የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ፤ መንግሥታዊ ወይስ ሃይማኖታዊ ?! (Yidnekachew Kebede)
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ፤ መንግሥታዊ ወይስ ሃይማኖታዊ ?!
———————-
“የእስልምና ጠቅላይ ጉዳዮች ምክር ቤት (መጂሊስ) እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን (ሲኖዶስ) የሃይማኖት መሪዎች ለእምነታቸው ካላቸው ተገዢነት ይልቅ ፣ በሥልጣን ላይ ላለው መንግሥት ታማኝነታቸውና አገልግሎታቸው የበዛ እንደሆነ ይነገራል፡፡”
————————-
በአገራችን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት፣ የሰው ልጅ መሠረታዊ መብቶችን ከሚያስከብሩ ሰነዶች መካከል፣ ሃይማኖትን አስመልክቶ የያዘው ድንጋጌ ከመብት አንፃር ሲቃኝ ጤናማ የሆኑ የሰው ልጅ መሠረታዊ መብቶች በውስጡ ይገኛል፡፡ይህ ማለት በተፈፃሚነታቸው ላይ የሚታየው ፣ መንግሥታዊ ዳተኝነት ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በሕገ መንግሥቱ ተደንግጎ የሚገኝ ለዚህ ጹሑፍ ተዛማጅ የሆኑቱ እንደ መነሻ ሃሳብ ሊያገልግል ይችላል፡፡
1. ‹‹ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ሃይማኖትም በመንግስት ጣልቃ አይገባም፡፡ ›› አንቀጽ 11 ንዕሱ አንቀፅ 3 ፡፡
2. ‹‹ ማንኛውም ሰው የማሰብ፤የሕሊና እና የሃይማኖት ነጻነት አለው ፡፡ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣የመተግበር ፣የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል፡፡››አንቀጽ 27 ንዕሱ አንቀፅ 1 ፡፡
3. ‹‹ ማንኛውም ሰው የሚፈልገውን እምነት ለመያዝ ያለውን ነጻነት በኃይል ወይም በሌላ ሁኔታ ማስገደድ ወይም መከልከል አይቻልም፡፡ ›› አንቀፅ 27 ንዕሱ አንቀፅ 3 ፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በውስጡ ስድስት ቤተ እምነቶች በጋራ የሚንቀሳቀሱበት ተቋም ነው፡፡ተቋሙ ዋና አላማዬ የሚለው “ልዩነታችንን ጠብቀን በሃገር ደረጃ ሰላምና መረዳዳት እንዲኖር በጋራ ለመስራት፣በሃገራችን ለዘመናት የኖረው የሃይማኖት መከባበርና መቻቻል ተጠብቆ እንዲቀጥል ለማድረግና አክራሪነት”ን ለማውገዝ፣ ሁሉም ሃይማኖት በእኩል የሚሳተፉበት” እንደሆነ ስለጉባዔ ሲነሳ ሁሌም “የጉባዔው” መልዕክተኞች የሚናገሩት አላማቸው ነው፡፡
ጉባዔው እንቅስቃሴ አደረኩ በሚልበት በማናቸውም ወቅት፣በመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን፣ ተያይዞ የሚዘገበው ዜና “የጋራ ጉባዔው በፌዴራል ደረጃ ከተመሰረተ በኋላ በዘጠኙ ብሔራዊ ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች መዋቅሩን በማስፋት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በተለይም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ወደ ዞንና ወረዳ የሰፋበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በቀጣይም በሌሎች ክልሎች ማዋቅሩን ለማስፋት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል።”እየተበላ በተደጋጋሚ የዜና ሽፋን ተሰጥቷል፣የሁኔታዎች ለውጥ እስካልመጣ ድረስ የዜናው ዘገባ በዚህ ሊቀጥል ይችላል፡፡
ይሁን እንጂ የሃይማኖት ተቋማቱ ከገለጹት ዓላማ እንዲሁም ቤተ እምነቶቹ ከሚመሩበት ሃይማኖታዊ ትእዛዝ ውጪ ፣የመንግሥት ሥራ በጉያቸው ሸሽገው ፣ሲመቻቸው በአስተምህሮት ሳይሳካ ሲቀር በመግለጫ የተቋቋሙለትን ዓላማ ሳይሆን ፣ያቋቋማቸውን የመንግሥት ሥራ እየፈጸሙና ለማስፈጸም እየጣሩ ይገኛሉ፡፡ለዚህም ተግባራቸው ከጠቅላይ ሚኒሰትር ኃይለማርያም ደሳላኝ ጀምሮ የጉዳዩ ቀጥተኛ አስፈፃሚ የሆኑት የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም ጨምሮ በይፋ “የቤት ሥራችንን ካልሠራን አክራሪነት በድህነት አረንቋ ላይ የሚወልደውን ብጥብጥ ነው፡፡ የአክራሪነትና የጽንፈኝነት አመለካከት ለመዋጋትና በእንጭጩ ለመቅጨት” የሃይማኖት ጉባዔው ወሳኝ ሚና አለው፡፡በማለት በመንግሥታዊ ልማታዊ ቃል፣ የመንግሥት እና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው በተደጋጋሚ በሚኖራቸው ስብሰባ እንዲሁም በጋራ በሚሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የሚባለው ስብስብ ፣የትኛውንም ቤተ እምነቶቾ የሚወክሉ ትክክለኛ ተወካዮች ስለመሆናቸውም፣ የቤተ እምነቶቾ ተከታዩች በጥርጣሪ ብቻ ሣይሆን በእርግጠኝነት አይወክሉንም ሲሉ መግለጻቸው የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ቆይቷል፡፡ለዚህም እንደ መሳያ የእስልምና ጠቅላይ ጉዳዮች ምክር ቤት (መጂሊስ) እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን (ሲኖዶስ)፣በእምነነቱ ተከታዮች፣ የሃይማኖት መሪዎች ለእምነታቸው ካላቸው ተገዢነት ይልቅ ፣በሥልጣን ላይ ላለው መንግሥት ታማኝነታቸውና አገልግሎታቸው የበዛ እንደሆነ ይነገራሉ፡፡መንግሥትም ቢሆን እጁን አስረዝሞ በእምነት ተቋማት ውስጥ የሃይማኖት መሪዎችን እስከ-መምረጥና እስከ-ማስመረጥ መድረሱ ለቤተ እምነታቸው ቅርብ የሆኑ አማኞች የሚመሰክሩት ሐቅ ነው፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ፣በአገራችን በደካማ የመንግሥት አስተዳደር እንዲሁም ተፈጥሯዊ በሆኑ ምንያቶች ለሚከሰቱ ችግሮች ፣በቤተ እምነታቸው የእምነቱ ተከታይ፣ሃይማኖታዊ ይዘት ጠብቆ የመፍሔ አካል እንዲሆን ከማስተማርና ከማስተባበር ይልቅ ፣ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን ባልተወከሉበት እነሱ ግን እንወክለዋለን በሚሉት አማኞች ስም በድፍረት ጉዳዮችን ሁሉ፣ መንግሥታዊ አቅጣጫ እንዲይዝ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡መንግሥትም ለአገዛዙ ሥርዓት አይበጀኝም ብሎ የሚያስባውና የሚያሰጋው ማናቸውም ነገር ቅድመ ትእዛዝ ማስተላለፊያ መንገድ የሚጠቀመው የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔን ነው፡፡
ለዚህ እንደ-ማመላከቻ ይሄን ማስታወስ በቂ ነው፡፡ ባላፉት አራት አመታት “የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች” ሕገ ወጥ እስር በመቃወም፣ በሰለማዊ መንገድ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄውን እያቀረበ ይገኛል፡፡ መንግሥትም ለሠላማዊ ጥያቄ እየሰጠ ያለው ምላሽ ምን-እንደሆነ ይታወቃል፡፡በመንግሥት ቀጥተኛ ትእዛዝ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ “አክራሪነትና ጽንፈኝነትን እናወግዛለን” በሚል መሪ ቃል መግለጫ እና ማሳሰቢያ ከመስጠት ባለፍ ለችግሩ የመፍትሔ አካል ሲሆኑ አልተገኙም፡፡ ይባስ ብሎ የመንግሥትን ድርጊት በመደገፍ ሠልፍ እስከመጠራት ደረጃ ደርሰዋል፡፡ይሄን ማድረጋቸው የሚያስገርም ባይሆንም የተቋቋሙለት ዓላማ ምን እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ይህ አይነቱ ድርጊት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን (ሲኖዶስ) እና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል፣ወቅቱን እየጠበቀ በሚደረገው ንትርከ እና እሱን ተከትሎ በሚመጣው ነገር ሁሉ ፤መንግሥት ከጀርባ በመሆኑ ሥራውን ሲሰራ ቆይቷል፣አሁንም እየሰራ ይገኛል፡፡በዚህም መሐል የእምነቱ ተከታዮች የጉዳዮ ባለቤት በመሆን ለችግራቸው ትክክለኛ መፍትሔ እንዳያመጡ፣ ካስፈለገ በቀጥታ ሳይሆን ሲቀር በሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ስም የመንግሥትን ፍላጎት ለመፈጸም ጥረት ይደረጋል፡፡
መንግሥት ከየትኛውም ሃይማኖት ወገንተኛነት የተገለለ መሆኑ ከላይ በመግቢያ ላይ በተገለጸው ሕገ መንግሥት ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ይሁን እንጂ ባሁን ወቅት መንግሥትና ሃይማኖት መለያየት በሚያስቸግር ሁኔታ ፣መንግሥት ሰተት ብሎ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ገብቷል፡፡ይህ አይነቱ አሳፋሪ ተግባር ሽፋን ለመሰጠት እየተሞከረ ያለው፣ በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አማካኝነት ነው፡፡
ይህም በመሆኑም እንደኔ የግል እይታ፣ የቤተ እምነት ተከታዮች ፣ፖለቲካዊ አወቃቀር እና ይዘት ያለው “የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ” እየተባላ የሚጠራው ተቋም፣ የሚያደርጋቸው ማናቸውም እንቅስቃሴ ፣በንቃት በመከታተል ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲንቀሳቀስ ከአወቃቀሩ ጀምሮ እስከ-ሚወከሉት የሃይማኖት መሪዎች ድረስ እነማን እንደሆኑ ዋነኛ ተግባር ሊሆን ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