ኬንያ እንደመኖር ነው ? ? ? – ግርም ካሳ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ኬንያ እንደመኖር ነው ? ? ? – ግርም ካሳ

ጃዋር መሐመድ እኛ እንድናነብው ይመስለኛል በአማርኛ ትንሽ ዘርዘር ያለ ነገር ጽፏል። አንድ መሰረታዊ ነጥብ ላይ ጥቂት ማለት እፈልጋልሁ።

“ ኦሮሚያ የኦሮሞ ነች ስንል ኦሮሚያ የኦሮሞ ህዝብ ሀገር ነች ( Oromia is homeland of the Oromo people) ማለት ነዉ” ይለናል ጃዋር።

ኦሮሚያ የኦሮሞዎች አይደለችም ያለ ሰው ማን ነው ? በሚገባ Oromia is homeland of the Oromo። ሆኖም እነ ጃዋር የማይቀበሉት አንድ ሐቅ አለ። በአዲስ አበባ 90% የሚሆነው ሕዝብ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪ አይደለም። በአዳማ፣ በቢሺፍቱ፣ በሻሸመኔ፣ በጂማ …እንዲሁም በርካታ የኦሮሚያ ከተሞች የሚኖሩት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኦሮሞ ያልሆኑ አሉ። ጃዋር ራሱ ከጥቂት ሳምንታት በፊት እንደተናገረዉም ኦሮሚያ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል ናት። ታዲያ ለነዚህ ወገኖች ኦሮሚያ የነርሱም homeland አይደለችምን ? በሚገባ ናት። አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ጂማ. ነጆ፣ ጊምቢ …ሁሉም የኦሮሚያ መሬት የሁሉም ኢትዮጵያዉያን homeland ነው። የሁላችንም ነው።

ቤኔሻንጉል ክልል ከ25% በላይ፣ በሃረር ክልል ከ56% ነዋሪዎች ኦሮሞዎች ናቸው።፡በአማራዉ ክልል በከሚሴ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ልዩ ዞን አላቸው። በራያና አዘቦ ኦሮሞዎች በብዛት አሉ። በሶምሌ ክልል ዉስጥ የሚኖሩ ብዙ ኦሮሞዎች አሉ። ታዲያ ከኦሮሚያ ዉጭ ያሉ ቦታዎች የኦሮሞ homeland አይደሉምን ? ሁሉም የኢትዮጵያ መሬት የኦሮሞዎች መሬት ነው።

ስለዚህ ኦሮሚያ የነዋሪዎቿ ናት በሚል ብንስማማ ይሻላል !!!!

“ኦሮሚያ የኦሮሞ ነች ማለት ኬኒያ የኬኒያኖች እንደ ማለት ነው። ይህ ማለት ኬኒያ ወይም ኦሮሚያ ውስጥ ሌላ ሰው መኖር ዜጋ መሆን አይችልም ማለት አይደለም። በሚገባ ይችላሉ” ሲል ጃዋር ነገሮች የበለጠ ይለጥጣቸዋል። አዲስ አበባ በኦሮሚያ ዉስጥ እንደመሆኗ፣ አዲስ አበባን ጨመሮ በኦሮሚያ ዉስጥ የሚኖሩ ኦሮሞ አይደለንም የሚሉ፣ ወይንም ኦሮሞ ሆነው አፋን ኦሮሞ የማይናገሩ፣ የኦሮሞና የሌሎች ብሄረሰቦች ድብልቅ የሆኑ (እንደኔ) ግን “ኦሮሞ” አይደላችሁም የሚባሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉይን ፣ በኦሮሚያ ዉስጥ ሲኖሩ፣ በኬንያ እንዳሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እንደሆኑ ነው ጃዋር ለማሳየት የሞከረው። ያን ያህል ለቋል።፡

ሲያጠቃልልም “ኦሮሚያ የኦሮሞ ነች የሚለውን መፈክር ልናፍርበት ሳይሆን በደማችን እውን ለማድረግ እየታገልንለት ያለ ህያው አላማችን ነው። ይህን አላማችንን የሚቃወም ካለ ከኦሮሞ ጋር መስራት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን ፀረ-ኦሮሞ በመሆኑ አጥብቀን አንታገለዋለን “ ሲል በነርሱ አይምሮ ዉስጥ ያለችዋን የኦሮሞዎች ብቻ የሆነች ኦሮሚያ፣ እዉን ለማድረግ ደም እንደሚፈስም ያስጠነቅቀናል። ይሄ extrem radicalism ነው። የከረረ አክራሪነት !!!!! ይህ አይነት ፖለቲካ እጅግ በጣም አደገኛ ፖለቲካ ነው። ሁላችንም በፍቅር፣ ተከባብረን የምንኖርባት ኢትዮጵያ እንዳትገነባ እንቅፋት የሚሆን ነው። ማንም ኢትዮጵያዊ ሊታገሰው የሚገባ ፖለቲካ አይደለም። በተለይም የኦሮሞ ልሂቃን ሊያወግዙትና ሊመክቱት የሚገባ ፖለቲካ ነው።

ጃዋር ለምን ይህ አይነቱን መርዛማ ፖለቲካ እንደሚረጭ ሊገባኝ አልቻለም። ብዙ ኦሮሞዎች ጠንካራ ተቃዉሞ እንዳቀረቡበት አውቃለሁ። በቁቤ የጻፈውና እነ አበበ ገላው ያስተረጎሙትን ጽሁፍ የጻፈው ከኦሮሞዎች የቀረበበትን ጠንካራ ትችት ለመመከት ነበር። ” While bereaving the sacrificed, rejecting the cause is unacceptable I have realized my reaction towards our adversary has offended some of our people (Oromos)” ሲል ራሱ ጃዋር በኦሮሞውሽ ዘንድ ተቃዉሞ እንደደረሰው ማመኑን እናያለን። ይሄ ተስፋ የሚሰጥ ነው። ሰዉዬ ብዙ ጭፍን ተከታዮችን እንዳሉት የሚቃወሙትም እጅግ በጣም ብዙ ናቸው።

