እስቲ ኦሮሞነት የለብኝም የሚል እጁን ያውጣ – ግርማ ካሳ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


እስቲ ኦሮሞነት የለብኝም የሚል እጁን ያውጣ – ግርማ ካሳ

ኦሮሞነት ኢትዮጵያዊነት ነው። ጀነራል ጃጋማ ኬሎ እንዳሉት ኦሮሞ ግንድ ነው። ግምቴ የተሳሳተ ባይሆንም ከ80% በላይ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ ኦሮሞነት አለበት።፡በተለይም “አማራ” የሚባለውና “ኦሮሞ” የሚባለው የተደባለቀ ነው።በጎንደር ከአጼ ቴዎድሮስ በፊት ኦሮሞች ነበሩ የሚገዙት። በወሎ እነ ንጉስ ሚካኤል ኦሮሞዎች ነበሩ። እነ እቴገ ጣይቶ፣ እለ ሉላ ራስ ሞኮንን ጋዲሳ ፣ በቅርቡ ሃዉልታቸዉን ያስመረቅነው አባ መገርሳ ( አቡነ ጴጥሮስ) …እያልን ብዙ መጥቀስ እንችላለን። ኦሮሞ ከሌላው ጋር የተሳሰረ ነው። “አማራ” ከሚባለው ጋር ብቻ አይደለም። ኦሮሞው ከሶማሌ ጋር ተደባልቋል። ከጉራጌ ጋር ተደባልቋል። አሁን ለምሳሌ የሶዶ ጉራጌ ከጨቦ ኦሮሞ ጋር የተደባለቀ ነው። እንደዉም ብዙዎች ባርኔጣ እየቀየሩ አንዳንዴ ጉራጌ፣ አንዳንዴ ኦሮሞ የሚሆኑበት ሁኔት አለ በሶዶ ጉራጌዎችና በጨቦ ኦሮሞዎች አካባቢ።፡

ኦሮሞነት የሚለካበት መንግድ የተለያየ ነው። የወላጆች “ዘር” የሚታይ ከሆነ፣ እኔ አንድ አያቴ ከቦረና(ኦሮሞ) ፣ ሁለተኛ አያቴ ከወለንጭቲ(ኦሮሞ) ነበሩ። ሶስተኛ አያቴ አባታቸው ከሸንኮራ(ሸዋ) የነበሩ ሲሆን፣ እናታቸው ደግሞ የጂማ ኦሮሞ ነበሩ። አራተኛው አይቴ ከጎጃም ናቸው። ያው እንደሚታወቀው ጎጃም አማርኛ ይናገር እንጂ ከኦሮሞ ጋር የተደባለቀ ነው።ወለጋ እንደማለት ነው። ስለዚህ እኔ እጄን አላነሳስም !!!! ቢያንስ 5/8ኛ ኦሮሞ ነኝና። ቢያንስ የሚለው ላይ አስምሩበት።

ኦሮሞነት በቋንቋ ከሆነ፣ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪ ስላልሆንኩ፣ ኦሮሞ አይደለሁም። እጄንም አላነሳም። አፋን ኦሮሞ አለመናገሬ ደግሞ ፈልጌ ያመጣሁት አይደለም።

ኦሮሞነት ኦሮሚያ በመወለድ ከሆነ ፣ የኦሮሚያ እምብርት ፊንፊኔ በመወለዴ ኦሮሞ ነኝ። ስለዚህ እጄን አነሳለሁ።፡ኦሮሞነት በፍላጎት ከሆነ ( Self identification ) ኦሮሞ አይደለሁም።እኔ ከብዙ ብሄረሰቦች የተደባለኩ ኢትዮጵያዊ ነኝ። ማንነቴ የሚገለጸው በአማራነት፣ ኦሮሞነት ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት ነው። አማራ አይደለሁም፣ ኦሮሞ አይደለሁም። አራት ነጥብ።

እንግዲህ ተመልከቱ ነገሮችን በዘር ማሰብ እንዴት ዉስብስብ እንደሆነ። ኢትዮጵያዉያን ኦሮሞ ይሁኑ ሌላ መሰረታዊ ጥያቄዎቻቸው የሚከተሉት ናቸው፡ ዳቦ፣ ሰላም፣ ልማት፣ የመብት መከበር ፣ የሕግ የበላይነት እና እኩልነት።

ታዲያ የሁሉም ጥያቄ ተመሳሳይ ሆኖ እያለ፣ ኦሮሞ ፣ ትግሬ መባባል እስከመቼ ሊያዘልቀን ይችላል ? ምን አለበት የሰው ልጅ በዘሩ ሳይሆን በስራው፣ በምግባሩ ቢመዘን ? ምን አለበት የዚህ ዘር፣ የዚያ ዘር ከምንባባል ያለንን በፍቅር ብንካፈል ?

በምኖርባት አሜሪካ ከቻይና፣ ከሕንድ፣ ከቬኑዝዌላ፣ ከፖላንድ፣ ከናይጄሪያ.. ከአላማች የተለያዩ ግዛቶች የመጡ ጎሮቤታሞች ሆነ በፍቅር ይኖራሉ። መሰልጠን ይሉታል ይሄ ነው። ታዲያ እኛ የአንድ አገር ልጆች ሆነን በዘር መከፋፈላችን የኋላ ቀርነታችንን አያሳይምን? በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ተማርን፣ ሰለጠን የምንል ነን ያስቸግርነው።

ባይገርማችሁ እዚህ አሜሪካ ተቀምጠን የዘር ፖለቲካ አቀንቃኝ የሆንን፣ በመስሪያ ቤቶቻችን ከሌሎች ጋር በሰላም ነው የምንኖረው። ሌሎች የውጭ አገር ዜጎችን እናቅፋለን፤ የአገራችንን ዜጎችን ግን እንደጠላት እናይለን። አይ ግብዝነት !!!!

ይህ ወገኖቼ ትልቅ በሽታ ነው። አገራችን ድሃ ናት።እንኳን ዘንቦብሽ ድሮም ጤዛ ነሽ እንደሚባለው፣ እንኳን ተከፋፍለን እና እርስ በርስ እየተበላላን፣ አንድ ሆነን ብንቆም እንኳን፣ ከፊታችን የሚጠብቀን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበረሰባዊ ፈተናዎች በጣም ከባባዶች ናቸው። ማሰብ አለብን። በዘር መከፋፈል ማቆም አለብን። ለኦሮሞው፣ ለትግሬው፣ ለጉራጌው ፣ለድብልቁ …የሚጠቅመውንአ የሚብጀው ፍቅር ነው። በፍቅር አገራችንን እንገንባ።