍ?
–    አዎን፡፡
–    ተጣላህ እንዴ ሰውዬ?
–    የምን ጥል ነው?
–    ሰላማዊ ሠልፍ ተከልክሏል ብዬ ነዋ፡፡
–    አልገባሽም እባክሽ፡፡
–    ለነገሩ ሰላማዊ ያልሆነው ሠልፍ የበዛው ሰላማዊው ስለከተለከለ ይመስለኛል፡፡
–    እስቲ ፖለቲካውን ትተሽ በአስቸኳይ በዘመዶችሽ ስም አራቱ ድርጅቶች ይከፈቱ፡፡
–    ምን ያደርጉልናል?
–    ወረፋ ይይዛሉ፡፡
–    የምን ወረፋ?
–    የዶላር ወረፋ!
[አንድ ዳያስፖራ ለክቡር ሚኒስትሩ ደወለላቸው]
–    ክቡር ሚኒስትር አንድ ሐሳብ ነበረኝ፡፡
–    የምን ሐሳብ?
–    አንድ ተቋም የመክፈት፡፡
–    የምን ተቋም?
–    የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም፡፡
–    በአገሪቷ ውስጥ ምንም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ችግር የለም፡፡
–    ክቡር ሚኒስትር የእርስዎን ድፍረት እኮ አንበሳ ራሱ የሚቀናበት ይመስለኛል፡፡
–    ምን እያልከኝ ነው?
–    አገሪቱ በሰብዓዊ መብት ችግር የተንበሸበሸች አይደለች እንዴ?
–    ምን ይላል ይኼ?
–    ብቻ ይተውት፡፡
–    ለማንኛውም ችግሩ ቢኖርም በውጭ ገንዘብ እዚህ ላይ መሥራት አይቻልም፡፡
–    እኔ እኮ የምልዎት ሌላ ነገር ነው፡፡
–    በቃ ጨርሻለሁ፡፡
–    ክቡር ሚኒስትር…
–    ጢጢጢ…
[ዳያስፖራው መልሶ ደወለ]
–    ክቡር ሚኒስትር…
–    አንተ ሰውዬ ለምን አተወኝም?
–    እኔ የምልዎት ሌላ ነው፡፡
–    ምንድን ነው የምትለኝ?
–    ማቋቋም የምፈልገው ተቋም ለውሾች የሰብዓዊ መብት የሚሟገት ነው፡፡
–    ለውሾች?
–    አዎን ለውሾች፤ ውሾች አሉን አይደል እንዴ?
–    ያውም ብዙ ውሾች ነዋ፡፡
–    ተቋሙ መጠለያ ለሌላቸው ውሾች፣ ጐዳና ለወጡ ውሾች፣ አሳዳጊ ለሌላቸው ውሾች መብት የሚሟገት ነው፡፡
–    ሥራ ፈተሃል ልበል?
–    ትልቅ ሥራ ይዤ ነው እንጂ የመጣሁት፡፡
–    እንዴት?
–    ክቡር ሚኒስትር ይኼ ጠቀም ያለ ዶላር የምናገኝበት ሥራ ነው፡፡
–    ዶላር?
–    አዎና ክቡር ሚኒስትር፣ ጠቀም ያለ ፈንድ እናገኝበታለን፡፡
–    በቃ የተቋሙ የበላይ ጠባቂ እሆናለዋ፡፡
–    ለዛ አይደል እንዴ አደዋወሌ?
–    ወይ ኒዮሊብራሎች እኛ ለሰው ዶላር አጥተናል እነሱ ለውሻ ይሰጣሉ?
–    ዶላር በሽበሽ ነው አልኩዎት እኮ፡፡
–    ዶላር ካለውማ እንኳን የውሻ መብት ተሟጋች የሌላም መክፈት ትችላለህ፡፡
–    የሌላ የምን?
–    የዝንብ!

http://www.ethiopianreporter.com/content/%E1%8A%AD%E1%89%A1%E1%88%AD-%E1%88%9A%E1%8A%92%E1%88%B5%E1%89%B5%E1%88%AD-9