ይሄን ጥቂት ቁልፍ ነጥቦች ላስቀምጥ፡

1. የጃዋር ፖለቲካ ከምንም በላይ የሚጎዳው የኦሮሞ ማህበረሰብ ነው።

2. ጃዋር በኢሳት ላይ ጠንካራ ትችት ያቀርባል። የአኖሌና የጨለንቆ ሃዉልቶች ያሉበት ምስሎች ይቆርጣሉ፣ የኦነግ ባንዲራን አያሳዩም ….ምናምን petit ምክንያቶች ነው ያቀረበው። ግን ዋናው ኢሳት ላይ ያለው ችግር ቦታዬን ሊወስዱብኝ ነው በሚል ነው። ኢሳት የአፋን ኦሮሞ ፕሮግራም ጀምሯል። የኦሮሞ ማህበረሰብ ከኦሮሞ ሜዲያ ኔትዎርክ በተጨማሪ ሌላ አማራጭ አገኝ ማለት ነው። ቢቢሲ በአፋን ኦሮሞ ስርጭት እንዲያቀርብ ዘመቻ ስናደረግ አልነበረመ እንዴ ? ብዙ አማራጮች ለህዝብ ይጠቅማሉ። ጃዋር ግን በባህሪው እኔ ብቻ መሰማት አለብኝ የሚል በመሆኑ የኢሳትን የኦሮምኛ ፕሮግራም አልወደደዉም።

3. ጃዋር በግንቦት ሰባት ላይ ትችት አቅርቧል። ግንቦት ሰባት ለምን ተተቸ አልልም። እኔም የማደርገርው ነው። ሆኖም ጃዋር፣ ችግር ያለው ግንቦት ሰባት ላይ ሳይሆን ከግንቦት ሰባትና ሌሎች ኢትዮጵያዊ ኃይሎች ፣ በጋራ ለመስራት እያተነጋገሩ ያሉ የኦሮሞ ኃይሎች ላይ መሰለኝ። በተዘዋዋሪ መንገድ እነ ሌንጮ ለታን እያስፈራራ መሰለኝ።

የኦሮሞ ማህበረሰብ በአሁኑ ወቅት ወሳኝ ትግል እያደረገ ነው። ብዙዎች እየታሰሩ፣ እየተገደሉ ነው። ላለፉት ሶስት ወራት አገዛዙ ኮስሜቲክና ዉጫዊ ለዉጦች ከማድረግ ዉጭ፣ የለወጠው ምንም ነገር የለም። በተናጥል የተደረገውን የኦሮሞዎች እንቅስቃሴ ለጊዜውም ቢሆን አገዛዙ የተቆጣጠረው ይመስላል። በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ይሄን ያህልም ግፊት አልታየም። ያ ሁሉ ሰው ሞቶ፣ ያዉ ሁሉ ተደብድቦ በአጭሩ የመጣ ለዉጥ የለም። ሐቁ ይሄ ነው።

ይሄም የሆነበት ምክንያት እንቅስቃሴው በዋናነት በኦሮሚያ ወዳሉ ትላልቅ ከተሞች እንዲሁም በሌሎች ክልሎች ባለመዛመቱ ነው። ከዚህ የተነሳ ሌላው ማህበረሰብ የኦሮሞዎችን እንቅስቅሴ እንዲቀላቀል፣ የትግሉ አጀንዳ በተቻለ መጠን አገራዊና አሰባሳቢ እንዲሆን ማድረጉ አስፈላጊ በመሆኑ፣ የኦሮሞ ኃይሎች ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻቸው ጋር ዉይይቶች ጀምረዋል። እንዴት ትግሉን እናቀናጀው በሚል ። ጃዋር እዚህ ላይ ነው ችግር ያለው።

ጃዋር ይሄንን ለመብት፣ ለነጻነት፣ ለዲሞክራሲ የሚደረግን የጋራ እንቅስቃሴ ለምን ይጠላዋል ? የኦሮሞ ማህበረሰብ እርሱ ከሚመራው የኦሮሞ ሜዲያ ኔትዎርክ ዉጭ ሌላ አማራጭ እንዳይኖረዉስ ለምን ይፈልጋል?

አንድ መልስ ነው ያለው።ሰዉዬው የራሱን ተክለ ሰዉነት ለመገንባትና ሰው ሁሉ ስለርሱ እንዲያወራ የሚፈልግ ሰው በመሆኑ ነው። የሚሰራው ለኦሮሞ ማህበረሰብ ጥቅም ሳይሆን ለራሱ ጥቅም ነው። ይሄንን ሁላችንም በተለይም የኦሮሞ ማህበረሰብ መረዳት አለብን። አንድ ሰው የትብብርን መንፈስ እንዲያደፈርሰ ሊፈቀድለት አይገባም። ዉይይት ጥሩ ነው። ግን ትኩረቱ መሆን ያለበት መሰባሰቡ ላይ ነው። ተስፋ አለኝ እነ ጃዋር የሚያስቀምጡትን መሰናክሎች አልፈን እንደምንሄድ። እነ ጃዋር ወደኋላ ሊጎትቱን ነው። ላለፉት 25 የተከፋፈልነው አይበቃም እንዴ ? አሁን የሚያስፈለገው አንድነት ነው።